>

የኦርቶዶክስንና አማራን አከርካሪ የመምታት የመጨረሻው ምዕራፍ (ምሕረት ዘገዬ)

የኦርቶዶክስንና አማራን አከርካሪ የመምታት የመጨረሻው ምዕራፍ

ምሕረት ዘገዬ

  1. የጠ/ሚንስትሩ የመደመር ልቦለድ መጽሐፍ እየተመረቀ ባለበት በአሁኑ ቅጽበት በአዲስ አበባና በዙሪያዋ ምን እየተደረገ ነው?
  •  መዝገብ የያዙና በሥውር የፖሊስ ኃይል ጥበቃ የሚደረግላቸው የወለጋና አርሲ ቄሮዎች በጀሞና በሌሎች የአዲስ አበባ ከተማ ህጋዊ ይዞታዎች ሥር የሚገኙ መሬቶችን እየተከፋፈሉ ነው፡፡ ካለበቂ ጥበቃ የሚገኙ ኮንዶሚኒየሞችን በር በመስበርም እየተሻሙ ነው፡፡ እነሱን ሃይ የሚል ህግ የለም፡፡ …
  • የሌሎች ዜጎች በተለይም የአማሮች ቀደምት ይዞታዎች በሻማና በኩራዝ እየታሰሱ እንዲፈርሱና ሰዎቹ ወደው ባልተፈጠሩበት ነገዳቸው ምክንያት ማቄን ጨርቄን ሳይሉ ከቦታቸውና ከሀገራቸው እንዲፈናቀሉ እንዲሰደዱም እየተደረገ ነው – በአዲስ አበባ ዙሪያ ሁሉ፡፡ …
  • አማሮች ከያዟቸው የፌዴራልና የክልል ሥልጣንና ኃላፊነቶች እየተነሱ የገዢው ኃይል ታማኝ የሆኑ ሆዳሞችና ምሥጢረኞች እንዲሁም የአማራን መጠሪያ ስሞችና የአማራነትን ዘውጋዊ የውሸት ማንነት በዳግም ጥምቀት ያገኙ አሰለጦች እየተተኩ ነው፡፡ አማራ በቋንቋውም ሆነ በባህሉ ለማንምና ለሁሉም እኩል ክፍት በመሆኑ ይህ ሁኔታው ክፉኛ እያስጠቃው ይገኛል፡፡ በተቅጠፈጠፈ አፉና በአስመሳይ ኢትዮጵያዊ የሥነ ልቦና ቀመሩ ሠርጎ የሚገባ ዘረኛ ሁላ አማራን በቀላሉ ለጥቃት ይዳርገዋልና ለዚህ ዓይነቱ ችግር አፋጣኝ መፍትሔ ካልተገኘ ችግራችን እንደጠነነ መቀጠሉ ነው፡፡  ለዚህም አንዱ ምሣሌ ከአማራ ሕዝብና አዴፓ አባላት ጋር ውኃና ዘይት የሆነው የጠሚው ልዑክ – ስሙም ጠፋኝ – የአማራው ክልል አዲስ ፕሬዝደንት ነው፡፡ ይህ ሰው መንፈስ ቢጤ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የት ነው ያለው ግን? ምን እየሠራስ ነው? ዋና ተልእኮው ለጠሚው ነው ወይንስ ለአማራ? የዘር ሐረጉ የሆነውን ይሁን ግዴለም – ግን ለክልሉ ምን እየፈየደ ነው? በፍንጭ ሰጭ ቃላት ጉግል አድርጌ ስሙን አሁን አገኘሁት – እውነቴን ነው – ተመስገን ጥሩነህ፡፡ ወይ መሪና ተመሪ! ተለያየን፡፡
  • 2 ኦርቶዶክስንና አማራን በደርግ አማርኛ ድባቅ የመምታት የነአቦይ ስብሃት ነጋ ዘመቻ የመጨረሻ ክፍል በነኦነግና ጃዋር ተጧጡፏል፡፡ እንደዓሣ በባህር እንደሰው በምድሩ የሁለት ዓለማት ፍጡር ዐቢይም ቅን ታዛዥነቱን ቀጥሏል፡፡ በማያባራ ፈገግታው ሰዎችን በፍቅር እያሰመጠ ሀገር ላይ የሚያደራውን የእፉኝቶች ድር በፊታውራሪነት ማድራቱንና ሀገርን ተብትቦ ወደ ዕልቂት ማምራቱን ተያይዞታል፡፡ 
  • ከየከፍተኛ ተቋማት በቅርብ የተመረቁ ወጣቶችን እሮሮ ብትሰሙ ከማዘን አልፋችሁ ታለቅሳላችሁ፡፡ ልባችሁም በሀዘን ይደማል፡፡ ሥራ ፍለጋ ሲሄዱ የመጀመሪያው ማንጓለያ ዘርና ሃይማኖት ነው፡፡ ኦሮሞ ያልሆኑ መቀጠር ይቅርና ማመልከቻ እንኳን ማስገባት የማይችሉ ዜጎች አሉ – እነሱም ኦርቶዶክስና አማራ ናቸው፡፡ የቅርብ ጊዜ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በዐቢይ መንግሥት ከተቀጠሩ ሠራተኞችና ኃላፊዎች መካከል 80 በመቶው ኦሮሞ፣ፕሮቴስታንትና በተወሰነ ደረጃ ሙስሊም ዜጎች ናቸው፤ ይህ መድሎ እጅግ ያሳስባል፡፡ ባጭሩ ኦሮሞ ከሆንክ በዚያ ላይ ፕሮቴስታንትነትን ከደረብክበት ትምህርትና ችሎታ ኖረህም አልኖረህም በፈለግኸው የመንግሥት ድርጅት ተቀጥረህ ሥራን የማበለሻሸት መብትህ የተጠበቀ ነው፡፡ ከሚኒስትር እስከ ጦር መኮንኖች ተመልከቱ – ለማስመሰያነት ሲባል እንዲሁ ለላንቲካው ከሚቀመጡ የሥልክ ታዛዦች በስተቀር ከሞላ ጎደል ሁሉም ኦሮሞና ፕሮቴስታንት ናቸው፡፡ይህን ክስተት አጋጣሚ ነው የሚል ካለ ጭንቅላት ያለው መሆኑ ያጠራጥረኛል፡፡ መደመር የሚሉት የቀልድ መጽሐፍ የተመረቀው እንግዲህ በዚህን ወቅት ነው፡፡ ዕንቆቅልህ ምን አውቅልህ፡፡ ዋናው አራት ኪሎን መያዝ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሁኔታ ሌላው አያሳስብም፡፡ ሁሉም አንጎሉን እቤቱ አስቀምጦ ከእግር እግርህ እየተከተለ በጭብጨባና አድናቆት ስለሚያፈዝህ አንተ የፈጠርከው እስኪመስልህ ብታሽቆጠቁጠው የፈለግኸውን ያደርግልሃል፡፡ ያልታደለች ሀገር፡፡ እነአጋፋሪ ዳንኤል ክብረትና ምድረ አለቅላቂ አርቲስትና ደራሲ ነኝ ባይ ሁሉ የሚያሳየው ማሽቃበጥ የሚያረጋግጥልን እውነታ ይህንኑ ነው፡፡ ሆድ ውስጥ አራት ሰዓት ለማይቆይ እህል ውኃ ይህን ያህል መዋረድ? ዘመን ሲያረጅ ያለው ጣጣ፡፡ ማባያውን እርሱትና አንዲት እንጀራ ይህን ሁሉ የተዘበራረቀ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ገጽታ ታሳየን? ሴቴኒዝም ማለት ይሄው ነው፡፡
  • ዜጎች የጋራ ሀገር አለችን ብለው ላባቸውን ጠብ አድርገው ባገኙት ገንዘብ ልጆቻቸውን አስተማሩ፡፡ ሥራ የሚገኘው ግን በዘርና በሃይማኖት መሥፈርት ሆነና ወላጆች በተገላቢጦሽ የልጆቻቸው ጧሪ ለመሆን ተገደዱ፡፡ እግዜር ይመዝግብልን፡፡ (ለዚህ ሁሉ አንጸባራቂ ድል ያበቁን ወያኔዎች ግን ምን ይሰማቸው ይሆን? እኛ ብቻ የተቸገርን ከመሰላቸው አሁንም ከኋላቀርና ጅላጅል ብልጠታቸው ገና አልተላቀቁም ማለት ነው፡፡ ባይገባቸው እንጂ የኦነግ ኦህዲዳዊ ዱላ ተቋዳሾች ሁላችንም ነን፡፡)
  • ለዚህ ሁሉ ችግራችን መፍትሔው ምንድን ነው ብላችሁ የምትጠይቁኝ ልትኖሩ ትችላላችሁ፡፡ እኔ የማውቀው ብቸኛው መፍትሔ በንጹሕ ልቦና ፈጣሪን መለመን ነው፡፡ በበኩሌ ከሰው ጨርሻለሁ፡፡ የማያልቀው የተስፋ መንገድ የእግዜሩ ብቻ ነውና ወደርሱ እንጩህ፡፡ 
  • የራሷን የመታነቂያ ገመድ ራሷው ፈትላ አሁን ለምትገኝበት የነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ አሳሳቢ ደረጃ የደረሰችው ኦርቶዶክስም እንኳን ምዕመኗን ራሷንም ልታድን አትችልምና ጸሎት ምህላችንን ተቋማዊ መሠረት ማስያዝ ብዙም አያዋጣም፡፡ ከፓትርያርክ እስከ ዲያቆን በብልጭልጩ ዓለም ተማርከው በሰይጣን ግዛት ስለሚመላለሱ ሕዝብ በተኩላና በቀበሮ ተበላ፡፡ ሙስናው፣ እብለቱ፣ ጉቦው፣ ክህደቱ፣ አጋንንታዊ ድግምቱና መተቱ፣ ወንጀሉ፣ ኃጢኣቱ … በነሱ ባሰና መቆሚያ መቀመጫ አሳጣን፡፡ ንስሃ አባቱ ከሚስቱ የሚወልድበት ምዕመን እስላምና ጴንጤ መሆን ቀርቶ የለየለት የሉሲፌሪያን ቤተ አምልኮ ካህን ቢሆን አልፈርድበትም – እንደቀሲስ አንቷን ሌቪ፡፡ በዚህ አቅጣጫ ብዙ ማለት እችላለሁ፡፡ ኦርቶዶክስን ያጠፋናት እኛው ኦርቶዶክሶች ነንና በሌላ አናሳብ፡፡ ይቺን ታህልም መኖራችን የእርሱ ቃል ኪዳን ጠብቆን እንጂ እንደሥራችን ቢሆን ኖሮ ይሄኔ አንድም ቤተ ክርስቲያን ተከፍቶ የታይታዊም ቢሆን አገልግሎት ባልሰጠ፡፡ ይህን እንረዳ – ከልብ ያልሆነው ጸሎትና ሽብሸባችን – የቀን ከሌቱ ሕይወት አልባው አሰልቺ ከንቱ ጩኸታችን የጽርሃ አርያምን ደጆች ማንኳኳት ይቅርና ከዛፎች በላይ አርጎ ደመናትንም ሊያልፍ አይችልም፡፡  የክርስቶስ ትምህርት መች ገባን? ስለጸሎት እርዝማኔ ለምሣሌ ምን አለን? በከንቱ ልፋ ቢለኝ እኮ ነው….

በሉ ያ መጽሐፍ ሳያልቅብኝ ሄጄ ወረፋ ልያዝና ልግዛ፤ ቻው፡፡

 

እንደማሣረጊያ፡-

መጥምቁ ዮሐንስ አሁን በሕይወት ቢኖር ኖሮ “መንግሥተ ሰማይ ቀርባለችና ንስሃ ግቡ!” እያለ ይጮህ ነበር – በበረሃ ሳይሆን በሶዶምና ገሞራዋ ተምሣሌት አዲስ አበባ ወፍንፍኔ ውስጥ፡፡

mz23602@gmail.com

Filed in: Amharic