>

ሪትሙ ስለተቀየረ ዳንሳችንን እንቀይር!  (ኤርሚያስ ለገሰ)

ሪትሙ ስለተቀየረ ዳንሳችንን እንቀይር! 
ኤርሚያስ ለገሰ
 ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ እንኳን ወደ አገሮት ኢትዬጵያ ተመለሱ። መቼም “በሰላም ተመለሱ” እንዳንል የአገራችን የሰላም ሁኔታ ከድጡ ወደ ማጡ መሄዱ ገሃድ ወጥቷል። እርሶም ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ፎቶ ሳይነሱ፣ መመለሶ ሳይሸበርቅና ሳይደምቅ በሐፍረት አንገቶን መቅላትዎ ልባችንን አድምቶታል። እኛ በዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢዋ የምንኖር የእርሶ ተደማሪዎች በተፈጠረው ሁኔታ በእጅጉ አዝነናል። ተቆጭተናል።
ይህም ሆኖ ከሞስኮ ከተመለሱ በኃላ  ” ለኢትዬጵያ ሕዝቦች”  ያስተላለፉትን መግለጫ በጥሞና ተከታትለነዋል። ክቡርነትዎ! እቺ “ሕዝቦች” የሚሏትን ኢህአዴጋዊ ቃላት ባትመቸንም በመልእክትዎ መሬት የማይወድቁ ቁምነገሮች አንስተዋል። በመግለጫው ላይ “መደመር(+)” የሚለው ቃል የብልጽግና ጉዞ በሚለው መተካቱን ብንጠረጥርም ያቀረቡት ማስጠንቀቂያ የመደመር(+) ጉዞን አመላካች ሆኖ አግኝተነዋል።
 ከእነዚህም ውስጥ፣
  •ስንዴውን ለይተን አረሙን እንነቅላለን!+
   • የህግ የበላይነት እናስከብራለን!+
   • አጥፊዎችን ህግ ፊት እናቀርባለን!+  
   • የሚከፈለውን መስዋእትነት በሙሉ ያለማወላወል እንከፍላለን! ማለትዎ በጥሞና ተመልክተነዋል። 
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እኛ ከእስር ጫማ ስር መዳከር ምርጫችን የብሔር ፓለቲካ አጥፍተው ወደ ኢትዬጵያዊነት ማማ ይወስዱናል ብለን በመቶ ፐርሰንት በማመናችን ነበር። የእኛ ምኞት ሁሉም ኢትዬጵያዊ ይቺ አገር የጋራ አገር መሆንዋን እንዲረዳና “ኢትዬጵያዊነት” በተባለ ጥልቅ የአገር እሴት ዙሪያ እንዲሰባሰብ ነው። ይሄ ሃሳብ ደግሞ የሚኒሊክ ቤተመንግስት ገብቶአል ብለን እናምናለን። አሁንስ “እናምን ነበር” ብንል ሳይሻል አይቀርም።
                       ***
ክቡር ጠቅላያችን! ወደ ተነሳንበት ዋና ቁምነገር እንድንመለስ ፍቃድዎ ይሁን።  ከዛ በፊት ግን አስቀድመን መለስተኛ ማብራሪያ የሚያስፈልገው ጥያቄ እናንሳ። እርሶ ለኢትዬጵያ ህዝቦች ባስተላለፉት መልእክት ውስጥ ስለ ስንዴና አረም አንስተዋል። ማነው ስንዴ? ማነው አረም? ማነው የህግ የበላይነት የማያከብረው? ማነው አጥፊ? መቼ ነው አጥፊዎች ወደ ህግ የሚቀርቡት? መግደል መሸነፍ ሆኖ ይቀራል ወይንስ የገደለ በወንጀሉ ልክ ይቀጣል?•••
በእኛ እምነት የህግ የበላይነት የማያከብሩ፣ አጥፊዎች እና ከስንዴ ጋር የተደባለቁ አረሞች በቅደም ተከተል “ጀዋር መሀመድ” እና ” ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ” ናቸው። እናም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በመግለጫው እንደገለጡት ያለማወላወል መስዋእትነት ለመክፈል ቁርጠኛ ከሆኑ እርምጃ መውሰዱን ከእነዚህ ፀረ-ኢትዬጵያ ሃይሎች ይጀምሩና እኛም በኩራት ከቀኝ ጐንሆ እንሰለፍ።
 ክቡር ጠቅላያችን! ታዲያ አደራዎትን እንደለመዱት አህያውን ፈርተው ዳውላ እየቀጠቀጡ እንዳያሳፍሩን። አረሙን ትተው ስንዴውን እንዳይነቅሉ። ህገ-ወጡን በክብር ሸኝተው ምስኪን ወደ ጦላይ ማጐሪያ ካምፕ በመውሰድ በበሽታ እንዳይቀጡት ብለን ነው። አምና ቄሮን እና አዲስአበቤን እንዳደረጉት ማለት ነው። ቄሮ አህያ! አዲስአበቤ ዳውላ! አሁን እንኳን የአሰላልፍ ለውጥ ባይኖርም የቦታ ለውጥ አለ። ለምሳሌ በአሁኑ አሰላልፍ ጃዋርን በአህያ ልንመስለው እንችላለን። ከዛም አልፎ ጓድ ታዬ ደንደአ በኖቤል ሽልማቶ እና የመደመር(+) መጽሐፎ የቀኑ “ቅናተኛ” ብሎታል። ጓድ ታዬ በዚህም አላረፈም። ለመደመር(+) ምስጋና ይግባውና ለዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ እና ህይወት መጥፋት ተጠያቂው አህያው ነው ብሎ እኛንም አስደስቶናል።
በሌላ በኩል ከቀደምት ልምድ በመነሳት ስጋት ጭሮብናል። ስጋታችን ጓድ ታዬ እንደ ጓድ አለሙ ስሜ ዳውላ እንዳይሆን ነው። ” ዳውላው ታዬ” ተመልሶ እንዳይመጣ እንሰጋለን። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የጠረጠርነው የሚሆን ከሆነ ጉዳችን ይፈላል።  በተቃራኒው ከሆነ እንደሰሞኑ አንደበታችን ይተሳሰራል። አንገታችንን እንደደፋን እንቀራለን።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር! ሀቁን ንገሩኝ ካሉ በዚህ መልኩ መቀጠል ሰልችቶናል። እጅጉን ደክሞናል። ነፃነታችንን የምናገኝበት ቀን  እንደ ምፅአት ቀን ናፍቆናል።እንደድሮው ቀና ብለን መንቀሳቀስ የምኞታችን መዳረሻ ሆኗል።  እንደ ሰገሌው ዘመን ደረታችንን ገልብጠን፣ ኮፍያችንን ዝቅ ሳናደርግ መንጐማለል እንፈልጋለን። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በህብረተሰቡ ዘንድ የአገዛዙ አፈ ቀላጤ መባላችን አስመርሮናል። በስካይ ላየን፣ በሲልቨር ስፕሪንግ፣ በአሌክሳንደሪያ፣ በዲሲ፣ በሜሪላንድ፣ በቨርጂኒያ ሳንሸማቀቅ መዝናናት አምሮናል።
                       ***
እንደ እውነቱ ከሆነ እኛ የእርሶ የለውጥ አጋዦች እድሜ ልካችንን ” ህወሓት!” ፣ “27 አመት” ፣”መቀሌ የመሸጉ”፣ ” ጌታቸው አሰፋ!” ፣ ” ደብረጺዩን”፣ ” ጌታቸው ረዳ” በማለት የሞቱ አሳዎች ላይ ማላከካችን በህዝቡ ዘንድ ተባኖብናል። ተነቅቶብናል። ይልቁንስ ከመጠን በላይ በመደጋገማችን የተነሳ “ኤጭ አሁንስ በዛ” የሚለን በዝቷል። የክረምት ወራት እየመጣብን ተቸገርን እንጂ አንዳንድ ወዳጆች ዘለግ ያለ ረፍት ወስዳችሁ ተመለሱ በማለት የሰጡንን ምክረ-ሃሳብ በተገበርነው ምን ያህል ደስ ባለን። ይሄን ደካማ እና ውስጡ ተቦርቡሮ ያለቀ ስርአትን ሸፋፍኖ የችግሩ ሁሉ ምንጭ ” ህወሓት ነው” ብሎ ከማቅረብ ረዘም ያለ ጊዜ እረፍት መውሰዱ ሳይችል አይቀርም።
በዚህ አጋጣሚ እርሶ (አሳ አስጋሪው) መረቦትን ወደ መቀሌ ብቻ መዘርጋቶት ብዙ ሰው በቂም በቀል እና አቅጣጫ ማስቀየሻ እየወሰደቦት መሆኑን መግለጡ ይጠቅሞታል ብለን እናስባለን። በተለይ ከውስኪ፣ መጠጥ እና ሆቴል ጋር አያይዘው ” በተከበረው የመቶ ፐርሰንት ፓርላማ” ያቀረቡት ትችት አመድ በዱቄት ይስቃል አስመስሎቦታል። በእርሶ ዙሪያ ከተሰባሰቡት እና የሆቴል ቀለብ ተቆርጦላቸው የሚንፈላሰሱት ዘመናዊ አረቄና ቁንዱፍቱ ገልብጠው ጥንቢራቸውን የሚያዞሩት ከቁርስ ሰአት ጀምሮ መሆኑን አጥተውት አይደለም። የመንግስት እና የፓርቲ ጋዜጠኞች “እነ እከሌን ከቀትር በኃላ ጀምሮ ቃለ መጠይቅ እንዳታደርጉ” የሚል ቀጭን ትእዛዝ በፕሮፐጋንዳው ዘርፍ ከተሰማሩ የኦህዴድ ካድሬዎች መሰጠቱን ካልሰሙ እኛ ከዋሽንግተን ዲሲ መረጃ ልንሰጦት እንፈልጋለን። አሁንማ አንዳንዶቹ ከመደመር መፅሀፍ ገምጋሚነት አልፈው ኢትዩጵያን ወክለው ከእርሶ ጋር ተደራዳሪ ሆነው በራሺያ ስንመለከታቸው እንድንጠራጠር እድርጐናል። እውነት ይሄ አንዳንዶች የሚሉት “ተረኝነት” አለ ወይ? ብለን ለመጠየቅ ተገደናል።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሌላም የሚጨንቀን ነገር አለ። አንዳንድ የቀድሞ ወዳጆቻችን አስቤዛ ለመሸመት ገበያ (ሾፒንግ) ስንሄድ፣ ቡና ለመጠጣት ስታርባክስ ስንገባ፣ መዳኒት ለመግዛት CVS ሄደን ሲያገኙን ጥሩ መልክ አያሳዩንም። ጥቂቶቹ አፍ አውጥተው ግጥሙና ዜማው ስለተቀየረ ዳንሳችሁን ቀይሩ ብለው ምክረ-ሃሳብ ይለግሱናል። አልፈው ሄደውም ይቆጡናል። በእርግጥም ግጥሙ ሙሉ ለሙሉ መቀየሩን ከቀድሞ ወዳጆቻችን በተጨማሪ መካሪ አዛውንቶችን ስናገኛቸው በገደምዳሜ ያጫውቱናል። ጆሮ ለባለቤቱ ባዕድ ሆኖብን እንጂ ዜማውም የተቀየረ ይመመጥቷል።እያየነው ህዝበ ኢትዩጲያዊው ከዝምታ አልፎ ወደ አደባባይ ተቃውሞ እየሄደ ነው። ወደ ሰላማዊ ትግልም (Civil disobedience) ሽግግር እየታየ ነው። ይሄ የማይቀር እዳ ሆኖ መጥቷል።
                   ***
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር! ቀደም ብለን እንደጠቀስነው የእርሶ ደጋፊዎች ሆነን በዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ የምንኖር ዜጐች ከፍተኛ ፍራቻ ውስጥ ገብተናል። ሞጋቾቻችን “በኦህዴድ ውስጥ ያለው የለውጥ ሀይል ብዛቱ ስንት ነው?” የሚለውን ሚጢጢ ጥያቄ እንኳን መመለስ አቅቶናል። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንቱ አቶ ሽመልስ አብዲሳ የለውጥ ሀይል ነው? የኦህዴድ የፕሮፐጋንዳ እና ድርጅት ጉዳይ ሀላፊ አቶ አዲሱ አረጋ የለውጥ ሀይል ናቸው? የኦሮሚያ ፓሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነሩ የለውጥ ሃይል ናቸው? ማእከላዊ ኮሚቴ አባሉና የፓርቲ ጽህፈት ቤት ካድሬው ታዬ ደንደአ የለውጥ ሀዋርያ ነው?
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አሁን ለደረስንበት መጥፎ ሁኔታ በአንድ ነገር መግባባት ያለብን ይመስለናል። በአገራችን ኢትዬጵያ ዛሬ የተለኮሰውን የእልቂት ሁኔታ የፈጠሩት ወይም የመጀመሪያውን ጥይት የተኮሱት የለውጥ ሀይል ተብለው ሲሞካሹ የነበሩ የአገዛዝዎ ቁንጮ ናቸው። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እንደ እኛ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መደመር የተሳናቸው ዜጐች እና የኢትዬጵያ የቅርብ ተመልካቾች ልዩ ትኩረት አገራችን እየተበተነች የእልቂት ማእከል የሆነችበት ምክንያት የራስዎ ቀኝ እጆች እንደሆኑ ምስክርነት እየሰጡ ነው። በዚህም ምክንያት አሁን የደረስንበት ደረጃ የእርሶን መንግስት ለማዳን የማይቻልበትና ራሱም ቢሆን በምንም የጉልበት መጠን የተቆረጠ ዕድሜውን ለመቀጠል ከማይችልበት ሁኔታ ላይ ደርሷል። ባለፈው ሁለት አመት ከእርሶ አገዛዝ ጋር የቆየነውም ቢሆን ምንኛ በውርደት አዘቅት ውስጥ እንደሰጠምን የተረዳንበት እና በተግባራችንም ያፈርንበት ወቅት ላይ እንገኛለን።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር! ሰሞኑን የደረሰውን የጭካኔ መጠን፣ በገጀራ፣ ሜጫ፣ ድንጋይ እና ጥይት የወደቁት ዜጐች ፍጅት ስናጤን ኢትዬጲያችን እየወደቀች የምትገኝበትን መቀመቅ ስንገመግም የሚያመላክተን ነገር ስርአትዎ ከእርሶ ቁጥጥር ውጪ መሆኑን ነው። ምንአልባትም ባሳለፍነው ሳምንት እና አሁንም የቀጠለው የዘር ፍጅት ሥርአቱ ወደ ሕዝብ አሸባሪነትና ወደ ፀረ ሰላም ተግባር በሰፊው ተቀይሯል። ተረኛው ገዥ መደብ የስልጣን ጥማት ወደ ፀረ-ህዝብ ተቀይሯል። ከእርሶ አቅም በላይ የሆነው ስርአት በጥልቀት ለተመለከተው የቀድሞ ዘረኛ እና አምባገነን ስርአት ወራሽ መሆኑን ነው። ይሄን በጥሞና ለተመለከተ በቀጣይ በዚህ መልኩ የሚመጣው አዲሱ ሆኗል። ሰላም እና እኩልነትን የማያመጣ፣ የሕግ የበላይነትንና ዲሞክራሲን የማይወልድ መሆኑን የሚያመላክት ሆኗል። ኢትዬጲያዊ መንግስት መመስረት እንደማይችልም ከወዲሁ የሚያሳይ ሆኗል።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር! ለተራዘመ ወራት ብዙውን ኢትዮጵያዊ ጭንቀት ውስጥ እንዲገባ ያደረግነው አንድ ከባድ ጥያቄ በመጠየቅ ድርድር በማስገባት ነበር። ይኽውም የእርሶ መንግስት ከወደቀ በኃላ የሚተካው መሪ አይኖርም። በምትኩም በአገሪቱ ላይ ሽብር እና እልቂት ይነግሳል። የዘር ግጭት ተነስቶ እርስ በራስ መጨራረስ ይከሰታል። ኢትዬጵያ ወደ ሶማሊያ እና ሶርያ ትቀየራለች በማለት እናስፈራራ ነበር። የእርሶ መንግስትንም ” ትንሽ ፉታ እንስጠው” በማለት ስንሰብክ ነበር።
ይሁን እንጂ በእርሶ የስልጣን ዘመን አመጹና የዘር ፍጅቱ ተጠናክሮ ቀጠለ እንጂ የቀነሰ አይደለም። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በቅርብ ጊዜ ከጀርመን ድምፅ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ” ባለፉት ሁለት አመታት የደረሰው እልቂት እና የእኔ የስድስት አመት ቢወዳደር የአሁኑ ይበልጣል” የሚል መርዶ አሰምቷል። የባለስልጣናት ማጋጣነት፣ ዘረኝነት፣ ወራሪነት፣ የተደራጀ ሌብነት እና ዝርፊያ፣ ፍርደ ገምድልነት ተባብሶ ቀጥሏል። ዜጐች ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ የማይችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በአጭሩ ተረኝነት እና ስርአት አልበኝነት በሰፈንበት ሁኔታ መያዣ መጨበጫ ያጣው ስርአት ሽብርተኝነትን እንደ ዋነኛ ማስፈፀሚያ መሳሪያ መጠቀሙ የማይቀር ሃቅ ሆኖ ቁልጭ ብሎ ታይቷል።
በሌላ በኩል ሥልጣን ለመረከብ የተዘጋጀ ሃይል የለም ለሚለው መከራከሪያችን እየቀረበ ያለው ታሪካዊ ትንታኔዎች በቂ ምላሽ መስጠት አልቻልንም።  ቀዳማዊ ኃይለስላሴን ኮረኔል መንግስቱ ይተካዋል ብሎ ማን አሰበ? ኮረኔል መንግስቱን መለስ ዜናዊ ይተካዋል ብሎ ያሰበ ነበር? መለስ ዜናዊ ሞቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የሚኒሊክ ቤተመንግስት ይገባል ማን አለ? ለመሆኑ አቢይ አህመድ የሚባል ግለሰብን ከሶስት አመት በፊት ስንቶቻችን እናውቃቸዋለን? ስለዚህ መጠየቅ ያለብን በምንም መንገድ የሚመጣው መንግስት ባሕርያት የምንፈልገውን ፍትህና ዲሞክራሲ ያመጣልናል ወይ? የሚለው ይሆናል። በአሁን ሰአት የአንድን ስርአት በአፍጢም መደፋትና የአዲስ ስርአት መወለድ ለመግለጥና ትሩፋቱን ለመጠቆም ማንም እርግጠኛ አይደለም። ይልቁንስ የማይቀረውን የስርዓት ለውጥ አምኖ ተቀብሎ ስለሚወለደው አዲስ ስርአት መነጋገሩ ሳይበጅ አይቀርም።
Filed in: Amharic