>

ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የቀረበ ጥሪ... ለፍትሕ በጋራ እንቁም! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የቀረበ ጥሪ ለፍትሕ በጋራ እንቁም!
ያሬድ ሀይለማርያም
ባለፉት ሦስት ቀናት በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች እና በአዋሳኝ አካባቢዎች በተቀሰቀሰው ግጭትና አመጽ እስከ አሁን ባለው መረጃ ቁጥራቸው ከሰባ ያላነሰ ሰዎች መገደላቸውን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ምሆኑን፣ ብዙዎች መኖሪያ ቤታቸው ተቃጥሎ እና ንብረቶቻቸው የተዘረፈ መሆኑን፤ እንዲሁም የእምነት ተቋማት ላይ እና አማኒያን ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችም መድረሱን በተለያዩ ሚዲያዎች ሲገለጽ ቆይቷል።
በአንዳንድ የኦሮሚያ ክልል ከተሞችም ድርጊቱ አሁንም አለመቆሙን መረጃዎች ያሳያሉ። በዚህ ጉዳይ ላይ ይህን አመጽ በመቀስቀስም ሆነ በዜጎች ላይ ጥቃት በሰነዘሩ እና ለድርጊቱ ተባባሪ በሆኑ ግለሰቦች፣ ቡድኖች፣ የመንግስት ባለሥልጣናት፣ የማህበራት ወይም የቡድን መሪዎች እና የጸጥታ ዘርፍ አባላት ላይ ክስ ለመመስረት ስለሚቻልበት ሁኔታ አገር ወዳድ በሆኑ የሕግ ባለሙያዎች፣ የመብት ተሟጋቾች እና ሌሎች ልሂቃን ውይይት ተጀምሯል። ይህ ቡድን ዝግጅቱን አጠናቆ እና ጠበቆችን መድቦ ጉዳይ ወደሚመለከተው የፍትሕ አካላት እንዲቀርብ ለሚደረገው ጥረት መረጃ በማቀበል ትተባበሩን ዘንድ በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን።
+ ጥቃቶችን የሚያሳዩ የቪዲዮ፣ የድምጽ እና የፎቶ ማስረጃዎች፣
+ የተገደሉ ሰዎች ስም ዝርዝር፣ ዕድሜ፣ የሚኖሩበት ሥፍራ እና ድርጊቱ የተፈጸመበት ሥፍራ፣ ስለድርጊቱ ፈጸሚዎች ማንነት እና የአፈጻጸማቸው ሁኔታ፣
+ ድርጊቱ በተፈጸመበት ቦታ የመንግስት አካላት የነበራቸው ሚና፣
+ የመንግስት አካላት ጥፋቱን ለማብረድ የወሰዱት በጎ እርምጃዎች ካሉ፣
+ የወደሙ ንብረቶች አይነት፣ የዋጋ ግምት፣ ንብረቶቹ የወደሙበት አካባቢ እና በማን እና በምን አይነት ሁኔታ ንብረቶቹ እንደወደሙ፣
+ ሌሎችም በጥቃቶቹ ዙሪያ በጃችሁ የሚገኘውን ማስረጃ ወይም መረጃ በፌስ ቡክ ሜሴንጀር ወይም ከዚህ በታች ባሉት አድራሻዎች እንድትልኩልን በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን።
ተቆርቋሪ የመብት ተሟጋቾች መገናኛ ብዙሃን እና ለፍትሕ ተቆርቋሪ የሆናችው ሁሉ ይህን ጥሪ በማሰራጨት የበኩልዎን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ለወንጀል ፈጻሚዎች የሚደረግ ከለላ ሊቆም ይገባል!
Filed in: Amharic