>

የአዲስ አበባ መንግሥት? (ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ)

የአዲስ አበባ መንግሥት?

 

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ

 

ይህ የአፍሪካ መዲና፣ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፣ የዐለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ… አያሌ ኃላፊነቶች ደራርባ የያዘችው የአዲስ አበባ ድምጽ ነው። በስመ-ፌደራሊዝም፣ ዘውጌ-ብሔርተኞች የነጠቋትን የፖለቲካ መብቶች ለማስመለስ የሚደረግ የትግል ጥሪ ነው።

ኢሕአዴግ ከቀበራቸው የሰዓት ቦምቦች አደገኛው፣ አዲስ አበባን ተለዋዋጭ የፖለቲካ ካርድ አድርጎ ያበጀበት ሴራ ነው። ሥርዐቱ አስተዳደራዊ መዋቅሯንና የሥልጣን ገደቧን እንደ ‹አየር ሁኔታው› ሲቀያይረው ቆይቷል። ኦነግ የተካተተበት የሽግግር መንግሥቱ ዘመን፣ የ93ቱ ህንፍሽፍሽ፣ የምርጫ 97 ማግስት፣ ‹ማስተር ፕላኑ›ን በመቃወም በኦሮሚያ የተነሳው ሕዝባዊ ተቃውሞ… በዋነኛነት ይጠቀሳሉ። ከኦዴፓ ወደላይ መውጣት ጋር ደግሞ ውጥረትም አብሮ ጨምሯል። ከመግለጫ እስከ ገጀራ በአደባባይ ፎክሮባታል፤ አስፎክሮባታል። በተለይ ‹ቲም ለማ› ተሰንጥቆ፣ አንደኛው ቤተ-መንግሥት ሌላኛው ከጽንፈኞች መወዳጀቱ ሥርዐት አልበኝነቱን አንሮታል።

አዲስ አበባን የውጥረት መናገሻ ያደረጋት፣ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ መብቶቿ በ‹ገበሬ አብዮት› ሥልጣን በጨበጡ ካድሬዎች መነጠቋ ነው። እናም፣ ሰላም ለማስፈንም ሆነ ፖለቲካዋን ለማስከን የተሻለው አማራጭ ጥቃቅን ጉዳዮችን ወደጎን ማለት ነው። ከዚያም የተወሰደውን ማስመለስ፣ የተሻረውን መቀልበስ።

በዚህ ዐውድ አዲስ አበባን ከውዝግብ ለመታደግ ምን አይነት አስተዳደራዊ መዋቅር ሊበጅላት ይገባል? በሚለው ጥያቄና መፍትሔ ላይ እንወያያለን።

የንግሥት ከተማ

በወርሐ ሕዳር 1879 ዓ.ም ለዋና ከተማነት በእቴጌ ጣይቱ መታጨቷን ድርሳናቱ ዘግበውታል። አዲስ አበባ እንደሌሎቹ የአገሪቱ አካባቢዎች፣ ከሁለት ሺ ዐመት በላይ ኃይልን የተመረኮዘ ተፈራራቂ ሰፋሪዎችን ማስተናገዷ ይወሳል። የትላንት ጉልበታም በዛሬው፣ የዛሬው በነገው፣ የነገው… ተመላልሰውባታል። ጊዜ ያነሳው፣ ጊዜ የከዳውን አስገብሯል። ሁነቱ የሸገር ብቻ አይደለም። ከሰሜን እስከ ደቡብ ተከስቷል። ከሚሴ እና አዲስ አበባ ዙሪያውን በሌላ ብሔር በተከበበ መሬት ላይ የቁጥር የበላይነት የያዙበት ምስጢር መለኮታዊ ተዐምር አይደለም፤ የሀገረ-መንግሥቱ ምስረታ መውጣትና መውረድ ውጤት እንጂ።

ከመቶ ሰላሳ ሦስት ዐመት በፊት ዳግማዊ ምንሊክና ጣይቱን ወደ አራት ኪሎ ያሳፈረው ባቡር ለሺ ዐመታት በዚሁ ሀዲድ የተጓዘ ስለመሆኑ መከራከር ጉንጭ አልፋ ነው። ‹ተፈጥረዋል› የሚባሉት ሕፀፆችም አዲስ አይደሉም፤ ከራያ እስከ ሀረርጌ ተስተውለዋል። የማንነት ጭፍለቃውንም ቢሆን ያልቀመሰው፣ ያልተሞረደበት፣ የራሱን ወደ ሌላው፣ የሌላውን ወደ ራሱ ያልነለቀጠን ማግኘት ይቸግራል። እናም ከተማዋ በተበጀላት ፈስሳ፣ በራሷ መገለጫዎች የሚበየን አዲስ ማኀበረ-ማንነት ማንበሯ ተፈጥሯዊ መሆኑን አምኖ ለመቀበል እንገደዳለን። የባለ ርስትነት መከራከሪያ ጭብጥንም ዘንድሮ እንጂ፣ ጥንት ላይ መቸከሉ አልቦ-አመክንዮ ነው።

መረሳት የሌለበት ቁም ነገር አዲስ አበባን ጣይቱ ቢቆረቁሯትም፣ ዛሬ ለያዘችው ቁመና የከተማው ደሃ ራሱን እያቆረቆዘ የከፈለው ዋጋ ዋንኛው መሆኑ ነው። ተጎራባቿ የኦሮሞ አርሶ አደሮች፣ የግሪክ፣ አርመን፣ ህንድ፣ አረብ… ነጋዴዎች፣ ጣሊያን (ምክንያቱ የተለየ ቢሆንም) የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስዱ አንዘነጋም። የጠቅላላው የአገሪቱ ሕዝብ አስተዋፅኦም አይካድም። ይህንን ይዘን ለእቴጌይቱ አክብሮታችንን እንገልፃለን። ንግሥት ሆይ፡- እናመሰግናለን!

 

ከዘውዱ ወደ ደርጉ

 

መዲናችንን፣ ከቀዳሚው ከንቲባ ወልደፃዲቅ እስከ ታከለ ኡማ ድረስ በአስተዳዳሪነት ተፈራርቀውባታል። ከአገሪቱ የፖለቲካ ሥርዐት አኳያም አብዛኛው መሬቷ በባለአባቶች ተጠቅልሎ በመያዙ፣ የዐፄ ኃይለሥላሴ ፍፃሜ ድረስ ወሰኗን መለየቱ አደናጋሪ ሆኖ ቆይቷል።
አዲስ አበባ ሕዝባዊ (አካባቢያዊ) አስተዳደር የተበጀላት ከ1966ቱ ለውጥ በኋላ ነው። ወታደራዊው መንግሥት ወደ ሥልጣን በወጣበት ሰሞን፣ ዶ/ር ወንድሙ አበበ በተባሉ መሀንዲስ መሪነት ወሠን ለማካለል ተሞክሯል። ይህን ተከትሎም በአምስት ዞን፣ በ25 ከፍተኛ (ዘግይቶ 3 መጨመሩን ልብ ይሏል) እና በ285 ቀበሌዎች ተዋቅራለች። በሥልጣን ተዋረዱም የታችኛው እርከን (ቀበሌ) ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ጠንካራ የፖለቲካ ጉልበት አዳብሯል። እያንዳንዱ ቀበሌ ከአስተዳዳሪነቱ በተጨማሪ፣ የራሱ ፍርድ ቤት፣ የራሱ ፖሊስ (‹አብዮት ጠባቂ› የሚባል) እና እስከ ሦስት ወር የሚደርሱ ውሳኔዎችን የሚያስፈፅምበት የራሱ እስር ቤት የነበረው መሆኑ በማሳያነት ይጠቀሳል። ከ1979ኙ የሕዝብ ቆጠራ በኋላ ደግሞ በከንቲባ ኢንጂነር ዘውዴ ዘመን በፈረንሳይ ኩባንያ የተዘጋጀ የመጀመሪያው ‹ማስተር ፕላን› ይፋ ሆኗል። ይሁንና ከትግበራው ቀድሞ ሥርዓቱ በመውደቁ፣ ዕቅዱ ወደ መዝገብ ቤት አምርቷል።

ከወታደር ወደ አርሶ አደር

ከከተሜነት በራቀ ሥነ-ልቦና በተገሩ ወጣቶች የተመሰረተው ኢሕአዴግ በመንበሩ ተተክቷል። አራት ኪሎ በደረሰ ሰሞንም አገራዊ ‹ኮንፍረንስ› አዘጋጅቶ ነበር። ለሁሉም ዘውጌ የፖለቲካ ድርጅቶች የተሳትፎ ጥሪ ተላልፎ፣ ከሰኔ 24/1983 ዓ.ም እስከ ሐምሌ 24/1983 ዓ.ም ድረስ ያካሄደው ጉባኤ ሲጠናቀቅ ‹‹የኢትዮጵያ የሽግግር ወቅት ቻርተር›› በሚል የሰየመውን መንግሥት መመስረቻ ሰነድ አጽድቋል።
‹‹የዕድገት መሰረታዊ ሁኔታዎች የሆኑትን ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን ማናቸውም ዓይነት የጠላትነት ስሜቶችን ማስወገድ፣ በግጭቶች ምክንያት የተፈጠረ መቆሳሰል መሻርንና እንዲሁም መልካም ጉርብትናንና የመረዳዳት ግንኙነትን መመስረት የሚያስፈልግ በመሆኑ፤ […] ከባብያዊ አድልዎችን ማካካስና ማስቀረት አስፈላጊ በመሆኑ…›› በሚሉ ሽንገላዎች የሚጀምረው ቻርተር፣ የሩብ ክፍለ ዘመኑን የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ቧልታዊ-ገፅታ ያጎላበት አንቀጽ 17 እንዲህ ይነበባል፡-

‹‹ባለፉት መንግሥታት ሲሰራጭ የኖረውንና የሰረጸውን በዘረኝነት ላይ የተመሰረተ የጥላቻ አሉባልታ፤ እንዲሁም በሕዝቦች መካከል ዘረኛ ጥርጣሬ እንዲስፋፋ የተደረገውን ሥራ ለማስፋቅ ልዩ ጥረት ይደረጋል።››

እንዲህ ያሉት ኢሕአዴግና ኦነግ ናቸው። ወደ አዲስ አበባችን እንመለስ።

በአንቀጽ 2-ለ ‹‹በራሱ የተወሰነ መልክአ ምድራዊ ክልል ውስጥ የራሱን ጉዳይ በራሱ የማስተዳደር፤ እንዲሁም በማዕከላዊው መንግሥት ውስጥ በነፃነት፣ አድልዎ በሌለበትና ተገቢ በሆነ የውክልና አግባብ ውጤታማ ተሳትፎ የማድረግ መብት አለው›› በሚለው ድንጋጌ መሰረት፣ አዲስ አበባ ‹‹ክልል 14›› በሚል ቅፅል ሥያሜ ተጠርታ የሥርዓቱ አንድ አካል በመሆን ለአራት ዐመት ያህል ቆይታለች። በወቅቱ ከኦነግ እና ኦህዴድ በተጨማሪ፣ ከአምስት ያላነሱ የኦሮሞ ድርጅቶች በጉባኤው ተሳትፈው፣ ከተማዋ ራሷን ችላ በክልልነት እንድትዋቀር በፊርማቸው ማረጋገጣቸው በሰነዶች ላይ ሰፍሯል።
በ1984ቱ ምርጫ ጥቂት የግል ተወዳዳሪዎች ወንበር ከማግኘታቸው በቀር፣ በኢሕአዴግ ‹አሸናፊነት› ሲደመደም፣ ከተመሰረተው ምክር ቤት በተጨማሪ ‹ከፍተኛ› ተብሎ የሚጠራው መካከለኛ እርከን ‹ወረዳ› በሚል ተቀይሯል። ቀበሌ በነበረበት ቀጥሏል። ከላይ የተጠቀሰውን ‹ማስተር ፕላን›ንም ለመተግበር ሰፊ ውይይት ተካሄዶ ነበር። የክልል 14 (የአዲስ አበባ) ፕሬዚዳንት ተፈራ ዋልዋም ሆኑ የምክር ቤቱ አባላት እቅዱን አንብበው መረዳት የሚችሉበት ግንዛቤ ስላልነበራቸው፣ የቀድሞ ከንቲባ ኢንጂነር ዘውዴ ተጠርተው ማብራሪያ መስጠታቸውን ሰምቻለሁ። የከተማዋ ወሰን ከመሀሉ (ከሴንተሩ) ከ20-25 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ቢሆንም፣ ደርግ ያሰናደው ‹ማስተር ፕላን› 75 ኪሎ ሜትር ድንበር ጥሶ ናዝሬትን ጭምር ይጠቀልላል። በዕቅዱ ላይ እንደተዘረዘረው ከሸዋ አውራጃዎች የሚወሰደው መሬት ሰዎች የሚሰፍሩበት ሳይሆን፣ ለከተማዋ ገበያ የሚቀርቡ የእርሻና እንሰሳት ተዋጽኦ ግብዓት የሚውል ነው። በወቅቱ የኦሮሚያ ክልል አስተዳዳሪ አቶ ሀሰን አሊም ሆኑ ኦህዴድ ተቃውሞ አላሰሙም። አጀንዳውን የሚያስፈፅም ከሁለቱ እህታማች ክልሎች የተውጣጣ የጋራ ኮሚቴ እስከማቋቋም ተደርሶ ነበር። (ይህ ሲሆን ኦነግ በሕወሓት የአሻጥር-ግፊት ከመንግሥት ስለወጣ በጉዳዩ አልተሳተፈም።)

በሴራ የፈረሰ አስተዳደር

የምልዓት ስምምነት ያልነበረው ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 39፣ ‹‹ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከ መገንጠል ያለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለገደብ የተጠበቀ ነው›› ብሎ ቢደነገግም፣ ለ‹አዲስ አበባ ሕዝብ› የተሰጠው ራስን-በራስ የማስተዳደር መብት በግላጭ ተገርስሶ ‹ክልል 14› ፈርሷል፤ ከፌደራል ሥርዐቱም ተባርሯል። በአዋጁ አንቀጽ 14 ‹‹የብሔራዊ ክልላዊ ምክር ቤቶች ተጠሪነት ለመረጣቸው ሕዝብና ለማዕከላዊ የሽግግር መንግሥት የተወካዮች ምክር ቤት ይሆናል›› የሚለው መብቱ ተገፍፎ፣ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 49 ቁ.3 ‹‹የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተጠሪነቱ ለፌደራሉ መንግሥት ይሆናል›› በሚል ተተክቷል። ለከተማዋ ሕዝብ ‹ፖለቲካና ኮረንቲ በሩቁ› ያደረገው ደግሞ፣ አድሎኛና ገጠሬው ሕገ-መንግሥት እንኳ ያልሰጠው፣ ነገር ግን ‹‹የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁ. 87/1989 ዓ.ም›› አንቀጽ 10 ‹‹ስለ ምክር ቤቱ መበተን›› በሚል ርዕስ በቁ. 1 ላይ የተቀመጠው ነው፡-

‹‹የፌደራሉ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ምክር ቤቱን የማሰናበትና ከአንድ ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ የማድረግ ሥልጣን ይኖረዋል።››

በዚህ አይነቱ ቆረጣ ጠቅላይ ሚንስትር የሆነ ሁሉ፣ በከተማይቱ መስተዳደር ላይም የሚፈነጭበትን ‘ሕጋዊ’ ፍቃድ አግኝቷል። የአዲስ አበባ ሕዝብ ‹አስተዳድረኝ› ብሎ በድምፁ የወከለውን፣ የዐድዋ ነዋሪዎች የመረጧቸው አቶ መለስ ዜናዊ በአንድ ቃል ማባረር ይችሉ ነበር። በርግጥ፣ ‹ነበር› የሚለው ቃል አሳሳች ነውና ቢፍታታ መልካም ነው። ቻርተሩ በ1995 ዓ.ም አዋጅ ቁ.361 በሚከተለው ድንጋጌ ተሻሽሏል፡-

‹‹የከተማው ምክር ቤት ሊበተን የሚችለው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይም በእራሱ ውሳኔ ይሆናል።›› (አንቀጽ 17 ቁ.2)

ከጭልጋና ጅጅጋ፣ ከደምቢዶሎና ጋምቤላ፣ ከመቀሌና ባሌ… ኮሮጆ ገልብጦ ፓርላማ የገባ በሙሉ፣ አዲስ አበቤ የመረጠውን፣ በራሱ ቋንቋ ‹ንካው…› ወደሚልበት መቀየሩ ‹አልሸሹም ዙር አሉ› ነው።
ለዚህ የተሰጠው ምክንያት ሕገ-መንግሥቱ ብሔርን እንጂ ሰውን አለማየቱ ነው። ፌደራሊዝሙ ቋንቋ እንጂ ሕዝብን አለማወቁ ነው። እውነታው ግን በሸገር ቆምሮ የኃይል ሚዛንን ማስጠበቅ እንጂ፣ የሚሉት አይደለም። ለዚህም ደግሞ ማስረጃው በመልከዓ-ምድር የተዋቀሩት የደቡብ እና የጋምቤላ ክልሎች ናቸው። የሐረሪ ምክር ቤት የሥራ ቋንቋም አማርኛ እንደሆነ እያሰላሰልን እንቀጥል።

በርግጥም የ‹አራዳ ልጅ› መምረጥ እንጂ መመረጥ እንዳይችል፣ በመረጠውም እንዳይተዳደር ‹ሿሿ› ተሰርቷል። የምክትል ከንቲባ አመራረጥም በዶ/ር ዐቢይ ተሻሽሏል። ክፍለ ከተማዎች ከተዋቀሩ ጀምሮ የተፈራረቁት ዋና ሥራ-አስፈፃሚዎችም ከየክፍለ ሀገሩ የተሰባሰቡ ናቸው። ምናልባት ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ የተካሄደው የኃይል ማፈናቀል ፖሊሲ ትግበራ የቀለለበት ገፊ-ምክንያት ከዚህ ጋር የተያያዘ ይሆን? የሚያጠናው ከተገኘ ደህና ርዕስ ነው። ከተማና ገጠር በብዙ ጉዳዮች ሰፊ ልዩነት እንዳላቸው ልብ ይሏል።

‹ልዩ ጥቅም›

የኦሮሞን ፖለቲካ አዛብቶና አዛንፎ፣ አጋንኖና ለጥጦ በማበጀቱ ረገድ የብሔሩና የሕወሓት ልሂቃን ቁንጮዎች ናቸው። ሲሻው ‹ልዩ ጥቅም አለኝ› የሚል፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ የባለቤትነት ጥያቄ አንስቶ የሚያምታታ አድርጎታል። ሕወሓት ይህንን አጀንዳ ወደ ሕገ-መንግሥቱ አቅጥኖ የሰነቀረው፣ በ‹እሳት› እና ‹ጭድ› ያቧደነውን ማኀበረሰብ እንደ‹ተዞረበት› ለማቆየት አስልቶ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የኦዴፓና የብሔሩ ልሂቃን እርስ-በርስ በገጠሙት መተናነቅ፣ አንዱ ሌላውን የሚያጠቃበት ‹ፈንጂ-ወረዳ› አድርገውታል። የዶ/ር ዐቢይ አህመድ ፈተና፣ የኢንጂነር ታከለ ኡማ የመልቀቂያ ደብዳቤ፣ የውህድ-ፓርቲው ደንቃራ… እዚህ ተቦክቶ፣ እዚህ የተጋገረ ነው። ሁለቱን ብሔሮች ማጋጨት ለውስጠ-ፓርቲ ትግል ተመራጭ ስልት ሆኗል። በአናቱም ከተማይቱ ‹የፌደራል መቀመጫ ናት› ከመባሉ በዘለለ፣ በሕገ-መንግስቱም ሆነ በተከታታይ በወጡ ቻርተሮች የሥልጣን ገደቧና ባለቤትነቷ አለመብራራቱ የጠርዘኛ ብሔርተኞችን መሬት የመዋጥ አምሮት አንሮታል።

የሆነ ሆኖ ‹ልዩ ጥቅም› የሚባለው ምናምንቴ በሰነዱ ውስጥ ከመካተቱ በፊት የሕገ-መንግሥቱን ረቃቅ ለማፅደቅ የተሰባሰበው ቡድን ተወያይቶበታል። የውይይቱን መንፈስ ከ‹ቃለ-ጉባኤ›ው ብንመለከት ዛሬ ከሚጦዝበት በእጅጉ የራቀ መሆኑን እንረዳለን። በግል ተመርጠው ጉባኤውን የተቀላቀሉ ተወካዮች፣ ‹ሃሳቡ መነሳቱ ራሱ ስህተት ነው› በሚል ለሰነዘሩት ጠንካራ ተቃውሞ፣ ኦሮሚያን ወክለው የተሳተፉት አቶ ተሰማ ጋዲሳ የሰጡት ምላሽ ሁነቱን ለማብራራት ያግዛል፡-

‹‹የኦሮሚያ ጥቅም ይጠበቃል ሲባልም በፅሕፈት ቤት አቅርቦትና በመሳሰለው እንጂ እንደተባለው በግብር የመሰብሰብ ጉዳይ ንዑስ አንቀጹን አዛብቶ ከመረዳት የሚመነጭ ትንቢት [ነው]›› (ቅጽ 4)
የአዲስ አበባ መስተዳደር በተቋቋመበት የመጀመሪያው ቻርተር አንቀጽ 33 ላይ ‹‹በአዲስ አበባ ስለኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ልዩ ጥቅም›› በሚል ርዕስ-ሥር የተዘረዘሩት አራት ነጥቦችም ግልፅ ናቸው። 1 እና 2 ስለወሰን አከላለልና የኦሮሚያ መቀመጫነትን በተመለከተ የሚያወሩ በመሆኑ ስለማያወዛግቡ እንለፋቸው፤ የተቀሩት እንሆ፡-
‹‹3- የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ለአዲስ አበባ ሕዝብ የሚያቀርባቸው አገልግሎቶች በመስተዳድሩ አዋሳኝ ለሚኖረው የኦሮሚያ ክልል ሕዝብ ሊዳረሱ የሚችሉ ሲሆን ነዋሪዎቹ በተመሳሳይ ሁኔታ የአገልግሎቶቹ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደረጋል።

‹‹4- የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ለአዲስ አበባ ሕዝብ ከሚያቀርባቸው አገልግሎቶች ጋር የተያያዙ የልማት ሥራዎችን በኦሮሚያ ክልል ውስጥ መሥራት የሚችለው በቅድሚያ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጋር በመመካከርና በመስማማት ይሆናል።››

እነዚህ አንቀጾች ‹አሻሚ ናቸው› ብሎ የሚደናገር ያለ አይመስለኝም። ‹ባለቤትነት›ን በተመለከተ ያሰበውም አልነበረም። መቼም ከ97 በመቶ በላይ ባድማ የነበረን መሬት ረምርመው፣ ጨፌውን ደልድለው፣ ዱሩን መንጥረው፣ መንገድ ጠርገው የገነቡትን የገዛ አገራቸውን ከተማ፣ አንድ ዘውግ ድንገት ተነስቶ ‹የእኔ ነው› ማለቱ በሕግም፣ በ‹ሎጂክም› ተቀባይነት ይኖረዋል ማለት ዘበት ነው። ‹መሬት የመንግሥት ነው› የሚል ሕገ-መንግሥት፣ ‹የሚሻሻለው በመቃብሬ ላይ ነው› ሲሉ ዝተው ሲያበቁ፣ በጓሮ ዞሮ ደግሞ ‹መሬቱ ድሮ የምንጅላቴ ነበር› ክርክር ለ‹ኮሜዲ› ነው የሚቀርበው።

ዋናው ጉዳይ የአዲስ አበባ ኢኮኖሚ በጠነከረ ቁጥር፣ የፊንፊኔ ዙሪያ አርሶ አደሮች በሌላው የአገሪቱ አካባቢዎች ከሚገኙ አርሶ አደሮች በተለየ ተጠቃሚ የመሆናቸው እውነታ ነው። ሰፊ የገበያና የሥራ ዕድልን ጨምሮ፣ በተለያየ መንገድ የበረከቱ ተቋዳሽ የሚሆኑበት ልዩ ጥቅም እንደሚፈጥርላቸው አይጠረጠርም።

‹ክልል ነበርን፣ ክልል እንሆናለን!›

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኃላፊነት በጎደላቸውና በላዔሰባዊ-ዝማሜ በተጫናቸው ‹አክቲቪስቶች› እና ፖለቲከኞች አዲስ አበባ ወደ መከራ-ቋትነት እየተገፋች ነው። ለእንዲህ አይነቱ ችግር በቀዳሚነት አቶ ጃዋር መሐመድ ይጠቀሳል። ከዚህ ቀደም ያስተላለፈውን አጥፊ የክተት ጥሪ ወደጎን ብንለው እንኳ፣ ሰሞነኛውን የእልቂት ‹ጽንሱ›ን ሳልጠቅስ ማለፍ አይቻለኝም። የሰውየውን ጭካኔና የነጠፈ ሰብዓዊነት የሚያስረግጠው ለህልፈታቸው ምክንያት የሆናቸው ወጣቶች በረገፉበት ቀውጢ ሰዓት እንኳ በርካታ የሚዲያ ካሜራዎች ፊት ቢቀርብም፣ ስለራሱ ከመደስኮር ባለፈ ቅንጣት ሀዘኔታ እንደተሰማው ለማሳየት አለመፍቀዱ ነው። ሌላው ነገር ቦሌ ተቀምጦ፣ ጉለሌና ባሌን ‹ቦስንያ› የማድረግ ‹ፕሮጀክት› አእላፍ ‹ጂኒ›ዎችን የመቀስቀሱ እውነታ ነው። ማን ያውቃል? አንዱ በቆፈሩት ጉድጓድ የሚከት ይሆናል?

በዶ/ር ዐቢይ አህመድ እና አቶ ለማ መገርሳ መሀል የተፈጠረው ስንጥቃትም ለሴራ ፖለቲካ አመችቷል። ኢትዮጵያዊነትን አቅል-ከሚያስት የሀሽሽ ሱስ ጋር ያነፃፅር የነበረ ሰው ‹ተገፋሁ› በሚል የግል-ጉዳይ ወደኋላ ዞሯል ሲባል ያስደነግጣል። አልፎ-ተርፎም የዜጎች እልቂት በሚመራበት ጥቁር መስመር ላይ ሲቆም፣ ‹ኦፍ ሳይድ› ብሎ ብቻ ማለፍ ይቸግራል። መቼም በግላጭ የለቀቁትን ‹መሰላል› በሸፍጥ ለመሳብ መሞከር፣ ‹የላይኛውን ብቻ አፍርጦ አለመስከኑን መረዳት የፖለቲካ ሀሁ ነው።

ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ፣ አዲስ አበባ ዋንኛ የፀብ ሜዳ ሆናለች። ሰገነቱን የሞሉት አክራሪ-ብሔርተኞች ‹በአገሪቱ ሁለት መንግሥት ነው ያለው፤ የቄሮና የዐቢይ› እስከማለት ከመድፈር በዘለለ፣ የከተማውን ነዋሪ ህልውና የካዱ ድርጊቶችን ደጋግመው ፈፅመዋል። በጥቂቶች የሚታጀብ ተቃውሞ ሰልፍ በሚከለከልበት መዲና፣ ገጀራና ቆንጨራ ለታጠቁ ወጣቶች፣ ያውም ፀረ-ሕዝብ ሰልፍ ማካሄድ ሙዝ የመላጥ ያህል አቅልለዋል። በአንድ ወቅት የከተማውን ወጣቶች ሰላማዊ ጥያቄ ማፈን ዒላማ ያደረገው የ‹አደገኛ ቦዘኔ ሕግ› ዛሬም በ‹ህይወት› መኖሩ የድራማው አስቂኝ ክፍል እንደሆነ ለተከበረው ዐቃቢ-ሕግ ማስታወስ እወዳለሁ። ከ1997 ዓ.ም በፊት ተጠሪነቱ ለፌደራል ፖሊስ የነበረው የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ በድኀረ-ምርጫ ወደ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ የዞረ ሲሆን፣ ዶ/ር ዐቢይ አህመድም ባላየ አልፈውታል።

የሆነው ሆኖ መሬት የረገጡ እውነታዎች የሚነግሩን ከዚህ በኋላም በተደራጁ ቡድኖች ከሚሰነዘር ጥቃት ‹የሚታደግ አለ› ብሎ መዘናጋቱ ለማይታረም ስህተት መዳረጉን ነው። እየመከርኩህ ያለው ጉዳይ ‹የመንግሥትን ኃላፊነት ተወጥቼ፣ ራሴን ከጥቃት እከላከላለሁ› ወደሚል መደምደሚያ እንድታዘነብል አይደለም። እንዲህ አይነቱ ግብረ-ምላሽ አደገኛ አደጋ ያስከትላል። ይህ ከፍርሃት ጋር አይያያዝም፤ አርቆ አሳቢነት እንጂ። በተረፈ የአዲስ አበባን ልጆች ቁርጠኝነትና ጀብደኝነት የተጠራጠረ የኢሕአፓን የከተማ ውስጥ የትጥቅ ትግል ታሪክ መለስ ብሉ ቢቃኝ መልካም ነው። የኢሕአፓ አብዛኛው አመራር ከተለያየ የአገሪቱ አካባቢ እንደመጣ ባይካድም፣ ከሰለጠነና እስከ አፍንጫው ከታጠቀ የመንግሥት ሠራዊት ጋር ፊት-ለፊት ተጋፍጠው፣ በሸገር ጎዳና ተጋድሎ ከፈፀሙት እጅግ የሚበዙት የእኛ ልጆች ናቸው። እናም ‹ከተማዋ የሁሉም ኢትዮጵያዊ መኖሪያ እንጂ፣ መደባደቢ እንድትሆን አንፈቅድም› ወደሚሉበት ትዕግስት አስጨራሽ ትንኮሳ ከመግፋት መታቀብ ይመከራል። በነገራችን ላይ የሸገር የወል መስተጋብር የትኛውንም ብሔር አይወክልም። ዛሬ የያዘውን ቅርፅ የሰጠውም የባህል መመሳሰል አይደለም። ከእድርና ዕቁብ ጀምሮ የተለያዩ የጋራ ግንኙነቶች ክዋኔ ባዋለዱት ማኀበራዊ ሕይወት ላይ መመስረቱ እንጂ።

በዚህ ዐውድ የቀረበው ብቸኛ መፍትሔ አዲስ አበባን ለማያውቋት ካድሬዎች መቀለጃ፣ ለሕገ-ወጦች መፈንጪያ የዳረጋትን የፌደራል መንግሥት፣ በከተማው ላይ የያዘውን ሥልጣን አስጥሎ ሕገ-መንግሥቱን ማስከበር ነው። ይህንን ለማሳካት በተደራጀና በተቀናጀ ትግል አስተዳደራዊ መዋቅሩን እንደ ከዚህ ቀደሙ ክልላዊ ማድረግ ይጠይቃል። ይህ አይነቱ መንገድ የፌደራሉን ወመኔነት ከማስቀረቱም በላይ፣ ከጠርዘኛ የመሬት ቀበኛ ኢምፔሪያሊስቶች ይታደጋል። ለዚህ ደግሞ በሽግግር መንግሥቱ ዘመን ክልሎች የተዋቀሩበት አዋጅ (7/1984)፣ የሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 47 እና 49 ይደግፍሀል። ከ1989 እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ የተሻሻሉ ቻርተሮች የነዋሪውን ራስን-በራስ የማስተዳደር ሙሉ ስልጣን አለመካዳቸውም በማስረጃነት ይቆጠራሉ።

ሚዲያ ላይ ቀርበው ‹ሕገ-መንግሥቱ የአዲስ አበባን ሕዝብ አያውቀውም› ለሚሉ ወንድሞቻችንን እያዘንን፣ ከዚያው ሰነድ የሚመለከተንን እንምዘዝ። ክልል ለማዋቀር በአንቀጽ 47 ቁጥር 3 የተቀመጡት አምስቱ መስፈርቶች የሚከተሉት ናቸው፡-

‹‹ሀ- የክልል መመሥረት ጥያቄው በብሔሩ፣ በብሔረሰቡ ወይም በሕዝቡ ምክር ቤት 2/3ኛ ድምፅ ተቀባይነት ማግኘቱ ሲረጋገጥ ጥያቄው በጽሑፍ ለክልሉ ምክር ቤት ሲቀርብ፣

ለ- ጥያቄው የቀረበለት የክልል ምክር ቤት ጥያቄው በደረሰው በአንድ ዓመት ውስጥ ለጠየቀው ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ሕዝበ ውሳኔ ሲያደራጅ፣
ሐ- ክልል የመመሠረት ጥያቄ በብሔሩ፣ በብሔረሰቡ ወይም ሕዝቡ ሕዝበ ውሳኔ በአብላጫ ድምፅ ሲደገፍ፣

መ- የክልል ምክር ቤት ሥልጣኑን ለጠየቀው ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ሲያስረክብ
ሠ- በሕዝበ ውሳኔ የሚፈጠረው አዲስ ክልል ጥያቄ ማቅረብ ሳያስፈልገው በቀጥታ የኢትዮጵያ ፌደራል ዴሞክራሲዊ ሪፐብሊክ አባል ሲሆን ነው።››
እነዚህን ማረጋገጫዎች ይዘን ሁለት አንጓዎችን እናንሳ፤ የመጀመሪያው በአምስቱም ነጥብ ላይ ስለ መብቱ ተጠቃሚዎች የተገለፀው ‹‹በብሔሩ፣ በብሔረሰቡ ወይም በሕዝቡ›› የሚል አማራጭ በመስጠት የአዲስ አበባ ሕዝብንም ማካተቱ ነው። ሁለተኛው፣ ስለእነዚህ ሦስት አካላት ማንነት በአንቀጽ 39 ቁጥር 5 ከሰጠው ብያኔ ነው፡-
‹‹በዚህ ሕገ መንግሥት ውስጥ ‹ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ› ማለት ከዚህ ቀጥሎ የተገለፀውን ባህርይ የሚያሳይ ማኀበረሰብ ነው። ሰፋ ያለ የጋራ ጠባይ የሚያንፀባርቅ ባሕል ወይም ተመሳሳይ ልምዶች ያላቸው፣ ሊግባቡበት የሚችሉበት የጋራ ቋንቋ ያላቸው፣ የጋራ ወይም የተዛመደ ሕልውና አለን ብለው የሚያምኑ፣ የሥነ ልቦና አንድነት ያላቸውና በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓ ምድር የሚኖሩ ናቸው፤››

ከ5 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የሚኖርባት አዲስ አበባ፣ ክልል ለመመስረት በቅድመ ሁኔታ የተጠቀሱትን ሁሉንም መስፈርቶች ታሟላለች። ነጣጥለን እንያቸው፤ ‹የጋራ ባሕል ወይም ተመሳሳይ ልማዶች› ለተባለው በግርድፉ ‹ከተሜነት› የሚል ምላሽ አስቀምጦ ማለፉ ያስማማል፤ (ወደፊት በአዲሱ ፓርቲ ይዘረዘራል።) ለሁለተኛው እንኳ ‹ሊግባቡበት የሚችሉበት የጋራ ቋንቋ› እንጂ፣ የአፍ መፍቻ አለማለቱን ካስታወስን በቂ ነው። የሕልውናችን ተዛምዶም ማብራሪያ የሚፈልግ አይመስለኝም። አራተኛ ላይ ላለው ‹የሥነ ልቦና አንድነት›፣ በአጭሩ የዜግነት ፖለቲካ ማቀንቀናችን መለዮ ይሆነዋል። አምስተኛውን እናንተው ጨርሱት።

አዲስ አበባ እንደ ነዋሪዎቿ ከተሜ አስተደደር ያስፈልጋታል። እየሸራረፉት ካለው የህልውና ስጋት በአስተማማኝ መልኩ መታደግ የሚቻለውም ሆነ የፖለቲካ ተሳትፎና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሚረጋገጠው መሰረታዊ የመዋቅር ለውጥ ሲመጣ ብቻ ነው። ይህንን አጀንዳ ውህድ-ፓርቲው ይፈታዋል ብሎ መዘናጋት ካሳለፍናቸው ስህተቶች አለመማር ነው። ‹ይሁን› ቢባል እንኳ ዛሬ ሥልጣን የጨበጠ፣ ነገ የመልቀቁን አይቀሬነት አንዘነጋም። የእንዲህ አይነቱ ጉዳይ ዋስትና ተቋማዊ በሆነ መንገድ መቋጨቱ ብቻ ነው። ለአንዳንድ አጨቃጫቂ ጉዳዮች የዐለም አቀፍ ተሞክሮዎችን መጠቀም ይቻላል።

የ‹ብራሰልስ ሞዴል›

የአዲስ አበባ አወዛጋቢነት ከሞላ ጎደል ከታሪካዊ ባለቤትነትና ከምስረታዋ በበለጠ መስፋፋቷን የተንተራሰ ነው። የመጀመሪውን በተመለከተ በቂ ሰነዶችና የመከራከሪያ ጭብጦች ስላሉ፣ ተጻራሪው መሟገቻ ባዶ-ቀልሀ ከመሆን አይዘልም። ሁለተኛው ግን፣ ምናልባት ቢስተባበል እንጂ የሚካድ አይደለም። በተለይ በድኀረ-ደርግ አርሶ አደሮችን በማፈናቀል አዋሳኝ መሬቶችን የመጠቅለል ዝማሜ ታይቷል።
ይህንን ችግር የ‹ብሔር ነጋዴዎች›ን ገለል አድርጎ፣ ከነዋሪዎቹ ጋር በመነጋገርና በመደራደር፣ በሰጥቶ መቀበል መፍታት አያዳግትም። የከተማይቱ ድሆች እና የፊንፊኔ ዙሪያ አርሶ አደሮች ዋንኛ ጥያቄ፣ ኢኮኖሚያው ተጠቀሚነትና በቀዬ የመኖር ዋስትና ነው። ቋንቋ የግጭት መነሾ አይሆንም። ትልቅ ከተማ በገበያ እንጂ፣ በቋንቋ አይመራም። ያም ሆኖ ከክልል እስከ ወረዳ ባሉ አደረጃጀቶች የነዋሪውን ፍላጎትና ውሳኔ ያከበረ የአስተዳደር መዋቅር የመፍጠር ግዴታ መዘንጋት የለበትም።

አውሮፓዊቷ ቤልጂየም ዘርና ቋንቋ-ነክ ችግሮቿን የፈታችበት መንገድ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን፣ ኢትዮጵያን እየፈተኑ ላሉ ተግዳሮቶች መፍትሔ ይሆናል። ቋንቋን ተመርኩዞ የተዋቀረውና በሦስት ክልሎች (ፍላንደርስ፣ ዋሎኒያ እና ብራሰልስ) የተከፋፈለው የፌደራል ሥርዐቷ፣ ከዴሞክራሲው በቀር እኛን ከገጠመን ጋር ይመሳሰላል። ከሆላንድ ቅኝ-አገዛዝ በ1830 ዓ.ም (እ.አ.አ.) ነፃ በወጣች በዐመቱ ያፀደቀችው ቋንቋን መሰረት ያደረገ ሕገ-መንግሥት እስከ 2001 ዓ.ም (እ.አ.አ.) ስምንት ጊዜ ተሻሽሏል። የሦስቱም ማኀበረሰቦች ቋንቋ፣ በመንግሥት በዕኩል ይታያል። ዋንኛዎቹ ጎሳዎች ‹‹ዋሎንስ (Walloons)›› እና ‹‹ፍለሚንግስ (Flemings)›› የራስ አስተዳደር መብታቸው ቢረጋገጥም፣ በጋራ በሚኖሩበት የብራሰልስ ክልል ቋንቋ፣ ዘርና ብሔራዊ ማንነትን የተንተራሰ ፍጥጫ ውስጥ ሲገቡ ይስተዋላል።

የፌደራል መንግሥት ዋና ከተማነትና የአውሮፓ ሕብረት መቀመጫነትን ደርቦ የያዘው የ‹ብራሰልስ ክልል› (Brussels-Capital Region) አወቃቀር፣ ለአዲስ አበባ ሞዴል ይሆናል። በአገሪቱ አብላጫ ቁጥር ያላቸው ፈረንሳይኛ ተናጋሪዎቹ ‹‹ዋሎንስ (Walloons)›› እና ደች (ፍላሚሽ) የሚያወሩት ‹‹ፍለሚንግስ (Flemings)›› ናቸው። ጀርመንኛ ተናጋሪ ህዳጣኖችም አሉ። ከአገሪቱ ሕዝብ 56 በመቶ የሚሆኑትና የ‹ብራሰልስ ክልል› የተመሰረተበት ‹መሬቱ የኛ ነው› የሚሉት ‹ፍላሚሾች›፣ ዋና ከተማው ባለበት ክልል ውስጥ ህዳጣን ጎሳ በመሆናቸው፣ ከአብላጫው ‹ዋሎንስ› ጋር እሰጥ-አገባ ደጋግመው ፈጥረዋል። የብራሰልስ ክልል የታችኛው አስተዳደራዊ እርከን ሳይቀር ቋንቋን መሰረት አድርጎ የተዋቀረበት ገፊ-ምክንያትም ይህ ነው። ቶኒ ቶሀሩዲን የተባሉ ጸሐፊ ‹‹Individualism, nationalism, ethnocentrism and authoritarianism›› በሚል ርዕስ ባሰናዱት ጥናት፡-

‹‹ደች፣ ፈረንሳይኛ እና ጀርመንኛ ከ1961 ዓ.ም ጀምሮ የሥራ ቋንቋ መሆናቸው በሕግ ቢደነገግም፣ ብሔርንና ቋንቋን መሰረት ያደረገውን አግላይነት ማስወገድ ግን ቀላል አልሆነም›› ሲሉ ሁነቱ የሕግ የበላይነት በሰፈነበት አውሮፓም አስቸጋሪ እንደሆነ ይሞግታሉ።

 

የአዲስ አበባ ክልላዊ መንግሥት?

ከተማይቱን በክልል ደረጃ ለማዋቀር ብርቱ ትግልን ይጠይቃል። ሰፊ የማንቃት ሥራ መፈለጉና በአስቸጋሪ ፈተናዎች የማለፉ አይቀሬነትም ተገማች ነው። የድሉን ዕድሜ ለማሳጠር እንደ ‹ባልደራስ› ያሉ ‹ፎረሞች›ን በብዛት መመስረት ወሣኝ ነው። እነዚህን መሰል ድርጅቶች ጥናታዊ ጽሑፎችን በገፍ እያሰናዱ በአጀንዳው ላይ ብዥታ የሚፈጥሩ ጉዳዮችን ለማጥራት መስራታቸው መንገዱን ያቀልለዋል። መንግሥት ሳይናጋ፣ ሰላም ሳይደፈርስ፣ የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት ውይይቶችን ማካሄድ፣ በዙሪያው ካሉ የኦሮሞ ተወላጆች ጋር ስለ ወል ተጠቃሚነት መደራደር፣ መግባባት፣ መስማማት ቀዳሚ የቤት ሥራ ነው። በአካባቢው ያሉ የገጠር ነዋሪዎች ህይወት ሊቀየር የሚችለው የግንኙነት መስተጋብሩ ከአዲስ አበባ ጋር ሲጠብቅ እንደሆነ መተማመን ያስፈልጋል። በተለይ፣ ከእነሱ የኢኮኖሚ ባህል አኳያ ግብርና-መር ኢንዱስትሪያላይዜሽን እንዲስፋፋና ተመጋጋቢ ዕድገት እንዲኖር የሚያስችል ዕቅድ የሰጥቶ-መቀበሉ አካል ማድረግ ለቅቡልነት ያግዛል። የብሔረሰቡ ባህልና ቋንቋ እንዲዳብር መደገፍ እና ኢንቨስትመንት ማበረታታት ላይ አተኩሮ መስራትም ነጥብ ያሰጣል። የሕዝቡን ፍላጎትና ውሳኔ ባከበረ መልኩም አስተዳደራዊ መዋቅሩን ለመዘርጋት መስማማት ግድ ይላል። ባህልን ከማኀበራዊ ሕይወት ነጥሎ የሚያየው ከተሜ፣ በአቻቻይ ፖለቲካ ለሁሉም ችግሮቹ እንደ ባሕሪያቸው መፍትሔ መቀመሩ አይነሳውም። በነገራችን ላይ አዲስ አበባን እና ኦሮሚያን የሚያጋጨው የከተማዋ እየተለጠጠች መሄድ፣ ወደ ክልልነት ስትቀየር ስለሚቆም ዘላቂ መፍትሄ ማምጣቱንም ከግምት መግባት አለበት። ከተማ እንጂ ክልል አይስፋፋም።

በመጨረሻም፣ በቀጣዩ ምርጫ በሸገር የሚወዳደሩ ፓርቲዎች ይህንን ጥያቄ በፕሮግራማቸው ቢያካትቱት አንድ እግርን ወደ መዘጋጃው ጽ/ቤት የማስገባት ያህል እንደሆነ በትህትና አስረዳለሁ። አሊያም ደግሞ አዲስ አበባን ክልል የማድረግ አጀንዳ የቀረፀ አዲስ ፓርቲ አቋቁሞ አራዳ ላይ ለመንገሥ ቀላሉ መንገድ ይህ ነው። በድምጽም በትግልም ሚሊዮኖችን ማሰለፍ ያስችላልና። ከተማይቷን የፖለቲካ ‹ሙት መሬት› ያደረገውን ሕገ-መንግሥት መገፍተሪያው ጊዜ ደርሷል። ጎሳን ጥለን፣ ከተሜነትን አንጠልጥለን መደራጀት ብቸኛ አማራጭ ሆኗል። በአዲስ አበባ ጉዳይ የማረቆ ወይም የኢሮብ ካድሬ የሚወስንበት የረገጣ-አገዛዝን በዚህ መንገድ አሰናብተን፣ ሳናንቀላፋ የምንጠብቀውን አስተዳደር እንተክላለን።

Filed in: Amharic