አቻምየለህ ታምሩ
የኦነጋውያንን የፈጠራ ታሪክ በአሕመዲን ጀበል በኩል የሃይማኖት ካባ ለብሶ ስለቀረበ ብቻ ያለስስት ሲጋተውና ሲያስተጋባው የከረመው ሁሉ እየተነሳ ቀደም ብዬ ባተምሁት ጽሑፍ ላይ የዘረዘርኳቸውን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ሙስሊም ባለሥልጣናትን ስም ዝርዝር ከየት አምጥቷቸው ነው እያለ ሰው ሊያሳስት ይኖክራል።
ከሁለት ሳምትን በፊት በጃዋር ቴሌቭዥን የቀረበ አንድ የሶማሌ ብሔርተኛ ዶክተርም ከሽማግሌ የማይጠበቅ ነጭ የፈጠራ ታሪኩን አብዝቶ ይዋሽ ነበር። ይህ ሰውዬ በጃዋር ቴሌቭዥን ያሰራጨውን የፈጠራ ታሪክ ከአንድ ዓመት በፊት ላይብራሪ ኦፍ ኮንግረስ ያገኘኋቸው አንድ የሶማሌ ብሔርተኛ የሆኑ አዛውንት የላይብራሪው ሰራተኛም በመድገም «ከ“አብዮቱ” በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ «አንድም የሙስሊም ባለስልጣን አልነበረም» ብለው በድፍረት ተከራከሩኝ።
ግና የምንኖርበት ዘመን የማይዋሽበት በመሆኑ ካሰባሰብዃቸው ዶሴዎች መካከል ከጉዳዩ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለውን ሰነድ አውጥቼ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በ1948 ዓ.ም. ሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት ብቻ የሾሟቸውን የሶማሌ፣ የአደሬና ኦሮሞ ሙስሊም ባለስልጣናት ብዛት አሳየኋቸው። ገረማቸው! «አይ የእኛ ትውልድ ያለ እውቀት ብዙ ሰው አሳስተናል» አሉ። መጨረሻ ላይ አንተ ግን «ወላሂን አፉ በለኝ» ብለውኝ ተለያየን።
«ይህን ያህል ብዛት ያለው የሙስሊም ባለሥልጣናት ቁጥር በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ነበር ወይ?» ብሎ የሚጠራጠር ሰው ቢኖር በ1948 ዓ.ም. «ስለ ሹመት የወጣ የመንግሥት ማስታወቂያ» በሚል በነጋሪት ጋዜጣ ላይ የወጣውን የሹመት ዝርዝር ፈልጎ ያንብብና ያረጋግጥ! ካረጋገጠ በኋላ የኅሊና ሰው ከሆነ ውሸት ሲያስተምሩና ሲያሳስቱት ለኖሩት ቀጣፊዎች «ኢትዮጵያን አታውቋትም» ይበላቸው!
ሀገር ለመመሥረት ጫካ የገቡ ኦነጋውያን የፈጠረቱን ትርክት አሕመዲን ጀበል የሃይማኖት ቡልኮ አልብሶ እንካችሁ ያለውን ፕሮፓጋንዳ ሁሉ ሳይመረምር እንደ እውቀት ያለስስት የተቀበለው አፍ ነጠቅ ሁሉ እየተነሳ ስለ አባቶቻችን ኢትዮጵያ በጻፍንና በተናገርን ቁጥር «ሙስሊም እንደሁለተኛ ዜጋ ተቆጥሮ መብቱ የተገፈፈበትን ዘመን፤ ለሙስሊሙ የጭቆና ተምሣሌት የኾነውን ዘመን፤ ሙስሊሙ ሁለተኛ ዜጋ የኾነበትን ዘመን የሚናፍቅ» በማለት ሊከሰን ይፈልጋል። እንደዚህ ብሎ የሚከሰኝ ሐጂ ኢትዮጵያን ከዓለም ነጥሎ በማውጣት፣ በሌሎች ሀገሮች በእስልምና ውስጥ የነበረውን የክርስትና ይዞታ በኢትዮጵያ ክርስትና ውስጥ ከነበረው የእስልምና ይዞታ ጋር በተወሰነ ደረጃ እንኳ አነጻጽሮ ለማየት ሳይችል ነው። እስቲ በአንድ እስላማዊ መንግሥት ውስጥ የክርስትናን አያያዝ ወይንም እንግዳው እስልምና ነባሩን ክርስትና እንዴት እንዳደረገው የተወሰኑ ሀገሮችን ታሪክ ወስደን እንይ! በሳውዲ እስልምና ውስጥ ክርስትና ፈጽሞ ቦታ የለውም። በሳውዲ እስልምና ውስጥ አይደለም ክርስቲያን ሊሾም መኖርም አይችልም።
በቱርክስ ቢኾን! በቱርክ እስላማዊ መንግሥት ውስጥ ክርስትና ቦታ የለውም። በቱርክ ውስጥ እንግዳው እስልምና ነባሩን ክርስትና ከምድረ ገጽ አጥፍቶታል። ኢትዮጵያ እስከ 1966 ዓ.ም. ድረስ ክርስቲያናዊ መንግሥት የነበረችው ልክ ሳውዲ ዐረቢያ እስላማዊ መንግሥት እንደኾነችው ነው። በሳውዲም ኾነ ኢትዮጵያ ሁለቱም ጋር ሃይማኖታዊ መንግሥታት የነበሩበትን ዘመን እንውሰድና በኢትዮጵያ ክርስትና ውስጥ የነበረውን የእስልምና ይዞታ፣ በሳውዲ ዐረቢያ እስልምና ውስጥ የነበረውን የክርስትና ይዞታ እስቲ እናወዳድር? የትኛው ነው ጨቋኝ ሥርዓት? እስልምና በኢትዮጵያ ውስጥ ከመስፋፋት አልፎ የነገድ ማንነት ሳይቀር ቀይሯል። እስልምና ከረንን በሙሉ ከክርስትና ወደ ሙሉ እስልምና መቀየር የቻለ ሃይማኖት ነው። የኢትዮጵያ ክርስትና የየትኛውን ነገድ ማንነት ለወጠ? መልሱ የማንንም የሚል ይኾናል! እና የትኛው ነው ጨቋኝ?
ቱርክ የክርስትና ማዕከል ነበረች፤ የኦርቶዶክስ ክርስትና ዋና ማዕከል ቱርክ ኮንስታንቲኖፕል ነበር። የምዕራቡ ክርስትና ዋና ማዕከል ሮም ሲኾን የምስራቁ ደግሞ ኮንስታንቲኖፕል በመኾን ሁለቱም እኩል የክርስትና እምነት እምብርቶች ነበሩ። እስልምና ወደ ቱርክ ሲስፋፋ ግን የቱርክን ክርስትና ከምድረ ገጽ አጠፋው። የምሥራቅ ኦርቶዶክስ ማዕከል የነበረው ኃጊያ ሶፊያ ዛሬ መስጅድ ኾናለች። ኃጊያ ሶፊያ ልክ እንደ ቫቲካኑ ቅዱስ ጴጥሮስ የጳጳሳት መቀመጫ ነበረች። ከአክሱም ጽዮንም ትበልጥ ነበር። የቱርክ እስልምና ኃጊያ ሶፊያን ብቻ ሳይሆን መስጅድ ያደረገው ክርስትናንም ከምድረ ቱርክ አጥፍቷል። የነቅዱስ ኦውስቲን ሀገር ሊቢያ፣ የነአትናቲዎስ እና አርዮስ ሀገር ግብፅ እኮ ሀገሮቹ ብቻ ሳይኾን ዘሮቹም ዛሬ ጠፍተዋል። ይህ የኾነው በእስልምና ምክንያት ነው። በጨቋኝነት የሚወነጀለው የኢትዮጵያ ክርስትና የቱርክ እስልምና እንዳደረገው ሃይማኖት አላጠፋም። በጨቋኝነት የሚወነጀለው የኢትዮጵያ ክርስትና የሊቢያ እስልምና እንዳደረገው ሃይማኖትና ዘር አላጠፋም። እስልምና በቱርክ፣ በሊቢያ፣ በግብፅ፣ በሱዳን ሀገር የቀየረውና ዘር ያጠፋው በስብከትና በቅስቀሳ ሳይኾን በኃይል ነው።
1. አብዱራህማን ሼህ ሁሴን፡- በጠ/ሚር አክሊሉ ሀብተወልድ ጽ/ቤት አማካሪ ሚንስትር (የካቢኔ አባል)፣
2. አብዱራህማን ሙሜ፡- የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር (በጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ካቢኔ)
3. ሳኒት ሒነት፡- የፕላንና የእድገት ዳይሬክተር፣ የፖስታና የቴሌፎን ሚኒስትር፣ የሥራና የውኃ ሀብት ሚኒስትር (በጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ካቢኔ)
4. ኮሎኔል ሰሎሞን ከድር፡- የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት የደኅነት ኃላፊ
5. ፊታውራሪ ሮጋ አሻሜ፡- የኃይቆችና ቡታጅራ አውራጃ ዋና አስተዳዳሪ
6. አብዱ ሙሄ፡- የገንዘብ ሚንስቴር ምክትል ሚንስትር (በጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ካቢኔ)
7. ደጃዝማች አሕመድ ዐሊ ጣሴ፡- የሴኔት አባልና የጨርጨር አውራጃ አስተዳዳሪ
8. ፊታውራሪ ኢብራሂም ሀሚድ፡- የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዋና ዳኛ
9. ፊታውራሪ ሙሔ አርፎ፡- የጋራ ሙለታ ዋና አስተዳዳሪ
10. ፊታውራሪ ሰይድ ወገር፡- ዋና አስተዳዳሪ
11. ፊታውራሪ አደም አብዶ፡- ዋና አስተዳዳሪ
12. ዶክተር ጀማል አብዱልቃድር፡- የጤና ሚንስትር
13. ቢትወደድ ዐሊ ሚራህ፡- አውራጃ ዋና አስተዳዳሪ
14. ደጃዝማች ዑመር ሰመተር፡- የኦጋዴን አውራጃ አስተዳዳሪ
15. ዑስማን መሐመድ፡-አምባሳደር፣ የሕዝብ ሀብት ምክትል ሚኒስትር
16. ሞሊሳ ራቡ፡- በትምርት ሚኒስቴር ዋና ዲሬክተር
የኛ ሀገር ክርስቲያናዊ መንግሥት እነዚህና መሰል እስላም ቢትወደዶች፣ ደጃዝማቾች፣ ፊታውራሪዎች፣ ሚኒስትሮችና ከፍተኛ ባለሥልጣናት የነበሩበት ሥርዓት ነው። የኛ ሀገር ክርስትና ለእስልምና ቦታ የማይሰጥ ቢኾን ኖሮ ቀድሞውኑ ክርስቲያናዊቷ ኢትዮጵያ እስላሞችን አትቀበልም ነበር፤ እንግዳው እስልምና ነባሩን ክርስትና እንዲቀይር አትፈቅምድ ነበር፤ አልፎም እንግዳው እስልምና ነባሩን ክርስትና በቱርክ እንደዳረገው ክርስቲያናዊቷ ኢትዮጵያም እንግዳውን እስልምና ከምድረ ገጽ ታጠፋው ነበር።
በሃይማኖቱ ምክንያት ሰው እንደሁለተኛ ዜጋ ተቆጥሮ መብቱ የተገፈፈበት፣ የተጨቆነበት፣ እንዲጠፋ የተደረገበት፣ የሃይማኖት የጭቆና ተምሣሌት የኾነ ሀገር በምሳሌነት ይቅረብ ከተባለ ሊጠቀሱ የሚችሉት በከሰሰኝ ሐጂ እንደ ቅዱስ ምድር የሚታዩት እነ ቱርክ፣ ግብጽ፣ ሊቢያ፣ ወ.ዘ.ተ ዓይነት ሀገሮች እንጂ እስልምናን ያቀፈችዋ ያባቶቻችን ኢትዮጵያ ፈጽሞ ልትኾን አትችልም! ነቃፊዬ ሐጂም እውነተኛ የኅሊናና የሃይማኖት ሰው ከኾነ ክርስትናን ከማዕከሉ ነቅሎ ከምድረ ገጽ ያጠፋውን የቱርክን እስልምና ትቶ፣ የሀገሩን መልክና ማንነት የቀየረውን የሊቢያን እስልምና ትቶ፣ የአንድ ነገድ ማንነት በሙሉ የቀየረውን የኢትዮጵያን እስልምና ትቶ፣ ከእንደነዚህ ዓይነት የጭቆና ልኮች ጋር አንዳች ግንኙነት የሌለውን የኢትዮጵያን ክርስትና እና ክርስቲያናዊውን መንግሥት የጭቆና ምልክት አድርጎ ማቅረብ ግብዝነት ነው።