>

ማሰብና ማስተዋል የተሳናቸው የፖለቲካችን ዘዋሪዎች!!! (በእውቀቱ ስዩም)

ማሰብና ማስተዋል የተሳናቸው የፖለቲካችን ዘዋሪዎች!!!
በእውቀቱ ስዩም
ብሄረተኝነት የሚጀመረው በቅብጠት አይደለም፤ ከጭቆና የሚወለድ ነው ፤ ይሁን እንጂ  ብሄርተኝነት   ካልተገራ   የሆነ ደረጃ ሲደርስ ይዘቅጣል፤ራስን ለማስገበር የተጀመረ ትግል  ጎረቤትን በማስገበር ይጠናቀቃል፤  በኢትዮጵያም ሆነ በሌላው አለም ፖለቲካ ሲዘቅጥ የሚመራው በጣጠኛ ሰዎች ነው፤
የዛሬ የፖለቲካችን ዘዋሪዎች የሚከተሉት አይነት ናቸው!!
1. አደራጅተው መናገር የሚችሉ ፤ግን ማሰብ ማስተዋል ማመንታት እሚባሉ ነገሮች የተሳናቸው፤
2 ፤ ፖለቲካን በጊዚያዊ ድል ብቻ የሚለኩ፤ ከጎረቤት ጋር አብረን  እንዴት በሰላም እኖራለን ሳይሆን ከጎረቤታችንን እንዴት እንበልጣለን በሚል ሃሳብ የተጠናወታቸው!
3፤ ሰነፎች፤ የስራ ችሎታ እንኩዋ ቢኖራቸው የስራ ፍላጎት የሌላቸው፤   ሰርተን እንለወጣለን የሚል ሀሳብ  የማይጎበኛቸው ፤ሌላው ያበሰለውን ለመብላት ሌላው የገነባውን  አጋጣሚውን ሰፍ ብለው የሚጠብቁ፤
3 ፍቅር ብርቅ የሆነባቸው!   ትኩረት የጤረረባቸው!  አትለፉኝ!  ተቸግሬ ነው! በፈጠራችሁ አይናችሁን ትርኩረታችሁን ጣል ጣል አርጉልኝ ማለት የሚቃጣቸው!
4. ድብርት ያጠቃቸው፤ የግጭት አራራ ያለባቸው፤ የተረጋጋ ማህበረሰብ ማየት የሚያዛጋቸው፤ ሰላም የሚያታክታቸው፤ መታከት boredom የሚያባርርላቸው እስከሆነ ድረስ  አገር በደም ሲዋኝ ለማየት የሚያስጎመጃቸው!
5 ትግስት የለሾች፤ አንድ ማህበረሰብ ብዙ ጉድለት ሊኖረው ይችላል፤ሰላም ካለው ግን  ቀስ በቀስ ጉድለቶቹን ለመሙላት አያቅተውም ፤ ቅብጥብጦች  ይህንን እውነታ  አይረዱም፤ባንድ ጀንበር ምኞታቸውን  ከማብረድ ውጭ ሌላ ሀሳብ አይታያቸውም፤   “ የባቄላ ችኩል ሲያርሙት ያስፈሳል’  የሚለው የዳሞቴ ተረት  በደንብ ይገልፃቸዋል!!
6 ትዳር የመከነባቸው፤ ትዳር  ባናታቸው  ላይ የተደረመሰባቸው ፤የወለዱ ግን የወለዱትን የማሳደግ ትግስትም ሆነ ችሎታ የሌላቸው! የከሸፈ   አባወራነታቸውን የህዝብ  አባወራ  በመሆን ለማካካስ የሚፈልጉ!
7  ጉርምስና የፈላባቸው! ወይ የመካከለኛ እድሜ ድቀት ግራ ያጋባቸው!  ሰውነታቸው ያስጠላቸው!
8 መፃጉእዎች!  ሙሉ አካል ወይም ሙሉ አእምሮ የሌላቸው፤   የሆነ ጡብ የጎደላቸው፤ ያላለቁ ሰዎች ፤ በልጅነታቸው በጉድለታቸው ወይም በብሄረሰባቸው ምክንያት  ጋጠወጥ የማህበረሰብ ክፍል  ያዋከባቸው፤እድሜ ልካቸውን በቀል ሲጠነስሱ የኖሩ፤
 እኒህ ሰዎች በምክርም ሆነ በትምርት አይለወጡም፤ የነዚህ ሰዎች ብቸኛው ፀባይ ማረሚያ፤ ሞት ነው ፤ ይሁን እንጂ ሞትም ጣጣ አለው፤  በትርፍ አንጀት በሽታ   ቢሞቱ እንኩዋ ጦሳቸው ለህዝብ ይተርፋል፤
 በድሮ ጊዜ  አንዱ ባላገር  የሚጠላት የንጀራ እናቱ ሞታ ለመቅበር ይሰናዳል! እና ወደ ጉድዱዋዱ ዝቅ ብሎ ሲያይ እጀጠባብ ደረት ኪሱ ላይ የነበረ መቶ ብር ጉዱጉዋዱ ውስጥ ወደቀ፤ ይህን ያላዩ መቃብር ቆፋሪዎች የሰውየውን ብር ካሮጊቱዋ ጋር   አብረው ቀበሩት፤
እና ባላገሩ፤
‘ይች ሙት ይዛኝ ሞተች “ አለ ይባላል!
Filed in: Amharic