>
5:13 pm - Monday April 18, 7538

የእስሩም የመፈታቱም ሂደት የሴራ ፖለቲካ ድምር ውጤት ሆኗል! (ጋዜጠኛና አሳታሚ አለማየሁ ማህተመ ወርቅ)

የእስሩም የመፈታቱም ሂደት የሴራ ፖለቲካ ድምር ውጤት ሆኗል!
ጋዜጠኛና አሳታሚ አለማየሁ ማህተመ ወርቅ
የጋዜጠኛን የመታሰር ዜና ቀድሞውኑ መታሰር በማይገባቸው  ጋዜጠኞችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች የመፈታት ዜና ማለባበስ!!!  የ”እኛ”ና “እነሱ” ርካሽ ፖለቲካ ድምር ውጤት ነው!!!
 
በሀገሬ የፍትህ ስርአት ላይ ሁሌም እምነቱ ባይኖረኝም ዛሬ ግን ተስፋ አስቆራጭ ሆኖ ነው ያገኘሁት ። ይሄ የህግና የስርአት ጉዳይ ሳይሆን በቀደመው የህወሀት ኢህአዴግ ርዝራዥ ባለስልጣናት የተወሰደ የበቀል  እርምጃ፤ በሌላ አንግልም ስናየው የእኛና የእነሱ ርካሽ ፖለቲካ ድምር ውጤት ሆኖ ነው የታየኝ።
 መንግስት በ”መፈንቅለ መንግስት” ጠርጥሬያቸዋለሁ ብሎ በፈጠራ ክስ ያሰራቸውን እነ ኤልያስ ገብሩን ጨምሮ 22 እስረኞችን ሊያውም በመታወቂያ ዋስ ሲፈታ ለእኛ “የህሊና እስረኞች ይፈቱ” እያልን በየጊዜው ለፈጣሪም ለፍጡርም ለምንጮህ ወገኖች ትልቅ ድል ቢሆንም ለአሳሪው አካል ግን ድርብ ድርብርብ ድል ነው።
አንድም:- መንግስት እኒህን የህሊና እስረኞች በመፍታቱ ዋንኛ የለውጥ ሀይል የሚላቸውን ከዛም አልፎ “ወደ መደበኛ አደረጃጀት አመጣቸዋለሁ!” የሚላቸውን  ቄሮ የተሰኙ ሰብአዊነት ያልፈጠረባቸው በዘር የተቧደኑ የጥፋት ሀይሎች በየእለቱ በማን አለብኝነትና በተረኛነት ስሜት እየተገበሩ ያሉትን ኢ- ሰብአዊ ድርጊት ከሚድያ ቀዳሚ ዜናነት ማናጠብ።
ሁለትም :- መጭውን ምርጫ ታሳቢ በማድረግ ከወዲሁ “ከእኛ ወገን አይደሉም” የሚሏቸውን ሚድያዎች ከገበያ ለማስወጣት ለዚህም  የነጻው ፕሬስ የጀርባ አጥንት እንደሆነ የፕሬስ ቤተሰቦች በአጽንኦት የሚመሰክሩለትን ብርቱ ጋዜጠኛ ወደ እስር ማጋዝ መቻል ለእነርሱ ትልቅ ድል ነው ።
ብርቱውን ጋዜጠኛ በማሰር ሌሎችንም የማሸማቀቅ ሴረኛ አካሄድ!!!
 ከሀያ አመት በላይ የነጻው ፕሬስ አባል በመሆን የተለያዩ መጽሄትና ጋዜጦችን በአከፋፋይነት፣ በአዘጋጅነት፣ በማኔጂንግ ዳይሬክተርነትና በአሳታሚነት የሚሰራ ብርቱ ጋዜጠኛን ሊያውም በቀድሞው ስርአት በተመሰረተ ክስ የሰባት አመት እስር ከመፍረድም በላይ በእኔ በጸሀፊው ላይም በሌለሁበት የ25 አመት እስራት በመፍረድ፤  በስደት አለም ሆኜ አገሬ ወገኔ እንደናፈቀኝ እንድቀር ተፈርዶብኛል። “በሴራ ፖለቲካችን ድርብ ድል ተጎናጽፈናል” የሚሉ ተረኞችም ውስኪ በማጋጨት ደስታቸውን በማጣጣም ላይ ይገኛሉ።
ይህን ግፍ ሳይ በአገሬ ምድር እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ የፍትህ ሚዛን ማጋደሉን ባሰብኩ ጊዜ አይኖቼ በእንባ ወረዙ።
ፍትህ በግፍ እየፈሰሰ ላለ የወገን ደም!
ፍትህ በግፍ እየፈሰሰ ላለ የወገን እምባ!
ፍትህ በግፍ ለታሰሩ የህሊና እስረኞች!
Filed in: Amharic