>
11:33 pm - Wednesday November 30, 2022

“በተከሰተው ሁከት በጥፋቱ ተሣታፊ የሆኑ ሰዎች ሁሉ በሕግ ተጠያቂነታቸው መረጋገጥ አለበት!” (ከኢሰመኮ የተሰጠ መግለጫ)

በወቅታዊ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የተሰጠ መግለጫ!!!

 
“በተከሰተው ሁከት በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ በጥፋቱ ተሣታፊ የሆኑ ሰዎች ሁሉ በሕግ ተጠያቂነታቸው መረጋገጥ አለበት!”
በኢትዮጵያ የተጀመረው የለውጥ እና ተሃድሶ እርምጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ተጨባጭ ውጤቶች እንዳስገኘ ሁሉ ውስብስብ ተግዳሮቶችም እየገጠሙት ይገኛል፡፡ በተለይ ጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በተቀሰቀሰው ውዝግብ እና ሁከት የተሞላ ነውጥ የበርካታ ሰዎች ሕይወት ከመጥፋቱ፣ የአካል ጉዳት ከመድረሱ፣ ንብረት ከመውደሙ እና የሰዎች መደበኛ ኑሮ እና ሰላማዊ ሕይወት ከመረበሹ በተጨማሪ፤ የህግ በላይነትን በእጅጉ የተፈታተነ እና መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶችን ከፍተኛ አደጋ እና ስጋት ላይ የጣለ እጅግ አሳሳቢ ክስተት ነበር፡፡
በዚህ ሁከት ምክንያት ከሚዲያዎች ዘገባ  መሰረት እስከ አሁን ባለው መረጃ ከ70 – 80 የሚደርሱ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አስር ያህሉ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በተፈጠረ ግጭት በጥይት ተመተው የሞቱ ሲሆን አብዛኛዎቹ ሰዎች በሁከቱ ተሳተፉ ሰዎች እጅግ አሰቃቂ በሆነ መንገድ በግፍ እና ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በዱላ በድንጋይ እና በስለት ተደብድበው እንዲሁም በእሳት ተቃጥለው ተገድለዋል፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ የአካል እና የሥነ ልቦና ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በሚሊዮኖች የሚገመት የግለሰቦች፣ የሕዝብና የአገር ንብረት ወድሟል፡፡ እንዲሁም የሃይማኖት ተቋማት ሆን ተብሎ በተፈጸመ ጥቃት ለጉዳት ተዳርገዋል፡፡
አሁን ባለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ማናቸውም ዓይነት ቅሬታ ወይም ጥያቄ በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ሊቀርብ የሚችልበት ምቹ ሁኔታ መኖሩ ይታመናል፡፡ ለዚህ ውዝግብ መነሻ በሆነው ጉዳይ ላይ በሰላማዊ መንገድ ሃሳባቸውን ለመግለጽ የሚሹ ሰዎች ቢኖሩም ሁከት የቀሰቀሱ፣ የፈጸሙ እና ያስፈጸሙ እንዲሁም ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ድጋፍ የሰጡ ሰዎች መኖራቸው ግን አይካድም፡፡ ማናቸውንም ዓይነት ቅሬታና ጥያቄ በአመፅ እና በእልቂት ማስፈራሪያ ለማስፈፀም የታየው ተግባር እና የአስከተለው ጉዳት የሕግ የበላይነትን፣ የአገር ሰላም እና ሥርዓትን በአደባባይ በመገዳደር እና በመጣስ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ቀውስ ያስከተለ በመሆኑ በየደረጃው በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ በጥፋቱ ተሣታፊ የሆኑ ሰዎች ሁሉ በሕግ ተጠያቂነታቸው መረጋገጥ አለበት፡፡ ይህን ጥፋት የፈፀሙ እና ወይም የጥፋቱን ተግባር እንደ መልካም ሥራ ያወደሱ ሰዎች ሁሉ በዱላ እና በስለት ተደብድበው በእሳት ተቃጥለው የተገደሉ ሰዎችና ቤተሰቦቻቸውን ለአፍታ እንኳን በእራሣቸውና በቤተሰቦቻቸው ተክተው አለማሰባቸው የደረሰውን ጉዳት ይበልጥ መሪር አድርጐታል፡፡ የድርጊቱ ተሳታፊዎች በደረሰው ጥፋት ማዘን መፀፀት እና ለሕግ የበላይነት መከበር የመተባበር ኃላፊነት እና ግዴታ አለባቸው፡፡
መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥና አጥፊዎችን በሕግ ፊት ለማቅረብ ሳያወላውል እንደሚሠራ መግለጹ ተገቢ ሲሆን፤ ይህ የመንግስት ኃላፊነት እና ተግባር በስልታዊ የምርመራ ሥራ እና በሕጋዊ ሥርዓት በአፋጣኝ በሥራ ላይ ሊውል ይገባል፡፡
ከዚህ በመቀጠል ለሚደረገው የወንጀል ምርመራ ሥራ ማንኛውም ሰው በመተባበር እና ውጤቱን በትዕግስት በመጠባበቅ፣ በየአካባቢው የተጐዱ ሰዎችንና ቤተሰቦችን በማጽናናት በመደገፍ እና በመጠገን፤ እንዲሁም የመንግሥት፣ የፖለቲካ እና የልዩ ልዩ ቡድኖች መሪዎች የፖለቲካ ውጥረቱን ከሚያባብሱ ቆስቋሽ ንግግሮች እና ድርጊቶች እራሳቸውን በመቆጠብ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን እና ሰብዓዊ መብቶች ሁሉ እንዲከበሩ የሚደረገውን ጥረት ማገዝ እና ይህን የመሰለ ጥፋት ዳግም እንዳይፈጸም የሚመለከታቸው አካሎች ሁሎ በከፍተኛ ኃላፊነት ስሜት ሊሰሩ ይገባል፡፡
Filed in: Amharic