>

ከእውነት የበለጠ እውነት ኢትዮጵያን ያሻግራል (ዶ/ር ዘላለም እሸቴ)

ከእውነት የበለጠ እውነት ኢትዮጵያን ያሻግራል

 

ዶ/ር ዘላለም እሸቴ

 

ኢትዮጵያን እንበታትናለን ብሎ ሲሰራ የነበረው ዕብሪተኛ ሰው ባለጊዜ ሆነና፥ ራሱ ብቻውን መንግስት ሆኖ መላውን ኢትዮጵያ እንደ ጎልያድ በማን አለብኝነት ሲያስጨንቅ የሚታይባት ምድር ኢትዮጵያ ናት።

 

አንድ ቤተሰብ የሆነውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በክልል እያጠሩ ባላንጣ መንግስታትን ፈጥረው፥ ጨለማውን ብርሃን እያሉ ሲጠሩ የማይታፈርበት ምድር ኢትዮጵያ ናት። 

 

ከነገድ ከቋንቋ ዋጅቶ በክርስቶስ ፍቅር አንድ ስለመሆን የሚሰብከው ሃይማኖት ተከታይ ነኝ እያሉ፥ በወንድማማች መካከል ጠብ የሚዘሩ ጉደኞች የሞሉባት ምድር ኢትዮጵያ ናት።

 

በመርህ ላይ ሳይሆን በዘረኝነት ላይ ብቻ ተመስርቶ የመንጋ አንድነት ያለው ፓርቲ፥ መላውን ኢትዮጵያ አንድ የሚያደርግበት ምሪት ይሰጣል ተብሎ ጉም የሚጨበጥበት ምድር ኢትዮጵያ ናት። 

 

ወዶም ሆነ ተገዶ ሁሉም በየጎሳው ዙሪያ አንድነቱን አጠናክሮ እየተደራጀ ራሱን ለማዳን ሲዳክር፥ ራሱን ለእርስ በርስ ዕልቂት እያመቻቸ መሆኑ እየታወቀ፥ የ “ሰው” ነት ፖለቲካ ቦታ የማይሰጠው ምድር ኢትዮጵያ ናት።

 

እኩይ የሆነው ዘረኝነት ኢትዮጵያን ሊያሰጥም ጫፍ የደረሰበት ጊዜ ሆኖ ሳለ፥ ሩዋንዳ ልንሆን ነው ብሎ ከመፍራት ያለፈ፥ በማስተዋል ለመጠበቅ ምንም እርምጃ የማይወሰድባት ምድር ኢትዮጵያ ናት።

 

ይህ ሁሉ እውነት ነው።  ግን ከዚህ እውነት የሚበልጥ ሌላ እውነት ደግሞ አለ።

 

የኢትዮጵያ መዳን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው!

 

ዕድሜ ልካችንን በመከራ ውስጥ አልፈን ስናበቃ፥ የብርሃን ጭላንጭል አሳይቶ እንቁልጭልጭ የሚጫወትብን ጨካኝ አምላክ የለንም። እግዚአብሔር በምድራችን የጀመረውን መልካም ሥራ ዳር ሳያደርስ መንገድ ላይ አይጥለንም።  

 

እግዚአብሔር ያያል። 

እግዚአብሔር ይፈርዳል። 

ፈጥኖ ይፈርዳል። 

በቀናት ውስጥ ክብሩን ይገልጣል።

 

ዲያብሎስ የደገሰልን የዕልቂት እኩይ ሤራ ይገለበጣል። ኢትዮጵያ ወጀቡን አልፋ ትሻገራለች።  ታበራለች። 

 

መከራ ያየነው ከዓለም በኃጢአት አንደኛ ስለሆንን አይደለም።  የቃል ኪዳን ሀገር የሆንነው ከዓለም በፅድቅ አንደኛ ስለሆንን አይደለም።  ያለፈው መከራችንም ሆነ የሚመጣው ጉብኝታችን ምክንያቱ የኢትዮጵያ አምላክ ክብር እንዲገለጥብን ብቻ ነው።  

 

ጠላት ለኢትዮጵያ መበታተን ያጠመደው ክፉ ወጥመድ ለእኛ ጭንቀት ቢሆንብንም፥ ለፈጣሪ ክብሩን እንዲገልጥ ጥሩ አጋጣሚ ነው። ምድር ሁሉ በኢትዮጵያ አምላክ አለ እስኪል ድረስ ሥራውን ሊሰራ ፈጣሪ ራሱ ይወርዳል።

ወጥመዱን ይሰብራል።

ኢትዮጵያንም ያስመልጣል። 

 

ከቅዱስ ቃሉ የተወሰደ፡

  • የኢትዮጵያ ድንኳኖች ሲጨነቁ አየሁ
  • አንተም የዘንዶውን ራሶች ቀጠቀጥህ፤ ለኢትዮጵያ ሰዎችም ምግባቸውን ሰጠሃቸው።

ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች።

Filed in: Amharic