>

ቤተ-መንግስት ተቀምጠህ ' ጀዋር የሚያሾረው ካቢኔ መሪ ' ከመባል በላይ ምን የሚያሳፍር ነገር አለ??? (ሀብታሙ አያሌው)

ቤተ-መንግስት ተቀምጠህ ‘ ጀዋር የሚያሾረው ካቢኔ መሪ ‘ ከመባል በላይ ምን የሚያሳፍር ነገር አለ???
ሀብታሙ አያሌው
አንተው የሾምከው ያንተው ታማኝ አገልጋይ የኦዴፓው ሽመልስ አብዲሳ ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ እንዳሻው ጣሰው ትዕዛዝ ሰጥቶ ጃዋርን ጠብቅ ብሎ ሲያስገድደው ከሰማህ በኋላ ኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ (የፀጥታ ተቋም) አላት ብለህ መናገር በእውነት ሐጢያትህን ያበዛዋል እንጂ አይጠቅምህም።
 
መከላከያን ለማ መገርሳና ጀነራል ብርሃኑ ጁላ ጠብ እርግፍ እንዲያደርጉት፤ ደህንነቱን ደመላሽ የኦዴፓ መጫወቻ እንዲያደርገው፤ አየር ኃይሉ በጀነራል ኃይሉ መርዳሳ እጅ እንዲወድቅ፤ አዲስ አበባ ላይ የጫንከው ታከለ ኡማ የራሱ አጋዚ እንዲያደራጅ አንተው እራስህ ከፈቀድክና ካመቻቸህ በኋላ “ኢትዮጵያ አትፈርስም ፣ ህግ እናስከብራለን ፣ እንደመራለን …” እያሉ እሪ ማለት ምን ማለት ይሆን ?
 
የተሳሳትከው ከመነሻው ነው። ላመነህ ህዝብ አልታመንክም። ክህደት የጀመርከው የሞት ፅዋህን ለመጠጣት ካንተ ያስቀድመን ባሉት በአዴፓ አመራሮችና በአዲስ አበባ ወጣቶች ነው። ህዝብ እንደ ቅጠል ረግፎ ያመጣውን ለውጥ አገዝክ ብለን ስንደሰት ኦዴፓ ስር ወስደህ ሸጎጥከው። ስንዝር ስትሰጠው ክንድ ከሚጠይቅ ከማይጠረቃ፣ ጥላቸ ካናወዘውና የበታችነት ስሜት ካሰከረው የኦሮሞ ፅንፈኛ ቡድን ጉያ ስር ተሸጉጠህ መደራደሪያ የኃይል ሚዛን ፍለጋ ባዘንክ።
 
ሶማሌው፣ አፋሩ፣ አማራው፣ ቤንሻንጉሉ፣ ሐረሪው፣ ደቡቡ፣ ጋምቤላው፣ እኩልነት ፈላጊው በርካታ የኦሮሞ ህዝብ፣ ቀላል ቁጥር የሌለው በተስፋ በሩን የከፈተልህ የትግራይ ህዝብ ቀኝ እጅህ ሆነው በደጅህ ቆመው ሳለ ቀኝህን ከዳህ። በዳውድ ኢብሳ የሚመራውን ኦነግ፣ በጀዋር የሚመራውን በጥላቻ የተመረዘ የቄሮ ቡድን፣ በወንጀል ተነክረው 27 ዓመት ህወሓት ሲጋልባቸው የነበሩ ኦህዴዶችን በልብህ ማህደር ይዘህ ከንፈርህን ብቻ ለቃላት ውርወራ ኢትዮጵያውያን ጋር ጣልከው።
 
አየህ ቀድሞውኑ ይህንን ያደረግከው በክፋት ከነበረ የሐጢያት ሁሉ ሐጢያት ነው። የስልት ስህተት ከሆነም ምክር አልሰማህ ብለህ የፈጠርከው ቀውስ ነው። ያም ሆነ ይህ መፅሐፉ እንደሚለው “ብረሳሽ ቀኜ ይክዳኝ ባላስብሽ ምላሴ ከትናጋዬ ይጠበቅ” ብለህ ተመለስ። የጃዋር መጫወቻ ሆነህ ከምትኖር ላመኑህ ኢትዮጵያውያን ታምነህ በየቀኑ ዜጎቻችንን እየቀሰፈ ካለው ከነውጠኞቹ መዳፍ ለመውጣት የስውር ውሉን አፍርስ።
 
ይህንን ሁሉ ስልጣን ሰጥተህ አንተ ቤተመንግስት ይዘህ ጀዋር የሚያሾረው ካቢኔ መሪ ከመባል በላይ ምን የሚያሳፍር ነገር አለ። በአላማ አንድነት ተጣብቀህ ካልቀረህ በቀር አባብለህም ተቆጥተህም የማትመልሰው አደገኛ ቡድን ስር ውሎ ማደር ከውርደት በቀር ትርፍ የለውም። እናም እባክህ ግራ ተጋብተህ ግራ አታጋባን።
Filed in: Amharic