
ኧረ በቃ ይበልሽ!

ጌታቸው አበራ
አከተመ ብለን ስንፈነጥዝ – ያረመኔነቱ ዘመን፣
እጥፍ-ድርብ አርጎ አመጣው – ለመስማት እስከሚዘገንን፤
ምንስ ተሰማ ዛሬ ደግሞ? – ምንስ ሆኖ ተነገረ?
ዓለም ተገርሞ ሳያበቃ፣ – ምድርሽ ለሰቆቃ ገበረ!
ምነው አልነጋ አለን እማማ – ሐጢዓታችን በዝቶ ተከመረ፣
በድንጋይ ዘመን አስተሳሰብ – የሰው ልጅ በድንጋይ ተወገረ፤
ለዘመናት የኖረው ሕዝብሽ -በፈሪሃ-እግዚአብሔር ታምኖ፣
በጥቂቶች እኩያን ሳቢያ – እንዴትስ ይበታተን ባክኖ፤
አወቁ፣ በቁ… የተባሉት – ሲያምዘገዝጉሽ ሁሌ ቁልቁል፣
ምን ዓይነት እንቆቅልሽ ነው?- እማይፈታ ያንቺ ውል፤
የግፍ ክምችት ባንካችንን – የዘመናት ክምር ዕዳ፣
ከፍለን የጨረስን ሲመስለን – በአዲስ ዘመን የጸዳ፣
ዳግም አገረሸብን ሱሱ – የደም አዙሪት ጥማቱ፣
መቼ ያበቃ ይሆን ፍዳችን -እማንቀጠፍበት በከንቱ!
የነገው ዘር ቁጥቋጦሽ -የትውልዱ ባላደራ፣
ድንጋይ፣ ዱላ ፣ ተሸክሞ -አንዳች ጥበብ ሳይሰራ፣
ህልውናሽ እሚቀጥል -እንዴት ሆኖ በተዐምር፣
“ለዘላለም ትኑር” ቢልሽ -በምላስ ስልት በመፈክር፤
በተፈጥሮሽ ውበት፣ ሃብት… ከምድር ማማ መንብረሽ፣
ከልጆችሽ ተርፎ እሚፈስ – ህይወት ሲሳይ… ተጎናጽፈሽ፣
ጥሮ-ግሮ፣ በጥበቡ -ብልጽግናን እሚያካብት፣
ከልህ ወጥቶ፣ ለሰላምሽ፣ – ለእድገትሽ… እሚዋትት፣
ጠቢብ አጥሮሽ – በብልሃት መንገድሽን እሚመራ፣
መርገምት ሆነ ያንቺ ነገር፣ – ዶፉ ዘንቦ እማያባራ…፤
ብቻ ደግሞ… – ወደቅሽ ሲሉሽ እምትነሺ፣
ሞተች ሲሉ ትፈወሺ…፣
መለኮትን ታምነሽ የኖርሽ – ያምላክ አገር የሚስጥሩ፣
ነሽና ያልተለየሽ – ሕያው ተግባር ተዐምሩ፣
ብላቴናሽ እንዳዜመው- ኢትዮጵያ ስምሽ ገኖ
እናት ነሽና ተስፋ አንቆርጥም -እምንኖረው ላንቺ ሆኖ!
ለአብሮነት ባህላቸው – ለትህትና ቅድሚያ ሰጥተው፣
በዝምታ የተዋጡ – በ’እስኪ እንየው‘ አንገት ደፍተው፣
እልፍ-አእላፍ ልጆችሽ – አንችን ብለው ካንቺው ያሉ፣
ለህልውናሽ.. ለመድኅንሽ – ንቦች ሆነው ይነሳሉ!
እምታምኚው አምላክሽ -የሙስሊሙ፣ የክርስቲያኑ…፣
ከመከራ ሰውሮ – በቃ!ይበልሽ በስልጣኑ!
* አረመኔያዊ በሆነ መንገድ በታላቅ ስቃይ ህይዎታቸውን ላጡ ሰላማዊ ዜጎች እግዚአብሔር አባት የሰማዕትነትን ክብር ያውርስልን፤ * በከፍተኛ ጭካኔ ሰቆቃ ተፈጽሞባቸው በታላቅ ስቃይ ላይ ለሚገኙ ጉዳተኞች፣ አምላክ በቶሎ ፈውስን ያጎናጽፍልን ዘንድ እንጸልይ!
* በዚህ አሰቃቂ ጭፍጨፋ ውዶቻቸውን ላጡ ቤተሰቦች ሁሉ መጽናናት ይሁን!
* እግዚኦ! የሚያሰኘው ባገራችን የደረሰው ዘግናኝ መዐት ዳግም ባገራችን እንዳይከሰት እግዚአብሔር ይርዳን!
*እውነተኛ የኢትዮጵያ ልጆች ዝምታችንን ሰብረን፣ አገራችን ከገጠማት አስከፊ አደጋ ተላቃ እንደ አገር እንድትቀጥልና ሕዝቡ ሰላማዊ ህይወቱን ይጎናጸፍ ዘንድ እንድናስችል ታሪካዊና ሞራላዊ ግዴታ አለብን!