>

ከህዝብ እና ከእውነት የቱ ይበልጣል? (ደረጄ ደስታ)

ከህዝብ እና ከእውነት የቱ ይበልጣል?
ደረጄ ደስታ
* ህዝብ ላይ ቆመህ ህዝብ ላይ አታስጨብጭብ። ርካሹ ዝና ሳይሆን ህሊናህ ያጨብጭብልህ። ህዝብ ላይ ከመሰለፍ ከህዝብ ጋር መሰለፍን የመሰለ ነገር የለም!!!
እንደሽንፍላ ያልጠራው ኦህዴድን ጨምሮ፣ እንደ ሕወሓትና ኦነግ ያሉት ብሔርተኞችና ደጋፊዎቻቸው ቀውስ እያሸተቱ ነው ።
ኦህዴድ በሥልጣን ለመደላደል፤
ኦነግ ወደ ሥልጣን ለመምጣት፤
ህወሃቶች ደግሞ ለትንሳኤያቸው ተስፋ የሰጣቸውን ቀውስ ለማባባስ እየሠሩ ነው!
ኦነጎቹ ኦሮምያ በኛ ካልተያዘች ዋጋ የላትም ሲሉ፣ ህዋቶችም ይህ ሁሉ ችግር እነሱ በመወገዳቸውና ባለመኖራቸው ምክንያት የመጣ መሆኑን አምነዋል። እውነት ነው አስከፊ ችግርና ፈተና ተደቅኗል። የችግሩ ምንጭና ምክንያት ግን የኦነጎችም ሆነ የወያኔዎች አለመኖር አይደለም። የትላንትና የዛሬዎቹ ኦነጎችም ሆኑ ወያኔዎች መኖር ውጤት ያመጣው ነው።
 እነሱ በመፈጠራቸው የመጣውና የተባባሰውን ችግር እነሱ በመወገዳቸው የመጣ ችግር እየመሰላቸው ሊመጻደቁ ይፈልጋሉ። ቀውሱ የሥራቸው ፍሬና ውጤት ነው።  ያውም ገና ታይቶ ያላላቀ ውጤት።
 እንኳን እነሱ በህይወት ኖረው እሚያራግቡት ችግር ቀርቶ፣ ድራሻቸው ጠፍቶ እንኳ እሚቀጥል ችግር ቢኖር የነሱ አስተዋጽኦ ገና ለዘመናት ይኖራል። የረጩትን የጎሰኝነት መርዛቸውን መምጠጥ ያስፈልጋል። ጎሰኝነትን ለማጥፋት በጎሰኝነት ደዌ ባለመበከል ፈተናውን በጽናት መጋፈጥና ቀውስን ወደ ሰላም ለመለወጥ መታገል ግድ ነው። እውነት ነው ትግሉ ቀላል አይደለም። ከብሔርተኝነት ጀርባ ሁሌም ህዝብ አለ። ከነሂትለርም ከነሙሶሎኒም ጀርባ ህዝብ ነበር። ሁለቱም ወደ ሥልጣን የመጡት በህዝብና በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ነበር። አከራካሪም ቢሆን ትራምፕንም የመረጣቸው ህዝብ ነው። ስለዚህ ከህዝብ በላይ ግን እውነት አለ።
በታሪክ የተረጋገጠ የህዝብን ስህተትና ውድቀት ያጋለጠ እውነት! ሐቅህን ለምክንያታዊነት እንጂ ለድምጽ ብልጫ አታቅርብ። ያውም በአደባባይ ጩኸት እንጂ በአግባቡ ላልተቆጠረ ድጽምህ። ያም ሆነ ይህ ግን ብቻህን አይደለህም። በሁካታ የተሸፈነ አንተን የመሰለ ሌላም የህዝብ ውስጥ ህዝብ አለ። ከኦሮሞው ከአማራው ትግሬውም ሆነ ሌላው መካከል ሞልቶልሃል። እሱን ፈልገህ አግኘው። አብረኸው ተሰለፍ። ትንሽ እንኳ ብትሆን ትበዛለህ። ምናልባትም የበለጠውን የህዝብ ብዛት ታገኝና ያነሱትን ትበልጣለህ። ህዝብ ላይ ቆመህ ህዝብ ላይ አታስጨብጭብ። ርካሹ ዝና ሳይሆን ህሊናህ ያጨብጭብልህ። ህዝብ ላይ ከመሰለፍ ከህዝብ ጋር መሰለፍን የመሰለ ነገር የለም። ፍቅር ይፍታህ!
Filed in: Amharic