>
5:16 pm - Tuesday May 23, 4913

"የሰው ልጅ ታሪክ የጀመረው ከምንሊክ ነው " የሚለው የጥላቻ ትርክት የወጣቱን አስተሳሰብ በክሎታል!!! (ያሬድ ጥበቡ)

“የሰው ልጅ ታሪክ የጀመረው ከምንሊክ ነው ” የሚለው የጥላቻ ትርክት የወጣቱን አስተሳሰብ በክሎታል!!!
ያሬድ ጥበቡ
*  ኦሮሞ በታሪኩ ገፈት ቀማሽ ብቻ ሳይሆን፣ ግፍ ፈፃሚ የነበረ መሆኑንም ወጣቱ ካልተረዳና ከባሌ ቀበሌዎች ተነስቶ ወደ ሰሜን ምስራቅና ምእራብ ኢትዮጵያ ሲስፋፋ ሌሎችን እያጠፋና ከ20 በላይ ብሄረሰቦችን ውጦና ሰልቅጦ ማንነታቸውን አክስሞና ኦሮሞ አድርጎ መቀሌ ድረስ መስፋፋቱን የኦሮሞ ወጣት ካልተማረና ስለራሱ ታሪክ ሚዛናዊ አስተሳሰብ ካልያዘ ለአመታት የተጋተው የገፈት ቀማሽ ስነልቡና ገና ብዙ ጥፋት ያደርሳል!!!
ከጃዋር የጥበቃ ችግር ጋር በተያያዘ የተነሳውን የኢትዮጵያውያን በግፍ መጨፍጨፍ በተመለከተ ሁሉ ነገር እስኪጠራ በሚል ዝምታን መርጬ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ከሩሲያ ጉብኝታቸው ሲመለሱም በመፅሀፋቸው ካስነበቡን ኢትዮጵያዊ ህልማቸው ጋር በሚመጥን መንገድ አመራር ይሰጣሉ ብዬ ተስፋ አድርጌ ነበር። ሆኖም፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ በወጣው መግለጫ፣ ሐረርና አምቦ ካደረጉዋቸው ስብሰባዎች፣ የፕሬስ ሃላፊያቸው እሳቸውን ተክተው የሰጡት መግለጫ፣ አንዳቸውም ሀላፊነት ከሚሰማው መሪ የወጡ ሆነው አልተሰማኝም። ከተጠቃው ህዝብ ጎን ቆመው ሀዘናቸውን ከመግለፅና ለህግ የበላይነት አመራር ከመስጠት ይልቅ ስለ ኦሮሞ ህብረት ሲመክሩ መሰንበታቸው ገርሞኛል፣ ግር ብሎኛልም።
የሆነው ሁሉ ለምን ሆነ? ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊነግሩን አልፈቀዱም። እርሳቸው ወደ ሩሲያ ለማቅናት አውሮፕላናቸው አየር ላይ ሲሆን፣ የጃዋር ጠባቂዎች ሳያስታውቁት ኮቴያቸውን አጥፍተው እንዲወጡ አመራር የሰጠው ማን ነው? ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን እቅድ ያውቁ ኖሯልን? ካወቁ፣ ለምን አፀደቁት? እቅዱ ቢሳካ ኖሮ፣ ሃገር ሰላም ነው ብሎ የተኛውን ጃዋር በሌሊት ገብቶ የሚገድለው ተዘጋጅቶ ነበርን? ካልሆነና ጠቅላይ ሚኒስትሩ እጃቸው ከሌለበት፣ ጉዳዩን ለማጣራት ለምን ጊዜ ወሰደ? የጃዋር ዘበኞች በህይወት አሉ፣ ያዘዛቸው መኮንን በህይወት አለ ወዘተ። ይህን አጣርቶ ለህዝብ ለመናገር ከአንድ ቀን በላይ ለምን እንደሚወስድም አልገባኝም፣ አይገባኝምም።
ይበልጥ ግን ያልገባኝ በቄሮ መንጋ የተጨፈጨፉት ኦሮሞ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያን ሆነው ሳለ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን የመረጡት በኦሮሚኛ የሐረርና አምቦ ኦሮሞዎችን ማናገር ነው። ለምን? የጭፍጨፋው ሰለባ የሆኑትን አማሮች፣ ጉራጌዎች ወዘተ እንኳ የስብሰባው አዳራሽ ውስጥ አስገብተው በጋራ ሊያናግሯቸው አልመረጡም። ጄኔራል መሀመድ የሚባል ከእውቀት የፀዳ ሰው “ችግሩ የተቀሰቀሰው በሰላማዊ መንገድ አውራጎዳናዎችን በድንጋይ ይዘጉ የነበሩ ቄሮዎችን ለመከልከል ሙከራ ያደረጉ በፈጠሩት ነው” ማለቱን በማህበራዊ ሚዲያ ተዘግቦ አይቼ ዓይኔ ማመን አልቻለም ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን ከውጪ ጉዞዋቸው ተመልሰው የኢትዮጵያን ህዝብ ከማናገርና የሟች ቤተሰቦችንም ጎብኝተው ከማፅናናት ይልቅ ከአባገዳዎች ጋር ለመወያየት መፍቀዳቸው ከመከላከያው ጄኔራል ጋር የሚጋሩት የአስተሳሰብ ችግር እንዳላቸው ነው የተረዳሁት። እስከመቼ?
እስከመቼ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲህ በጭካኔ ይቀጥላሉ? መስከረም 5ቀን 2011 አም በቡራዩ የጋሞና ጉራጌ ብሄረሰብ አባላት ላይ የተደረገውን ጭፍጨፋ በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ የወጡትን አምስት የአዱስ አበባ ወጣቶች አስገደሉ። ሆኖም ከ23 እስከ 60 ለሚሆኑ በቡፋዩ ለተጨፈጨፉት ኢትዮጵያውያን ያደረጉት የፍትህ ማካካሻ የለም። በወቅቱ ጃዋር ከኪሱ አውጥቶ ከኦነግ አቀባበል ሰልፍ የሚመለሱ 40 ኦሮሞዎች ላይ ያንኑ ቀን አስቀድሞ ግድያ ተፈፅሞ ነበር ብሎ ሲዋሽ፣ ጃዋር ይህን ያህል መሄድ የተገደደው በጋሞዎቹ ግድያ እጁ ቢኖርበት ነው የሚል ጥርጣሬያችንን አምቀን ይዘን፣ የፍትህ ስርአቱ ያጋልጠዋል ብለን ተስፋ አድርገን ነበር። ሆኖም ወፍ የለም። የንፁሀን ደም በከንቱ ፈሶ ቀርቷል። ቡራዩ አሁንም ለፍትህ ይጮሀል። የግድያው አቀናባሪዎችም ሳይነኩ ቤተሰቦች እንዳለቀሱ ቁጭ ብለዋል።
አሁንም በናዝሬት፣ ሐረር፣ ባሌና አርሲ ገዳዮችና አቀናባሪዎች የሆኑት በየወረዳውና ዞን አስተዳደሮች ተቀምጠው፣ በየፖሊስ ጣቢያው መሳሪያቸውን ይዘው በነፃነት ሳሉ፣ ለሰሞኑ ጭፍጨፋና ግፍ እየታደኑ የሚታሰሩት የቄሮ መንጋን ግፍ ለማስቆም አብያተ ክርስቲያናት እንዳይቃጠሉ የድረሱልኝ ደወል የደወሉ ቀሳውስት፣ ቄሮን በአልሞትባይ ተጋዳይነት የተጋፈጡ ኢትዮጵያውያን ጀግና ወጣቶች መሆናቸውን መረጃዎች እየወጡ ነው።
ከብዙ ኢትዮጵያውያንና ብዙ የማከብራቸው ሰዎች በተለየ የጃዋር መታሰር መፍትሄ ነው ብዬ አላምንም። ጃዋርን በህግ የሚያስጠይቀው ነገር ካለ መጠየቅ የለበትም እያልኩ አይደለም። ከጭፍጨፋው መነሳት ሶስት አራት ቀናት አስቀድሞ ጃዋር በኤል ቲ ቪ ቀርቦ “ለምን ከሌሎች ሰዎች ጋር አትከራከርም?” ተብሎ ሲጠየቅ የመለሰው መልስ “የኔ ቃል የአንድ ተራ ሰው ንግግር አይደለም፣ ብዙ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል” ብሎ የተናገረ ሰው፣ በዚያ የሃላፊነት ስሜት አልተንቀሳቀሰም። ደጋፊዎቹ ያን ሁሉ የህይወትና ንብረት ውድመት ሲያካሂዱ  በቶሎ እንዲያቆሙ አልተማጠነም። ይህ ሊያስጠይቀው ይችላል ብዬ አስባለሁ።
ሆኖም ሃገራችን ኢትዮጵያ የገጠማት ችግሩ ከጃዋር የበለጠ ነው።  ኢትዪጵያ የገጠማት ችግር ፀረ ኢትዮጵያ የሆነው የኦሮሞ ብሄርተኝነት ትርክት ነው።  የሰው ልጅ ታሪክ የጀመረው ከምንሊክ ነው የሚለው የጥላቻ ትርክት የወጣቱን አስተሳሰብ በክሎታል። በኦሮሚያ ክልል የሚኖረውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ በወራሪነት እንዲያይ ተደርጓል። ስለዚህም የራሱን ሥራአጥነትና ሥራጠልነት፣ ከሱ የተሻሉ ኢትዮጵያውያንን ንብረትና ሃብት በመንጠቅ የሚያልፍለት ይመስለዋል። ስለሆነም፣ የደህንነት ሥርአቱ ላይ ክፍተት ባየ ቁጥር ኦሮሞ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያንን ለማጥቃት ይነሳል። የተስፋዬ ገብረአብን ልቦለድ ድርሰት ነብስ ዘርተው ሃውልት ያቆሙለት የኦዴፓ መሪዎች፣ ጡት ቆራጭ ወጣቶችን እንደሚፈለፍሉ አስጠንቅቀን ነበር። የሆነውም የፈራነው ነው። ስለሆነም፣ ችግሩ ጃዋርን በማሰር መፍትሄ አያገኝም።
ኦሮሞ በታሪኩ ገፈት ቀማሽ ብቻ ሳይሆን፣ ግፍ ፈፃሚ የነበረ መሆኑንም ወጣቱ ካልተረዳና ከባሌ ቀበሌዎች ተነስቶ ወደ ሰሜን ምስራቅና ምእራብ ኢትዮጵያ ሲስፋፋ ሌሎችን እያጠፋና ከ20 በላይ ብሄረሰቦችን ውጦና ሰልቅጦ ማንነታቸውን አክስሞና ኦሮሞ አድርጎ መቀሌ ድረስ መስፋፋቱን የኦሮሞ ወጣት ካልተማረና ስለራሱ ታሪክ ሚዛናዊ አስተሳሰብ ካልያዘ ለአመታት የተጋተው የገፈት ቀማሽ ስነልቡና ገና ብዙ ጥፋት ያደርሳል። ኢትዮጵያውያንን በሙሉ ከክልሉ ካላስወጣ የሚቆም አይደለም።
ጠቅላይ ሚኒስትሩም ለችግሩ መፍትሄ የሚሹ ከሆነ በር ዘግቶ ከአባገዳዎች ጋር መምከር ሳይሆን፣ በኦሮሞ ብሄርተኝነት የተፈበረኩ ትርክቶች ላይ ሃገሩን በጋራ ማነጋገር አለባቸው። ጨለንቆ ኦሮሞን የማይመለከት ከሐረሪ አሚር ጋር የተደረገ ውጊያ መሆኑን የተረክ እርምት ሊደረግ ይገባል። አኖሌ ላይም ከቡርቃ ዝምታ ገጾች ውጪ የተፈጠረ የጡት ቆረጣ እንዳልነበር ስምምነት ላይ ተደርሶ ሃውልቱ መፍረስ ይኖርበታል። በአንድ ሃገር መኖር ከተፈለገ በግልፅና በሀቅ መነጋገርና መደራደር የግድ ነው።
አሁን ባለው ሁኔታ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው ያሳዩት ጭካኔ በተወሰነ ደረጃ የዚሁ የተበላሸ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ትርክት ሰለባ ስለሆኑ ነው ብዬ አስባለሁ። የተጨፈጨፉትን ኢትዮጵያውያን ህይወት በተንሸዋረረው የኦሮሞ ብሄርተኛ ትርክት መነፅር ስላዩት መሆን አለበት፣ ጭፍጨፋው ያላሳዘናቸውና ወጥተውም ሊያወግዙት ያልቻሉት ብዬ አሰስባለሁ። እንደ ደንቡ የተወሰኑትን የልኡካን አባላት ሶቺ ሩሲያ ላይ ትተው መመለስ ነበረባቸው። እንደደረሱም ሃዘናቸውን መግለፅ ነበረባቸው። የብሄራዊ ሀዘን ቀንም ማወጅ ነበረባቸው። አንዱንም ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆኑም። ይህ ከአንድ ሃገራዊ መሪ የማይጠበቅ ፈፅሞ ተቀባይነት የሌለው ጭካኔ ነው። በአፋጣኝ ሊታረምም ይገባዋል። አሁንም የረፈደ ቢሆንም፣ ማድረግ ያለባቸው ሃላፊነት ነው፣ ሊሸሹት አይገባም። በአቢይ ጭካኔ እጅግ አዝኛለሁ።
በጭካኔውም ብቻ አይደለም፣ ግልፅና ቁርጠኛ አመራር ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑም እንዲሁ አዝኛለሁ። ለመዋሸት ያሳየውም ፈቃደኝነት ረብሾኛል። ስለ ፓርላማ ቆይታው ሐረር ላይ ሲናገር፣ የጃዋር አሜሪካዊና የርሱ ኢትዮጵያዊ የእንግሊዘኛ ቃል አረዳድ የፈጠረው ችግር እንደሆነ አድርጎ ያቀረበበት ብልጣብልጥነት አስደንግጦኛል።  ይሄ ብልጣብልጥነት መቆሚያው የት ይሆን? ወደፊትስ ስንት ጥፋት ያደርስ ይሆን?
በኦሮሚያ ክልልና አዲስአበባ ያሉ ኦሮሞ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያን እጣ ያሳስበኛል። እየመጣ ያለው አደጋ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርቲ በኦዲፒ አመራርና በክልሉ አስተዳደርና የፖሊስና ደህንነት ሃይሎች ትብብር የሚካሄድ ለመሆኑ እያንዳንዱ ቀን ግልፅ እያደረገው ነው። ተሰባስቦና ተደራጅቶ ካልተጋፈጡት በቀር፣ እስካሁን በተያዘው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይታደጉናል በሚል ለረጅም ወራት ሲካሄድ የቆየው መዘናጋትና በፍርሀት ቆፈን ተቀፍድዶ መቀመጥ ፈፅሞ መፍትሄ አይደለም። ራስን የማጥፊያ መንገድ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸውና መፅሀፋቸው የሚያሽሞነሙኗት ኢትዮጵያን ከእልቂት የመታደግ ተነሳሽነት ካላቸው የሚከተሉትን ቢያደርጉ ተገቢ ይመስለኛል።
ሀ) የአዲስ አበባን ፖሊስ ከከተማዋ ነዋሪዎች የተውጣጣና ለአንድ ክልል ወይም ብሄር ተጠሪነት የሌለው እንዲሆን አድርጎ መልሶ ማደራጀትና ማብቃት፣ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይልን ከአዲስ አበባ ማስወጣት፣
ለ)በኦሮሚያ ክልል ከተሞችና የገጠር ቀበሌዎች የሚኖሩ ኦሮሞ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩባቸው እንደ ናዝሬትና አሰላ በመሳሰሉ ከተሞች እነዚህ ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉባቸው የፖሊስ አደረጃጀትና የከተማ አስተዳደሮችን ማቋቋም። እነዚህ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩባቸው ቀበሌዎች ራሳቸውን መከላከል የሚያስችሏቸው የመንግስት ፈቃድ ያላቸው ትጥቆች እንዲኖራቸው ማድረግ፣
ሐ)በአጭር ጊዜ ርቀት፣ የመከላከያውን/ፈጥኖ ደራሹን ሃይል ብዛት መጨመር፣ ከሌሎች የልማት መርሀግብሮች ቀንሶ መከላከያውን ማጠናከር። ግጭት ሊቀሰቀስባቸው በሚችሉ አካባቢዎች በሙሉ የመከለከያ ተቋም በቅርብ ርቀት እንዲኖር ማድረግና፣ ችግር ሲቀሰቀስ ከአንድ ሰአት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ፈጥኖ ደራሽ ሊሆን የሚችልበትን ስምሪት ማድረግ። እነዚህ ፈጥኖ ደራሽ ሃይሎች ከከባቢው የፖለቲካ ተጠቃሚዎች ጋር እንዳይተሳሰሩ የሚያደርግ፣ የብሄረሰብ ስብጥርና ተዋፅኦን የጠበቀ አመራር  አሰራርና ዲሲፕሊንን ማንበር ያስፈልግ ይመስለኛል።
መ) ዋነኛው መፍትሄ ግን የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲመጣ ማድረግ በመሆኑ፣ ነፃ የሆነ የኦሮሞ ሪፐብሊክ ለመመስረት ተብሎ የተፈበረኩ ትርክቶችን መጋፈጥና በግልፅ መወያየት፣ የጋራ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር ያለመው እሳቤን ነብስ ለመዝራት መወሰድ ባለባቸው እርምጃዎች ላይ አስፈላጊውን የልሂቃን ድርድር ማድረግ ትናንት መደረግ የነበረበት ለነገ ግን ይደር የማይባል መሆኑን መቀበል ይረዳ ይመስለኛል።
Filed in: Amharic