>

ዐብይና ጃዋር (መስፍን አረጋ)

ዐብይና ጃዋር

መስፍን አረጋ

 

አውራውን እያሉ ባሕር የሚያሻግር መርከበኛ አምበል
ጭፍራውን ይላሉ መርከብ የሚያናውጽ አደገኛ ማበል፡፡

 

ዐብይ አህመድን እና ጃዋር ሙሐመድን በተመለከተ አብዛኞቹ የጦቢያ ብሔርተኞች (በተለይም ደግሞ አማሮች) ትልቅ ስህተት ሲፈጽሙ ይታየኛል፡፡ ስህተቱም ዐብይን የጦቢያ በረከት፣ ጃዋርን ደግሞ የጦቢያ መርገምት አድርጎ የመመልከት አባዜ ነው፡፡

ጃዋር ሙሐመድ በመሠረተቢስ ትርክቱ እንደ በግ የሚነዳውና ሊነዳውም የሚችለው ማይሙን የቄሮን መንጋ ብቻና ብቻ ነው፡፡ ማይሙ የቄሮ መንጋ ደግሞ የመንግስት ድጋፍ እስከሌለው ድረስ ተልባ ቢንጫጫ ባንድ ሙቀጫ መሆኑን የጥቅምት 13 እና 14 ክስተቶች በግልጽ አስመስክረዋል፡፡ ስለዚህም የጦቢያና የጦቢያውያን ችግር ቄሮ ሳይሆን ቄሮን በቀጥታና በተዛዋሪ የሚደግፈውና የሚያሰማራው የዐብይ አህመድ መንግስት ነው ማለት ነው፡፡

ጃዋርም ቄሮም የቆሙት በአብይ አህመድ መንግስት ላይ ነው፡፡ ከዐብይ አህመድ በፊት የቄሮ መንጋ ከፋ ቢባል ማድረግ የሚችለው ለሰዓታት መንገድ መዝጋት ነበር፡፡ የቄሮ መንጋ መቁረጥ፣ መፍለጥ የጀመረው በዐብይ አህመድ ዘመን ነው፡፡ በተጨማሪ ደግሞ በቄሮ የሚሳበበውን አብዛኛውን አረመኔያዊ ጭፍጨፋ የሚያካሄደው ራሱ ቄሮ ሳይሆን፣ ቄሮን ተመሳስሎ የሚዘምተው የለማ መገርሳ መከላከያ፣ የሽመልስ አብዲሳ ልዩ ኃይልና፣ የኦሮሚያ ፖሊስ መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም፡፡

የዐብይ አህመድ ዋና ኦነጋዊ ሚና ጦቢያውያንን (በተለይም ደግሞ አማሮችን) ባፉ እየሸነገለ በማደንዘዝ፣ እስገምግሞ እየመጣ ያለውን የሞት ሽረት ትግል እንዳያዩና ለትግሉ እንዳይዘጋጁ ማድረግ፣ አይተው መዘጋጀት የጀመሩ ካሉ ደግሞ ያለ ርህራሄ መጨፍጨፍ ነው፡፡ ይህን ሚናውን ደግሞ ባመርቂ ደረጃ እየተወጣ ይገኛል፡፡

በዐብይ ስብከት የደነዘዙ አያሌ አማሮች አሁንም ድረስ የዐብይን የበግ ለምድ እንጅ ተኩላነቱን እንዳያዩ ዓይናቸውን ግምባር እንዳደረጉ ናቸው፡፡ የጠቅል (ጀነራል) አሳምነው ጽጌ፣ የዲባቶ (ዶክተር) አምባቸውና፣ የሕጋቶ አዘዘው አረመኔያዊ አገዳደል፣ አማራውን ያለ መሪ ከማስቀረቱ በተጨማሪ ሽብር ለቆበታል፡፡ ዐብይ አህመድ የቄሮን ጭራቅ እንዳሻው እንዲሆን የሚፈቅድለትና የሚያበረታታው ደግሞ አማራውን ፈልጦና ቆርጦ ይጨርሰዋል በማለት ሳይሆን ሽብር እንዲለቅበት ነው፣ የተሸበረ ሕዝብ ራሱን በራሱ ያፈናቅላልና፡፡

በሌላ በኩል ግን ራሱን አባቄሮ ነኝ የሚለው ጃዋር ሙሐመድ በድርጊቱ የጦቢያውያንን ፀረ ኦነግ ትግል በብዙ ረገዶች እያገዘ ይገኛል፡፡ በመጀመርያ ደረጃ ግልጽ የሆነው የጃዋር ለከት የለሽ ፀራማራ ትርክት፣ በዐብይ አህመድ ተማምነው የተኙትን አማሮች ይቀሰቅሳል፡፡ አማሮች ተቀስቅሰው ባንድነት ከተንቀሳቀሱ ደግሞ የፀራማራው የኦነግ የወረቀት ነበርነት ባጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚረጋገጥ ራሱ ኦነግ በደንብ ያውቃል፡፡ ኦነግ የሚወቅሰውና የሚከሰው እስካፍንጫው የታጠቀውን ጦረኛውን ወያኔን ሳይሆን ሰላማዊውን አብንን የሆነበትም ምክኒያት ይሄው ነው፡፡ ስለዚህም የኦነግን መቃብር በተዛዋሪ መንገድ እየቆፈረ ያለው ራሱ ጃዋር ሙሐመድ ነው ማለት ነው፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የዐብይ አህመድን ሚስጥር ገሃድ የሚያወጣልን ጃዋር ሙሐመድ ነው፡፡ በዚህ ደግሞ ከልብ ልናመሰግነው ይገባል፡፡ ለምሳሌ ያህል ዐብይ አህመድ ማናቸውን ድርጊት የሚያደርገው ከካቤኔ አባሎቹ ጋር ሳይሆን ከጃዋር ጋር እየመከረና እየዘከረ መሆኑን የነገረን ራሱ ጃዋር ነው፡፡ እኛ ጦቢያውያን መስማት የማንፈልገውን አልሰማ አልን እንጅ፣ ጀዋር ሙሐመድ ግን ዐብይ አህመድና ለማ መገርሳ ጦቢያ፣ ጦቢያ የሚሉት ውሸታቸውን እንደሆነ በግልጽ አማርኛ ነግሮናል፡፡

ከሁሉም በላይ ደግሞ ጃዋር ሙሐመድ ባፉ ጨካኝ ቢመስልም በልቡ ቡቡ መሆኑን ሁኔታውን አይቶ በቀላሉ መገመት ይቻላል፡፡ /የሚሰማውን/ ሁሉ የሚናገር፣ የሆዱን ሁሉ የሚዘረግፍ የጃዋር ዓይነት ግልጽ ሰው አብዛኛውን ጊዜ ሩህሩህ ነው፡፡ የዐብይ አህመድና የለማ መገርሳ ዓይነት ሆዱ የማይገኝ ጭምት፣ መያዣ መጨበጫ የሌለው ሸለመጥማጥ ሰው ግን አብዛኛውን ጊዜ አረመኔ ነው፡፡

አማራን ቁረጡት ፍለጡት ለሚለው ለጃዋር ሙሐመድ አንድ ያማራ ወጣት ከፊቱ አቅርበው ግረፍ ቢሉት እንባውን ባይዘረግፍ እንኳን እንደሚያቅማማ ግን በርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል ግን መግደል መሸነፍ ነው፣ ፍቅር ያሸንፋል፣ እናቴ ሞቴ፣ ሚስቴ ሂወቴ ናት እያለ ቀን ከሌት ለሚደሰኩረው ለዐበይ አህመድ አንድ ጨቅላ ሕፃን ከፊቱ አቅርበው ለሁለት ገምሰህ ለባልና ሚስት አካፍል ቢሉት ላፍታ የሚያመነታ አይመስለኝም፡፡

የዐብይ አህመድንና የለማ መገርሳን አረመኔነት ለመረዳት ከባሕርዳሩ ጭፍጨፋ የበለጠ ግልጽ ምስክር አይገኝም፡፡ ዶክተር አምባቸውና ምግባሩ ከበደ ራሳቸው ሙተው ጦቢያንና ጦቢያዊነትን ከሞት አፋፍ ያደረሱት የዐብይ አህመድ ማር በመርዝ የተለወሰ መሆኑን ባለመጠርጠራቸው ነበር፡፡ ያልጠረጠረ ተመነጠረ፡፡ ይበልጥ የሚያሳዝነው ደግሞ በርካታ ጉምቱ ጦቢያውያን (በተለይም ደግሞ አማሮች) ከነ ዶ/ር አምባቸው ሳይማሩ የዐብይ አህመድን በመርዝ የተለወሰ ማር አሁንም ድረስ እየላሱ መሆናቸው ነው፡፡

ስለዚህም ጃዋርን ጃዋር እንዲሆን ትተን፣ ሙሉ ትኩረታችንን ማድረግ ያለብን በምግባራቸው የጦቢያና የጦቢያዊነት ነቀርሳ በሆኑት በዐብይ አህመድና በለማ መገርሳ ላይ ብቻ ሊሆን ይገባል፡፡ ጦቢያውያንን በሽንገላ እያደነዘዙ በኦነግ ጅብ የሚያስበሉት እነዚህ ሁለት ነቀርሶች ባጭር ጊዜ ውስጥ ካልተመነገሉ፣ ወደ አፋፍ የሚገፏትን ጦቢያን አንኮታኩተው በመቃብሯ ላይ የኦሮሚያን አጼጌ (empire) የሚመሠርቱበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡

ይሆናል ያልነው ሰው የኢትዮጵያ ሙሴ
ሆነና አረፈው የምሥር ራምሴ፡፡
አንዴ ቢሸውደን የሱ ነው እፍረቱ
ሁለቴ ቢደግም የኛ ነው ጥፋቱ፡፡

መስፍን አረጋ
mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic