የማያዛልቅ ባል ቅንድብ ይስማል
ዳግማዊ ጉዱ ካሣ
ሽሉም ገፍቶ ቂጣውም ጠፍቶ የተፈራው ነገር ሁሉ ደርሶ እዚህ ደርሰናል – ጥቅምት 22 ቀን 2012ዓ.ም. ፡፡ ማታም ሆነ፤ ቀንም ሆነ አንድ ዓመት ከስድስት ወርና ከ22 ቀናት፡፡
እውነት ነው – የማያዋጣ ባል ቅንድብ ይስማል፡፡ የማያዛልቅ ባልም ይሁን ጓደኛ የሚፈልገውን እስኪያገኝ የሚያሳየው መቅመድመድ አይጣል ነው፡፡ ይሉኝታን አውልቆ ይጥላል፡፡ ሀፍረት ሲያልፍ አይነካውም፡፡ አንጎሉን አስቀምጦ በስሜቱ ብቻ ዕውር ድንብሩን ቀን ከሌት ይባዝናል፡፡ የሰባተኛው ንጉሣችን ነገርም እንደዚሁ ሆኖ ዐረፈው፡፡ክፉኛ እየተቸገርኩበት ያለ ነገር አለና እሱን ላስቀድም፡፡
ቋንቋን በአግባቡ ካልተጠቀሙበት እጅን አወዛጋቢ ነው፡፡ በመሆኑም “አማራ፣ትግሬ፣ኦሮሞ…” ስንል የትኛውን አማራ? የትኛውን ትግሬ? የትኛውን ኦሮሞ? ማጣቀስ እንደፈለግን በመለየቱ ረገድ በጣም የምንቸገር ብዙዎች ነን ብዬ አምናለሁ፡፡ ስለዚህ በበኩሌ ትንሽ ለዬት ያለ የቃላት አጠቃቀምን “መፍጠር” ጠቃሚነቱን ተረድቻለሁና የፈለገ ያለ “ደራሲው ፈቃድ” መጠቀም እንደሚችል ከወዲሁ እየገለጽኩ ወደ “ፈጠራየ” ላምራ፡፡
ጽንፈኛነት ወይም ጽንፈኝነት በሁሉም ጎሣና ነገድ መታየቱ እውነት ከሆነ ሰነበተ፡፡ ጽንፈኛነትና አክራሪነት ደግሞ ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ሁሉም አማራም ሆነ ትግሬና ኦሮሞ ደግሞ ጽንፈኛም ሆነ አክራሪ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለዚህ ጤነኛውን ከበሽተኛው ለመለየት እንዲህ ብናደርግስ ብዬ አሰብኩ፡፡
ጽንፈኛ ኦሮሞን ለመጥቀስ ሲፈለግ በጅምላው ኦሮሞ ከማለት ይልቅ “ጽ-ኦሮሞ” ቢባል፣ ጽንፈኛ ትግሬ ለማለት “ጽ-ትግሬ” ቢባል፣ አክራሪ አማራ ለማለት “አ-አማራ” ቢባል… ንጹሓንን በጅምላ ከመውቀስ እንታቀባለን፡፡ “ዐይጥ በበላ ዳዋ ተመታ” እንዳይሆን ነው ዓላማው፡፡ ቅጽሎችን መጠቀም ቁጣን ያበርዳሉና በንግግራችንም ሆነ በጽሑፋችን ጥንቃቄ እናድርግ፡፡
የሌሊት ወፉ ሰባተኛው ንጉሥ ችግር ላይ ነው፡፡ እግዜር ካልረዳው በቀላሉ ወደማይወጣው አረንቋ ውስጥ ተዘፍቋል፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ አያውቀውም፡፡ እየሣቀ የሚገድል መሆኑን አልተረዳም፡፡ ጭብጨባ አናቱ ላይ ወጥቶ አናፍሎታል፡፡ ሆዳምና ሥልጣን ወዳድ ጭፍን ታዛዦች ከበውት እንደነዚያድባሬና ሞቡቱ ሴሴኮ የንግሥና ክንፍ ሳያበቅሉለት የቀሩ አይመሰለኝም፡፡ የሕዝብ ዕንባና ልቅሶ መቀመቅ እንደሚከት የተገነዘበ አይመስልም፡፡ በመንታ ምላስ እየተቅጠፈጠፈ ዕድሜ ልኩን የሚገዛ ሳይመስለውም አልቀረም፡፡ ከነመንግሥቱና አባቱ መለስ በፍጹም አልተማረም – የሥጋ ፍላጎቱ የነፍሱን መሻት አወየበበት፡፡ ሃይማኖቱን ከባዕድ አምልኮት ጋር አጫፍሮ በመያዝ የዲያብሎስ ታዛዥነቱን ገፋበት – በዚህስ ያሳዝነኛል፡፡ በሁለትና ሦስት ማንነቶች አንዲትን ሀገርና አንድን ሕዝብ ለመግዛት የቋመጠ ይመስላል – ፍጹም የማይቻለውን ነገር፡፡ የቃላት ሽንገላና በተለያዩ ቋንቋዎች የሚደረግ እርስ በርሱ የሚጋጭ ዲስኩር ከአንድ ጀምበር የበለጠ ዕድሜ እንደማይሰጥ አላወቀም፡፡ ራሱ ተታሎ አገርና ሕዝብ እያታለለ ነው፡፡ የአቢይ አወዳደቅ ከሌሎች ቀደምት ገዢዎች አወዳደቅ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ቁልጭ ብሎ ይታየኛል፡፡ ምክንያቱም የሌሊት ወፍ አጥቢም በራሪም ልትሆን ፈልጋ በየምትጠጋበት ሁሉ “የኛ አይደለሽም” እያሉ ፊት እንደነሷትና እንዳባረሩዋት ሁሉ አቢይም የቤተ መንግሥት ቆይታውን በደቂቃና ሰዓቶችም ቢሆን ያራዘመ እየመሰለው ባህርዳርና ደሴ የሚናገረው ሐረርና ጂማ ከሚናረው ዐይንና ናጫ እየሆነበት ተቸግሯልና በዚህ መንገድ ብዙ አይገፋም፡፡ በርግጥም ያሳዝናል፡፡
ወደ ሥልጣን በመጣ ሰሞን የማይሆነው ነገር አልበረም፡፡ ሚኒስትሮችን ሲያስተምር፣ የጦር አበጋዞችን ስለውጊያና የጦርነት ንድፍ አወጣጥ ሲያሰለጥን፣ ሽማግሎችን ሲመክር፣ ቀሣውስትን ስለሃይማኖት ሲሰብክ፣ ወጣችቶን ሲገራ፣ ሴቶችን ስለወር አበባ አመጣጥና አካሄድ ሲያስረዳ፣ ፓይለቶችንና ሆስተሶችን ስለአውሮፕላን አብራሪነትና መስተንግዶ ሲያሰለጥን፣ ወጌሾችን ሰብስቦ ስለስብራት ዓይነቶች ማብራያ ሲሰጥ፣ መምህራንን ስለየሙያቸው ሲያስጠና… በሌላ ወገን ደግሞ እስረኞችን ባገር ቤት ወደዘብጥያ እየደመረ ከውጭ ግን ሲያስፈታ፣ መሥሪያ ቤቶችን በጽ-ኦሮሞ ሲያጥለቀልቅ … 24 ሰዓት ዕንቅልፍ አጥቶ ሲባዝንና ሲብከነከን ብዙ ጊዜ አሳለፈ፡፡ ያለርሱም ኢትዮጵያ ብታድር የማትውል፤ ብትውል የማታድር እስክትመስል ድረስ ወጧ እንዳማረላት ሴት ሽር ጉዱን አጧጧፈው፤ እኛና እርሱም ያለርሱ እንደማይሆንልን በሚገባ ተረዳን፡፡ የኤርትራ ሕዝብና መንግሥትም ሰገዱለት፤ ሀገራችን ለይስሙላም ቢሆን ፓርላማና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ተብዬ የሌላት እስክትመሰል ድረስ የአንድ ሰው ፊታውራሪነት በምሥራቅ አፍሪካ ነገሠና እኛም የሌላው ዓለም ጭምት ታዛቢም ጉድ አልን፡፡ ጎረቤቶቻችንን ጨምሮ የሌላው ዓለም በተለይም የዐረብ ኢምሬቶች በፍቅሩ ነሆለሉለት፤ ከነፉለትም፡፡ አንድ ቅዱስ አባት ቅድስት ማርያምን “በምንት ንመስለኪ” በሚል ብዙ ስያሜዎችን እንደሰጣት ሁሉ እኛም ለአቢያችን ለጥቂት ክርስቶስነትን ከመስጠት ተቆጠብን እንጂ – ለምን እንደተቆጠብን ሳስበው ይገርመኛል – ከመሢሕነት ጀምሮ ለርሱ ያልሰጠነው ስም አልነበረም፡፡
ይህ ሁሉ ግን ልጁን አማረጠውና፣ ቆጥ ሰቀለውና፣ ከሃሌ ወአእማሬ ኩሉ ስሜት በትንሹዋ ጭንቅላቱ ውስጥ አሳደረና መጨረሻው አላምር አለ – ከመቆሙ መቀመጡ ግልጽ ሆነ፤ ዐይን ገባው – የሀበሻ ዐይን ደግሞ እንኳን ሥጋ ለባሽን ድንጋይን ሳይቀር ይሰብራል፡፡ እናም እንደሸምበቆ ሽቅብ ከመወንጨፉ እንደሙቀጫ ቁልቁል መንከባለሉ ከአድማስ ወዲህ ፍንትው ብሎ ታዬ፡፡ እኛም አልን – “የት ይደርሳል የተባለ ጥጃ ሉካንዳ ቤት ተገኘ”፡፡ (አሁን ደግሞ “የሰሞኑ ዕልቂት የተፈጸመው ዜጎች እርስ በርስ ተቧድነው በፈጠሩት የግልና የቡድን ጠብ እንጅ ጃዋር ወንድሜን ለቀቅ አድርጉት!” እያለ ነው አሉ- ሀፍረትን ባወጣ ቸብችቦ የበላው ዶ/ር አቢይ፤ ዘይገርም ሻሸመኔ ትብስ ኮፈኔ ማለት አሁን ነው፡፡) ብቻ እኛ ብሂላችንን ቀጠልን “የማያድግ ልጅ እንትኑ ይበዛል፡፡” ሰለስንም “ የማያድግ ልጅ በአባቱ ብልት ይጫወታል፡፡” ዶክተር ኢንጂኔር አልሃጂ አልሞብሱጥ ፊልድ ማርሻል የዕድሜ ልክ ፕሬዝደንት ዘኢትዮጵያ ወእጨጌ ዘኦሮምያ ወአማርያ ካሙዙ ባንዳ ማለትም ዶክተር አቢይ አህመድ አሊ – ይቅናህ፡፡ የምታስጨፈጭፋቸው የእናትህ ዘሮች ደም እሳት ሆኖ እንዳይበላህ በጊዜ ወደ ኅሊናህ ብትመለስና የሥልጣንና የዝነኝነት አራራህን ብትገርዝ ግን ደስ ባለኝ፡፡ ይሁንና አትችልም፡፡ ተፈጥሮን ተመክሮ አይመልሰውምና፡፡ አትጠራጠር(ሩ)- ኢትዮጵያ ግን ነፃ ትወጣለች፡፡ ጥያቄው “መቼና በምን ያህል መስዋዕትነት?” የሚለው እንጂ ነፃነት በር ላይ ቆማ እያንኳኳች መሆኗ ግልጽ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ችግር የመጀመሪያዋም የመጨረሻዋም አይደለም፡፡ ሰይጣን እስኪታሰር ብዙ ፈተና በምድር ላይ ይሆናልና፡፡
በነዚህ ሁለት ቀናት ካነበብኳቸው በርካታ መጣጥፎች ውስጥ የአባዊርቱ፣ የታምራት ላይኔ፣ የመስከረም አበራ፣ የዶ/ር አብርሃም ዓለሙ የቲም ለማ የሐረር ንግግር ትርጉም፣ የሻለቃ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ… ጥቂቶቹ ናው፡፡ ከሻለቃ ዳዊት የቀነጨብኩትን እዚህ በታች የተቀመጠ ቅንጭብ እንድታነቡልኝ ጋብዤያለሁ፡፡ መልካም መጨነቅ ለኔን መሰሉ ቦዥቧዣ – መልካም ዕረፍት ለግዴለሾች፡፡
…. ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ የኦሮሞ እክራሪዎችን «አይደግፍም!» የሚሉ ብዙዎች አሉ። የኦሮሚያ ክልል ም/ፕሬዚደንት ማለትም የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ምክትል፣ በአደባባይ አማራን ሙልጭ እድርጎ ሲያወግዝ – ሲዘልፍ ታሪኩን ሲያጎድፍ፣ መሪው ምን አለ? ምንም! ቀደም ብሎ የነበረው የክልሉ ፕሬዝደንት የአዲስ አበባን ዲሞግራፊ ለመለወጥ 500,000 ሺህ የኦሮሞ ተፈናቃዮችን ከሶማሌ ክልል «አምጥቼ በአዲስ አበባ ዙሪያ አስፍሬአለሁ!» ሲል፣ አጠገቡ ተቀምጦ የነበረው መሪው ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ምን አለ? ምንም! በቡራዩ፣ በለገጣፎ ኦሮሞ ያልሆኑ ዜጎች ሲጨፈጨፉ፣ ሲገደሉ፣ መሪው ምን አለ? ምንም! ዛሬ የኢትዮጵያ ባንዲራን የያዘ፣ የለጠፈ ሲወገዝ፣ ባንዲራው ከሰውና ከመኪና አልፎ ከቤተ-ክርስትያናት ላይ ሲፋቅ፣ መሪው ምን አለ? ምንም! ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ ያለው «ሁለት መንግስት ነው። የቄሮና የአቢይ።» ብሎ ጃዋር መሃመድ ሲናገር፣ መሪው ምን አለ? ምንም! አዲስ አበባ የኦሮሚያ «ነች!» ሲባል ከህግ አግባብ ውጪ የተሾመው ታከለ ኡማ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ዋና ከተማ ሲያደርጋት፣ መሪው ምን አለ? ምንም!
ቀን ባለፈ ቁጥር ጠ/ሚኒስትር አቢይ መጨረሻው ከላይ እንደተጠቀሱት መሪዎች መሆኑን ሲገነዘብ፣ ስልጣኑ ላይ ለመቆየት ሲል የበለጡ ስህተቶችን ይሰራል እንጂ ከስህተቱ «ይማራል!» ብሎ ማመኑ በብዙሃኑ ዘንድ አክትሟል። ለዚህም ነው አስቀድመን፣ «ሳይቃጠል በቅጠል» ብለን ስንፅፍ – ስንናገር የከረምነው። አንድ ኢትዮያዊ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰላም የኖቤል ሽልማት ሲያገኝ ደስ ይለናል፤ የመከፋት ስሜት አይሰማንም። ለእውነት ስንናገር ግን ይህ ሰው ሽልማቱ ይገባዋል? የኖቤል ሽልማት ማግኘቱ ስልጣን ላይ ለመቆየት ያለውን ፍላጎት ያጠናክረዋል እንጂ አይቀንሰውም። ዛሬ በአገራችን ውስጥ ሰላም የለም። ከኤርትራ ጋር ያለውም አለመግባባት ህጋዊ ይዘት ባለው ስምምነት አልተቋጨም። ኤርትራም ለጦርነት ያላት ስጋት እልቀነስም። ድንበሩም እንደተዘጋ ነው። ኢትዮጵያ በትግራይ በኩል ባላት ድንበር ላይ ከባድ የስጋት ድባብ እያንዣበበ መሆኑ ይታወቃል። ሰላም ቢፈጠርም እንኳን፣ ( አልተፈጠረም እንጂ) ለሁለቱም መሪዎች እንጂ የኖቤል ሽልማቱ ለአንድ መሪ ብቻ መበርከት አልነበረበትም። ሰላም በሁለት ወገኖች መልካም ፈቃድ የሚመጣ እንጂ በአንድ መሪ ግፊት ብቻ ወይም ፈቃድ የሚገኝ አይደለም። ….
ma74085@gmail.com