>

በምድር ላይ ያለውን ጽድቅ እንዳታዩ ማን አዚም አደረገባችሁ (ከይኄይስ እውነቱ)

በምድር ላይ ያለውን ጽድቅ እንዳታዩ ማን አዚም አደረገባችሁ

Wake up and Smell the Coffee

 

 

ከይኄይስ እውነቱ

 

ለርእስነት የመረጥኩት “wake up and smell the coffee” የሚለው ብሂል የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ሰዎች በዙሪያቸው የሚደረገውንና እየሆነ ያለውን ተገንዝበው፣ ከክህደታቸውና ከስህተታቸው ወጥተው እውነታውን እንዲጋፈጡ ሲፈልጉ የሚጠቀሙበት ኢመደበኛ ብሂል ነው፡፡ የዚህ አስተያየት አቅራቢም ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ንቁ! በሰው መታመን ከንቱነቱን ተረድታችሁ አገራችሁን ካየነውና ሊመጣ ካለው ጥፋት በኅብረትና ባንድነት ታደጉ የሚል የመቀስቀሻ ጥሪ ለማድረግ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ከዐቢይ ጋር አታያይዙ፡፡ የጋራ ቤታችን ከዐቢይ በፊት ነበረች÷በኋላም አለች ወደፊትም በሉዐላዊነቷ ፀንታ ትኖራለች፡፡ ኢትዮጵያ ከዚህ በታች የሚያዋርዳት አገዛዝ ይዛ መቀጠል አትችልም፡፡ ተያይዞ ለመጥፋት ካልሆነ በቀር፡፡ ዐቢይ በገዛ ፈቃዱም ሆነ ‹ተገዶ› የመንደርተኞቹን ፈቃድ ለመፈጸም የቁልቁለቱን መንገድ ሲጀምር የኢትዮጵያ ‹መሪ› መሆኑን በተግባር አቁሟል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ብዙዎቻችን እዚህ ደረጃ ላይ ከመድረሳችን በፊት ለዐቢይና ለለማ ያላሰቡትን ምክንያት ሁሉ በእነሱ ተገብተን ስናቀርብላቸው ከርመናል፡፡ በበኩሌ እኔ ተሳስቼ ዐቢይ ትክክል እንዲሆን ያልተመኘሁበት ጊዜ የለም፡፡ ኅሊናዬ ተቃራኒውን እየነገረኝም፡፡ የሚያሳዝነው ግን በምድር ላይ ያለው እውነት (ዐቢይ በተግባር እየፈጸመ ያለው የቀጠለበትም ድርጊት) ከግምቴ ጋር አንድ በመሆኑ ምኞቴ ከንቱ ሆኖ ቀርቷል፡፡ ስለሆነም በሰመመን ውስጥ ያላችሁ፣ የቀን ቅዠት ውስጥ የምትገኙና  ያልባነናችሁ ከአፈዝ አደንግዙ የምትወጡበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ 

በእኔ እምነትና አስተያየት ዐቢይም ሆነ እሱ የሚመራው አገዛዝ ኢትዮጵያን ሊመራ አልቻለም፡፡ በብስለትም÷በዐቅምም÷ በብቃትም ወዘተ. በተለይም ከአንድ ዓመት ወዲህ እንደታዘብኩት ምክርም ሆነ ተግሣፅ፣ የሕዝብ እሪታና ዋይታ የሚሰማ ዕዝን እንደሌለው በተግባር አረጋግጦልናል፡፡ እሱም ሆነ አገዛዙ  ከእንግዲህ ወዲህ ለማገገምም ዕድሉ ያላቸው አይመስለኝም፡፡ አሁንም ተስፋ ያልቆረጡት÷ እሱን እያመኑና እያመለኩ ለመቀጠል የሚፈልጉ የአገዛዙ ተጠቃሚዎችም ሆነ ጅሎች በመረጡት መንገድ መቀጠል መብታቸው ነው፡፡ ይሁን እንጂ ለአገርና ሕዝብ ብለው አሁን ካልነቁ ፈቅደውም ሆነ በጅልነታቸው ራሳቸውን የአሸባሪዎችና ጥፋቷን የሚመኙ ግለሰቦችና ቡድኖች ተባባሪ ሆነው ያገኙታል፡፡ ከዛ በኋላ የሚሆነው ጸጸትም ሆነ ልቅሶ የማይጠቅም ይሆናል፡፡ በበሰበሰ ድርጅት ተተብትቦ÷በዘረኞችና መንደርተኞች ተጠልፎ÷ በድንክዬዎች ተከቦ እንደ ኢትዮጵያ ያለች ታላቅ አገርን አይደለም ወያኔ ትግሬ የፈጠረላቸውን የጐሣ ‹መንደር› በቅጡ ማስተዳደር የሚቻል አይመስለኝም፡፡ የዐቢይ መግለጫ ጩኸቴን ቀሙኝ ሆኖብኛል፡፡ ከጊዜያዊው ይልቅ ዘለቄታውን÷ከጭፍጫፊው ይልቅ አንኳሩን÷ ከዘረኞች ቡድናዊ ፍላጎትና ጥቅም ትልቁን አገራዊ ሥዕል በማየት የታገሠው ዐቢይ ሳይሆን በሕይወቱ÷በአካሉ÷በነፃነቱና ከቤት ንብረቱ በመፈናቀል ጭምር ባገሩ ባይተዋር በመሆን የከፈለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡ ለዘረኞች የማይጠረቃ ፍላጎት÷ለአንድ ግለሰብ ሥልጣንና ሰብእና ግንባታ ሲባል (እንደ ሕወሓት በአገር ህልውና እያስፈራሩና ሥጋት ውስጥ እየከተቱ) ሕዝብና አገርን መያዣ አድርጎ ለመግዛት መሞከር ያለፈበት ነው፡፡ አብዛኛው ሕዝባችን  ዐውቋል/ነቅቷል፡፡ አዎ የአገራችን ህልውና ያስጨንቀናል፡፡ የሕዝባችንም ደኅንነት እንደዚሁ፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ ደማችንን ማፍሰስ ካለብን ራሳችንን ደም ከጠማቸው ዘረኞች÷ ከአሸባሪዎችና መሣሪያ ካደረጓቸው ግሪሳ ወረበሎች በመከላከል፣ ሺህ ዘመን ወደ ኋላ ከሚጎትተን የጎሠኝነት አገዛዝ ነፃ ወጥተን ‹መደመር/መቀነስ› በሚል የአገዛዞች ማጭበርበሪያ ሳንታለል የሕግ የበላይነት የሚሰፍንበት እውነተኛ የእኩልነት፣ የአንድነትና የአብሮነት ዘመናዊ ሥርዓት በኢትዮጵያችን እንዲነግሥ መሆን ይኖርበታል፡፡ 

ዐቢይ በቀረው ጊዜ ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ ቋሚ ውለታ ለመሥራት ከፈለገ በመላው የአገራችን ግዛት የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ዓውጆ፣ አዘዋለሁ የሚለውን የመከላከያ ኃይል አሠማርቶ በቅድሚያ ሕግና ሥርዓትን (ሰላምና ፀጥታን) ማስከበር፤ እኔም ሆንኩ ታላላቆቼ ከዚህ ቀደም ደጋግመን እንዳሳሰብነው በዚህ የአስቸኳይ ዓዋጅ ጊዜ አገራዊ የሽግግር ጉባኤ ጠርቶ የኢትዮጵያን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ በጉባኤው ውሳኔ መሠረት (የግለሰብ መብት/ነፃነትን ማዕከል አድርጎ ከሚጻፍ አዲስ ርእሰ ሕግጋት ጀምሮ በነፃና ፍትሐዊ ምርጫ በሕዝብ እስከሚመሠረት መንግሥት) ወያኔ ትግሬ የፈጠረውን የጐሣ (የተረኝነት) ፖለቲካ÷ የውሸት የቋንቋና የጐሣ ፌዴራሊዝም (የ9 ‹አገሮች› እና ‹ሕዝቦች› ነውረኛ ትርክት) ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከኢትዮጵያ ምድር መጥፋት ይኖርበታል፡፡ ይህ ሲሆን ብቻ ነው ኢትዮጵያና ሕዝቧ ሰንበት የሚያደርጉት፡፡

አንዳንዶች ዐቢይን መክሰስና መውቀስ ለወያኔ ትግሬ በር መክፈት ይመስላቸዋል፡፡ በጭራሽ፡፡ አሁንም በዚሁ መንፈስ የሚያላዝኑ እንዳሉ በመደበኛውም ሆነ በማኅበራዊው ብዙኃን መገናኛዎች የምንታዘበው ነው፡፡  ደጋግመን እንደተናገርነው የጐሣ ፖለቲከኞች በሙሉ የወያኔ ትግሬ ግርፎች ናቸው፡፡ ዛሬ ጀዋር እንደሚጠቀምባቸው ጋጠ ወጦች፣ የእጁ ሥራዎች የሆኑት 3ቱም ድርጅቶች በአሽከርነታቸው ዘመን የኢትዮጵያን ሕዝብ በየተቧደኑበት ጐሣ ቁም ስቅሉን ሲያሳዩት ኖረዋል፡፡ አሁን ደርሰው የጐሣ/ነገድ ጠበቆች ለመምሰል የሚሞክሩት በሙሉ እጃቸው እንወክለዋለን በሚሉት ማኅበረሰብ ደምና ሀብት ዝርፊያ የጨቀየ መሆኑን ዘንግተዉት ከሆነ ፍትሕ እስኪደላደል የኢትዮጵያ ሕዝብ መቼም አይረሳውም፡፡ ሕወሓት ለሽብር ባያንስም ከእንግዲህ ወዲህ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ቦታ የለውም፡፡  አሁን ለተፈጠረው አገራዊ ምስቅልቅል መሠረቱ ሕወሓት ቢሆንም የዐቢይ አገዛዝ፣ ዙሪያውን የሰበሰባቸው የጐሣ ፖለቲከኞች (የጐሣ ፖለቲካ የድንቁርናና የዕብደት ፖለቲካ በመሆኑ ጽንፈኛና ለዘብተኛ ብሎ መከፋፈሉ ትርጕም የለውም፡፡ መነሻቸውም ሆነ መድረሻቸው አንድ ነው፡፡) ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ አንዱ በሽብር አከፋፋይነቱ፣ ሁለተኛው ተረኝነት ባመጣው ማንአለብኝነት÷ ጥጋብና ሽብር ቸርቻሪነት፣ ሌላኛው ደግሞ በአስደንጋጭ ዳተኝነቱና በተግባር ከነውረኞች ጋር በማበሩ፡፡ 

ስለዚህ ኢትዮጵያዊ ወገኔ ንቃ! ፈጣሪህን ይዘህ በኅብረትና ባንድነት አገርህን ለመታደግ ተነሣ፡፡ ኅብረትና አንድነትህ ቃልን ከተግባር አዋሕደው ኢትዮጵያን ከሚያገለግሏት ጋር መሆኑን አረጋግጥ፡፡ ኅብረትና አንድነትህ ዜጎችን በጐሣ ማንነታቸውና በሚከተሉት እምነት ምክንያት ልዩነት ከማያደርጉት ጋር መሆኑን አረጋግጥ፡፡ ኅብረትና አንድነትህ በስምህ ከሚነግዱ የጐሣ ፖለቲካ ነጋዴዎች ጋር ሳይሆን በሰውነትህ÷በዜግነትህ ከሚቀበሉህና በአገራችን ሁለንተናዊ ሕይወት እኩል መብትና ተሳትፎ እንዳለህ ከሚያስቡ ጋር መሆኑን አረጋግጥ፡፡ ኅብረትና አንድነትህን ያገርህ ሉዐላዊ ባለቤት መሆንህን በተግባር ከሚመሰክሩ ጋር አድርግ፡፡ ኅብረትና አንድነትህ ለዘመናት በዘለቀው መስተጋብርህ ለሠራሀቸው አኩሪ የጋራ ታሪክህ፣ ላዳበርካቸው ዘመን ተሻጋሪ የጋራ እሤቶችና ቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችን በደማቸው ላስከበሩት ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ተገቢውን ክብርና ዕውቅና ከሚሰጡ ጋር አድርግ፡፡ 

በቅንነትም ሆነ በቂልነት እውነታውን ለማየት በሽሽት ያላችሁ ወገኖቼ (ረቂቅነቱ ‹ሁለተኛው እግዚአብሔር› ያሰኘውን የሰውን ኅሊና ለመመርመር ከመሞከር) በምድር ላይ የሚዳሰሰውንና የሚታየውን እውነት ፊት ለፊት ተጋፈጡትና ወደ ኅሊናችሁና ወደ አእምሮአችሁ ሳይረፍድ ተመለሱ፡፡ ማስተዋሉን ይስጣችሁ፡፡

Filed in: Amharic