>
11:17 pm - Wednesday November 30, 2022

አገዛዙና ጃዋር ምንና ምን ናቸው??? (አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

አገዛዙና ጃዋር ምንና ምን ናቸው???
አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው 
አገዛዙ ጃዋርን በተመለከተ የያዘው አቋም ኢአመክንዮአዊ፣ ኢፍትሐዊ፣ ጭፍን ወገናዊ፣ ፍጹም ያልተገባና አደገኛ መሆኑን የሚያረጋግጡ እነኝህን ጥያቄዎች መመለስ ይቻለዋልን??? በፍጹም አይችልም!!!
አገዛዙ እነኝህን ከጃዋር ጋር በተያያዘ የማነሣቸውን ጥያቄዎች መመለስ የማይችለው በሌላ በምንም ምክንያት ሳይሆን ለእውነት መቆም ካለመፈለጉና ዋነኛው የችግሩ አካል በመሆኑ እንደሆነ ተንትነን እናያለን፦
ማሳሰብ የምፈልገው ጉዳይ ግን ግንዛቤያችንና እንቅስቃሴያችን እውነታው በሚነግረን ወይም መሬት ላይ ካለው ተጨባጭ ሐቅ ጋር በተገናዘበ መልኩ መሆን እንዳለበት ነው፡፡ ይሄ ካልሆነ በስተቀር ነገራችን ሁሌም ታጥቦ ጭቃ እንደሚባለው ይሆንና፣ ምንም ዓይነት ለውጥ ማምጣት አንችልምና ነው!!! ለውጥ ከፈለግን የአቋምና የመርሕ ሰዎች መሆን ይጠበቅብናል!!!
ለምሳሌ ሲኖዶስ የተባለውን አካል የተመለከትን እንደሆን መሬት ላይ ያለው ተጨባጩ ሐቅ አገዛዙ ከአሸባሪዎች ጋር ሆኖ ምእመናንን እያጠቃ እንደሆነ እያሳየ፣ እነሱም እራሳቸው በመግለጫዎቻቸው ይሄንን በማንሣት እየወቀሱ ባሉበትና “… ከአሁን በኋላ ግን ተመሳሳይ ጥቃት በቤተክርስቲያን ላይ ቢፈጸም….!” የሚል መግለጫ ባወጡ ማግሥት አገዛዙ ለቤተክርስቲያኗ ካለው ከፍተኛ ንቀት የተነሣ ከዚህ ቀደም ሲያደርገው ከቆየው በከፋ ሀኔታ በተለያዩ የሀገሪቱ ስፍራዎች የጸጥታ አካላቱ ቆመው ምእመናንን እንዳሳረዱ፣ የሙጥኝ ብለው የተጠጓቸውን ምእመናንን አሳልፈው ሰጥተው ከፊታቸው እንዳሳረዷቸው፣ ቆመው ባሉበት ስፍራ ተቀጥቅጠው የተገደሉ ምእመናንን አስከሬናቸውን በጎዳና እንዳስጎተቱ፣ ቤተክርስቲያንን ከመቃጠል የተከላከሉ ምእመናንን እየለቀሙ እንዳሰሩ ሌላም ሌላም ግፍ በቤተክርስቲያን መፈጸሙ በታወቀበት ሁኔታ እንደገና ተመልሰው አገዛዙ ምንም ችግር የሌለበትና ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሆነ በሚያስመስል መልኩ ክብር ሰጥተው፣ ተቀባይነትን አረጋግጠውለት በየመድረኩ፣ በየስፍራው፣ በየሁነቱ እየተጓተቱ እየተገኙ የሚያደርጓቸው ነገሮች በቤተክርስቲያን ላይ እየቀለዱ መሆናቸውን፣ ምእመናንን ለማታለል ለይምሰል ተቆርቋሪ መስለው እየተወኑ ውስጣቸው ግን የአገዛዙ አገልጋዮች መሆናቸውን፣ የአሸባሪዎች የግፍ ሰለባ በሆኑ ወገኖቻችን ደም መሳለቃቸውንና በሌላ አነጋገር ነውረኛ ምንደኞች መሆናቸውን ከማረጋገጡ ሌላ ምንም የሚያሳየው ቁምነገር ያለ አይመስለኝም!!!
ተመሳሳይ ተግባር የምንፈጽም ሌሎቻችንም ብንሆን እንደዚሁ ነን!!! ይሄ ተግባር የአቋምና የመርሕ ሰው ካለመሆን ይመነጫል፡፡ በተለይ ግን እውነትንና እውነትን ብቻ መላበስ የሚጠበቅባቸው ወይም የእውነት ሰዎች መሆን የሚጠበቅባቸው የሃይማኖት አባቶች ከሚባሉ ሰዎች ይሄንን ዓይነት ርካሽ ወይም ነውረኛ ምግባር ማየታችን የዘመኑ ፍጻሜ ምልክት መሆኑን ካልሆነ በስተቀር ሌላ ምን ሊያሳይ ይችላል ወገኖቸ???
እስኪ አንድ ጥያቄ ልጠይቃቹህ? ለምን ይመስላቹሃል ይሄ የወያኔ ኩሊ ዐቢይ መጀመሪያ ላይ አጭበርብሮ አግኝቶት የነበረውን የሕዝብ ድጋፍ ለጽንፈኛ የጥፋት ኃይል ወገኖቹና ለኦሮሞ ኢፍትሐዊ ተጠቃሚነት ሲል በየጊዜው በሚፈጽማቸው በደሎችና የተጋነኑ አድሏዊ አሠራሮች ምክንያት በየዕለቱ እያጣ መሔዱና አሁን ላይ ባዶ መሆኑ የማያሳስበው ለምን ይመስላቹሃን??? መልሱን ለእናንተው ልተወውና እኔ ወደ ጉዳዩ ልመለስ፡፡
ሰሞኑን አሸባሪው ጃዋር በዋናነት በዘር አማራ የሆኑትን ወገኖቻችንን፣ በሃይማኖት ደግሞ ኦሮሞዎችን ጨምሮ ክርስቲያን የሆኑ ወገኖቻችንን በአሸባሪ ጀሌዎቹ ባስጨፈጨፈበት ቀን ይሄንን ብያቹህ ነበረ፦
“የዚህ የጃዋርና የአገዛዙ ድራማ ሌላው ዓላማ አገዛዙ ጃዋርን ማሰር ስለማይፈልግ ዛሬ የሆነውን ሁሉ እንዲሆን በማድረግ የኢትዮጵያ ሕዝብ ‘ጃዋር ቢነካ እንደዚህ ዓይነት የከፋ ቀውስ ይቀሰቀሳልና የማያስሩት ለዚህ ነው፡፡ ለእኛም አደጋ አለው!’ ብሎ እንዲያስብ በማድረግ ሕዝቡ ‘ጃዋር በሕግ ይጠየቅ!’ እያለ የሚያሳድረውን ጫና እንዲያቆም ለማድረግ ተከሽና የተተወነች ድራማ ናት!!!” ብየ ነበረ፡፡
ያልኩትም አልቀረ ይሄው እነ ዐቢይ ወይም አገዛዙ በተለያዩ አካላት አሸባሪውን ጃዋርን ለምን ሕግ ፊት እንደማያቀርቡት ሲጠየቁ “ሀገርን ለከፋ ችግር ላለመዳረግ ሲባል ነው!” የሚል መልስ እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ወይኔ! እናንተየ ሳላውቀው ማምለጫ የሚሆናቸውን መልስ አቀብያቸው ይሆን እንዴ??? ግድ የለም ማርከሻ መድኃኒቱ ይሄው እንካቹህ፦
እነ ዐቢይ ይሄንን የሚሉት ውሸታቸውን ነው!!! አሸባሪውን ጃዋር የማያስሩበት ምክንያት ዐቢይና ለማ ሰሞኑን ሐረር ላይ የጃዋር ደጋፊ ወገኖቻቸውን ሰብስበው በኦሮምኛ እንደተናገሩት ጃዋር ማለት አብረውት የሚሠሩት ተለዋጭ መንግሥታቸው ስለሆነ፣ የጸጥታ አካላቸው በመግለጫው እንዳለው የዓይን ብሌናቸው ስለሆነ ወዘተረፈ. ነው!!!
የእኛ ችግራችን በቀኝ ጆሯችን ሰምተን በግራ ጆሯችን እያፈሰስን ሁልጊዜ አዲስ ስለምንሆን ነው እንጅ እነሱ ዛሬ ብቻ ሳይሆን ከመጀመሪያውም ጀምሮ በኦሮምኛ በሚያወሩበት መድረክ ሁሉ እውነቱን ሳይደብቁ ነግረውናል፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላ “መቀለጃ አሻንጉሊታቸው ልሁን!” የሚል ካለ ይሄንን ሰው ምን ማለት ይቻላል???
“ይሄንን የአገዛዙን ምክንያት ሐሰተኝነት እንዴት እናረጋግጣለን?” ከተባለ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የተቀሰቀሱትንና እራሱ አገዛዙ “ተሞከረ!” ብሎ በሐሰት በመወንጀል ሁኔታውን ለመቆጣጠር የወሰዳቸውን እርምጃዎችና ሁኔታዎችን ለመቆጣጠር የሔደበትን እርቀት መመልከት የግድ ይላል፡፡
እንደምታስታውሱት ወያኔ የሶማሌ ክልል በሚለው የሀገራችን ክፍል አብዲ ኢሌና እስከ አፍንጫው የታጠቀ በርካታ ቁጥር ያለው ልዩ ኃይሉ በተጨማሪም የነውጠኛ ወጣት አደረጃጀቱ በሀገሪቱ ህልውና ላይ ከፍተኛ ሥጋት ጋርጠው እንደነበረ ይታወቃልና እዚህ ላይ አልደግመውም፡፡ አገዛዙ ለዚህ የአብዲ ኢሌ የጥፋት ኃይል ምቹ ሁኔታን በመፍጠር በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናንና ካህናት ላይ እንዲሁም በአብያተክርስቲያናት ላይ እንዲያደርስለት የፈለገውን ጥፋት፣ ውድመትና አረመኔያዊ ጥቃት ካደረሰለት በኋላ እንዴት አድርጎ ይሄንን ግዙፍ ሥጋት የጋረጠውን የአብዲ ኢሌ የጥፋት ኃይል በቀላሉ እንደተቆጣጠረው የምታውቁት ነው፡፡ ጃዋር ከአብዲ ኢሌ ልዩ ኃይልና የነውጠኛ ወጣቶቹ አደረጃጀት የላቀ ኃይል ስለሆነ ነው ወይ አሁን ታዲያ አገዛዙ “ጃዋርን ሕግ ፊት ማቅረብ የማልችለው የከፋ አደጋ ስለሚፈጠር ነው!” እያለ የሚያወናብደው??? ቄሮና ጃዋር ከአብዲ ኢሌና ወጣቶቹ የሚያይል ስለሆነ ነው ወይ??? እንዳልሆነ ለማንም ግልጽ ነው!!!
ስንቀጥል አገዛዙ “ጃዋርን ሕግ ፊት የማላቀርበው የከፋ አደጋ ስለሚፈጠር ነው!” የሚለው ነገር በትክክል ያሳሰበው ሥጋት ከሆነ ሰኔ 15 ባሕርዳር ላይ በፈጠራ ክስ በጄኔራል አሳምነው ጽጌና በልዩ ኃይል አባላቱ እንዲሁም በፋኖና በአማራ ብሔርተኛ ወጣቶች ላይ ባጠቃላይ ብሶት ብቻ ሳይሆን አረመኔያዊ ግፍ በወለደው በአማራ ብሔርተኝነት ትግል ላይ “እስከ ታች ድረስ ወርደን እንመነጥረዋለን!” የሚል መፈክር በማሰማት በዘመቻ ያንን የመሰለ ግፍና ጥቃት ሲፈጽሙ አብን የተባለ ቅጥረኛ ድረጅታቸው በሰፊው ተሰማርቶ ሕዝቡን “ታገሱ ተረጋጉ፣ ከመንግሥት ጋር ተባበሩ፣ አሳልፋቹህ ስጡ አታስጠጉ….!” እያለ ሕዝቡ በስንት መከራ ያነቃቃውን የብሔርተኝነት ትግሉን ለመታደግ ሊወስደው ይችለው የነበረውን ኃይለኛ የአጸፋ እርምጃ አኮላሸው እንጅ ያኔ አገዛዙን በሚወስደው የግፍ እርምጃ ከአማራ ሕዝብ ሊቃጣ የሚችለው የአጸፋ ወይም እራስን የመከላከል ሕጋዊና ተፈጥሯዊ እርምጃ ይሄ “ሀገርን ለከፋ አደጋ ሊዳርግ ስለሚችል!” የሚለው ሥጋቱ እንዴት ሳያሳስበው ሊቀር ቻለ??? በቅጥረኛ ድርጅታቸው አብን ስለተማመኑ ነበር እንዴ??? ነው ወይስ ጃዋርና ቄሮ ከእነ ጄኔራል አሳምነውና ፋኖ የአማራ ወጣቶች የላቀ ኃይል ስላለው ነው??? በፍጹም እንዳልሆነ ለማንም ግልጽ ነው!!!
ቄሮን የልብ ልብ እየሰጠው ያለው ጉዳይም ይሄው የሌለውን አቅምና ጉልበት እንዳለው ተደርጎ መታየቱና አረመኔያዊ የሽብር ጥቃቶችን ሲፈጽምም የአገዛዙ የጸጥታ ኃይል በዝምታ የሚመለከተው መሆኑ፡፡ ከዚህም አልፎ ከጸጥታ ኃይሉ ድጋፍ ስለሚደረግለት ነው፡፡ አገዛዙም የጸጥታ ኃይሉ ቄሮን በዚህ መልኩ የልብ ልብ እንዲሰማው እንዲያደርግ የሚያደርግበት ምክንያት የቄሮ ጫናና ግፊት ኦሕዴድ/ኦነግ የፖለቲካ ጥቅማችን የሚሉትን ለማስፈጸም ይጠቅመናል ብለው ስለሚያስቡ ነው፡፡
ይሁንና ግን በተለይ ደግሞ አሁን አሁን የሚለፉትን፣ የሚደክሙትን፣ የሚጥሩትን ያህል የኦሮሞ ሕዝብ በቄሮ እንቅስቃሴ እየታቀፈና እየተንቀሳቀሰላቸው አይደለም፡፡ እንደምታዩት ከ35 ሚሊዮኑ የኦሮሞ ሕዝብ አንድ ዐሥረኛ እንኳን አይሆንም እየተሳተፈላቸው ያለው፡፡ ጥቂቶችን ነው በጭነት መኪና በየስፍራው እያጓጓዙ ጥቃት እንዲፈጽሙና የፈለጉትን እንዲያደርጉላቸው ማድረግ የቻሉት!!!
እንዲህ እንዲህ እያልን የሲዳማን ነውጥና እዚያም የተወሰደውን እርምጃ እየጠቀስን ይሄ የአገዛዙ “የከፋ ችግር እንዳይከሰት ነው!” የሚለው ምክንያት እነሱ እራሳቸው በቃላቸው እንዳረጋገጡት ጃዋር የትግል አጋራቸው ስለሆነ እንጅ እያሉት ያለው ነገር ፍጹም ሐሰት መሆኑን ማረጋገጥ ይቻላል!!! አገዛዙ ለሁሉም እያሳየው ያለው ወጥ የሆነ አቋም ያለመሆኑ ችግር (double standard) በጃዋርና የኦሮሞ ጽንፈኞች ላይ የሚያሳየው ልኩን ያለፈ ትዕግሥት ወይም አድልኦ ምክንያቱ ይሄ ነው ሌላ አይደለም!!!
“የኃይል እርምጃ የኖርንበትና መፍትሔ ሊሆን ስለማይችል ነው በትዕግሥት በፍቅር ነገሮች እንዲለወጡ ለማድረግ እየጣርን ያለነው!” ምንንትስ ቅብርጥስ የሚሉትም ነገር ሐሰተኛ ምክንያት መሆኑን የሚያረጋግጠውም ይሄ ከላይ የገለጽኩት የሴማሌው፣ የአማራውና የሲዳማው የኃይል እርምጃ ነው!!!
የእኔ ጥያቄዎች፦
1ኛ. አገዛዙ እንዲህ የማይሆንና የማይመስል ምክንያት እየሰጠ አሸባሪውን ጃዋርንና መንጋውን የመሳሰሉ የመጨረሻ አደገኛ ወንጀለኞችን ያለተጠያቂነት በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ ለቆ ከዚህ በኋላ እንዴት ብሎ ነው “ሕግና ሥርዓትን አስከብራለሁ!” ብሎ አይደለም እነ አቶ ጌታቸው አሰፋንና ሌሎች የወያኔ ባለሥልጣናትን ይቅርና ተራ የወንጀልና የፍትሐብሔር መተላለፎችን የፈጸሙ ዜጎችን እንኳ “ሕግ ፊት አቀርባለሁ!” ብሎ ሊንቀሳቀስ የሚችለው??? ይሄንን የማለት የሞራል ብቃት ይኖረዋል ወይ???
2ኛ. አገዛዙ በዚህ በሚጠቅሰው ሐሰተኛ ምክንያት እነ ጃዋርን ከሕግ በላይ ሲያደርጋቸው ወይም ተጠያቂ ሳያደርገቸው ሲቀር ወይም አሸባሪውን ጃዋርንና መንጋውን “እንደፈለጋቹህ መሆን፣ በፈለጋቹህት አካል ላይ የፈለጋቹህትን ዓይነት እርምጃ መውሰድ ትችላላቹህ ማንም አይጠይቃቹህም!” የሚል ዋስትና እየሰጣቸው እንደሆነ ይገባዋል ወይ???
3ኛ. አገዛዙ አሸባሪውን ጃዋርን በሚጠቅሰው ሐሰተኛ ምክንያት ተጠያቂ እንዳይሆን ሲያደርግ በሀገሪቱ ላሉ የተለያዩ ብሔረሰቦችና እምነቶች “ከሕግ በላይ ሆናቹህ እንደፈለጋቹህ መንቀሳቀስ ከፈለጋቹህ እንደ ጃዋርና መንጋው ሁኑ!” የሚል አደገኛ መልእክት እያስተላለፈ መሆኑን ይገባዋል ወይ???
4ኛ. በዚህም ምክንያት በሀገሪቱ ያሉ ብሔረሰቦችና እምነቶች የየራሳቸውን ጃዋሮች ለመፍጠር እንደሚገደዱና ለዚህም በርትተው እንዲሠሩ እያደረጋቸው እንደሆነ ይገባዋል ወይ??? በመሆኑም አገዛዙ በዚህ አቋሙ ሀገሪቱን ወደ ከፋ ሁኔታ እየገፋት እንጅ እየታደጋት ነው ወይ??? ማን ከሕግ በላይ በሆኑ የአሸባሪዎች መንጋ እየተጠቃና እያለቀ እጁን አጣጥፎ ይቀመጣል ይመስለዋል??? አገዛዙ እነኝህን ጥያቄዎች መመለስ ይችላል ብላቹህ ታስባላቹህ???
እዚህ ላይ በጃዋር ደጋፊዎች አንድ በተደጋጋሚ ሲጠቀስ የምሰማው ቃል አለ፡፡ “‘ጃዋር ተከበብኩ፣ ጥቃት ሊሰነዘርብኝ ነው!’ አለ እንጅ እንዲህ አድርጉ ብሎ ትእዛዝ ስላላስተላለፈ ተጠያቂ አይደለም!” የሚል፡፡
እነኝህ አካላት አገዛዙ እራሱ ጃዋር የሽብር ጥቃቶችን እየፈጸመ ሀገሪቱን እንዲያብጥ በግብጽ እንደተቀጠረ መረጃ አለኝ ማለቱን የሚያውቁ አልመሰለኝም፣ ጃዋር እስላማዊ ኦሮሚያን በኃይል ለመመሥረት እንደሚንቀሳቀስ በአደባባይ መናገሩን አያውቁም መሰለኝ፣ የሜንጫ መፈክርን እያሰማ ጥሪ ማቅረቡን አያውቁም መሰለኝ???
ይሄ ይሄም ይቅርና አሁን ከሰሞኑ እንኳ “ተከበብኩ ጥቃት ሊደርስብኝ ነው!” ያለው ነገር እውነት ቢሆን እንኳ እስከላይ ድረስ “አለኝ!” በሚለው ግንኙነት በተደጋጋሚ “መንግሥቴ ነው!” እያለ መንግሥትነቱን ላረጋገጠለት አገዛዙ መደወልና ማመልከት ወይም ክሱን ማቅረብ ሲኖርበት “ቄሮ ሆይ ፈጥነህ ድረስልኝ፣ ማድረግ የምትችለውን ሁሉ አድርገህ ከጥቃት ወይም በቁጥጥር ስር ከመዋል አድነኝ!” የሚል እንድምታ የያዘ መልእክት ማስተላለፍ ነበረበት ወይ??? ባቀረበው ጥሪ በተፈጸመው ሁሉ ተጠያቂና ወንጀለኛ ያደርገዋልና!!!
ሲቀጥል ደግሞ ባቀረበው ጥሪ ያ ሁሉ ጥፋት ከደረሰ በኋላ ቢጤዎቹን ኦነጋውያን እቤቱ ሰብስቦ በቴሌቪዥን ጣቢያው የቀጥታ ስርጭት በሰጠው መግለጫው ላይ ቄሮ የፈጸመውን ጥቃት እያሰበ “ኦሮሞን መንካት እንዲህ ዋጋ ያስከፍላል!” በማለት የተፈጸመውን የወንጀል ጥቃት ሁሉ በአጸፋ እርምጃነት የተወሰደ መሆኑን በማረጋገጥ በራሱ አንደበት ኃላፊነትን የወሰደ በመሆኑ ቄሮ የተባለው አሸባሪ መንጋው ለፈጸመው አረመኔያዊ የአሸባሪ ጥቃቱ ሁሉ ተጠያቂ ነው!!! ስለሆነም ጃዋር “እንዲህ አድርጉ ብሎ አላዘዘም!” የሚለው የየዋሃን አነጋገር አያስኬድም ወይም ጃዋርን ከተጠያቂነት ሊያመልጥ አይችልም!!!
ሌላው ጃዋር ከተጠያቂነት እንዲያመልጥ የሚፈልጉ ደጋፊዎቹ የሚያነሡን ጉዳይ ጃዋር “ወደ አሜሪካ ሔዷል!” የሚለው ወሬ መነዛቱን ተከትሎ እነኝሁ አሸባሪ ደጋፊዎቹ አሜሪካ በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር (Money laundering) የተከሰሰ ካልሆነ በስተቀር ዜግነቷን የወሰደ ሰው በትውልድ ሀገሩ ወይም በሌላ ሀገር ቢከሰስ አሳልፋ የመስጠት አሠራር እንደሌላት በመግለጥ በጃዋር እንዳይከሰስ ከወዲሁ የመከላከል ጥረት ማድረጋቸው ነው!!!
ነገር ግን ይሄ የአሜሪካ አሠራር ብለው የሚገልጹት ነገር ሐሰት መሆኑን ማረጋገጥ ካስፈለገ አሜሪካ ዜግነቷን የያዙ የቀይ ሽብር ተዋንያን የደርግ ባለሥልጣናትን የወንጀሉ ፈጻሚዎች መሆናቸው በታወቀ ጊዜ የሰጠቻቸውን ዜግነት እየገፈፈች እያነቀች በተደጋጋሚ ለወያኔ አስልፋ መስጠቷ በሚገባ ይታወቃልና፡፡ በተመሳሳይም እንዲሁ ዜግነቷን በወሰዱ የሌሎች ሀገራት ዜጎችም ይሄንኑ እርምጃ ለበርካታ ጊዜ መውሰዷ ይታወቃልና ይሄ አሸባሪዎቹ የጃዋር ደጋፊዎች ያሉት ነገር ሐሰት ነው!!!
ከዚሁ ጋር በተያያዘ እነዚሁ ኦነጋውያን አሸባሪ የጃዋር ደጋፊዎች ከሰሞኑ ጭፍጨፋቸው አስቀድመው “ጃዋር አሜሪካዊ ስለሆነ መንግሥት ግፋ ቢል ሊያደርግ የሚችለው ከሀገር እንዲወጣ ማድረግ ነው እንጅ ሊያስረው አይችልም!” የሚል ወሬ በመንዛት ሕዝቡ ጃዋር ለፍርድ እንዲቀርብ የሚያደርገውን ጥረት ተስፋ ቆርጦ እንዲተው ለማድረግ ሲጥሩ ነበር፡፡
እንዲህ የሚሉትን ሰዎች የተለያዩ  የውጭ ሀገራት ዜጎች ቃሊቲ እስርቤት በተለያየ ወንጀል ታስረው የሚገኙ መሆናቸውን ስለማያውቁ አይደለም፡፡ ወንጀል ሠርቶ እስከተገኘ ጊዜ ድረስ ማንኛውም ዜጋ በየትኛውም ሀገር ቢሆን ተይዞ ይታሰራል!!! ወንጀል ሠርቶ ቢገኝ ያ የውጭ ዜጋ ሊታሰር የማይችለው ሰውየው ያለመከሰስ መብት ያለው የውጭ ሀገራት ዲፕሎማት ከሆነ ብቻ ነው፡፡ እሱም ቢሆን “ፈጽሞ አይከሰስም አይጠየቅም እንደፈለገ ወንጀል መሥራት ይቻላል!” ማለት ሳይሆን ተይዞ ለሀገሩ ይሰጥና ቅጣቱን በሀገሩ ይወስዳል ማለት ነው እንጅ “ከሕግ በላይ የሆነ ሰው አለ!” ማለትም አይደለም፡፡ ሌላው ዲፕሎማት ያልሆነው የውጭ ዜጋ ግን እንደሚታሰር ቃሊቲ ወርዳቹህ ብታዩ ተቀፍድዶ ተቀፍድዶ ታገኙታላቹህ!!! እንኳንና እንደጃዋር ያለው የውጭ ሀገር ተወላጅ ያልሆነው ተራ ውሪ ይቅርና!!!
እናም በምንም በሉት በምን ጃዋር ከተጠያቂነት ማምለጥ የሚችልበት ምንም ቀዳዳ የለውም!!! ችግሩ “አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ!” ሆኖ ነው እንጅ ነገሩ፡፡ አሸባሪው ጃዋርና አጋሩ የሆኑ የአገዛዙ ባለሥልጣናት ለፍርድ ይቅረቡ!!! ይሄ እንዲሆን ሁላችንም የአቋምና የመርሕ ሰው በመሆን በርትተን እንታገል!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
Filed in: Amharic