>

የአህያ ሥጋ አልጋ ላይ ሲሉት ዐመድ ላይ (ግርማ በላይ)

የአህያ ሥጋ አልጋ ላይ ሲሉት ዐመድ ላይ

 

ግርማ በላይ

 

ስሜትን በአጭሩ ለመግለጽ ሥነ ቃሎች ግሩም አቋራጭ ናቸው፡፡ የተሻለ አማራጭ ቀርቦላቸው መናኛውንና አሰዳቢውን ለሚመርጡ ሰዎች ከሚሰነዘሩ ወርቃማ አባባሎች አንዱ “የአህያ ሥጋ አልጋ ላይ ሲሉት አፈር/ዐመድ ላይ ይላል” የሚለው ነው፡፡ አህያ ከተነሳች አይቀር “ለአህያ ማር አይጥማትም” የሚለውም ለተነሣሁበት የሃሳብ ዐውድ ይስማማል፡፡ እዚህ ላይ ብሂሎች የሚጠቀሱበት ግለሰብና የብሂሎቹ ገጸ ባሕርያት (ለአብነት አህያ ወይ ጅብ) ባሕርያዊ ግንኙነት እንደሌላቸው መረዳት ይገባል፡፡ ነገርን መጠምዘዝ የሚቀናቸው ሰዎች ግና ከፍካሬያዊ ትርጉሞች ይልቅ በእማሬያዊ ፍቺዎች ላይ እያተኮሩ ያልተፈለገ ብያኔ ሲሰጡና “አሃ! እንዲህ ለማለት እኮ ነው!” እያሉ ነገርን ሲያወሳስቡ ይታያል፡፡ ይህ ደግ አይደለም፡፡ “አንድ ዐይና በአፈር አይጫወትም” ቢባል ለምሣሌ የቁጠባን አስፈላጊነት ለመጠቆም እንጂ ብሂሉ ከአንድም ሆነ ከሁለት ዐይኖች ጋር ባሕርያዊም ሆነ ቤተ-ዘመዳዊ ግንኙነት የለውም፡፡ ሰው ሰው ነው፤ ሌላው እንስሳም ሌላ እንስሳ፡፡ ውሻ ብትለኝ ለአብነት ውሻ ስላልሆንኩ ስለውሻነቴ ልበሳጭ አይገባኝም፡፡ ይልቁናም ለምን ውሻ እንዳልከኝ ከውሻ ባሕርያት የምታማበትን አንዱን ወይ ሌላውን መዝዤ ራሴን ለማስተካከል መጣር ነው የኔ ኃላፊነት መሆን ያለበት፡፡ ዝም ብሎ መጮኹ ግን ከንቱ ነው፡፡

ተመልከት – ዶ/ር አቢይ አህመድ ልዩ ተልእኮና ዓላማ እስከሌለው ድረስ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በፍቅሩ ወድቆ እንዲያ እየወደደውና እየሞተለት ወንዝ ቀርቶ ኩሬ የማያሻግርና ዘለቄታም የሌለው የዘር ኩይሣ ውስጥ ገብቶ መርመጥመጡ ምን ትርጉም ሊያሰጠው እንደሚችል እንደገና ብፈጠርም አይገባኝም፡፡ ያሣለፍናቸውን የሁለት ዓመታት ክስተቶች ሲያስቧቸው በቁጭትም በንዴትም በሁሉም ረገድ ያሣምማሉ፡፡ መስቀል አደባባይ ላይ ስለአቢይ የሞቱ ዜጎች ነፍሳት ምን ይታዘቡ? ያቺ ቆስላ ሆስፒታል የገባች ወጣት የዩኒቨርስቲ ምሩቅ ሰዎች ሊጠይቋት ሲሄዱ “እኛን ተውን፤ እርሱን ብቻ ጠብቁት፤ እንዳይጎዳብን ከጠላቶቻችን ታደጉት!” ብላ የተናገረችው ልጅ ፈጣሪ የሆነው እግዚአብሔር ራሱ አቢይን እንዴት ይታዘበው? የዚህ ዘመን ሰዎች በውነቱ ከምን ዓይነት ጭቃ ነው የተሠራነው? መማርስ ለመቼ ነው የሚጠቅመው? የምንደቁነው፣ የምንቀሰው፣ የምንዶከትረው በጎውን አስተሳሰብና አሠራር ከክፉው ለይተን ለመያዝና ለትውልድም ለማስተላለፍ አይደለም እንዴ?

የ87 ቤረቤረሰብ አለቃ ሆኖ የሁሉም አዛዥ ናዛዥ መሆን ይቀላል ወይንስ የአንዱ አቦካቶ(ጠበቃ) ሆኖ ከሰማንያ ሰባቱ ጎሣና ነገድ እንዲሁም ከገዛ ኅሊና ጭምር የማያባራ ጦርነት መግጠም ይሻላል? የ87 ነገዶች መሪ ሆኖስ ለአንደኛው ብቻ ማዳላትና ከዚያ ነገድ የወጣን ሽፍታ እሽሩሩ ማለት – “ወንድ ጠፍቶ” – በምድራዊ ወንጀል ባያስጠይቅ በሰማይ ቤት ሥርየት በሌለው ኃጢኣትነቱ ማስጠየቁ ይቀራል? የሰዎች ምርጫ ግን እጅግ ይገርመኛል፡፡ ደግሞም የሰዎች መመሳሰል፡፡ ያኛው በከልቻ መቀሌ እስቴዲየም ውስጥ ሌሎች አይሰሙም ብሎ በትግርኛ “እንኳዕ ካባኹም ተፈጢርና! ካብ ወርቂ ሕዝቢ ብምፍጣርና ተሓጓስቲ ኢና…..” ሲል ተበጠረቀ – ፍጹም ስህተት፡፡ አሁን ደግሞ “ከመምህሩ ደቀ መዝሙሩ” እንዲሉ ሆነና በኦሮምኛ እየሰማነው ያለነውን ሁሉ ጉድ ለመስማት ተገደድነ፡፡ ወይ ዕድላችን! ከእሳት ወደ ረመጥ፡፡ ለማንቻውም ሃለቃ አቢይ ሆይ ካልመሸ ምርጫህን አስተካክልና አሟሟትህን ጨምሮ ታሪክህን በጥቁር ቀለም ከመጻፍ ታቀብ፡፡ ከዚያም ቢያንስ ልጆችህ አንገታቸውን ቀና አድርገው በኩራት የሚኖሩባትን አንዲት ሀገር ገንብተህ ከመቃብርህ በላይ ትኖራለህ፡፡

ጽሑፌን የምቋጨው በሰዎች ምርጫ ሁልጊዜ የምገረም መሆኔን በድጋሚ በማስታወስ ነው፡፡ ከምግብና ከመጠጥ ባያልፍም በኔ ምርጫ ጓደኞቼ ምን ይሉኝ ይሆን ግን? ሰው እኮ በፊትህ አይነግርህም ታ’ቃለህ? ስትለይ ነው ቡጭቅ የሚያደርግህ፡፡ ይህን የሃሜትና የምቀኝነት ባህላችንን ለማጥፋት ታላቅ ዘመቻ ካላካሄድን ግዴላችሁም አሁን ከምንገኝበትም በታች ወርደን ስንንቦራጨቅ ዓለም ማለፏ ነው፡፡ ምቀኝነት እኮ እግር አውጥቶ እንደልቡ ባደባባይ የሚሄደው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ሱባሃን! ኧረ አላህ ታረቀን! ኧረ እግዜር ሆይ ማን አገተህና ይህን ያህል በዚህች አገር ጨከንክ?!

Filed in: Amharic