>
5:13 pm - Friday April 19, 8030

ኢትዮጵያዊው ሳይንቲስት!!! (ግዮን መጽሄት)

ኢትዮጵያዊው ሳይንቲስት!!!
ግዮን መጽሄት
* የአሜሪካን ፕሬዝዳንት ደሞዝ የሚያስከነዳው ብቸኛው ከፍተኛ ተከፋይ የህክምና ተመራማሪ   ዶ/ር ኤሌክትሮ ክበበው …..
በዓለም አቀፍ ደረጃ ካንሠርን በተመለከተ በሚካሄዱ ምርምሮች ላይ ከተሰማሩ እውቅ
ተመራማሪዎች መሐል አንዱ ትውልደ ኢትዮጵያዊው ዶክተር ኤሌክትሮ ክበበው ይባላል፡፡
•~•
ከወር በፊት ከዓለማችን እውቅ ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ማዕከላት በአንዱ ስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ በአጠቃላይ የቀዶ ሕክምና የትምህርት ክፍል ዋና ኃላፊ ሆኖ እንዲሠራ መመረጡ በመላው አሜሪካ አነጋጋሪ ዜና ሆኖ ነበር የሰነበተው….፡፡
•••
ከጎጃም ማህጸን ከፈለቁ ሙህር ቤተሰቦቹ የተወለደው ትውልደ ኢትዮጵያዊው ዶክተር ኤሌክትሮ ክበበው ላለፉት ሰባት ዓመታት በሀገረ አሜሪካ ከፕሬዝዳንቱ ቀጥሎ ሁለተኛው ከፍተኛው ደመወዝ ተከፋይ በመሆን በሙያቸው እጅግ ከተሳካላቸው አሜሪካውያን ተርታ ለመሰለፍ በቅቷል፡፡
•~•
የ41 ዓመቱ ዕውቅ ተመራማሪ ዶክተር ኤሌክትሮ ክበበው የተጣበበ ጊዜው ሳይገድበው
በሚገኝባቸው የትውውቅ መድረኮች ሁሉ ለኢትዮጵያውያን ወገኖቹ በርትተው በመማር
በፅናት የሚያጋጥማቸውን ፈተና እና መሰናክል በማለፍ ስኬታማ ሆነው ወገናቸውና የተቀረው
ዓለም የተሻለ ሕይወት እንዲኖር እንዲጣጣሩ ጥሪውን ከማስተላለፍ ተቆጥቦ አያውቅም፡፡
•~•
ከአባቱ ከኢንጅነር ክበበውና ከእናቱ ዶክተር ሙሉጎጃም በላይ  አዲስ አበባ ውስጥ ተወልዶ እስከ ዐሥር ዓመቱ ድርስ ከእኩዮቹ ጋር የማይረሳ የልጅነት ጊዜ እንዳሳለፈ ይናገራል፡፡ ብዙዎችን ባስገረመ መልኩ የኤሌክትሪካል ምሁር የሆኑት አባቱ ኢንጂነር በ በክው በድህነት፤ በኋላቀርነትና በፖለቲካ ቀውስ የምትታመሰውን ሀገራቸው በእያንዳንዱ የገጠር መንደር የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ እንዲሆን የሰነቁትን ምኞት በልጆቻቸው ላይ ለማስረፅ በማሰብ ስማቸውን ኤሌክትሮን፣ ንስትሮን እና ኢዮትሮን ክበበው የሚል ስም ነበር ያወጡላቸው፡፡
•~•
ይሁንና አባት ልጆቻቸው በተመኙት መልኩ እንዲሰማሩ ቢያስቡም ሕይወት ግን ሌላ መንገድ
ነበር የቀየሰችው፡፡ የ1966ቱን አብዮት ተከትሎ በሀገሪቱ በተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ ሳቢያ
ኢንጅነር ክበበው ቤተሰቦቻቸውን ይዘው ወደ አሜሪካ ሄዱ፡፡ ይሔን ጊዜ ነበር የዐሥር ዓመቱ
ታዳጊ ኤሌክትሮን ከማያውቀው ማኅበረሰብ ጋር የመኖር ዕጣ ፈንታ የገጠመው፡፡
በሎሳንጀለስ ካሊፎርኒያ መኖር የጀመሩት እነ ኤሌክትሮን በምድረ አሜሪካ ገና ከቀለምና ከዘር ልዩነት አስተሳሰብ ያልፀዳ ማኅበረሰብ የነበረ ቢሆንም፤ በእናታቸው ፅናትና ጠንካራ አስተዳደግ ታግዘው የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በዚያው በማጠናቀቅ ውጤታማ ልጆች ለመሆን
በቅተዋል፡፡
•~•
ዶክተር ኤሌክትሮ አባቱ ያወጡለት ስም በወቅቱ ባልተዋሐደው የአሜሪካ ማኅበረሰብ ውስጥ እንዴት እንደተቀበሉት ተጠይቆ ሲናገር “ሰዎች እንደኔ ዓይነት ከሳይንስ ጋር የተያያዘ ስም ሲኖራቸው በሌሎች ዘንድ ለየት ያለ ትኩረት ይሰጣቸዋል፡፡
ብዙዎች ባግራሞት ተሞልተው ስሜ ትክክል መሆኑን ይጠይቁኝ ነበር፡፡ ዛሬ ለደረስኩበት ስኬት ስሜ በራሱ ተፅዕኖ ያለው ይመስለኛል ” ብሏል፡፡
•~•
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ በሎሳንጀለስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በኬሚካል ኢንጂነሪንግ የትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪውን ቢያገኝም ወደ ሥራ አልተሰማራም፡፡
•~•
የመጀመሪያ ዲግሪውን የተቀበለበትን ኬሚካል ኢንጅነሪንግን ትቶ የሕክምናውን ዓለም ለምን
እንደተቀላቀለ ሲጠየቅ “የኬሚካል ኢንጂነሪንግ ዘርፍን ትቼ ወደ ሕክምናው ዘርፍ ማተኮር የፈለኩት ተመርምሮ በማያልቅ በእግዚአብሔር እጅ ሥራ የታነፀው የሰው ልጅ ተፈጥሮ ሁልጊዜ
ስለሚያስገርመኝ ነው” በማለት መልሷል፡፡
ፊቱን ወደ ሕክምና የትምህርት ዘርፍ በማዞር በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሎስአንጀለስ የቀዶ ጥገና ትምሕርት ክፍል በመግባት የሁለተኛ ዲግሪውን አገኘ፡፡ በድጋሚ በዩኒቨርሲቲው አናኮሎጂ ዲፓርትመንት ውስጥ ሦስተኛ ዲግሪውን በማግኘት በዩኒቨርሲቲው ስመጥር ምሁራን ተርታ ያሰለፈውን እውቅና የተጎናፀፈበትን ውጤት አስመዘገበ፡፡
•~•
 የዶክትሬት ዲግሪውን እንደያዘ ከባለቤቱ ቫዮላንታ ጋር ትዳር በመመሥረት ሕይወቱን ሙሉ አድርጎታል፡፡ “ዛሬ ለደረስኩበት ስኬት የባለቤቴ አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው፤ ላለሁበት ከፍታ የእናቴና የእርሷ ድጋፍ እንዲሁም እገዛ ባይኖር የዛሬው እኔነቴ ሌላ ነበር ይላል” ዶክተር ኤሌከትሮ ክበበው፡፡
•~•
በሎሳንጀለስ ዩኒቨርሲቲ ኦንኮሎጂ ዲፓርትመንት ካንሠርን በተመለከተ በሚደረግ የጥናትና ምርምር ሥራ ውጤታማ ግኝት ላይ በመድረሱ ዝናው ከፍ እያለ ሄዷል፡፡ በዓለም አደገኛና ገዳይ ከሚባሉ በሽታዎች ውስጥ ዋነኛው በሆነው ካንሠር ዙሪያ የዶክተር ኤሌክትሮ አስደናቂ ግኝቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ በዓለም ላይ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኙ ምርምሮች መሆናቸውን የተረዳው የናሽናል ካንሰር ኢንስቲቲዩት ቦርድ ወዲያው ነበር የቦርዱ ሰብሳቢ እንዲሆን የመረጠው፡፡
•~•
በካንሰር ህመም በሚሰቃዩ ህሙማን ላይ ለዓመታት በተካሄደ ጥናትና ምርምር በተለይም
ኬሞትራፒ ህክምና የሚከታተሉ ህሙማን የታይሮድ ዕጢያቸው አዮዲን እንዳይቀበል ስለሚያደርግ አብዛኛዎቹ ህክምናውን የሚወስዱ ሕሙማን ለስኳር ሕመም ይጋለጣሉ፤ ይህ ደግሞ “ላይቶቶክሲል” የተባለውን የካንሰር መድኃኒት ዋጋቢስ ያደርገዋል፡፡ዶክተር ኤሌክትሮ ክበበው ይህን ችግር እስከ ወዲያኛው ሊቀርፍ የቻለ “ራዲዮ አዮዲን” የተሰኘ አዲስ ግኝት በመፍጠር ዓለምን ከጭንቀት አውጥቷል፡፡
•~•
ትውልደ ኢትዮጵያዊው ዶክተር ኤሌክትሮ ክበበው በቀዶ ጥገናው ሥራ ዘርፍ ከ2000 በላይ የተሳኩ የቀዶ ሕክምናዎችን ከማድረጉ በተጨማሪ ከ300 በላይ የጥናትና ምርምር ሥራዎቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂነት ባተረፉ ሜዲካል ጋዜጦች ላይ ታትመውለታል፡፡
በትዳሩ ደስተኛ እንደሆነ የሚናገረው ዶክተር ኤሌክትሮ ክበበው ከወይዘሮ ታይዳ ቫዮላንታ
“ራስ ኤሌክትሮ” እና “ኢዛና ኤሌክትሮ” የተባሉ ሁለት ወንድ ልጆችን አፍርቷል፡፡
ዕውቁ ተማራማሪ ስለ ልጆቹ እናት ሲናገር “ወይዘሮ ታይዳ ቫዮላንታ በዩኒሴፍ የኤች አይ ቪ ኤድስ ዲፓርትመንት ተቀጥራ በኢትዮጵያ ለዓመታት ሠርታለች፡፡ ይሄ ደግሞ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክና ባህል አጠቃላይ እውነታ ከእኔ በላይ የምታውቅ ስለሆነች ልጆቼ የኢትዮጵያን ታሪክ ፣ ባህል እንዲያውቁ የማድረጉን ኃላፊነት በመወጣት ረገድ ጉልህ ሚና ተጫውታለች”በማለት ነው፡፡
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2011 በሀገረ አሜሪካ ከአንድ ሺሕ ከፍተኛ ደመወዝ
ከሚከፈላቸው ዜጎች ዝርዝር ውስጥ ከቀድሞ ከፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ቀጥሎ ሁለተኛው
ከፍተኛ ደምወዝ የሚከፈለው ባለሙያ ትውልደ ኢትዮጵያዊው ተመራማሪ ዶክተር ኤሌክትሮን
ክበበው እንደሆነ ይፋ ሆኗል፡፡
“ከደመወዝ ክፍያ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ስሜ መጠቀሱ ብዙም አላስደሰተኝም፤ ከዚህ ይልቅ
በካንሰር እየተሰቃዩ ያሉ ሚሊዮኖችን ሕይወት ለመታደግ ከህክምናው ጋር ተያያዥ የሆኑ ችግሮችን ለማስወገድ የሚያስችል የምርምር ግኝት አግኝቼ ስሜ ቢጠቀስ እመርጣለሁ፤ ማን
ያውቃል ከሥራ ባልደረቦቼ ጋር እያደረኩ ያለው የምርምር ጥናት ለዚያ ውጤት ያበቃኝ ዘንድ
እመኛለሁ” ብሏል፡፡
~
በየዓመቱ በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ልጆቻቸው ኢትዮጵዊ ማንነታቸውን ብሎም ባሕልና ታሪካቸውን እንዲያውቁ አርአያ የሆኑ ባለሙያዎችን በሚጋብዙበት “Heritage and culture camp” ላይ በተደጋጋሚ ተጋባዥ በመሆን ልምድና ክህሎቱን ለተተኪዎች አካፍሏል….፡፡
 በተጋበዘበት ኢትዮጵያዊ መድረክ ላይም “ወገኖቼ በምንም ነገር ተስፋ አትቁረጡ፤ፅናትና ዓላማ ካላችሁ ያሰባችሁበት ትደርሳላችሁ፡፡ እናም ፈፅሞ ተስፋ አትቁረጡ ተማሩ ሁሌም ለመማር ዝግጁ ሁኑ” የሚለው ዕውቁ ዓለም አቀፍ ኢትዮጵያዊ ተመራማሪ የዶክተር ኤሌክትሮ ክበበው ምክር ማሳረጊያ ይሁነን…፡፡
Filed in: Amharic