>
1:20 am - Saturday December 10, 2022

ተባብረን በአንድነት ካልቆምን፤ ዛሬ ላይ የጎረቤታችን መከራ ነገ የእያንዳንዳችንን በር ያንኳኳል!!! (ውብሸት ታዬ)

ተባብረን በአንድነት ካልቆምን፤ ዛሬ ላይ የጎረቤታችን መከራ ነገ የእያንዳንዳችንን በር ያንኳኳል!!!
ውብሸት ታዬ
 
   የብዙዎች በር እየተንኳኳ ነው፡፡ መከራው በየቤቱ እየገባ ነው፡፡ ስንሰማው እሩቅ የሚመስለን በጣም ቅርብ ነው፡፡ እኛ ግን አሁንም መለያየትን እየሰበክን ወይም ሲሰበክልን አሜን ብለን እየተቀበልን ነው፡፡ ‹ተው!› ማለት አልቻልንም፤ አልፈለግንም፡፡ ሲሆን የከረመውንና እየሆነ ያለውን እያየነው ነው፡፡ በአገራችን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ፤ ለመግለጽ ቀርቶ ለመስማት የሚሰቀጥጥ ግፍ እየተፈጸመ ነው፡፡ የሆነው እና እየሆነ ያለው ታዲያ ከውጭ በመጣብን ወራሪ ሳይሆን
‹‹እርስ በርሱ፣
ስጋን በኩበት ጠበሱ!!!›
   እንደሚባለው እኛው በእኛው መሆኑ ያሳዝናል፣ ያስቆጫል እንዲሁም የመፍትሔ ውሉን ያጠፋዋል፡፡ ድርጊቱ ባለቤቶች አሉት፡፡ ሦስት ሃይሎች በተቀናጀ ሁኔታ የሚፈጽሙት የለየለት ሥርዓት አልበኝነት ሲሆን ባለቤቶቹ ድርጊታቸውን ከጀርባ ሆነው በማስተባበርና አደባባይ ወጥተው የጦር ፊታውራሪ የሆኑበት የጉድ ገመና ነው፡፡
   በአጭሩ ቅንጅቱ በውስጥ፤ በሕዝብ ሁለንተናዊ ትግል ጥቅማቸውን ካጡት በከባድ ወንጀል እስከሚፈለጉት ኃይሎች በአንድ በኩል፤ አጋጣሚውን ተጠቅመው ስልጣን የሚያማትሩት በሌላ በኩል ቴክኒካዊ አጋርነት የፈጠሩበት ሲሆን በውጭ ደግሞ አባይን ባማከለው አደገኛ ፖለቲካ ግብጽና ወዳጆቿ ይህን ‹ወርቃማ› ብለው የገመቱትን አጋጣሚ እንዳያመልጣቸው በእጃቸው የገባውን ጠጠር ሁሉ የሚወረውሩበት የዘመን መባቻ መሆኑን እያየን ነው፡፡
   ይህን ለማስፈጸም ጀርባቸውን ለግልቢያ ያመቻቹ የዕኛው ጉዶች ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ሞልተዋል፡፡ በመንግስት በኩል አደጋውን ለመከላከል ስላለው የመጨረሻ ዕድል ጥቂት እንኳ ለመገመት እንኳ አስቸጋሪ እንቆቅልሽ ሆኗል፡፡
   በእኛ በኩልስ… እንደ ሕዝብ፣ እንደ ዜጋ ምን እያደረግን ነው? እኛ የግድ በራችን እስኪንኳኳ እየጠበቅን ይመስላል፡፡ የጎረቤት ጥቃት የራሱ ዕዳ ብለነዋል፡፡ ጎረቤት ሲጮህ መድረስ አልፈለግንም፣ የዚያ ቤት ዕሳት የዚያው ቤት ጦስ ተደርጎ ከተወሰደ ደግሞ ውሎ አድሮ የእያንዳንዱ ቤት ደጃፍ ላለማንኳኳቱ ምንም ማረጋገጫ የለንም፡፡ ያየነውም የሆነውም ይኸው ነው፡፡ የዚህ አይነቱን ስሱ አደጋና ያለመተባበር ጦስ አስመልክቶ ጀርመናዊው ፓስተርና አንደበተ ርቱዕ[orator] ማርቲን ኒዬሞለር በአንድ ወቅት የተናገረው ይጠቀሳል፡፡
   ፓስተሩ ስለተናገሩት ነገር ‹contemporary moral issues› ከሚለው መፅሐፍ ገፅ 67 ያገኘሁትን እስኪ ላጋራችሁ፡-
   «In Germany, the Nazis first came for the communists and I did not speak up, because I was not a communist. Then they came for the jews and I did not speak up, because I was not a jew. …» እንዲህ እያለ ናዚዎቹ የተለያዩ ተቋማትንና የማሕበረሰብ ክፍሎችን ሲነኩ ‹አይመለከተኝም› እያለ ከመናገር መታቀቡን ይዘረዝራል፡፡ በመጨረሻ ግን ወደራሱ መጡ፡፡ እስኪ የሆነውን አብረን እንይ፡፡
   «…Then they came for me …and by that time, there was no one to speak up for anyone.» ይለናል፡፡ ጎረቤቶች ሲጮሁ አልደረሰምና እሱ የሚጮህበት ቀን ሲመጣ ቢጮህም የሚሰማው አልነበረም፡፡- ምክንያቱም ጎረቤቶቹ ሁሉ ተራ በተራ ሲጮሁ አጯጯሂ አጥተው የመጨረሻ ዋይታቸውን አሰምተው ከስመው ነበርና ነው፡፡ የመጨረሻውን ሰለባ ማጥቃት ደግሞ በጣም ቀላሉ ነገር ነው፡፡ እመኑኝ ተባብረን በአንድነት ካልቆምን፤ ዛሬ የጎረቤታችን የሚመስለን መከራ ሁሉ ነገ የእያንዳንዳችንን በር ያንኳኳል፤ የሚያመልጥም የለም !
እግዚአብሔር ግን መንገድ አለው
Filed in: Amharic