>

በኢትዮጵያዊያን ደም መነገድ - በራስ ላይ መቀለድ!!! (አቶ ታዬ ደንዳዓ)

በኢትዮጵያዊያን ደም መነገድ – በራስ ላይ መቀለድ!!!
አቶ ታዬ ደንዳዓ
በታሪካችን ጨቋኝ ስርዓት ኢንጂ ጨቋኝ ብሔር አልነበረም። መብቱ ተነፍጎ የተበደለ ኦሮሞ እንዳለ ሁሉ ፍትህ የተጓደለበት አማራ፣ ወላይታ፣ ትግሬ እና ሌላም አለ። በሀገር እና በወገን ላይ አስከፊ ወንጀል የፈፀመ ትግሬ እንዳለ ሁሉ ግፈኛ እና ወንጀለኛ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ወላይታና ሌላም አለ። በዝያ ደረጃ አንዱን ብሔር ጨቋኝ፥ ሌላዉን ተጨቋኝ አድርጎ በመሳል ኢትዮጵያዊያንን ማባላት አይቻልም። ደረጃዉ ቢለያይም ሁሉንም እንጋራለን። ከምንም በላይ ግን ሁላችንም በራዕያችን አንድ ነን። ነፃነት፣ እኩልነት፣ ፍተሃዊነት እና ብልፅግና የተረጋገጠባት ኢትዮጵያን እንፈልጋለን። ራዕያችንን ደግሞ ተደምረን እናሳካለን።
ትላንት ወልዲያ ላይ ለፖለቲካ ንግድ በተለኮሰ እሳት ሁለት ተማሪዎች ሲሞቱ ከአስር ያላነሱ ቆስሏል። ብዙዎች ደግሞ ለመንፈስ እና ሞራል ጉዳት ተዳርጓል። ይህ ሁላችንንም እጅግ ሊያሳዝነን ይገባል። በሁለት መሠረታዊ ምክንያቶች። አንደኛዉ ተማሪዎቹ የኢትዮጵያ ተስፋዎች መሆናቸዉ። ነገ ሀገሪቷን ተረክበዉ የሚመሯት፣ የሚያለሟት እነሱ ናቸዉ። እዝህ ደረጃ እንዲደርሱም ኢትዮጵያ የሌላትን ሀብት በነዝህ ተማሪዎች ላይ አፍሳለች። ያ ሀብት ከሁሉም ኢትዮጵያዊ እናቶች መቀነት ላይ የተለቀመ ነዉ። ለአንድ ሀገር ለዩንቬርሲቲ የበቁ ነገዋን ሊያሻሽሉ የሚችሉ ልጆቿን በከንቱ ማጣት ኪሳራዉ ከባድ ነዉ። ሁለተኛዉ ሰበአዊነት ነዉ። ለሁሉም የሰዉ ልጆች ደህንነት እና ሰላም ማሰብ አለም አቀፍ መርህ ከመሆኑም በላይ የስልጡንነት ማሳያ ነዉ። ተማሪዎቹ ኢትዮጵያዊነታቸዉ ቀርቶ ቻይናዊያን ወይም ናይጄሪያዊያን ቢሆኑም እነደሰዉ ልጆች የተፈፀመባቸዉ ግፍ ሊያሳዝነን ይገባል። ያ ከልሆነ ሰዉነታችን ወይም ጤንነታችን ያጠራጥራል።
አንዳንዱ ፋሺስታዊ አመለካከት የተጠናወተዉ ግለሰብ እና ፓርቲ በከንቱ በፈሰሰዉ የወንድሞቻችን ደም ፖለቲካን ይነግዳል። “ሟቾችና ተጎጂዎች ከኔ ብሔር አይደሉም” በሚል የታመመ አመለካከት በወንድሞቹ ሞት ይሳለቃል። ለአንድ ወገን ያደላ በመምሰል በወንድማማቾች መሀከል ጥላቻንና ጥርጣሬን ይፈጥራል። በወልዲያ የኢትዮጵያዊያንን ህይወት በከንቱ የቀሰፈዉን አስከፊ ክስተት በማቃለል በኦሮሚያ የተፈጠረዉን ተመሳሳይ ክስተት አጋኖ ያሳያል። በከንቱ ዉደሴ “ጀግና” ለመባል ይሞክራል። ለተወሰነ ቡድን ተቆርቋሪ በመምሰል “ወገኔ” ለሚለዉ ብሔር ጭምር በተጨባጭ ጉድጓድ ይምሳል።  በዝህ ልክ ጫፍ የረገጠ ብሔረተኝነት ሀገርን እና ዜጎቿን ይበላል። ደግሞ እንዲህ እያሰቡ  እንዴት የ21ኛ ክፍለ ዘመን ሰዉ ወይም ፓርቲ መሆን ይቻላል? እንዲህ አይነት ሰዉ ከመንግስት ከፍተኛ አመራር መሆኑ ደግሞ ነገሩን እጅግ አሳፋሪ ያደረገዋል። በዝህ አደገኛ አስተሳሰብ ሀገር ለመምራት የሚፈልግ ፓርቲን በ21ኛ ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ ማግኘትም ያስደነግጣል። መንግስት በዝህ ጉዳይ ይዘይዳል።
ኢትዮጵያዊያን ለሁሉም የሰዉ ልጆች መነሻ መሆናችንን አለም ያዉቃል። ቁሳዊ እና ሀሳባዊ ስልጣኔ ከኛ ጀምሯል። እርስ በእርሳችን ደግሞ ላንለያይ ተሳስረናል። ተጋብተን፣ ተዋልደን ተጋምደናል። በቋንቋ፣ በሀይማኖት እና በብሔር ብንለያይም አብረን ኖረን አብረን ሞተናል። መከራን እና ደስታን አብረን አይተናል። በተጨባጭ አንዱ ሌላዉ ዉስጥ ይገኛል። ስለዝህ አንዱ ሲጎዳ ሁሉም ሊታመም፥ አንዱ ሲደሰት ሁሉም ሊስቅ ይገባል። ያሰቡልን መስለዉ ሊያባሉን ከሚሰሩ የፖለቲካ ነጋዴዎች ራሳችንን መጠበቅ ግድ ይላል!
በኢትዮጵያዊያን ደም አይነገድ”
Filed in: Amharic