>

በድሬደዋ ቄሮ የሚባለው ቡድን ባደረሰው የወንጭፍ ጥቃት ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች ተጎዱ!!! (ኢትዮ 360)

በድሬደዋ ቄሮ የሚባለው ቡድን ባደረሰው የወንጭፍ ጥቃት ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች ተጎዱ!!!
ኢትዮ 360 
 
* በሰላም ወቶ መግባት ህልም የሆነባት ድሬደዋ
 
በድሬደዋ አዲስ ከተማ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ቄሮ የሚባለው ቡድን ባደረሰው የወንጭፍ ጥቃት ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች መጎዳታቸው ታወቀ።
 የኢትዮ 360 ምንጮች ከስፍራው እንዳደረሱን መረጃ ከሆነ ቡድኑ ገንደጋራና አዲስ ከተማ ተብለው በሚጠሩት አካባቢዎች ግጭት እንዲቀሰቀስ በርካታ ሙከራዎችን አድርጓል።
 ነገር ግን የአዲስ ከተማ ነዋሪዎች ጥቃቱ ወደ ከፋ ደረጃ እንዳይሄድ ራሳቸውን ለመከላከል ቢወጡም ከቡድኑ የሚወነጨፈው የድንጋይ ውርወራ አላንቀሳቅስ ማለቱን ምንጮቹ ይናገራሉ።
 ቄሮ የሚባለው ቡድን የጀመረውን ጥቃት አጠናክሮ ለመቀጠል ቢሞክርም በአካባቢው የደረሰው የመከላከያ ሃይል ግን እቅዱ እንዳይሳካ አድርጎታል ይላሉ።
 እንደ መረጃዎቹ ከአካባቢው የተባረረው ቡድን በሌሎች አካባቢዎች ጥቃት ለመፈጸም ቢሞክርም በመከላከያ ሃይሉ ጥረት ሊሳካለት አልቻለም ሲሉ ገልጸዋል።
 በድሬደዋ ዙሪያ ካሉ የገጠር ቀበሌዎች እየተጫኑ ከተማው ውስጥ እንዲበተኑ የሚደረጉት የጥፋት ሃይሎች ዛሬም የድሬደዋ ከተማ ህዝብን ከማሸበር ወደ ኋላ አለማለታቸውን ይናገራሉ።
 የከተማዋ ጸጥታ ሃይል ጥፋት እያደረሱ ባሉ ቡድኖች ላይ ርምጃ ለመውሰድ አቅም ማጣቱ፣የከተማዋ አስተዳደር ደግሞ የጥፋት ሃይሎችን ችግር ለመፍታት ከመሮጥ ያለፈ ለሰላማዊው የከተማዋ ነዋሪ የሚያደርገው አንዳችም ነገር የለም ሲሉ ይከሳሉ።
 የከተማዋ ነዋሪ በየጊዜው የነዚህ ቡድኖች ጥቃት እንዳስመረረውና አቤት የምልበት አካል ማጣቱን ምንጮቹ ይገልጻሉ።
በሰላም ወቶ መግባት ህልም የሆነባት የድሬደዋ ከተማ ነዋሪዎች ዛሬም ፍትህን ይሻሉ፣የፌደራሉ መንግስት አስቸኳይ መፍትሄ ካላመጣም በከተማዋ ያለው ችግር ከዚህም ሊከፋ ይችላል ሲሉ ስጋታቸው ምንጮቹ ይጠቁማሉ።
አሁንም በከተማዋ ያለው ውጥረት በመከላከያ ሃይሉ አማካኝነት ረገብ ያለ ቢመስልም እውነታው ግን አሁንም የድሬደዋ ከተማና ህዝቧ ስጋት ውስጥ መሆናቸው ነው ሲሉ ነዋሪዎቹ ለኢትዮ 360 የመረጃ ምንጮች ገልጸዋል።
Filed in: Amharic