>

በቀጣዩ ዓመት መንግሥት ካላገኘን አሁን ያለው ቀውስ የት እንደሚያደርሰን መገመት ያስቸግራል!!!”  (ፕ/ር መረራ ጉዲና)

በቀጣዩ ዓመት መንግሥት ካላገኘን አሁን ያለው ቀውስ የት እንደሚያደርሰን መገመት ያስቸግራል!!!

 

 

ፕ/ር መረራ ጉዲና

አዲስ አበባ፦ የኢህአዴግ ውህደት በስምምነት ላይ መመስረቱ ለአገሪቱና ለህዝቧ ጠቃሚ መሆኑን የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ተናገሩ፡፡ ምርጫውን ማራዘምም አገሪቱ ላለችበት ሁኔታ መፍትሔ እንዳልሆነና ለበለጠ አደጋ ሊያጋልጥ እንደሚችልም ገለጹ፡፡

ፕሮፌሰር መረራ እንደተናገሩት፣ የኢህአዴግ እህት ፓርቲዎች አንድ ውሁድ ፓርቲ የመሆን ሃሳባቸው የራሳቸው ቢሆንም እንደ ፖለቲከኛ ግን በስምምነት ቢዋሀዱ ይጠቅማቸዋል፡፡ ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ሊጥላቸው ይችላል ፡፡

የፓርቲዎቹ ለመዋሃድ አለመስማማት የለውጡን መንገድ እንዳያስትና እንዳያደናቅፍ፣ አገሪቷንም ወዳልተጠበቀ ቀውስ ውስጥ እንዳያስገባ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት ፕሮፌሰር መረራ፣ፓርቲዎቹ ከራስ በላይ ለአገር ማሰብና ለውጡም እንዳይጨናገፍ የራሳቸውን ሚና መጫወት እንደሚገባቸው አብራርተዋል፡፡

‹‹አሁን ያለው ፌዴራሊዝም ትልቁ ችግር የአንድን ቡድን ወይም ፓርቲ የበላይነትን ለማስፈን ተብሎ ዴሞክራሲ አልባ ሆኖ የቆመ መሆኑ ነው›› ያሉት ፕሮፌሰር መረራ፣ ይህ ውህደት የሁሉም ችግሮች መፍቻ ቁልፍ ሊሆን ስለሚችል በስምምነት ላይ ተመስርቶ  መከናወን አለበት፤ ይህ መሆን ካልቻለ ግን አገሪቷን ላልተፈለገ አደጋ ሊዳርጋት ይችላል ብለዋል፡፡

በአገሪቱ የሚነሳው የማንነት ጥያቄ ላለፉት በርካታ ዓመታት የዘለቀ በመሆኑ በስምምነት ላይ የተመሰረተ መልስ ካላገኘንለት በዚህ ወይም በዚያኛው ቡድን ፍላጎት  አልፎ ለመሄድ መሞከር ዋጋ ስለሚያስከፍል በጣም መጠንቀቅ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ‹‹ህዝቦች ለአስተዳዳሪዎቻቸው አንታዘዝም ፤የሚነገረንንም አንሰማም›› እያሉ በመሆኑ  ገዢው ፓርቲ በለመደው ሁኔታ መምራት እያቃተው ነው ያሉት ፕሮፌሰር መረራ፣ ለዚህ የሚመጥን ፖለቲካዊ መግባባት መፍጠር፣ ከሌሎች ኃይሎች ጋር ተዋህዶ ይህችን አገር የት ድረስ እንወስዳታለን የሚለውን አስፍቶ ማየት እና በዚያው ልክ መስራት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡

‹‹እኛ እንደ ተፎካካሪ ፓርቲ መንግሥትን ልንመክር የምንችለው በስምምነት ላይ የተመሰረተ ውህደት አድርጉ ነው የምንለው ›› ያሉት ፕሮፌሰር መረራ ፣ ውህደቱ በተለይም በቀጣይ የሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ነጻና ፍትሀዊ እንዲሆን ከፍተኛ ሚና እንዳለው ፤ ለዚህ ስኬት ደግሞ ሁሉም በአንድነት መቆምና መተባበር ወቅቱ የሚጠይቀው መፍትሔ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

አሁን ያለው የፌዴራል ስርዓት መለወጡ ዋጋ የሚያስከፍል በመሆኑ በሚቀጥሉት አሥርና ሃያ ዓመታት ይህንን ለመለወጥ ከመነሳት ይልቅ ዴሞክራሲ ላይ እንዲመሰረት ማድረጉ የተሻለ አማራጭ መሆኑን ፕሮፌሰር መረራ ተናግረዋል፡፡

ኢህአዴግ ስርዓቱን ዴሞክራሲያዊ ማድረግ ይጠበቅበታል ያሉት ፕሮፌሰር መረራ፣ ነጻና ፍትሀዊ ምርጫ በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲኖር ማስቻል ይጠይቃል፤ ከዚያ ውጭ የሚፈጠሩ ነገሮች በሙሉ አገሪቷን ይበትኑ ይሆናል እንጂ የሚያመጡት ትርፍ ስለማይኖር የኢህአዴግ አመራሮች ይህንን ደጋግመው ማሰብ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በየቦታው ያሉ ቀውሶች መንስኤያቸው አንድ ገዢ ፓርቲ ስልጣንን በበላይነት ይዞ በከፋፍለህ ግዛ ሴራ አገሪቱን ሲመራ በመቆየቱ߹ የአስተዳደርና ፖለቲካዊ ችግሮች ባለመፈታታቸው ፤ በነጻና ፍትሀዊ ምርጫ የመጣ መንግሥት ባለመኖሩ ነው ያሉት ፕሮፌሰር መረራ ፤ብሔራዊ መግባባት ላይ ቅድሚያ ተሰጥቶት ሊሰራ ይገባል ፤ ከዚያ ውጪ ግን ምርጫውን ማራዘም መፍትሔ አያመጣም፤ እንደውም ለበለጠ አደጋ ሊያጋልጥ ይችላል ብለዋል፡፡

በህዝብና በመንግሥት መካከል ለተፈጠረው ሰፊ ክፍተት ምርጫው ራሱ መልስ ሊሆን ይችላል የሚሉት ፕሮፌሰሩ፣ በሀቅ ወደ ምርጫ የምንገባ ከሆነ ህዝቡ በመረጣቸው ተወካዮቹ ወደ መመራት ይሄዳል፡፡ ስለዚህ በእኔ ግምት የሚቻለውን ያህል ጥረት ተደርጎ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ምርጫው መካሄድ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

” በቀጣዩ ዓመት አዲስ መንግሥት ካላገኘን አሁን ያለው ቀውስ የት እንደሚያደርሰን እርግጠኛ አይደለሁም” ያሉት ፕሮፌሰር መረራ፣ የሚሻለው አገሪቷ ላይ ብሔራዊ መግባባት እንዲመጣ ለመጀመሪያ ጊዜ ነጻና ፍትሀዊ ምርጫ እንዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

አዲስ ዘመን ህዳር 3/2012

እጸገነት አክሊሉ

Filed in: Amharic