>

መንግስት እና መገናኛ ብዙሃን ትኩረት የነፈጉት የድሬዳዋ እና ሐረር አሳሳቢ ሁኔታ!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

መንግስት እና መገናኛ ብዙሃን ትኩረት የነፈጉት የድሬዳዋ እና ሐረር አሳሳቢ ሁኔታ!!!
ያሬድ ሀይለማርያም
ትላንት እና ዛሬ ከድሬዳዋ እና ከሐረር አካባቢ የሚደርሱን ዜናዎች እጅግ አሳሳቢ እና አስደንጋጭም ናቸው። በተለይም በምስራክ ሐረርጌ ቤተክርስቲያንን እና አማኒያዊያንን ኢላማ ያደረገ ጥቃት እስከዚህ ምሽት ድረስ ቀጥሏል። ድሬዳዋም በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ እንደምትገኝ እና ነዋሪዎችም የድረሱልን ጥሪ እያቀረቡ መሆኑን ሰምተናል።
በእርግጥ ድሬዳዋ እና ሐረር ከተሞች የመንጋዎች መፈንጫ ከሆኑ ወራቶች ተቆጥረዋል። ሕዝቡ የመንግስት ያለህ እያለ ሲጮኽም እንዲሁ ወራቶች ተቆጥረዋል። ይሁንና በሌላው የአገሪቱ ክፍል፤ በተለይም በኦሮሚያ ክልል የፖለቲካ ውጥረት በነገሰ ቁጥር እነዚህ ሁለት ከተሞች ውስጥ የሚፈጸመው ጥቃት እና ሁከት በእጥፍ ይጨምራል። በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ሁከት ተከትሎ በድሬዳዋ እና በሐረር ከተማ እየደረሰ ያለው የመንጋዎች ጥቃት እስከ አሁን አልቆመም። ነዋሪዎቹም የመንግስት ያለህ እያሉ የድረሱልን ጥሪያቸውን እያቀረቡ ነው። ሰሚ ግን አላገኙም።
የሚገርመው የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ብቻ ሳይሆኑ እንደ #VOA እና #BBC ያሉ ሚዲያዎች በእነዚህ አካባቢዎች ስለሚፈጸመው ጥቃት ጆሮ ዳባ ልበስ ማለታቸው ነው። የዛሬው ቪ ኦ ኤ ምሽት ዜና ዋና ርዕስ አዋሳ ከተማ ሰላሟ ተመልሶ ተረጋግታለች የሚል ነው። ሰላም ያጡትን የድሬዳዋን እና የሐረር ጉዳይ ወደጎን ትቶ ከተረጋጋች ስለከረመችው የአዋሳ ሰላም መመለስ ማውራት ምን ይሉታል?
እራሳቸውን ቄሮ ብለው የሚጠሩ እና የተደራጁ ጎረምሶች እነዚህን ተወዳጅ ከተሞች ልክ እንደ አንበጣ ወረው ሕዝቡን እያሰቃዩ ነው። መንግስት ቢያንስ የአስቸኳይ ጊዜ አውጆ እነዚህን አካባቢዎች ከጥቃት መታደግ፣ ከመንጋዎቹ ማጽዳት እና ሕዝቡን ማረጋጋት ሲኖርበት ለጉዳዩ በቂ ትኩረት አለመስጠቱ እና ለሕዝቡም ጥሪ ምላሹ ዝምታ መሆኑ እጅግ ያሳዝናል። አካባቢው ላይ ካሉ ምንጮች ማረጋገጥ እንደቻልነው የከተሞቹ የጸጥታ ኃይሎች ሥራቸውን በአግባቡ እየሰሩ እንዳልሆነ እና በአንዳንድ አካባቢዎችም የዳር ተመልካች ሆነው ጥቃት ለሚፈጽሙት መንጋዎች ድጋፍ መስጠታቸውን ለማወቅ ተችሏል።
የድሬዳዋ እና የሐረር ሕዝብ የድረሱልን ጥሪ ይሰማ!
Filed in: Amharic