>
5:18 pm - Monday June 16, 6679

አርሶ አደሩ ማን ነው?  (መስከረም አበራ)

አርሶ አደሩ ማን ነው? 
መስከረም አበራ
‘የኢትዮጵያን ብሄር ብሄረሰቦች ከእስርቤት ፈትቼ ለቀቅኩ’ ያለው ህወሃት/ኢህአዴግ በስውር ከሚሰራው ቅሌቶቹ በተጨማሪ በግልፅ በአደባባይ ህዝብን ትኩር ብሎ እያየ የሚቀባጥረው ቅሌቱም ብዙ ነው፡፡ ከነዚህ የአደባባይ ቅሌቶቹ አንዱ ‘የሃገሪቱን ብሄር ብሄረሰቦች ከእስር ፈትቼ የለቀቅኩ የብሄረሰቦች መድህን ነኝ’ ባለበት አፉ ከሃገሪቱ ህዝቦች ግማሾቹን አጋር ኢትዮጵያዊያን ብሎ በግልፅ ከዋነኛ ስልጣኖች ውጭ ያደረገበት ቅሌቱ ነው፡፡
አጋር ያላቸው ኢትዮጵያዊያን የአብዮታዊ ዲሞክራሲ አባል ድርጅቶች የማይሆኑበትን ምክንያት ሲያስረዳ አጋር ፓርቲዎቹ የሚያስተዳድሩበት አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች አርብቶ አደር ስለሆኑ ነው ይላል፡፡ ስዚህ ጉዳይ ሰፋ ባለ አርቲክል የምመለስበት ይሆናል፡፡ለጊዜው ግን አንድ ትዝብት ላስቀምጥ፡፡
ህወሃት ማሌሊትን ሲመሰርት የላባደሩን ስርዓት ለመመስረት አስቦ እንደነበር አቶ ገብሩ አስራት በአንድያ መፅሃፋቸው ገፅ 102 ይገልፀሉ፡፡ ህወሃት ማሌሊትን ሲመሰርት ወግ እንዳይቀር ተመሳሳይ የአውሮፓ እና ሌሎች ሃገራትን ማርክሲስት ፓርቲዎች ጋብዘው ነበር፡፡ የጀርመኑን ማሌ ፓርቲ ወክሎ የተገኘውን ተወካይ በተመለከተ አቶ ገብሩ አስራት ይህን ፅፈዋል;
“ጀርመናዊው ከሃገሩ ተነስቶ በሱዳን አድርጎ ወልቃይትን እና ፀገዴን አቋርጦ ደጀና በሚለው የህወሃት መናኸሪያ አልፎ እጅግ አስቸጋሪ የሆነውን ምድር ካቋረጠ በኋላ ሲጓዝ ስየ፣አውአለምና ገብሩ አብረነው ነበርን፡፡ ይህን ሁሉ መንገድ ሲጓዝ የዘመኑ መገለጫ የሆኑትን የኤሌክትሪክ መስመሮችን፣የአስፋልት መንገዶች፣ዘመናዊ ከተማ፣ፋብሪካ ወዘተ በለማየቱ እጅግ ተደንቆ ‘ይህ ስፍራ በመፅሃፍ ቅዱስ የተገለጠ እንጅ ባለንበት ዘመን ያለ መሆኑን ለማመን ያቅተኛል’ የሚል አስተያየት ሰጠ፡፡ የላባደሩ ስርዓት ይገነባል የተባለው በዚህ የቡርዣው ስርዓት መሰረተ ልማቶች፣ተቋማትና እሴቶች ገና ባልተገነቡበት ሳይንስና ቴክኖሎጅ በቅጡ ባልተዋወቁበት አካባቢ መሆኑ እንዳስገረመው መገመት ይቻላል፡፡እውነትም ምንም አይነት የአዲሱ አለማዊ እውቀት ሽታ በሌለበት ምድር ሶሻሊዝምን እገነባለሁ ማለት ግራ የሚያጋባ ነበር፡፡” ገብሩ አስራት፣ሉአላዊነትና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ፤ገፅ፣103-104
.
የጀርመኑ ሰውየ  እንደገለፀው (ነው ሙድ እንደያዘበት? )የመፅሃፍቅዱሶቹን ቅፍርናሆምን እና ቤተሳይዳን የመሰሉትን ከተሞች ይዞ(መጀመሪያ መፀሃፉን ሳነብ የፈረንጁ ሙድ አያያዝ በጣም ነበር ያሳቀኝ:) የላባደሩን ስርዓት መመስረት ከታሰበ በአምስቱ ክልል ያሉ አርብቶ አደር ያልሆኑ በርካታ ህዝቦችን ይዞ አብዮታዊ ዲሞክራሲን መመስረት እንዴት አይቻልም? አጋር ድርጅቶች ባሉበት አካባቢ የአርሶ አደር እጥረት ስላለ ስንት ሚሊዮን አጋር ኢትዮጵያዊያን የሃገራቸው ጠ/ሚ የመሆን ነገር ሲያምራቸው ይቅር ነው የሚለው ቀልደኛው መለስ ዜናዊ!
 ለመሆኑ ሃረሪ ክልል ያሉ አርብቶ አደሮች እነማን ናቸው? በቤኒሻንጉል ካለው አርሶ አደርና አርብቶ አደር የትኛው ይልቃል? በሶማሌ ክልል ካለው ህዝብ ስንት ስንተኛው ነው አርብቶ አደር?በጋንቤላ ክልልስ ቢሆን ከአርሶ እና አርብቶ አደሩ የቱ ይልቃል? በአፋርም ለአብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚበቃ ያህል አርሶ አደር የለም ነው ጨዋታው……
ለማንኛውም አጋር ኢትዮጵያዊነት ላይመለስ መሄዱ ደስስስ ካላቸው አንዷነኝ! ስለዚህ ነገር አጥብቄ ስከራከር የቆየሁ ነኝና ዘግይቶም ቢሆን በስተመጨረሻው እውን መሆኑ ጥሩ ዜና ነው፡፡አጋር ኢትዮጵያዊ የለም፤ኢትዮጵያዊ ሁሉ ለኢትዮጵያ እኩል ያስፈልጋል…….!
Filed in: Amharic