>

“አባይ 30 ሚሊዮን ዓመት ሆነው!” (ደረጄ ደስታ)

“አባይ 30 ሚሊዮን ዓመት ሆነው!”
ደረጄ ደስታ
ግብጾቹ “የአባይ ውሃ እድሜ 30 ሚሊዮን ነው” እሚለውን የሰሞኑን “የላይቭ ሳይንስ ሪፖርት” ግኝት ይዘው እየተከራከሩ ነው። መቸም ሰሞኑን ወሬያቸው አባይ ብቻ ሆኗል። አንዳንዶቹ ሳይንቲስቶች 30 ሚሊዮን ሳይሆን  6 ሚሊዮን ዓመት ነው እያሉ ነው። አባይ ወንዝ ጣና ላይ ተወልዶ በቃ ከዛሬ ጀምሮ መፍሰስ ጀምሬያለሁ ካለበት ሰዓት ጀምሮ፣ እስከዛሬ ያለውን ነገር ሁሉ እየተነጋገሩበት ነው። ከሁሉ ከሁሉ ግን፣ አባይ በዚህ ሁሉ የፍሰት ህይወቱ ውስጥ፣ መስመሩን ስቶ አቅጣጫውን የቀየረበት ወቅትስ መች ይሆን ብለውም እየተመራመሩ ነው። ያው መቸም ኢትዮጵያ የአባይን አቅጣጫ ሳልቀይር መጠኑንም ሳልቀንስ ገድቤ እጠቀምበታለሁ አለች እንጂ አቅጣጫ መቀየር የገባች አይመስልም። ባይሆን የወሬውን አቅጣጫ ታስቀይር ካልሆነ ወንዙን አታስቀይሰውም።
 ግብጾቹ ግን ይገርማሉ፣ የግድቡ ሥራ መጀመሩን ገና ሰሞኑን የሰሙት ሰበር ዜና ይመስል ጥድፊያቸው ያስገርማል። ኢትዮጵያን መቀጠቀጥ እንደጋለች ነው ያሉ አስመስሎባቸዋል። ኢትዮጵያ ሰምታቸው እማታውቅ ወይም አልሰማ ያለች ይመስል “አባይ የህልውናቸው መሠረት መሆኑን” እየደጋገሙ ያስጠነቅቃሉ ። ለማንኛውም ይቺን ሁለት ቀን አዲስ አበባ ላይ ሱዳንን ጨምረው ድርድር ተቀምጠዋል። የአሜሪካ መንግስት እና የዓለም ባንክ ተወካዮችም አብረው ተቀምጠው በታዛቢነት እያፈጠጡባቸው ነው። ከግድቡ በፊት ብዙ እሚገደቡ ነገሮች ያሉባት ኢትዮጵያም ጭንቅ ላይ መሆንዋ አልተደበቀም። ሲያመጣው እንዲህ ነው። ግብጾች ደግሞ የ30 ሚሊዮን ዓመት ችግር ይዘው መጡ!
Filed in: Amharic