>
4:41 pm - Tuesday May 17, 2022

የሰባተኛው ንጉሥ መንግሥት...!!!! (በዲያቆን ብርሃን አድማስ)

የሰባተኛው ንጉሥ መንግሥት…!!!!
ዲያቆን ብርሃን አድማስ
ሰባተኛው ንጉሥ መሆናቸውን ደጋግመው የነገሩን ጠቅላይ ሚኒስትር በተሾሙ በሦስተኛው ወር ላይ ቀደም ብሎ የማውቃቸው ከኦሮሞው ብሔር የተወለዱ አንድ ትልቅ ሰው ጋር እንገናኛለን፡፡ እኝህ ሰው  በዕድሜም፣ በሥራ ልምድም በብዙ ነገር የበሰሉና ጠቅላይ ሚንስትሩን በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚያውቁ ሰው ነበሩ፡፡ እኝህ ሰው ጋር የተገናኘነው 5፡30 በሚወስድ የአውሮፕላን በረራ ላይ ስለነበር በቂ ጊዜ ወስደን የሀገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ ፣ ተስፋችንና ሥጋታችን ለመወያየት ችለን ነበር፡፡
 ታዲያ እኒህ ሰው ሰባተኛ ንጉሥ መሆናቸው እንደተነገረላቸው ስለ ራሳቸው ደጋግመው የሚናገሩትን ጠቅላይ ሚንስትሩን እምነት የማይጣልባቸው ሰው መሆናቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲነግሩኝ ገጠመኞቻቸውን በመጥቀስ ጭምር ነበር፡፡ ሀሳባቸው ሲጠቃለል ይህ ሰው ሀገር የመምራት አቅም ፈጽሞ የለውም፤ ሲያቅተው ደግሞ ያው የተለመደውን የአማራ ተጠያቂነት አምጥቶ ቅራኔውን ከዚህ በፊት ከነበረው ያሰፋዋል፤ በሚል ነበር፡፡
ታዲያ ብዙም ጊዜ ሳይፈጅ የሆኑ ወታደሮች ቤተ መንግሥት ደርሰው መመለሳቸውን ምክንያት በማድረግ ምክር ቤት ውስጥ ማብራሪያ ሲሰጡ “ብዙ ሰዎች ከሱልልታ፤ ከሰንዳፋና ከቡራዩ መንግሥታችን ተነካ” ብለው በመገስገስ ላይ ነበሩ ሲሉ በግሌ መንግሥታዊ ሃላፊነት የሚሸከም ትከሻ እንደሌላቸው የመጨረሻ ድምዳሜ ላይ የደረስኩባት ቀን ሆነች፡፡
ሌላው ቀርቶ “መንግሥታችን” የምትለው ቃል ለሆኑ አካባቢ ሰዎች ብቻ ሲሰጥ ሌላው ሁሉ ማባበያና የውሸት መሆኑን ለመረዳት አስቸጋሪ አልነበረም፡፡ ከሁሉም የገረመኝ ደግሞ መንግሥት ሆኖ የተቀመጠ አካል አሁንም በሆኑ አካባቢ ሰዎች በማስፈራራት መንግሥቱን ለማስቀጠሉ ማሰቡና የነገሩኝ ሰው ሞያዊ ግምት ስድስት ወር ሳይሞላ እንኳ ሲደርስ ምን ያህል አደጋ ፊታችን እንደሚጠብቀን ቢያንስ በግሌ ግልጽ ሆኖልኝ ነበር፡፡
የሚያስደንቀው ግን ሰባተኛው ንጉሥ መንግሥታችን ተነካ ብለው ሊመጡ ነበር ላሏቸው የሸዋ ኦሮሞዎች እንኳ ያለመድረሳቸው ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ አንዱ የጥቃቱ ኢላማዎች የሸዋ ኦሮሞ ክርስቲያኖች ናቸውና፡፡ ድርጊቱ ብሔርን ሽፋን አድርጎ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንን አጽድቶ ለመኖር የሚደረገው ዝግጅት  አካል  ነውና፡፡ ነገር ግን የብሔር ብቻ ለማስመሰልም ጥረት ይደረጋል፡፡ ይህን የሚሉት ግን የአክራሪዎቹ መሪዎች የሸዋ ኦሮሞዎችን አጋርነት ቀድሞ  ላለማጣት የተደረገ ሥልት ይመስለኛል፡፡ ጉዳዩ ለኦሮሞነት እንዳልሆነም አሁን ድረስ በስብከት ብርድ ልብሳቸው ተጠቅልሎ  ዐይኑን ላልጨፈነ ሁሉ ግልጽ የሆነ ይመስለኛል፡፡ ሌላው ቀርቶ ለኦሮሞ ብቻ እንኳ ቢያስቡ ሊጠቅሙት የሚችሉት ደም ባያቃቡት እንደሆነ ለመረዳት የሚያስቸግር አይመስለኝም፡፡ ሆኖም አንዳንድ ደጋፊዎቻቸው የታያቸው ምን እንደሆነ ባይገባኝም እስካሁንም በጭፍን መንገድ ውስጥ መሔዳቸው ይገርመኛል፡፡
በሀገራችን “የውሻ ደም የማያስቀረው አምላክ” የሚባል አባባል አለ፡፡  እውነት ነው፤ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር እንኳን የሰው በእንስሳትና በአራዊትም ሳይቀር የሚደርስ ፍጅት ላይ ፈጣሪ ተበቃይ መሆኑ የማይካድ ነው፡፡ ይህን ማሰብ ቀርቶ ከኢትዮጵያ ታሪክ እንኳ መማር የማይችሉ አካላት ልክ እንደ ሁሉን ቻይ ሆነው በአደባባይ መፋነናቸው የእነርሱን ትንሽነትና አጅግ መንፈሰ ዳካማ መሆናቸውን ከማስረዳት ያለፈ ነገን በራሳቸው ላይ እጅግ ከማከበዳቸው በላይ የሚፈይድላቸው ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡
እንደ እኔ ከሆነ ብናደርገው የሚሻለው
1) ክርስቲያኖቹ ከልብ በተሰበረ ልብ ውስጥ ሆነን ማዘንና መጸለይ አለብን፡፡ አሁንም የምደግመው እባካችሁ እባካችሁ ጭብጨባ፣ ድለቃ፤ ዝላይ፣ ይብቃ፡፡ ከልብ እንዘን፡፡ በተለይ መከራው ለማይቀርላቸው ሰዎች እግዚአብሔር ትዕግሥትንና በሃይማኖት መጽናትን እንዲሰጣቸው አጥብቀን እንጸልይ፤ እኛም እያንዳንዳችን የሚገጥመንን አናውቀውምና መጽናትን እንዲሰጠን መጸለይ አለብን፡፡ ቢያንስ ቢያንስ “አቤቱ ወደፈተና አታግባን” የሚለው ጸሎት  እንዲህ ያለ መከራ አታምጣብን ሳይሆን በእንዲህ ያለ የመከራ ወቅት ወደ ክህደትና ጥርጥር አታግባን መሆኑን ተረድተን በአግባቡ እንጸልየው፡፡
2) ለዐለም አቀፍ ማኅበረሰብም ሆነ ለእርስ በእርስ መረጃ መስጠት በሚያስፈልግበት ጊዜ እውነተኛ ያለሆኑና የሌላ ሀገር፣ ቦታ፣ ጊዜ የሆኑ ፎቶ ግራፎችን በምንም መንገድ አለመጠቀም አስፈላጊ ነው፡፡ ይህን የሚያደርግ ሰው ቢኖር ሳያውቅም ቢሆን ነገሩን ሐሰት ነው ለማስባል የሚያመች መረጃን በመስጠት ለአጥቂዎቹ እገዛ እያደረገ እንደሆነ በማወቅ በፍጥነት ማቆም አለበት፡፡ ለምሳሌ ለሐረሩ ጉዳይ የውጭ ሀገር ፎቶ ግራፍ የለቀቃችሁ በፍጥነት በእውነተኛው ፎቶ ግራፍ እንድትተኩት ካጣችሁም እንድታነሡት እጠይቃለሁ፡፡ ወደፊትም በፍጹም መደገም የለበትም፡፡
3) በሚዲያ ለምናደርጋቸው ሁሉ ከፍተኛ ሓላፊነት መውሰድና መጠንቀቅ አስፈላጊ ነው፡፡ የእኛ ድርጊት በከፍተኛ ከበባ ባሉት ላይ የሚያደርሰውን ተጽእኖ ሳያስታውሉና በተግባር ምንም ማድረግ ሳይችሉ በሚዲያ አላስፈላጊ ነገር ማድረግ በችግር ውስጥ ያሉትን ለበለጠ አደጋ ውስጥ እንዳይከት ትልቅ ሓላፊነት የሚጠይቅ መሆኑን ልንረሳው አይገባም፡፡ እንኳን እኛ ተጨምረንበት እነርሱም ሆነ ብለው ጠብ ጫሪ ለማድረግ የሚያደርጓቸው የሐሰት ዜናዎችና መረጃዎች ብዙ ናቸው፡፡ ሲሆን ሲሆን እነዚያን የማጋለጡን ሥራ ከጀመሩት አካላት ጋር ተቀናጅተን ብናደርገው መልካም ነው፡፡
4) መንግሥትን በተመለከተ ልናደርገው የሚገባ ካለ ሀገሪቱን በይፋ ከማፍረሱ በፊት ለሚችል አካል ሐላፊነቱን እንዲያስረክብ መጠየቅ ብቻ ይመስለኛል፡፡ እኔ በግሌ ይህ መንግሥት መፍትሔ ሊሰጥ እንደማይችል ከተረዳሁ ቆይቻለሁ፤ በጽሑፍም ገልጫለሁ፡፡  እንዲያውም ራሱ የተቀናጀው ጥቃት ስውር አካል ካልሆነ ተመስገን ነው፡፡ እኛም ለሀገር በእውነት ከሚያስቡ የትኞቹም ዜጎች ጋር ሆነን ሀገራችንንም ቤተ ክርስቲያናችን ለማዳን በተግባር መንቀሳቀስ ብቻ ነው፡፡
5) በእውነት የሀገር ሰላምና አንድነት ከሚያሳስባቸው እስላሞችም እውነተኛ ድርጊት ማየት በግሌ እመኛለሁ፡፡  ሳይሽሞነሙኑና ሳይቀባቡ አክራሪውን ኃይል ማውገዝና መቃወም አለባቸው፡፡ ይህ ካልሆነ ነገ ለመተማመንም አብሮ ለመኖርም ብዙ ሰው ሊቸገር እንደሚችል ከአሁኑ መረዳት አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ እኔም ያነሣሁት አስቀድሞ ለማሳሰብ ነው፡፡
6) ክርስቲያኖችን እያሉ የአንድ ብሔር የበላይነት የሚሳካ መስሏቸውም ሆነ በዚህ ሰበብ የሚነግዱ የአክራሪዎች የፕሮፖጋንዳ ሰለባ ለሆኑት ሁሉ ቤተሰብ ጓደኛ የሆናችሁ ሁሉ በፍቅርና በእውነት ሆናችሁ ምክር ለግሷቸው፡፡ ከዚያ ውጭ መድከም አያስፈልግም፡፡ ፍርዱን ከአምላክ ያገኙታልና፡፡
7) በመከራ ውስጥ ላሉት በምንም መንገድ የምንደርስባቸው ዘዴዎች ካሉ እነርሱን በጥንቃቄ መተግበርና ከቀጣይ እልቂት ለማዳን የሚቻለን አካላት ሁሉ ከዚህ ጊዜ መዘግየት ያለብን አይመስለኝም ፡፡
በአሁኑ ጊዜ ከመንግሥት በላይ ለቤተ ክርስቲያን ጠላትም ሆነ አጥቂ ያለ አይመስለኝም፡፡ ይህን ደጋግሜ ስላልኩ አሁን አልዘበዝብም፡፡ አሁን በግልጽ መጠየቅ ያለብን ሀገር ከመፍረሷ በፊት መንግሥት ሀገሪቱን ለማዳን ራሱ ተባባሪ እንዲሆን ነው፡፡
መንግሥት ሆይ እባክህን በአስቸኳይ መንግሥታዊ ሓላፊነትን መወጣት ለሚችሉ አስረክብ፡፡ የዜጎችን ጥቃት መከላከል እስካልቻልክ ድረስ ሰዎች ራሳቸውን መከላከላቸው ተፈጥሮአዊ ነውና ከመንግሥት ውጭ የሆኑ ብዙ ሃይላት ከመነሣታቸው በፊት እባክህን ወይ የመንግሥትን ተግባር ተወጣ ወይም ሊወጡ ለሚችሉት አስረክብ፡፡ ከራሰህ ውስጥ ሰው ካለህ እንደባለፈው አሁንም ሰው ለውጥና ሀገሪቱን በይፋ ከመፍረስ ታደጋት፡፡ ካልሆነም ከሌሎች ፓርቲዎችም ሆነ ሀላፊነት ከሚሰማቸው ተቋማት ጋር ለሚያሸጋግሩ አስረክብ፡፡ ግዴላችሁም ለሥልጣናችሁ ብላችሁ ሀገራችንን ለማፍረስ መሣሪያ አትሁኑ፡፡ ኢትዮጵያ መዳኗ እንደ ሀገርም መቆሟ አይቀርም፤ እናንተ ግን ለእርግማንና ለውረደት ተላልፋችሁ ከመሰጠታችሁ በፊት ለክብር የሚያበቃችሁን ታሪካዊ ሓላፊነታችሁን ተወጡ፡፡
Filed in: Amharic