>

አላልኳችሁም!? (ደረጀ ደስታ)

አላልኳችሁም!?
ደረጀ ደስታ
ኢትዮጵያ  እንደ የመን እንደ ሶርያ ዩጎዝላቪያ ትሆናለች እየተባልን ነው። ይህ መቸም “አያ ጅቦ መጣልህ!” ተብሎ ህጻናትን እንደሚያስፈራሩት ነገር ቀልድ አይደለም። ያለው ሁኔታ አስፈርቶናል ያሉት እየተነበዩ፣ ያልናችሁን ካልሰማችሁን እሚሉትም እየታበዩ እሚናገሩት ሟርት አገር አያረጋጋም። በተለይ ለዛሬ ሁኔታ በእጅ አዙር ብቻ ሳይሆን በቀጥታ ተጠያቂ የሆን ሰዎች ይህን ስንናገር አያምርብንም። እነሱንም የናንተ ብቻ ጥፋት ነው ማለትም ሐቅ አይሆንም። እንደ የደረጃችን ሁላችንም የየድርሻችን እናነሳለን። እውነት ነው ዜጎች እየተገደሉ ነው። የሚሞቱት ብቻ ሳይሆን የሚገድሉትም ዜጎች ናቸው። የግድያው ምክንያት ምናልባት ሰዎች ሳይሆኑ አገዳዳይ ሀሳቦች ይመስሉኛል። ሀሳቦቹ ብቻ ሳይሆን እነሱን ተከትለው የተፈጠሩ ነገሮችም እንዲሁ አባባሽ ናቸው። ዜጎቻችን በተለይም ወጣቶችን ለምን ይሰሙናል? አላስተማርናቸውም።
ያስተማርናቸውም ቢሆን እነሱንም ሆነ ማንንም እሚጠቅም ነገር አይደለም። በዚያ ላይ ሥራ አልሰጠናቸውም። የኑሮ ትርጉምና ተስፋ አላሳየናቸውም። የጭካኔ ግብረገብ ግተናቸው ቢገድሉም ቢሞቱም ምንም የማይመስላቸው ደፋሮችን ፈጥረናል። ወደድንም ጠላንም የኛው ሸክሞች ናቸው። እኛም የያዘ ይዞን ነው እንጂ የመጠፋፋት አብዮት ውስጥ አልፈናል። ግድያው ገጠር ከመግባቱ በፊት መጀመሪያ የተገዳደለው ከተሜውና ምሁሩ ነው። አብዮታዊ  ታሪካችንም ሆነ የቅርቡ ጊዜ መገዳደላችን እሚመሰክረው ከነሱ ያለመሻላችንንም ጭምር ነው። እውነትማ እንነጋገር ከተባለ በጣም እሚያስፈራው ሜንጫና ብረት ይዞ የሚሮጠው ብቻ አይደለም። በየዶክተሩ በየምሁሩ በየአክቲቪስቱም እሚንተከተከው ጥላቻና ቁጣም ባይበልጥ እንኳ እኩል እሚያሳስብ ነው። እስኪ ሁላችሁም አጠገባችሁ ወዳለው ሰው ተመልከቱ።
እሚንተገተግ እልህና ንግግር ታስተውላላችሁ። ይህ ነገር ካቅማችን በላይ ነውና እርዱን ማለት ባልተለመደባት አገራችን፣ “አንተ ትጠፋታለህ እንጂ ኢትዮጵያ አትጠፋም” እሚለውም አነጋገር እልህን በእልህ ነው እንጂ መፍትሄን አያመጣም። ኢትዮጵያ እንድትኖር ሰው መጥፋት የለበትም። እሱማ ያው ኢትዮጵያም እንድትጠፋ ሰው ማጥፋት የያዙትና አፋፍ ሆነው እንደሚዝቱት መሆን ነው። የተደቀነብን በጥይት ብቻ እሚጠፋ አደጋ አልመሰለኝም። እውነት ነው እልቂት ማስቀረት የተአምር ያህል ከባድ የሆነ ሁኔታ ውስጥ ተገኝተን ሊሆን እንችላለን። ሰዎች እንዳይገዳደሉ ማድረግም አንችል ይሆናል። አለመግደልና እሚያገዳድል ነገር አለመናገር ግን እንችላለን። ላይመለሱ የተጣመሙ ነገሮች አሉ ተብሎ የተጣመሙ ነገሮች አይደረጉም። አገሩን እሚወድ ሰው፣ የራሳችሁ ጉዳይ ያውላቸሁ አገራችሁ ብሎ አይናገርም። ይብላኝ ለእናንተ ማለት ጸያፍ ነው። አላልኳችሁም! ብዬ ነበር ተናግሬ ነበር እሚል ርካሽ ትንቢትም እንዲፈጸም ከመጓጓት፣ ትንቢታችን ገደል ገብቶ፣ ስጋታችንም ጠፍቶ አገራችንና ህዝባችን ሰላሙን ቢያገኝ የተሻለ ነው። እብሪትና ትንቢት ምን ያደርጋል? ደማችሁ ደማችን ነው ያለው ጎንደር ለጸሎት ሲያቀርቅር፣ ሌላው ደረቱን ነፍቶ እሚፎክር ከሆነም አልተግባብቶንም።
ጸሎትም፣ እባካችሁ ብሎ መማጸንም፣ ዝቅ ብሎ ማሳለፍም፣ ነገር ማብረድም፣ ለመፍትሔ መቆዘምም፣ ከሌላው የነጻነት ትግል ጋር አንዳንዴም አብሮ ሊሄድ የሚችል ነገር ነው። ለምን ሞተብኝ ብቻ ሳይሆን ምን ነክቶት ገደለብኝ ማለትም የራሱ ጥቅም አለው። ሟችም ገዳይም ያገር ገመና ናቸው። አገርን ሲወዱ እስከ ሁሉ ነገሯ ይመስለኛል። ተገፋን ተሰደብን ብሎ ነገርስ ምንድነው? ዘለፋ ስደትና እንግልት ሳይጠጣ የኖረ ማነው? ያልተጋደለ ያልተቋሰለስ ወዴት ነው? ተዋልደናል ተጋድለናል እጣፈንታችንም አብሮ ይሁን። ስለ እግዚአብሔር!!!
Filed in: Amharic