>
5:13 pm - Saturday April 19, 0758

ህወሀት የችግሩ ብቻ ሳይሆን የመፍትሄውም አካል እናድርገው!!! (ያሬድ ጥበቡ)

ህወሀት የችግሩ ብቻ ሳይሆን የመፍትሄውም አካል እናድርገው!!!
ያሬድ ጥበቡ
*  ከአሁን በኋላ በአዲስ የተደራጀው የብልፅግና ፓርቲ በኦሮሚያ ክልል ተወዳድሮ ያሸንፋልን? እንዲሁ በደምሳሳው ሳየው ወለጋን ኦነግ፣ ባሌ፣ አርሲና ሐረርን ጃዋር (ወይም እሱ የባረከው ፓርቲ)፣ ሸዋን እነ ዶክተር መረራ ያሸንፋሉ ብዬ ስገምት፣ ለብልፅግና የሚቀረው ጅማና ኢሉአባቦራ ብቻ ይመስላሉ….
—-
ነገ የኢህዴን/አዴፓ 39ኛ አመት በአል ነው። ነገ የአዲሱ የብልፅግና ፓርቲን ለመመስረት የኢህአዴግ ምክርቤት ውሳኔ የሚያደርግበት ቀን ነው (ለመሆኑ ከፓርቲው ስም ኢትዮጵያ የሚለው ተነስቷል የሚለው ወሬ እውነት ነውን?) ነገ ኢህአዴግ እንዲፈርስ ውሳኔ የሚደረግበት ቀን ነው። ነገ ህወሓት/ወያኔ ከኢህአዴግ የሚባረርበት ቀን ነው። ነገ የትግራይ የመነጠል አደጋ መቆጠር የሚጀምርበትና በኢትዮጵያችን ታሪክ ሌላ የእርስበርስ ጦርነትና እልቂት እንዲጀመር የሚያስችል አደጋ አፍጥጦ ዐይናችን ላይ የሚጋረጠበት ቀን ነው።  ወደዚህ የሚያመሩት ጥርጊያዎች ሲጠረጉ 20 ወራት ወስደዋል። መቀሌን ከጅቡቲ የባህርበር የሚያቆላልፈው የታጁራ\ባሎ\መቐለ መንገድ ባለፈው ሳምንት ተመርቋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፈረንሳይ የጦር አውሮፕላኖችና  ተዋጊ ሄሊኮፕተሮች በ4 ቢሊዮን 600 ሚሊዮን ዶላር ለመግዛት ለመዋዋል ማቀዳቸውን የሚያሳይ የረጅም አመታት ብድር የጠየቁበት ደብዳቤ ለሚዲያ ተለቋል። የኢህአዴግ ውህደት ሰከን ብሎና የየድርጅቶቹን መተዳደሪያ ህጎች አልተከተለም በተባለና፣ የድርጅቱን መሰረታዊ ኮሚቴዎችና ሰፊ አባላት ማሳተፉ ግልፅ ባልሆነበት ሁኔታ፣ ድርጅቱ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲና ልማታዊ መንግስት መርሆው፣ “ሀገር በቀል” ነው ወደተባለው የመደመር እሳቤ በፍጥነት እንዲሸጋገር እየተደረገ ነው።  እነዚህ ሁሉ ወዴት ያመሩናል?
ከ39 ዓመታትም በኋላ ህዳር 11ቀን 1973 ዓምን አስባለሁ። ህዳር 11 ቀን የኢህዴንን መስራች ጉባኤ ጨርሰን ድርጅቱን ያወጅንበት ቀን ነበር። አያሌው ከበደ የፃፈውና ቦግን (ህላዌ ዮሴፍ) ና ክበበው ዋና ተዋናይ የነበሩበት “ሰንገደ” የተሰኘው ድንቅ ቲያትር የታየበትም ቀን ነበር። “ሰንገደ” ስሙን ያገኘው ከአሲምባ ተራራ ራቅ ብሎ ከሚገኘውና የኢህአፓ ሰራዊት ስልጠና ከሚሰጥበት በረሀ መጠሪያ ነው። በኢህአፓ ላይ ጥያቄ ያነሱ በተለያዩ ደረጃ የሚገኙ የአመራር አባላት የተገደሉበት ቦታም ሰንገደ ስለነበር ነው ደራሲው ለቲያትሩ ስሙን የመረጠው። የዛሬ 39 ዓመት ሰንገደን ስናይ ይህች የዛረፀዋ መአልት መጥታ የተቀበሩበት መሬት ከኢትዮጵያ ይለይና ይነጠል ይሆን ብለን ስጋት አልነበረንም። ዛሬ ግን የኢህአዴግ ውህደት የሚሄድበት ፍጥነትና የህወሓት ከሂደቱ ማፈንገጥ የትግራይን የመገንጠል አደጋ ይዞ ከፊታችን ተደቅኗል።
እውን ህወሓት ለመገንጠል ይደፍራልን የብዙዎች ጥያቄ ነው። እኔም የማውቃቸውን የማህበር ተጋሩ ሰዎች ጠይቄ ነበር። በወታደራዊ ረገድ በራስ መተማመን ያሳያሉ። በፋይናንስ በኩል፣ ከፌዴራል በጀት የሚያገኙት 8 ቢሊዮን ብር ቢሆንም ወደ ፌዴራል የሚልኩት 11 ቢሊዮን ብር  በመሆኑ የተጣራ ገቢያችን ይበልጣል ብለው አስልተዋል። ምናልባት የሚያሳስባቸው የኤሌክትሪክ መቋረጥ ሊሆን ይችላል። የተከዜ ግድብና የሃይል ማመንጫው ያን ችግር እንዲቀርፍ ለማድረግ ያደረጉት ዝግጅት እምብዛም አይታወቅም። የኢትዮጵያ መሥራች የሆነው የትግራይ ህዝብ ሥነልቦናስ መገንጠሉን ይፈቅድላቸው ይሆን ለሚለው ጥያቄም የስነ ህዝብ መልስ ሰምቻለሁ። 70 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ከ35 አመት እድሜ በታች በመሆኑና የህወሓት እድሜ 45 አመት በመሆኑ፣ የህዝቡ አብዛኛው ቁጥር በህወሓት ፖለቲካ ተኮትኩቶ ያደገ በመሆኑ ኢትዮጵያዊስሜቱ ደካማ በመሆኑ የሥነልቦና ችግር አይኖረውም የሚል አመለካከት አለ።
ዋነኛው ጥያቄ ግን ዶክተር አቢይ የትግራይን መገንጠል ይፈቅዳሉ ወይ የሚለው ነው። ህገመንግስቱን ለመለወጥ ያላቸው ዳተኝነትና የፈቃደኝነት ማነስ በነበረው ከቀጠለ፣ ህወሓት አንቀፅ 39ን ተጠቅሞ የመገንጠል ሪፍሬንደም ሊጠይቅ ይችላል። ህወሓት ከመጠየቁ በፊት አቢይ አንቀፅ 39ን ማሻሻል ይችሉ ይሆን? አሁን ያለውን ፓርላማ ተጠቅመው ህገመንግስታዊ ማሻሻያ እንዳያደርጉ የሚያግዳቸው ማነው?
ጃዋር በኦሮሚያ ፖለቲካ ውስጥ፣ በተለይ በኢስላሚክ ኦሮሚያ ፖለቲካ ውስጠ  ያለው ተሰሚነት ወይም የበላይነት ጠቅላይ ሚኒስትሩን የህገመንግስታዊ ማሻሻያ ከማድረግ ያግዳቸዋል የሚል ግምት አለ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጃዋርን ነገር ምን ማድረግ ይችላሉ? ወደሃገር ቤት እንዳይገባ መከልከል ይችላሉን ብለው የሚጠይቁ አሉ? መከልከል ቢችሉስ ተመራጭ ነውን የሚለው ደግሞ የኔ ጥያቄ ነው። በዚህ የድህረ መረጃ የመጠቀ ቴክኖሎጂ ዘመን፣ በተለይ በኮሙኒኬሽን በኩል ያለው እድገት አለምን ወደ መንደርነት ቀይሯታል። እንደ እውነቱ ከሆነ ከአንድ የአዲስ አበባ ነዋሪ የዋሽንግተን ዲሲ ነዋሪ ስለኢትዮጵያ የበለጠ መረጃ አለው። በነፃ ሃገር ላይ ስለሚኖርም የበለጠ በነፃ ማሰብ ይችላል። ይህንንም ነፃነቱን ለእኩይ ተግባር ለመጠቀም ከወሰነ የበለጠም ሊጎዳ ይችላል። ስለሆነም እንኳንስ የቄሮ በይነመረብ (ኔትወርክ) ያለውን ጃዋር፣ በስልኩ ቪዲዮ ላይቭ (በአካል) የሚጎተጉተውን የማህበራዊ ሚዲያ ሰው እንኳ ከማራቅ ማቅረብ የተሻለው ስልት ይመስለኛል። ስለሆነም ጃዋርን እንዳይገባ ማገድ የበለጠ ይጎዳል የሚል ግምት አለኝ። ታዲያ ምን ማድረግ ይሻል ይሆን? የጨነቀ ነገር ነው።
ዶክተር አቢይና የተቀረው የኢህአዴግ አመራር ምንን ታሳቢ ቢያደርጉ ይሆን ይህን የፓርቲ ውህደትና የግንቦት ምርጫ የሚያጣድፉት? ከአሁን በኋላ በአዲስ የተደራጀው የብልፅግና ፓርቲ በኦሮሚያ ክልል ተወዳድሮ ያሸንፋልን? እንዲሁ በደምሳሳው ሳየው ወለጋን ኦነግ፣ ባሌ፣ አርሲና ሐረርን ጃዋር (ወይም እሱ የባረከው ፓርቲ)፣ ሸዋን እነ ዶክተር መረራ ያሸንፋሉ ብዬ ስገምት፣ ለብልፅግና የሚቀረው ጅማና ኢሉአባቦራ ብቻ ይመስላሉ።ይህ ግምት ተቀራራቢ ከሆነ፣ ኦሮሞ ክልል ላይ የተሸነፈው  ብልፅግና በሌሎች ክልሎች ያሸንፋል ብሎ ማሰብ ይቻላልን?
አሁንም የእኔ ምክር ልክ አዲስ አበባ በገባሁ በሳምንቱ ነሀሴ 16 ቀን 2011 እንደመከርኩት፣ ብሄራዊ እርቅ ይቅደም፣ የሽግግር ፍትህ ይዘግይ (የታሰሩት የሜቴክ መሪዎችና የጥረት አመራሮች ይፈቱ)፣ የፓርቲው ውህደት ይዘግይ፣ የህገመንግስት ማሻሻያ ውይይት ይጀመር፣ የግንቦት ምርጫ ለአንድ አመት ይዘግይ፣ ህወሓት የችግሩ ብቻ ሳይሆን የመፍትሄውም አካል ይደረግ። አድዋን አስገንጥለን ኢትዮጵያ አለች ማለት አይቻለንምና ህዳር 11ቀን ከደረስንበት የገደል አፋፍ ወደኋላ እናፈግፍግ። ለሁላችንም ልቦና ይስጠን!
Filed in: Amharic