ያሬድ ሀይለማርያም
አዲስ አበባን እና ዋሽንግተን ዲሲን!
ታከለ ኡማን እና Muriel Bowser!
እስክንድር እና ጃዋርን እያሰብኩ!
—-
ይህን ትዝብት በምጽፍበት ሰዓት ሁለት ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ግለሰቦች፤ እስክንድር ነጋ እና ጃዋር መሀመድ በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ በተለያየ አዳራሽ ግን በተመሳሳይ ሰዓት ደጋፊዎቻቸውን ሰብስበው እያወያዩ ነው። የሰው ልጅ ነጻነት የሚከበርባት ዋሽንግተን ዲሲ ሁለቱን ግለሰቦች እኩል እያስተናገደች ነው። ሁለቱም ደጋፊዎቻቸውን ያለ ምንም ችግር ሰብስበው ባሻቸው ጉዳይ እየመከሩ ነው።
በተቃራኒው ሁለቱን ግለሰቦች የራሳቸን የሆነችው መዲናችን አዲስ አበባ እኩል ልታስተናግዳቸው ሲያቅታት በተደጋጋሚ አስተውለናል። ጃዋር ባሻው ስፍራ፣ ባሻው ቀን፣ ባሻው ሰዓት አዲስ አበባ ውስጥ ሰልፍ፣ አድማ፣ ስብሰባ፣ ገንዘብ የማሰባሰብ ሥራ ማከናውን ይችላል። ተከብቢያለው ብሎ አገር አንቀጥቅጥ፣ ሕዝብ አጫራሽ ንቅናቄ መፍጠር እንደሚችልም አሳይቶናል። በተቃራኒው እስክንድ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት፣ ስብሰባ ማካሄድ፣ የተቃውሞ ሰልፍ ማካሄድ እንደማይችልም በግላጭ አይተናል። በመደራጀቱም ዛቻ እና ማስፈራሪያ ከጠቅላዩ እስከ ከንቲባው ተሰንዝሮበታል።
የዋሽንግተን ዲሲዋን ከንቲባ Muriel Bowser አዲስ አበባ ጋብዘው አገር ሲያስጎበኙ የነበሩት፣ በእንግዳዋ ስም መንገድ እና አደባባይ የሰየሙት ም/ክ ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ከዚህ ምን ይማሩ ይሆን? መቼ ነው ከሌላው አለም ስልጣኔን ከእነ ነፍሱ የምንኮርጀው? ወግ ወጉን እየያዝን ስልጣኔን፣ ዲሞክራሲን፣ ፍትሕን እና የመብት ጉዳይን ነፍሱን እዛው ትተን ቀፎውን ብቻ ወደ አገራችን የምናስገባውስ ለምን ይሆን? ለማንኛውም በዋሽንግተን ከተማ ስም መንገድ እና አደባባይ ከመሰየም ለፍትሕ፣ ለዕኩልነት፣ ለነጻነት እና ለሰብአዊ መብት ከልብ ብንሠራ እና አውልት ብናቆም አለም ከደረሰበት እንደርሳለን።