>
5:14 pm - Tuesday April 20, 8951

ላወቀበት በ514 ቃላት ትልቅ መጽሐፍ መጻፍም ይቻላል! (ይነጋል በላቸው)

ላወቀበት በ514 ቃላት ትልቅ መጽሐፍ መጻፍም ይቻላል!

ይነጋል በላቸው ከአዲስ አበባ

ብሶትህ ሲበዛ ተናግረህ ወይም ጽፈሕ የሚወጣልህና የሚያልቅልህም አይመስልህም፡፡ ብዙ በማተት የልብን ሁሉ አውጥቶ መናገር የሚቻል የሚመስለን እኔን መሰል የዋሆች እጅግ በርካታ ነን – ነገር በመደጋገምና ቅጽሎችን በማብዛታችን ሳቢያ ጠላታችንን ድባቅ የመታን የሚመስለን ጸሐፊዎች በርግጥም ጥቂቶች አይደለንም፡፡ በዛሬዋ የድረገጽ ዳሰሳየ ያገኘኋት ጽሑፍ ግን ብዙ አስተምራኛለችና እኔም በጥቂት ቃላት ብዙ መናገር እንደሚቻል በዚህች ማስታወሻ ጠቁሜ ታናናሾቼን “ላስተምር”፡፡ ከጊዜያችን የሩጫዎች መብዛት አኳያ በርግጥም ጸሐፊዎች ወደዚህ ደረጃ መምጣት አለባቸው፡፡ ባጭር መጻፍ ውጤታማ ነው፡፡

ይህች ዛሬ ከኢትዮሪፈረንስ ድረገፅ ላይ አግኝቼ ያነበብኳት ዮሐንስ አያሌው በሚል ጸሐፊ የተከተበች አጭር ጽሑፍ በመጽሐፍ መልክ ቢጻፍ በሽዎች ገፆች የማያልቀውን የአቦይ ስብሃት ኢምፓየር በ514 ቃላት ብቻ ዕጥር ምጥን ባለ ሁኔታ አቅርባ ሳነባት የኔ የዘመናት የብዙ ገፆች ድካም አሳዘነኝ፤ እውነቴን ነው ይህችን ጽሑፍ አንብቤ ስጨርስ ቢቸግረኝ ርዕሷንና አድራሻዋን በብጫቂ ወረቀት ላይ አስፍሬ ለአንድ ብርቱ ሥራ ላይ ለነበረ ወንድሜ ሰጠሁት – ከሥራ በኋላ እንዲያነባት ብዬ፡፡ የዘመኑ ሰው ጊዜ የለውም፡፡ ትግስት የለውም፡፡ ሥልቹ ነው፡፡ ረጃጅም ጽሑፎችን ለማንበብም ፍላጎት የለውም፤ በኑሮና በልዩ ልዩ የሃሳብ ውጣ ውረድ ስለሚባዝንና በብዙ ፍላጎቶችና ህልሞች መካከልም ተሰንቅሮ ስለሚናውዝ አንድ ነገር ላይ የማተኮር ዝንባሌው በእጅጉ ሳስቷል፡፡ … የቅርብ ጓደኞቼ  እነዚህን ችግሮች እያነሱ እኔም ስጽፍ ነገሬን ባጭር ባጭሩ እንዳደርግ – በዘመኑ አገላለጽ በቶሎ ወደ ገደለው እንድገባ – ይመክሩኝ ነበር፡፡ እኔ ግን ካልዘበዘብኩ የምነበብ እንዳይመስለኝ የተዞረብኝ ይመስል ብዙ ቆላና ደጋዎችን እረግጥ ነበር፡፡ ይህች ጽሑፍ ግን በሚገባ አስተማረችኝ፡፡ ጸሐፊውንም በዚህ አጋጣሚ ባመሰግን ደስ ይለኛል፤ ድረ-ገፆችንም ጭምር፡፡ በየትኛውም ዕድሜ ለመማር የሚያስችለንን አእምሯዊ ዝግጁነትና ፈቃደኝነት እንዲሁም ልበ-ክፍትነት ፈጣሪ ያድለን፡፡ ሀገራችንን ከተጣባት የ“ከኔ በላይ ዐዋቂ ለሣር!” መጥፎ ጠባይም ይገላግለን፡፡ ሰው እስኪሞት ተማሪ ነው፤ ይህችን ሚጢጢ ‹ኑዛዜየን› በአወንታዊነት ተረዱልኝ፡፡ …

ለማንኛውም ያንን ግሩም የዮሐንስ አያሌውን ጽሑፍ በቀጣዩ ርዕስና አድራሻ ፈልጋችሁ አንብቡልኝ – የኔ ግብዣ ነው፡፡ ዋና መልእክቴ ግን ልክ እንደዚህ ጸሐፊ በጥቂት ቃላት ብዙ መናገር የሚቻል መሆኑን ለማስታወስ ነው፡፡

ሀገራችንን ጠላቶቿ ከደገሱላት የመከራ ድግስ ፈጣሪያችን ይታደጋት፡፡

 

ስለ አቦይ ስብሃት ማንነት ልንገራችሁ

ዮሐንስ አያሌው https://www.ethioreference.com/archives/19951

 

 

Filed in: Amharic