>
11:22 am - Sunday December 4, 2022

ዐብይና አብን፡ ክርስቲያን ታደለን ለምን? (መስፍን አረጋ)

ዐብይና አብን፡ ክርስቲያን ታደለን ለምን?

 

መስፍን አረጋ

 

የኦነጉ ጌታቸው አሰፋ (ወንጀለኛው ብርሃኑ ፀጋየ) የአብኑን ክርስቲያን ታደለ መፈንቅለ መንግስት በተሰኘ ቧልት ወንጅሎታል፡፡  ለምን?

የባሕርዳሩን ጭፍጨፋ ማን እንደፈጸመው ለማወቅ የሚያስፈልገው የነጥቦችን አዝማሚያ መስመር (trend line) አስምሮ መስመሩን የመዘንደብ (የማርዘም፣ extrapolate) ችሎታ ብቻ ነው፡፡  ፈረንጆቹ ገጥምጥም መረጃ (circumstantial evidence) በማለት እስከሞት በሚያስቀጣ ወንጀል የሚወነጅሉትና የሚፈርዱትም ይህንኑ ዘዴ በመጠቀም ነው፡፡  

የባሕርዳሩ ክስተት ሲዘነደብ በቀጥታ የሚያመራው ወደ ማንም ሳይሆን ክስተቱ ከመፈጸሙ ከጥቂት ቀናት በፊት ደሴ ከተማ ላይ ጀነራል አሳምነውንና የጀነራል አሳምነውን ፖለቲካዊ መሪወች (ዲባቶ አምባቸው፣  አዘዘ ዋሴ ወዘተ.) በተዛዋሪ አነጋገር ወደ ወነጀለው ወደ ዐብይ አህመድ ነው፡፡ የዐብይ አህመድ ወንጀላበር (የወንጀል ተባባሪ፣ accompalice) ማን ሊሆን ይችላል ብሎ ለሚጠይቅ ደግሞ መጠይቁ በቀጥታ የሚያመራው ወደ ግንቦት ሰባት/ኢዜማ ነው፡፡  

በመጀመርያ የግንቦት ሰባትን ወንጀላበርነት እናጢን፡፡  የአንዳርጋቸው ኢዜማ በትረ ስልጣን ለመጨበጥ ያቀደው በዜግነት ፖለቲካ ነው፣ ያለው አማራጭ ይሄውና ይሄው ብቻ ነውና፡፡  ከጦቢያ ትላልቅ ብሔረሰቦች (አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ሱማሌ) ውስጥ ከሞላ ጎደል ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በዜግነት ፖለቲካ የሚያምነው ደግሞ አማራ ብቻ ነው፡፡  ስለዚህም ኢዜማ ስልጣን ለመያዝ የሚችለው ያብዛኛውን አማራ ድምጽ ማግኘት ከቻለ ብቻ ነው፡፡  

አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እስከተቀናቀነው ድረስ ግን ኢዜማ ያማራን ድምጽ አብዛኛውን ቀርቶ ጥቂትም እንደማያገኝ ግልጽ ነው፡፡  ስለዚህም ኢዜማ በምርጫ ያሸንፍ ዘንድ አብን የግድ መፈራረስ አለበት ማለት ነው፡፡ አብንን ማፈራረስ የሚቻለው ደግሞ በሁለት ርምጃወች ነው፡፡  

አንደኛው ርምጃ አማራ የለም በሚል ትርክት የአብንን አማራዊ መሠረት ለዘላለሙ መናድ ነው፡፡  ሁለተኛውና አስቸኳዩ እርምጃ ደግሞ ላማራነታቸው ቀናኢ የሆኑትን የአማራ ከፍተኛ አመራሮች ከተቻለ በመግደል ካልተቻለ ደግሞ በማሰር ባፋጣኝ ከጨዋታ ውጭ ማድረግ ነው፡፡  ዐብይ አህመድ እነ ጀነራል አሳምነውና ዲባቶ አምባቸውን ባሕርዳር ላይ በመጨፍጨፍ፣ ጭፍጨፋውን አሳቦ ደግሞ የአብን አመራሮች ከያካባቢው እየለቃቀመ በማሰር ለፈጸመው ከፍተኛ ወንጀል ዋናው ወንጀላበር ግንቦት ሰባት/ኢዜማ የሚሆንበትም (የሆነበትም) ምክኒያት ይሄው ነው፡፡  የምፀቶች ሁሉ ምፀት (irony) ደግሞ አስጨፍጫፊው ግንቦት ሰባት በቀንደኛ ዐባሎቹ በነ አበረ አዳሙ አማካኝነት የጭፍጨፋው መርማሪ መሆኑ ነው፡፡  

አንዳርጋቸውና ብርሃኑ የሂወታቸው አሌፍና ፓሌፍ (alpha and omega) ስልጣንና ስልጣን ብቻ የሆነ ቀንደኛ ኢሕአፔወች እንደነበሩ መዘንጋት የለብንም፡፡  እነዚህ ግለሰቦች የኖሩትም፣ የሚኖሩትም፣ የገደሉትም፣ የሚሞቱትም ለስልጣንና ለስልጣን ብቻ ነው፡፡  በነዚህ ሰወች ዘንድ ለስልጣን ሲባል እንኳን ተቀናቃኝን የገዛ ቤተሰብን መግደል፣ ምሁራንን መረሸን፣ ወጣቶችን ማስጨፍጨፍ፣ ሕጻናትን መማገድ፣ ዓላማን የሚያሳካ የውሸት ትርክት መፍጠር፣ አገር ማስገንጠል፣ ካገር ጠላት ጋር መመሳጠርና መተባበር፣ በጀርባ መውጋት፣ በማጅራት ማረድ የተፈቀዱ ብቻ ሳይሆኑ ግዴታወችም ናቸው፡፡  

ባጭሩ ለመናገር ብርሃኑ፣ አንዳርጋቸውና መሰሎቻቸው የስልጣን ጥም በሽተኞች ናቸው፡፡  የኦሮሞን በሞጋሳና በጉዲፈቻ የተደገፈ በጭፍጨፋ የመስፋፋት ታሪክ ችላ ብሎ አያቱ በኦሮምኛ ስለተሰየሙ ብቻ ኦሮሞ ናቸው እያለ፣ አማራ የለም የሚል ግለሰብ ጤነኛ ሊሆን አይችልም፡፡  በነገራችን ላይ አንዳነድ ቅን አሳቢ ጦቢያውያን በእናት፣ ባባት፣ ወይም ባያት ኦሮሞ ነኝ በማለት ጦቢያዊነት የሚወገርበትን ዱላ ለኦነጋውያን ከማቀበላቸው በፊት በኦሮሞ የተሰየመ ሁሉ ኦሮሞ ወይም የኦሮሞ እንዳልሆነ አድምቀው ሊያሰምሩበት ይገባል፡፡   ጎጃሜና ላኮመልዜ ይቅሩና ወለጌና አሩሲም ከቦረኔ ኦሮሞ ጋር የደም ቤተሰብ የመሆናቸው እድል እጅግ የመነመነ ነው፡፡       

ያዲሳባውን ባላደራ በተመለከተ ደግሞ ዲባቶ ብርሃኑ ነጋ ‹‹ባላደራ ምናምን› በማለት የተሳለቀበት፣ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የእስክንድርና የጃዋር የግል ጉዳይ አስመስሎ ለማቃለል የፈለገበት፣ የግንቦት ሰባቱ ኢሳት ደግሞ እስክንድርን በጀዋር ቀለም ለመቀባት የሞከረበት ምክኒያት ሌላ ምንም ሳይሆን የስልጣን ጥማት ነው፡፡  ግንቦት ሰባት/ኢዜማ ያማራን ሕዝብ ድጋፍ ሊያገኝ የሚችለው አብንን ቢችል በማፍረስ ባይችል በማዳከም ሌላ አማራጭ በማሳጣት ብቻ እንደሆነ ሁሉ፣ ያዴሳቤን ድጋፍ ሊያገኝ የሚችለውም ባልደራስን ቢችል በማፍረስ ባይችል በማዳከም ብቻ ነው፡፡  

ባልደራስ ወደ ፖለቲካ ፓርቲ ይቀየርብኝ ይሆናል የሚለው ስጋቱ ደግሞ ግንቦት ሰባትን የሚሆነውን አሳጥቶታል፡፡  የኢሳቱ ፋሲል የኔዓለም ባልደራስን ከበረከት ስምኦን ጋር ለማጎዳኘት ሲንዘባዘብ የታዘበ ሰው፣ ግንቦት ሰባት/ኢዜማ የስልጣን ጥማቱን ለማርካት የማይቆፍረው ጉድጓድ፣ የማይፈነቅለው ዲንጋይ፣ የማይሄደው ርቀት፣ የማይፈጥረው ትርክት እንደሌለ በግልጽ ይገነዘባል፡፡  

በነገራችን ላይ ቄሮ የተሰኘው ቅዱስ የኦሮምኛ ቃላችን ኢንተራሃምዌ ከተሰኘው የሁቱ ቃል ጋር ታኩሎ (በእኩል ዓይን ታይቶ፣ equate) ውጉዝ ሆነብን የሚሉ ኦሮሞወች፣ ማውገዝ ያለባቸው ቃሉን ለሽብር በመጠቀም ያረከሱትን ጃዋር ሙሐምድንና መሰሎቹን እንጅ የሽብሩ ሰለባ የሆኑትን ጦቢያውያንን በተለይም ደግሞ ባልደራስንና እስክንድርን አይደለም፡፡  የቃሉ በእኩይ መተርጎም የኦነጋውያን እንጅ የባልደራስ ችግር አይደለም፡፡ ጃዋርና መሰሎቹ ቃሉን ለሽብር መጠቀማቸውን እስካላቆሙ ድረስ፣ የሽብሩ ሰለባወች ደግሞ ቃሉን ከኢትራሃምዌ ጋር ማጎዳኘታቸውን የሚያቆሙበት ምክንያት የለም፣ ማቆምም የለባቸውም፡፡  ይህ ሐቅ የሚያንቀው ሕቅ ይበል፡፡  የመለማመጥ ትርፉ መከራን ማራዘም ነው፡፡   

አሁን ደግሞ ወደ ዋናው ወንጀለኛ ወደ ዐብይ አህመድ እንምጣ፡፡  ዐብይ አህመድ የኦነግን ዓላማ በማሳካት የኦሮሞን የበላይነት በአልኦሮሞ ጦቢያውያን ላይ ለመጫን ቆርጦ የተነሳ ቀንደኛ ኦነጋዊ ነው፡፡  በዚህ ላይ ምንም ጥርጣሬ ሊገባን አይገባም፡፡ ይህን በጦቢያ ፍረስራሽ ላይ የኦሮሚያን አጼጌ (empire) ለመገንባት ቆርጦ የተነሳ ፀረጦቢያ ግለሰብ አደገኛ የሚያደርገው ደግሞ ወደድንም ጠላንም ልናደንቅለት የሚገባን ጮሌነቱ ነው፡፡  ጮሌነቱ ደግሞ አማራ ለጦቢያና ለጦቢያዊነት ያለውን ስስ ልብ በደንብ በመረዳት፣ በማራኪ ንግግር ልቡን ሰውሮ እኩይ ድርጊቱን እንዳያይ፣ ካየም አይቶ እንዳላየ ችላ እንዲል ማድረግ ነው፣ ልብ ካለየ ዓይን አያይምና፡፡ 

ዐብይ አህመድ (እንዲሁም ለማ መገርሳ) በትክክል እንደተገነዘበው የኦነግ ዓላማ ሊሳካ የሚችለው በአክራሪ ኦሮሞ ጥንካሬ ሳይሆን ባማራ ድክመት ነው፡፡  ጦቢያዊነት ያለ አማራ፣ አማራ ያለ ጦቢያዊነት አይታሰቡም፡፡  ጦቢያዊነት የሚጠነክረው አማራ ሲጠነክር፣ አማራ የሚጠነክረው ጦቢያዊነት ሲጠነክር ነው፡፡  ስለዚህም የአማራ ብሔርተኝነት ጠንካራ እስከሆነ ድረስ የኦነጋውያን ህልም በህልምነቱ እንደሚቀር ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡  ዐብይ አህመድን የሚያሰጋው እስካፍንጫው የታጠቀው ወያኔያዊ ወይም ኦነጋዊ ብሔርተኝነት ሳይሆን፣ ብዕረኛው የአማራ ብሔርተኝነት ብቻ የሆነበትም ይሄው ነው፡፡   

ስለዚህም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ለስልጣን ጥመኛው ግንቦት ሰባት ስልጣን አደናቃፊ እንደሆነበት ሁሉ፣ ለኦነጉ ሕልመኛ ዐብይ አህመድ ደግሞ ህልም አጨናጋፊ ነው ማለት ነው፡፡  የባሕርዳሩ ጭፍጨፋና ጭፍጨፋውን የተከተለው አፈሳ በግንቦት ሰባትና በዐብይ አህመድ (ኦዴፓ) ትብብርና ቅንብር የተፈጸመ ከፍተኛ ወንጀል የሚሆንበትም (የሆነበትም) ምክኒያት ይሄውና ይሄው ብቻ ነው፡፡ 

ይህ ድምዳሜ ደግሞ የሚከተለውን መሠረታዊ ጥያቄ ያስነሳል፡፡  ግንቦት ሰባትና ዐብይ አህመድ (ኦዴፓ) ምንና ምን ናቸው? የግንቦት ሰባት ዓላማ ዐብይ አህመድን ተጠቅሞ የአማራን ብሔርተኝነት አዳክሞ ስልጣን መጨበጥ ነው፡፡  የዐብይ አህመድ (ኦዴፓ) ዐላማ ደግሞ ግንቦት ሰባትን ተጠቅሞ የአማራን ብሔርተኝነት አዳክሞ አነጋዊ ህልሙን እውን ማድረግ ነው፡፡ ስለዚህም የግንቦት ሰባትና የዐብይ አህመድ (ኦደፓ) የሁለቱም የጋራ ጠላታቸው የአማራ ብሔርተኝነት ቢሆንም፣ ዓላማወቻቸው ግን ሐራምባና ቆቦ ወይም እንጦጦና የረር ናቸው ማለት ነው፡፡  የድብብቆሽ ጨዋታቸውም አንዱ ሌላውን ከተጠቀመበት በኋላ እንደ አሮጌ ቁና ወርውሮ መጣል ነው፡፡ 

የአማራ ብሔርተኝነት በተለይም ደግሞ አብን የግንቦት ሰባትና የዐብይ አህመድ (ኦነግ) የሁለቱም የጋራ ጠላት እንደሆነ አይተናል፡፡  የአብን ሐምሹር (ሞተር፣ motor) ደግሞ ክርስቲያን ታደለ ነው፡፡  ስለዚህም ክርስቲያን ታደለን ማሰር ማለት በከፍተኛ ፍጥነት እየገሰገሰ በጠና የታመመቸውን ጦቢያን ወደ ሐኪምቤት እየወሰደ የነበረውን አምቡላንስ ለጊዜውም ቢሆን ማስቆም ማለት ነው፡፡  የግንቦት ሰባት (ኢዜማ) እና የዐብይ አህመድ እቅድ ደግሞ አንቡላንሷ በቆመችበት ተገትራ የምትቆይበትን ጊዜ (አንዱ የስልጣን ጥሙን፣ ሌለው የጎጠኝነት አራራውን እስከሚያረካ ድረስ) በተቻለ መጠን ማራዘም ነው፡፡  አቶ ክርስቲያን ታደለ መፈንቅለ መንግስት በተሰኘ ቧልት የተወነጀለውም በዚህና በዚህ ምክኒያት ብቻ ነው፡፡ የአብን ሊቀመንበር ዲባቶ ደሳለኝ ጫኔ ‹‹የታሰሩት አመራሮቻችን የሚፈቱት በፍርድ ቤት ሳይሆን በፖለቲካ ውሳኔ ነው›› ያለው ይህን እውነታ በዲፕሎማሲዊ አገላለጽ ለመግለጽ ነው፡፡  ቀንደኛው የሕግ ቀበኛ ዐቃቤ ሕግ ከሆነበት የዐብይ አህመድ ኦነጋዊ መንግስት ፍትህን መጠበቅ ከእባብ እንቁላል እርግብን መጠበቅ ነው፡፡     

በመጨረሻም የሚከተለውን ልበልና ልጨርስ፡፡  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኦሮሚያ በሚባለው አርቲፊሻል ክልል ውስጥ የሚከሰቱት ክስተቶች፣ ዐብይ አህመድ በአማራ ብሔርተኝነት ላይ እየፈጸመ ያለውን ጥቃት ይበልጥ እንዲያጠናክር እያስገደዱት መጥተዋል፡፡  ምክኒያቱ ደግሞ የሚከተለው ነው፡፡

በቲም ለማና በቲም ጃዋር መካከል የስልት እንጅ የዓላማ ልዩነት የለም፡፡  የሁለቱም ቲሞች ዓላማ በጦቢያ ፍርስራሽ ላይ የኦሮሚያን አጼጌ (empire) በመመሥረት የኦሮሞን የበላይነት በአልኦሮሞ ጦቢያውያን ላይ መጫን ነው፡፡  ቲም ለማ ዓላማውን ለማሳከት ያለመው አማራን (ስለሆነም ጦቢያዊነትን) በማዳከም ሲሆን፣ ቲም ጀዋር ደግሞ የኦሮሞ አክራሪነትን በማጠናከር ነው፡፡  የኦነግ ዓላማ ሊሳካ የሚችለው ግን በአማራ ድክመት እንጅ በአክራሪ ኦሮሞ ጥንካሬ አይደለም፡፡ የኦሮሞ አክራሪ መጠናር የኦነግን ዓላማ ለማሳካት ከእገዛ ያለፈ አይፈይድም፡፡ 

ስለዚህም ጦቢያ ለተጋረጠባት የህልውና አደጋ ቁልፉ አደገኛ ቡድን ቲም ለማ እንጅ ቲም ጃዋር አይደለም፡፡  ዐብይ አህመድና ለማ መገርሳ የወያኔን ፖለቲካዊ ሤራ በወያኔ ጉምቱወች እየተጋቱ ያደጉ ሤረኞች በመሆናቸው፣ እነሱን መታገል ከፍተኛ ብልህነትን ይጠይቃል፡፡  በሌላ በኩል ግን አፈስዱ ጃዋር ሙሐመድ አሳቡን አስቀድሞ ስለሚለፍፍ፣ ማድረግ የሚያስፈልገው ተዘጋጅቶ መጠባበቅ ብቻ ነው፡፡

የኦነግ ፀረጦቢያ ዓላማ የሚሳካው በቲም ለማ መሠሪ አካሄድ ሳይሆን በቲም ጃዋር አክራሪ አካሄድ የሚመስላቸው ጥሬ ኦነጋውያ፣  የአማራን ብሔርተኝነት በማዳከም ወደ ተራራ ያወጣቸውን የቲም ለማን መንገድ እየተው፣ የአማራን ብሔርተኝነት በመቆስቆስ ወደ መቀመቅ የሚያወርዳቸውን የቲም ጃዋርን መንገድ በስፋት ተያይዘውታል፡፡  ይህ ማለት ደግሞ ዐብይ አህመድ በኦነግ ተደግፎ የኦነግን ዓላማ የማሳካት እድሉ ከሞላ ጎደል ከሽፏል ማለት ነው፡፡ 

 ስለዚህም ዐብይ አህመድ የስልጣን እድሜውን በማራዘም የህይወቱ ተልዕኮ የሆነውን ኦነጋዊ አላማውን ማሳካት የሚችለው አብንን አዳክሞ የአማራውን ሕዝብ አማራጭ በማሳጣት በአማራው ሕዝብ እስከተደገፈ ድረስ ብቻ ነው፡፡  የብልጽግና ፓርት ዓላማም ይሄና ይሄ ብቻ ነው፡፡ በሌላ አባባል ብልጽግና ፓርቲ ማለት ዐብይ አህመድ ያለ ኦነጋውያን ድጋፍ የኦነጋውያንን ዓላማ የሚያስፈጽምበት ፓርቲ ማለት ነው፡፡ ይህ ጮሌ ፀረጦቢያ ግለሰብ አንዴ ያሳሳተን ኃጢያቱ በሱ ቢሆንም፣ ሁለቴ ቢደግም ግን ጥፋቱ የኛ ነው፡፡          

Email: mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic