>
3:03 am - Saturday December 10, 2022

በሁለት ጦር እየተወጋ ያለው አብይ...!!!   (መስከረም አበራ)

በሁለት ጦር እየተወጋ ያለው አብይ…!!! 

 መስከረም አበራ
አንድ ቀን ከአንድ ወዳጄ ጋር በስልክ እናወራለን፡፡ ጥሩ ግንዛቤ ያለው ሰው ነው፡፡ ከሃገር አቀፍ እስከ ዓለም አቀፍ ፖለቲካ፣ ታሪክ፣ርዕዮተ-ዓለማዊ ጭብጦችን ጠብሰቅ አድርጎ የሚረዳ ሰው ነው፡፡አልፎ አልፎ የምንደዋወል ቢሆንም የተደዋወልን ጊዜ ረዥም ሰዓት እናዎራን፤ከወሬያችን እኔ ብዙ አተርፋለሁ፡፡
 አንድ ቀን እንደተለመደው ስናወራ የገደል አፋፍ ላይ የቆመች ስለምትመስለኝ ሃገሬ ያለኝን ስጋት አነሳሁለት፤”ምን ማድረግ ይሻላል፤አይናችን ስር ሃገራችን ተና ስትጠፋ እንደዋዛ ልናይ ነውኮ!” አልኩኝ፡፡ “ሃገርሽን ትወጃለሽ አውቃለሁ፤ግን ሳታውቂው የምትፈሪውን የሃገር መፍረስ የሚያግዝ ነገር እየሰራሽ እንደሆነ አታውቂም፤ትገርሙኛላችሁ!” አለኝ ትዝብት ባዘለ ድምፅ፡፡ ደነገጥኩ ! “እኔ ሃገር  እንድትፈርስ? ጠጥተሃል እንዴ?” አልኩኝ፤ “ከጠጣሁ አንድ አመት ከስድስት ወር ሆነኝ” አለኝ በቀልድ፡፡
“ፅሁፎችሽን አነባለሁ፤አዝናለሁም፤አብይን “Discredit” በማድረግ ሃገር ለማዳን የምትሰሩ የሚመስላችሁ ነገር ግርም ይለኛል ፤እንዳልናገርሽ የማሰብ ነፃነትሽን መጋፋት ስለሚመስለኝ ነው እያዘንኩ ዝም የምለው” አለኝ፡፡”አልገባኝም በአይኔ ከማየው ውጭ ያልተደረገ ነገር ፈጥሬ ዶ/ር አብይንም ሆነ ሌላ አካል ወቅሼ አላውቅም፤ ምን እያልከኝ እንደሆነ አልገባኝም” አልኩኝ፡፡
“የውልሽ የምታይውን ነገር ተንተርሰሽ እንደምትፅፊ አውቃለሁ፡፡ ችግሩ ያለው ለምታይው ጥፋት እንች ምክንያት  ነው ብለሽ የምታስቢው ነገር ትክክለኛው ምክንያት አመሆኑ ነው፡፡ አንች የምታስቢው ጥፋቱ ሁሉ የመጣው ከዶ/ር አብይ አስተዳደራዊ ድክመት፣ችልታ፣አንዳንዴም የኦሮሞ ብሄርተኝት ዝንባሌ እና አድሎ አድርገሽ ነው፡፡ እውነታው ግን ሌላ ነው፡፡ እኔ በቅርብ የማውቅ ሰው ነኝ፤የእኔን የነባራዊ ሁኔታ ግምገማ ግንዛቤ ብዙ የምትጠራጠሪ አይመስለኝም፡፡ እውነታው ሌላ ነው፡፡ ብዙ ዝርዝር ነገር አልነግርሽም ግን እመኝኝ አብይ መደገፍ አለበት፤በአብይ ላይ የምትወረውሩት ድንጋይ እንወዳታለን የምትሏትን ሃገር ከቆመችበት አፋፍ ወደ ገደል ይወረውራል እንጅ ጥቅም የለውም፡፡ እሱ በሁለት ጦር እየተወጋ ያለ ሰው ነው፡፡ እንደዛም ሆኖ ከማናችሁም ያላነሰ ሃገሩን ይወዳል፤ሲቃ እየተናነቀው ስለ ኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ሲናገር የሰማሁት ከአስር አመት በፊት ነው፡፡ የማይሆን ነገር አልነግርሽም ብታምኝኝና ሃገርን ወደ ገደል መግፋቱን ብታቆሚ ጥሩነው አለኝ” እዝን ባለ ድምፅ፡፡
“መንግስት ባለበት ሃገር ህዝብ ሲሞት ስፈናቀል፣እንዲህ ሲሆን እንዲያ ሲሆን ዝምበይ ነው የምትለኝ” በንዴት ጠየቅኩ፡፡ “እሱስ ቢሆን ኢትዮጵያን ከወደደ ለምን እንዲህ እና እንዲያ ያደርጋል፤ለምን እንዲህ ብሎ ተናገረ” ብየ የበኩሌን ተከራከርኩ፡፡ብዙ አስረዳኝ፤ጥቂት በጣም ጽቂት ለዘብ አልኩ፡፡”የኔ ዝም ማለት ሃገር የሚያድን ከሆነ ዘላለም ዝም ለማለት ዝግጁ ነኝ” አልኩ፡፡”ዝም በይ እያልኩ እንዳልሆነ ታውቂያለሽ፤በመፃፍሽ የምታግዥው ነገር እንዳለ ግልፅ ነው፡፡ መፍትሄው ዝም ማለት ሳይሆን ስትፅፊ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መንገድ ይሁን፤እናንተ ዛሬውኑ ያድርግ የምትሉትን ነገር ማድረግ እየፈለገ የማይችልበት ነገርም እንዳለ ተረጅ፤ከሁሉም በላይ አብይ የሚያደርገው ማንኛውም እርምጃ ሃገር ለማዳን አንጅ ለማንም ተረኝነት ወይም የበላይነት አይደለም፤ከኢትዮጵያዊ ለይቶ ሊጎዳው ወይም ሊጠቅመው የሚፈልገው ህዝብ እንደሌለ በተረዳ መንገድ ስህተቶቹን ብትጠቁሚ መፃፍሽ ለምትፈልጊው የኢትዮጵያ ህልውና ያግዛል” ሲለኝ እኔ የማውጠነጥነው “ሃገር ወደ ገደል እየገፋሽ ነው!” የሚለውን አስደንጋጭ ቃል ነበር፡፡
የሆነ ሆኖ ይህ ወዳጄ ከሚነግረኝ ብዙ ነገር ባሻገር የራሴ ልቦና የሚነግረኝ የዶ/ር አብይ በጎ ጎኖች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ኢትዮጵያን መውደዱ ነው፡፡ ሁለተኛው ሰው ሰው የሚለው ማንነቱ ነው፡፡አብይ ሰው ነው! ሲናደድ ይታወቅበታል፣ያጠፋ ሲመስለው በግልፅ ይቅርታ ይጠይቃል፣ለመማር ዝግጁ ነው፡፡ለሃገሩ ይቀናል፤በተለይ የፖለቲካ ባህል ለውጥ ለማምጣት የሚሞክረው ነገር የምደሰትበት ነው፡፡ሰው ነውና የሚጠፋው ነገርም ይኖራል::
ያላወቅኩለት በኦዴፓ ውስጥ የነበረበትን ፈተና ነው፡፡ ወዳጄ “ብዙ ነገር አልነግርሽም ግን እሱ በሁለት ጦር የሚወጋ ሰው ነው፤አንዱ ጦር የእናንተ ኢትዮጵያን እንወዳለን የምትሉ ሰዎች ብልሃት ጎደለው ትችት ነው ሌላውን ጊዜው ሲደርስ እነግርሻለሁ” ያለኝ ነገር ዛሬ ገብቶኛል፡፡ አብይ በኦዴፓ ውስጥ የነበረበት ፈተና እኛ ከምንገምተው እጅግ የተለቀ እንደ ነበረ በዚህ ሁለት ቀን ውስጥ ተረድቻሁ፡፡አቶ ለማ ባፈነገጠበት ሁኔታ ለኦሮሞ ብሄርተኞች ኢትዮጵያን ስለማዳን፣ስለ ሲቪክ ፖለቲካ ተናግሮ፣ አሳምኖ በሙሉ ድምፅ የህብረ-ብሄራዊ ፓርቲ አባላት አንዲሆኑ ማድረግ ትልቅ ፈተና ነው፡፡ይህን ማሳካት ቀርቶ መሞከር ከባድ ነው፡፡
በበኩሌ አቶ ለማ የዶ/ር አብይ ቀኝ እጅ ሆኖ የሚሰራ ይመስለኝ ነበር፡፡ በኦዴፓ ውስጥ ያለውን የአክራሪነት ስሜት የሚፋለሙትም አብረው ይመስለኝ ነበር፡፡የለማ አጋርነት ለዶ/ር አብይ ትልቅ ካፒታል እንደሆነ ይሰማኝ ነበር፡፡ ለካ ነገሩ በተቃራኒው ነው፡፡ የለማ ከአብይ የመደመር እሳቤ በተቃራኒው መቆም ለአብይ እረፍት የማይሰጥ ሾተላይ ሆኖ ሳለ ይህን ተቋቁሞ በኦዴፓ ውስጥ ቀርቶ በእኛ ውስጥ የነገሰውን አቶ ለማን በሃሳብ ማሸነፍ ትልቅ ብርታት የሚጠይቅ ነገር ነው፡፡ በበኩሌ በጣም ተገርሜያለሁ….! ጠ/ሚው በአንድ ወቅት “እኛ እውነት ነው የያዝነውና እናሸንፋለን” ያሉት ስሜት የተቀላቀለበት ንግግራቸው ምን ማለት እንደሆነ አሁን ገብቶኛል፡፡ አብይ የሚስቱት ነገር ይኖራል፤በዛ ከእኔ የበለጠ አብጠርጥሮ የሚተቻቸው የለም፡፡ ይህን ወደፊትም የምቀጥልበት ነገር ነው፡፡
አብይ በኦሮሞ ብሄርተኝነት ቤት ውስጥ ሆኖ ኢትዮጵያን  የማዳን እዳ ተሸክመው የከፈሉትን ዋጋ በትልቅ ክብር በልቤ የምይዘው ነገር ነው! ለዚህ ትልቅ አክብሮት አለኝ፤ምስጋናም ጭምር፡፡ በኦሮሞ ብሄርተኝነት ቤት ሆነው የማይቻለውን ሃገራዊ ራዕይ ለማሳካት መሞከራቸው፤ሞክረውም የስኬት በር ላይ መድረሳቸው እኔ ብሆን የማልችለው ስለሆነ በብዙ ተገርሜያለሁ፡፡መንግስት ብቻ ሳይሆን ሃገር ለመሆን እየሞከረው የነበረው የኢህአዴግ ድርጅቶች ውህደት ለሃገሬ መቀጠል ወሳኝ ነገር እንደሆነ አጥብቄ አምናለሁ፤ይህ ለምን እንደሆነ ከሰሞኑ በማስነብበው አርቲክል እዳስሰዋለሁ፡፡
ከአስቸጋሪው ጋር ተፋልመው ኢትዮጵያን ለማዳን ለሰሩት ሁሉ አብይ መመስገን አለባቸው፤የመነጠልን ስብከት እምቢ ብለው የአብይን የመደመር መንገድ ለመከተል የወሰኑ የኦዴፓ መኳንንትም መመስገን አለባቸው፡፡
    መጭው ዘመን የተሻለ እንዲሆንልን ምኞቴም፣ፀሎቴም ነው!
Filed in: Amharic