>

"የቶሎሳ_ነገር!!!" (ወሰን ሰገድ ገ/ኪዳን)

“የቶሎሳ—ነገር!!!”

ወሰን ሰገድ ገ/ኪዳን
 
የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ ሊቀመንበር አቶ ቶሎሳ ተስፋዬ፣ በመቀሌው የፌዴራሊስቶች ስብሰባ ላይ “እኛ ህወሓትን ፍለጋ እዚህ የመጣነው እውነታው መቐለ ስላለ ነው! አሁን አራት ኪሎ የቀልድ የፌዝ ሆኗል!!!” አለ ፦ አሉ። አልገረመኝም። “መሸጥ የለመደ ….” እንዲሉ።
በመጀመሪያ
“ኦብኮ” ዶ/ር መረራ የሚመሩት ፓርቲ ነበር፡፡ ቶሎሳ ደግሞ ስራ አስፈፃሚ አባል፡፡ አንድ ቀን ቶሎሳ ከድንኳን ሰባሪው ኢሕአዴግ ጋር ተሻረከ፡፡ እናም በ97 ምርጫ ሰሞን የኦብኮን ቢሮ ሰብሮ ገባ፡፡ ከዚህ በኋላ የኦብኮ ሊቀመንበር እኔ ነኝ አለ፡፡ እነ ዶ/ር መራራን (በሽጉጥ ጭምር) አባረረ፡፡ በቃ እኔ ነኝ ኦብኮ አለ፡፡ ከጀርባው ያለውን ኢህአዴግ ተማምኖ ፎገላ፡፡ እነ ዶ/ር መረራ የሚችሉትን ያህል ታገሉ፡፡ አልቻሉም፡፡ ኦብኮ የሚለውን ስያሜ ትተው፣ በኦፌኮ ተክተው ትግላቸውን ቀጠሉ፡፡
ቶሎሳ ኦብኮን ይዞ በአይዞህ ባዮቹ ድጋፍ ፓርላማ ገባ። ጌቶቹን ተማምኖ ወደ ዝርፊያ ገባ። ወደ መሬት ዝርፊያ። ይቺ ጨዋታ ግን በጌቶቹ አልተወደደችለትም። ከግብረ አበሩ ጋር ተከሰሰ።
.
በ2001 ዓመተ ምህረት የምክር ቤት አባል በነበረበት ወቅት፤  ከአቶ ቦና ታደሰ ጋር በመሆን በ15 የግል ተበዳዮች ላይ ወንጀል ፈጽሟል ተብሎ ነበር የተከሠሰው።
የክስ ቻርጁ፦ “አቶ ቶሎሳ የምክር ቤት አባል ስለሆንኩኝ ባለኝ የሕዝብ ትውውቅ መሠረት በትርፍ ጊዜዬ እየሠራሁ መሬት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ አሰጣችኋለሁ፤›› በማለት፣ ከ15 ግለሰቦች ላይ በሁለት ጊዜ ክፍያ ከእያንዳንዳቸው 60 ሺሕ ብር በድምሩ 900 ሺሕ ብር ወስደዋል” ይላል ።
አቶ ቶሎሳ ተበዳዮቹን ያታለሉት፣ አቶ ቦና በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መሆናቸውን በመግለጽ፣ በአካል በማስተዋወቅና ለእያንዳንዳቸው 200 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው መሬት እንደሚሰጧቸው ገልጸው፣ ሐሰተኛ ሰነድ (ፎርጅድ ደረሰኝ) በመስጠት መሆኑን፤ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ የመሠረተውን ክስ የጠቀሰው የሪፖርተር ዘገባ ያመለክታከል።
 3 
የሆነ ሆኖ “ለውጥ” መጣ። እነ ዶ/ር አቢይ ወደ ስልጣን መጡ። ቶሎሳም እንደ እባብ ቆዳውን ገልብጦ ተከሰተ። በአንዳፍታ የ”ኦዴፓ” አወዳሽ ሆኖ ተከሰተ። ይህንን በተመለከተ አብነት ይሆነን ዘንድ ከ”አዲስ አድማስ” ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ካደረገው ቃለ ምልልስ እንቀጭብ፦
• ከገዥው ፓርቲ ኦህዴድ/ኦዴፓ ጋር ለመዋሃድ እንዴት ውሳኔ ላይ ደረሳችሁ?
✔እንደሚታወቀው ላለፉት 22 ዓመታት ኦህዴድ/ኦዴፓን ስንቃወም ቆይተናል፡፡ በተለይም እስከ 2008 ዓ.ም ድረስ የህዝብን ጥያቄ ሳይቀበል የቀረ ድርጅት በመሆኑ አምርረን ስንቃወመው የነበረ ድርጅት ነው። ባለፉት ጥቂት ዓመታት የኦሮሞ ህዝብ ባደረገው ያላሰለሰ ትግል፣ በከፍተኛ መስዋዕትነት በኦህዴድ ውስጥ ለውጥ መጥቷል፡፡ ይሄን ለውጥ ያመጡት ደግሞ የ“ቲም ለማ” አባላት ናቸው፡፡ የህዝቡን ጥያቄ ሙሉ ለሙሉ በመቀበል ከኦሮሞ ህዝብ ጎን በመቆም የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ እነ ዶ/ር ዐቢይ የሄዱበት ቆራጥነት የተሞላበት የመስዋዕትነት ጉዞ ለውጥ በመምጣቱ፣ ይሄ ለውጥም ወደ አማራ ክልልም ተሻግሮ ወደ ህዝቡ ልብ ውስጥ በመግባቱ፣ በአጠቃላይ በሃገሪቱ የምንፈልገው ለውጥ መጥቷል ብለን እናምናለን። ስለዚህ ኦዴፓን መቃወም አላስፈለገንም፡፡ ስለዚህ ተቀላቅለን አብረን ቀጣዩን ትግል መግፋት እንችላለን በማለት ነው ውሳኔውን ያሳለፍነው፡፡ አሁን የቲም ለማ አመራር የህዝብ ጥያቄ ይመልሳል የሚል ሙሉ እምነት አለን፡፡ በዚህ አይነት ሁኔታ በመሃከላችን ያለው ልዩነት ጠቧል ብለን ባሰብን ሰአት ከኦዴፓ ጋር ለመዋሃድ በጉባኤ ወስነናል፡፡ ከኦዴፓ ጋር ለመቀላቀል የሚያግደን የመስመርም የአቋምም ልዩነት የለንም የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰናል፡፡
አሁን ደግሞ ቶሎሳ መቀሌ ከትሟል። የስብሰባው ዋና አስተባባሪነት “ሹመት” ተቀዳጅቶ በስሙ ደብዳቤ በትኗል። ደብዳቤ መበተን ብቻ አይደለም፤ የኦዴፓን እና የአነ ዶ/ር አቢይን “ብፅዕና” በወሸከተበት አፉ “እኛ ህወሓትን ፍለጋ እዚህ የመጣነው እውነታው መቐለ ስላለ ነው። አሁን አራት ኪሎ የቀልድ የፌዝ ሆኗል።
የህዝቡን ትግል መንገድ ላይ የቀሙት ኃይሎች ህገመንግስቱን ቁራጭ ቀሻሻ ወረቀት ነው አይወክለንም ብለው በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት በቤተ መንግስት ውስጥ መናገር በመጀመራቸው ነው ችግር እየተፈጠረ ያለው።” አለ፦ አሉ። “መሸጥ የለመደ” ፖለቲከኛ ይኸው ነው።  እንደው ግን ሰው ስንት ጊዜ ነው ሕሊናውን የሚሸጠው?! የኢትዮጵያ ሕዝብስ እንደ ቶሎሳ፤ አየለ ጫሚሶ እና መሳፍንት የመሳሰሉ ህሊና ቢስ ፖለቲከኞች እስከመቼ ነው ተሸክሞ ነው የሚኖረው!? ሕዝብ መንግስትን የሚቆጣውን ያህል እነዚህን ታሪካቸው የቆሸሸ ተቃዋሚዎችን የማይቆጣበት፤ “በቃችሁ” የማይልበት አንጀት ያጣው ለምንድነው ?!
Filed in: Amharic