>
12:38 am - Wednesday July 6, 2022

የጃዋር “ቄሮ”፣ ባልደረቦቹና ባለሥልጣናት በአሸባሪነት እንዲፈረጁ ተመድ የቀረበለትን ክስና ማስረጃ ተቀበለ!

የጃዋር “ቄሮ”፣ ባልደረቦቹና ባለሥልጣናት በአሸባሪነት እንዲፈረጁ ተመድ የቀረበለትን ክስና ማስረጃ ተቀበለ!!!

ሙሉአለም ገ.መድህን
“ግድያ ከተፈጸመ በኋላ አስከሬኖችን ለመቀጣጫ ተጠቅመዋል” አሉ ፕሮፌሰር ጌታቸው። ሲያስረዱም “ገድለው የሰውነትን ክፍል በመበጣጠስ ሜዳ ላይ ጥለዋል። ይህ የሆነው አንተም እንዲህ ትሆናለህ፣ ለቀህ ጥፋ፣ ሂድ፣ የሚል የመቀጣጫ ማሳያ ለመጠቀም ሲባል ነው። ይህንን ያዩ፣ የፈሩ ቤተክርስቲያን ተሸሸጉ፣ ጫካ ውስጥ ተጠለሉ። ወደ ማይታወቅ ቦታ አመለጡ”።
ይህ የተባለው ትግሉን አጠናቆ ወደ ቤቱ የገባውና አደረጃጀት የሌለው መስዋዕትነት የከፈለውን ቄሮ ሳይሆን በጃዋር መሃመድ የሚመራ፣ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያዘዋውር፣ የተደራጀ፣ ትዕዛዝ አመንጪ ያለው፣ አዛዥና የዕዝ ሠንሠለት ያለው፣ የማዘዣ ኮማንድ የተበጀለት … የጥፋት ኃይል በአሸባሪነት እንዲፈረጅ ጥያቄ በቀረበበት ወቅት ነው።
በማስረጃ ተደግፎ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ክስ የቀረበበት ይህ ኃይል በአሸባሪነት እንዲፈረጅና ዓለም ይህ ድርጅት ምስራቅ አፍሪቃን ሳያተራምስ እንዲከስም አስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጥበት፣ ጉዳዩ አሳሳቢና ጊዜ የማይሰጥ መሆኑንን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ለተመድ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ተጠሪዎች ማብራራቱን ይፋ አድርጓል።
ከመረጃ ቲቪ ባልደረባ ጋር ቃለ ምልልስ ያካሄዱት ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌና እስክንድር ነጋ እንዳሉት የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ለቀረበለት ጥያቄ ቀና የሚባል መልስ ሰጥቷል። ከቀረበለት ማስረጃ በተጨማሪ ጉዳዩን በራሳቸው አግባብ እንደሚያጣሩና አስቸኳይ ምላሽ እንደሚሰጥ ማስታወቁን ገልጠዋል።
በኢትዮጵያ ተመድ ያስቀመጣቸው የጄኖሳይድ ጥቃት ስለመኖሩ ማስረጃ፣ ሰለባዎች በማንና እንዴት እንደተጠቁ በሰነድና በመረጃ መቅረቡን ያመለከተው እስክንድር የአልሸባብ፣ የሙጃሂድና የአልቃይዳን አፈጣጠር ለምሳሌነት መነሳቱን ጠቁሟል።
የተመድ ባለሥልጣናት ስማቸው እንዳይጠቀስ በማስገንዘብ ጉዳዩን በውል እንደሚያዩት ፕሮፌሰር ጌታቸው ተናግረዋል።
ከተመድ ጋር የተደረገው ውይይት ኢትዮጵያውያን በዋሽንግቶን ዲሲ ተወያተው ያሳለፉት ውሳኔ አካል እንደሆነ ያስታወሰው እስክንድር፣ ጃዋር የሚመራው ቄሮ የፈጸመውን የዘር ማጽዳት ወንጀል የሚያጣራ ግብረኃይል መቋቋሙንና ይህም ግብረኃይል ተጨማሪ መረጃዎችን በማሰባሰብ ለባለሥልጣናቱ ተጨማሪ ግብዓት እንደሚያቀርብ ጠቁሟል።
“ጤናማ ቄሮ አለ፣ ጽንፈኛ ቄሮ አለ። ጤማዎቹ ትግላቸውን ጨርሰው ወደ ቤታቸው ገብተዋል” ሲል ማብራሪያውን የሰጠው እስክንድር፣ አሁን በጽንፈኛነት የተሰማራው ኃይል ድርጊቱን ሲፈጽም “ቄሮ ነኝ” እያለ ራሱን በመግለጽ በመሆኑ በሌላ ስም ሊጠራ እንደማይችል አመልክቷል። መሪውም ጃዋር መሆኑንና ከመንግሥት እና (ከፓርቲ) መዋቅር ውስጥም ተባባሪ እንዳላቸው አክሏል።
ፕሮፌስር ጌታቸው እንዳሉት ይህ ኃይል የራሱ ሚዲያ ያለውና የጥፋት ጥሪውን በዚሁ ሚዲያው እንደሚያሰራጭ፣ ባለቤቱም የዚሁ ኃይል መሪ እንደሆነ ጠቁመዋል። ይህንንም በማስረጃ ማቅረባቸውን ይፋ አድርገዋል። ይህንን የገለጹት ከተመድ ባለሥልጣናት ለቀረበ ጥያቄ ሲመለሱ እንደሆነም አመልክተዋል።
ጃዋር መሀመድ “ያ – ቄሮ” በማለት መመሪያ እንደሚሰጥ ሕዝብ በተደጋጋሚ ያየው ሃቅ ሲሆን፣ በሲዳማ የደረሰው ቀውስ እየተፋፋመ በተለይ ቡና ጃዋር መመሪያ ይሰጥ እንደነበር ጎልጉል ምንጮቹን ጠቅሶ መዘገቡ የሚታወስ ነው። ጃዋር ራሱን ሰላማዊ ታጋይ አድርጎ ያቅርብ እንጂ ሬዲዮ፣ ሁለት የቴሌቪዥን ጣቢያ፣ ጋዜጦች፣ መጽሄቶችና በርካታ የማኅበራዊ ሚዲያ ሠራዊት ያለው አካል መሆኑ ይታወቃል። መንግሥትን በአንድ ቀን የመገልበጥ አቅም ያለው እንደሆንም በአደባባይ የሚናገር ከመሆኑ በላይ ከመከላከያ ሚኒስትር ለማ መገርሳ ጋር በጥምረት እንደሚሠራ መረጃዎች አሉ።
ከጽንፈኛው ቄሮ ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ስማቸው የማይነሳው አቶ በቀለ ገርባ በቄሮ አደረጃጀት ውስጥ (መሪም ናቸው ይባላል) ወሳኝ ቦታ እንዳላቸው የመረጃ ሰዎች ለውጡ በተጋጋለበት ወቅት ምስክርነት ሲሰጡ እንደነበር፣ ከለውጡም በኋላ ከጃዋር ጋር ይፋዊ አጋር መሆናቸውና በቅጽበት፣ በሚታይ ሁኔታ ወደ ጽንፈኛነት መቀየራቸው ደግሞ የዚሁ የጽንፈኛ ቡድን ቁንጮ መሆናቸውን የሚያመሳክር እንደሆነ ለጉዳዩ የሚቀርቡ የሚናገሩት የአደባባይ ምሥጢር ነው።
ይህንን ጽሁፍ እስከምናትተምናበት ድረስ ከተከሳሾቹ ወገን የተባለ ነገር የለም። ዜናውን የሰሙ አካላት ግን የተለያይ ስሜት እያንጸባረቁ ነው። ተመድ አምኖ ጊዜያዊ እርምጃ ከወሰደ በእነ ጃዋር ዙሪያ ባሉ አካላት ላይ የጉዞ ገደብ ሊጥል ይችላል፤ ገንዘባቸውም እንዲታገድ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።
Filed in: Amharic