>

ህውሃት የብልፅግና ፓርቲን ተቀላቀለም አልተቀላቀለ የትግራይ ህዝብ ከኢትዮጵያዊነቱ ንቅንቅ ሊል አይችልም! (አምዶም ገብረሥላሴ)

ህውሃት የብልፅግና ፓርቲን ተቀላቀለም አልተቀላቀለ የትግራይ ህዝብ ከኢትዮጵያዊነቱ ንቅንቅ ሊል አይችልም!

አምዶም ገብረሥላሴ
የትግራይ ህዝብ ላለፉት 40 ዓመት በላይ በህውሃት የአፈና ስርዓት ምክኒያት በርካታ ፍላጎቶቹን ተነፍጎ ሐሳቡንና ጥያቄውን አደባባይ ይዞ እንዳይወጣና ሐሳቡን እንዳያንሸራሽር ሲታፈንና ሲጨቆን የኖረ ህዝብ ነው።በተለይም በክልሉ የሚገኙ የተለያየ ማንነት ያላቸው ብሔረሰቦች መብትና ጥቅማቸውን ለማስከበር በሀገሪቱ ህገመንግስት ያገኙትን እድል ሳይቀር በሐይል ተነጥቀው አፈና ፣ ጭቆና ፤ እስርና እንግልት ሲፈጸምባቸው ከመዋል አልተላቀቁም።  ጥያቄ አለን ብለው አደባባይ ለመውጣት የሚሞክሩ ዜጎች ለእስርና ለእንግልት እየተዳረጉ ይገኛሉ።
የፌራሊዝም ስርዓት ብቸኛ መስራችና ጠበቃ ነኝ የሚለው ህውሃት በክልሉ ውስጥ የሚገኙ የተለያየ ማንነት ያላቸውን ብሔረሰቦች ፍላጎት ፣ መብትና ጥቅም እንኳ ከማፈን አልተላቀቀም። የእንደርታና የኩናማ ብሔረሰቦችን የማንነት ጥያቄ በሐይል ያፈነ ድርጅት ራሱን የፌድራሊዝም ስርዓት ጠበቃ አድርጎ ሊቆም አይቻልም።ህውሓት በሀገሪቱ እየተከናወነ ያለ ሪፎርም። ህገ መንግስቱና የፌዴራል ስርዓቱን ተጥሷል ፤ በውህደቱን አልቀላቀልም ቢልም የትግራይ ህዝብ በኢትዮጵያዊነቱ አይደራደርም። ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ህዝቦች ጋርም አይነጠልም።የፌድራሊዝም ስርዓቱ በስልጣን ላይ ላሉ ቡድኖች ለማስሰል የዘረጉ እንጂ እውነተኛ ፌድራሊዝም አልነበረም።
እውነተኛ ቢሆን ኖሮ አገሪቱ አሁን ላጋጠማት ውስብስብ ችግር አትጋለጥም ነበር። መንስኤ በማስመሰል ላይ የተመሠረተው የህውሃት አፈናና የውሸት ፌድራሊዝም ስርዓቱ የወለደው ነው።
ከችግሩ የማይማረው ህውሓት ዛሬም የትግራይን ህዝብ ከኢትዮጲያዊያን ወንድም ህዝቦቹ ጋር ለመነጠል ራሱን ፌድራሊዝም ስርዓት ጠበቃ አድርጎ የሐሰት ፕሮፖጋንዳው ሲያናፍስ ይውላል። የፓርቲዎች ውህደት እና የብልፅግና ፓርቲ ሀገሪቱን ወደ አህዳዊ ስርዓት ሊመልስ የሚችል ነው በሚል የአስመሳይነት ገጸ ባህርይ ይዞ በራሱ ሚዲያዎች ሲተውን ይውላል።
ነገር ግን ህውሓት የብልፅግና ፓርቲን ተቀላቀለም አልተቀላቀለ ለረጅም ዓመታት በአፈናና ጭቆና ስርዓት ውስጥ ያለፈው የትግራይ ህዝብ ከኢትዮጵያዊነቱ ንቅንቅ ሊል አይችልም። የትግራይ ህዝብ በህውሃት አገዛዝ እየደረሰበት ያለውን የአፈና ስርዓት ከሌሎች እትዮጲያዊያን ወገኖች ጋር በጋራ የሚታገልበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።
ኢትዮጵያዊነት ይለምልም!
Filed in: Amharic