>
8:55 am - Saturday November 26, 2022

አፄ ዮሃንስ እና የጎጃም አማራ!!! (ሙሉአለም ገ/መድህን)

አፄ ዮሃንስ እና የጎጃም አማራ!!!

ሙሉአለም ገ/መድህን
ከሰሞኑ ህወሃታውያን መቀሌ ላይ የፌክ ፌዴራሊስቶችን ሰብስበው ዳግማዊ አፄ ምኒልክን ሲረግሙ ሰንብተዋል። ስለሃያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን የፌዴራሊዝም ፅንሰ ሃሳብና ገቢራዊ ሃቲት ለማውራት ምኒልክን መርገሙ ምን አመጣው?
መግፍዔው ግልፅ ነው ሰዎቹ ዛሬም በማይበርድ የአማራ ጥላቻ ውስጥ ይገኛሉ።  መድረኩ ያስረገጠልን ሃቅ ይሄንን ነው ። የምኒልክን የግዛት አንድነት ዘመቻዎች የብቻ ክስተት አድርገው አንድን ትልቅ ሕዝብ [አማራን] ነጥለው በጠላትነት እንዲታይ ያልሄዱበት ርቀት የለም ።
እስቲ አፄ ዮሃንስ በጎጃም አማሮች ላይ የነበረውን  ዘመቻና ያደረሰውን ሰብዓዊ ፍጅት ወረድ ብለን እናስታውስ:-
አጼ ዮሐንስ የጎጃሙን ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት “ከምኒልክ ጋር አደመብኝ” በሚል ለራሱ እንኳን ኋላ ላይ ሲያስበው የዘገነነውን እልቂት በጎጃም አማሮች ላይ ፈጽሟል፡፡
አጼ ዮሐንስ የቅጣት ሰይፉን መዞ ፊቱን ወደ ጎጃም ሲያዞር የጎጃም ሰው፡-
“በላይኛዉ ጌታ በባልንጀራዎ
በቅዱስ ሚካኤል በባልንጀራዎ
በጽላተ ሙሴ በነጭ አበዛዎ
ጎጃምን ይማሩት ፈሪም አንልዎ
የሚል ተማጽኖ ቢያሰማም ከመዐቱ አልተረፈም፡፡ አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ “አጤ ምኒልክ” በሚለው መጽሃፉ “የትግሬ ወታደር ቄሱን ተበተስኪያን፣ ገበሬውን ከዱሩ፣ ነጋዴውን ተመደብሩ እያወጣ ጨረሰው (ገጽ፣ 54)”፤ “ጎጃምን የመሰለ ደግ አገርም ሦስት ወር ሙሉ በትግሬ አንበጣ ተደመደመ” (ገጽ፣52) በሚል በወቅቱ የደረሰውን እልቂትና ውድመት ይገልጸዋል፡፡
 አጼ ዮሃንስ ለራስ ዳርጌ በጻፈው ደብዳቤ “በእኔም በድሃውም ኃጢአት እንደሆን አይታወቅም አገሩን (ጎጃምን) ሳጠፋ ከረምሁ” (ኀሩይ ወልደ ሥላሴ፤ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ከሳባ እስከ ታላቁ የአድዋ ድል፤ ገጽ 179 ) በማለት ጸጸቱን ይገልጻል፡፡ ዘመቻው ሦስት ወር የፈጀ በመሆኑ በሂደቱ የደረሱ ሰብዓዊ ፍጅቶችን ማህበራዊ ሚዲያው ላይ ዘርዝረን አንጨርሳቸውም ። በአጭሩ የዘመቻው ውጤት ራሱ አፄውን እንዲፀፅተው ያደረገ ነበር ።
ነገሥታቱ እና ዘመቻዎቻቸው
በኢትዮጵያ የነገሥታት ታሪክ በተለይም በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ሂደት ወስጥ ብዙ ሰብዓዊ ጥፋት እንደደረሰ መካድ አይቻልም፡፡ ነገሥታቱ ከሰብዓዊነት አኳያ “አለማወቅ” የሚባል ሰብዓዊ ጉድለት እንደነበረባቸዉ “ፍትሐ ነገስት”ን በማስታወስ መረዳት አይከብድም፡፡
ከሁሉ በላይ ደግሞ የነገሥታቱ ሠራዊት ይህ ነዉ የሚባል ቋሚ ደመወዝ የሌለዉ በመሆኑ ዘመቻ በወጡ ቁጥር ቅጥ ካጣ ጭካኔቸዉ ጋር የገበሬውን ንብረት መዝረፍና ማውደም የሰርክ ተግባራቸው ነበር፡፡ በዚህ መሰል አሰቃቂ ሂደት የተጨፈለቁ የማህበረሰብ ክፍሎች፤ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች መኖራቸው እሙን ነው፡፡ እንደዚህ ባሉ ዘመቻዎች የቀደሙትን ነገሥታት ገትተን የዘመናዊት ኢትዮጵያ መስራች አባቶች የሆኑት የቴዎድሮስ፣ የዮሃንስ እና የምኒልክ ሠራዊት በተፈራራቂነት በገባራቸዉ ላይ ጥፋት አድርሰዋል፡፡ በጊዜ ሂደት መጠኑ እየቀነሰ ቢሄድም ገባሮቹ በባርነት ተፈንግለዋል፡፡መሬታቸውንም ተነጥቀዋል፡፡ ባህላዊና ሰብዓዊ ክብራቸው የተረገጡም አሉ፡፡ ትልቁ ቁም ነገር የዚህን ሁሉ ግፍ መደባዊ ይዘት መረዳቱ ላይ ነው፡፡
ህወሃታውያኑ ያለጥላቻ መቆም የማይችሉ በመሆናቸው ዳግማዊ አፄ ምኒልክን የኢትዮጵያ ፖለቲካ መሠረታዊ ችግር ፈጣሪ አድርጎ ከማቅረብ ወደ ኋላ አይሉም ።
1967 የህወሃት ማኒፌስቶ ላይ
1983 የሽግግር መንግሥት ምስረታ ላይ
1987  [የማርቀቅ ሂደቱ ሳይዘነጋ] የሕገመንግሥት ሰነዱን የማፅደቅ ጉባዔ ላይ ዳግማዊ አፄ ምኒልክና የነፍጠኛው ሥርዓት ተረግመዋል ። ከቶም አገርን ከጠላት ወረራ የማዳን ዘመቻዎች ሳይቀር ተኮንነዋል።
የየትኛዉም አገር ንጉስ መላእክት አይደለም ሰዉ እንጂ ሰዉ ደግሞ አንዱን ሲያቃና አንዱ ይደፋበታል(ይህ የተፈጥሮም ህግም ነዉ) ይህን ደግሞ እኛ አማራዊያን አሳምረን እናዉቃለንና በነሱ ልክ ወርደን አፄ ዮሐንስ ጎጃምን እንዲህ አረገ ዮዲት እንዲህ ሰራች ግራኝ አህመድም አርዶናል አቃጥሎናል እያልን ጌዜ አችን ማቃጠል የለብንም ግን ጀግኖቻችን ማክበርና መዘከር ከምን ጊዜዉም በላይ ይጠበቅብናል እነሱ የምኒልክን አዉሬነት ያለመረጃ ሲቀባጥሩ እኛ የምኒልክን ቅዱስነት በመረጃ እንዘክራቸዋለን እነሱ ምኒልክ ጨፍላቂ ናቸዉ ሲሉን እኛ ለነ አባ ጅፍር፣ለነ ካዎ ጦና፣ለነ ተክለሀይማኖት፣ለነ አሉላ አባ ነጋ………አካባቢያቸዉን እንዲያስተዳድሩ የሰጣቸዉን ስልጣንና ነፃነት በመረጃ እንግታቸዋለን እንጂ ከወረዱት ጋር ወርደን ለማይጠቅመን ነገር ሙት ወቃሽ መሆን የለብንም።
ህወሃትና የሥርዓቱ የአንቀልባ ልጆች ግን ይሄው ዛሬም 2012 ላይ ምኒልክንና ማህበራዊ መሠረቱ ነው ያሉትን አማራን  ሲረግሙ እያየናቸው ነው ።
 አፄ ዮሃንስ ፃድቅ ዳግማዊ  አፄ ምኒልክ እርኩስ አድርጎ ማቅረብ የህወሃታውያኑ የ45 ዓመት  የፖለቲካ መስመር ነው። ሰዎቹ ከታሪክ ጋር መታረቅ እስካልቻሉ በዚሁ የጥፋት መስመራቸው ከመጓዝ ወደ ኋላ አይሉም❗️
የታሪክ ቅራኔ ላይ የቆመው ፌኩ የፌዴራሊስቶች ስብስብ ዳግማዊ አፄ ምኒልክን በመርገም የራሱን ሃጢያት ለመሸሽግ ያለመ ነበር ። የመቀሌውን መድረክ ከህወሃታውያኑ የታሪክ አረዳድ አንፃር ካየነው ጥላቻን የማደስ ጥልቅ ፍላጎት የታየበት ነበር ።
Filed in: Amharic