>

ዳግማዊ አጤ ምኒልክ የመልካም አስተዳደር ጉድለት ላሳዩ ሹማምንቶቻቸው የሰጡት ትዕዛዝ....(ጳውሎስ ኞኞ)

ዳግማዊ አጤ ምኒልክ የመልካም አስተዳደር ጉድለት ላሳዩ ሹማምንቶቻቸው የሰጡት ትዕዛዝ…...
አፄ ምኒልክ በመንግሥታቸው የመልካም አስተዳደር ጉድለት መኖሩን ሲሰሙ ሹማምንቶቻቸውን ተጠያቂ ያደርጉ እንደነበርና እቴጌ ጣይቱም ኅዝብን ማስተዳደር እንዴት እንደሆነ የሚቻለው ያስታወቁበት ደብዳቤ ……
አጤ ምኒልክጳውሎስ ኞኞ
ይድረስ ከራስ ቢተወደድ መንገሻ….የሜጫ፣ የዲንሳና የይልማ ሰዎች ተሰብስበው መጥተው ጮኹልኝ፤ የጮኹበትን ነገር ቃሉን እንድታየው ብዬ የሰጡኝን ደብዳቤ ይኸው ሰድጄዋለሁ፤
ነገር ግን ይፍራታና ግድም እንደጮኸ እንደለፈለፈ ተለያየን፤ በጌምድርም እንደጮኸ እንደለፈለፈ ተለያየን፤ ሳይንትም እንደዚሁ ተፈታ ደግሞ አሁን ሜጫን፣ ይልማንና ዴንሳን እንዲህ አድርገህ ታስጨንቀዋለህን? እኔስ ጋሻ ስደድልኝ ማለቴ እዚያ ሀገር ጋሻ ሰጓጅ ብዙ ነውና በጥቂት ዋጋ ይገኛል ብዬ ገዝተህ እንድትሰድልኝ ነው እንጂ ከመኳንንቱ ከባላገሩ የጋሻ ፈሰስ ጥለህ መች እስወጣልኝ አልኩህ? ነጭ ማርም ስደድልኝ ያልኩህ የእዚያ ሀገር ማር መልካም ነውና ለአንተ ከሚገባልህ መርጠህ ላክልኝ አልኩህ እንጂ ነጭ ማር ካላመጣችሁ እያልክ ደሀውን ለምን የምታስጨንቀው በምን ነገር ነው፤ የዛሬ ደሀ ላም የለው በሬ የለው ምን ጎን አለው ብለህ ነው፤ ደግሞስ አንተ የምታውቃቸው እኔ የሾምኳቸው ያሳደኳቸው፣ የፊተኞቹም የአባቴ ሹመኞች ሁሉ አለቁ ያለኸው አንድ አንተ ነህ፤ እንግዲህማ ለእኔ እድሜ ማዘን ለመንግሥትም ማዘን ነበር እንጂ እንዲህ አድርገህ ደሀውን ብታስጨንቀው ምን ትጠቀማለህ? ይሄ ሁሉ የጨዋ ልጅ፣ ሽማግሌ፣ እንግዲህ ተመልሰን ሀገራችን አንገባም የራስ መንገሻን ፊት አናይም እንደወጣን እንቀራለን ብሎ እዚህ መ’ቶ ያለቅሳል ይሄን እግዚአብሔር ይወደዋልን? “የመረረው ደሀ ይገባል ከውሃ” የሚሉት ተረት ባንተው ደረሰ፤ አሁንም ከዚህ ቀደም እንደነበሩ እንደ ጥንታቸው ይኑሩ እንጂ ቀድሞ ያልነበረውን ነገር አትንካ፤ ነገር ግን ደብዳቤም ብልክብህ፣ ብመክርህም አትሰማኝም ተመክረህም አትድንም ሁለተኛ እንዲህ ያለ ነገር የሰማው እንደሆነ መንገሻ ሙት #ማርያምን ደሃው ከወደደበት እንዲኖር አዋጅ እነግርለታለሁ።
ኅዳር 8 ቀን እንጦጦ ተፃፈ
አፄ ምኒልክ የወላይታ ኅዝብ እንዳይበደል በግል ቁጥጥራቸው ውስጥ አርገውት ነበረ ግዛቱንም በግል እንደራሴያቸው በአዛዥ ባደግ ሥር አደረጉት፤ አዛዥ ባደግ ግን ኅዝቡን እየበደሉ አስቸገሩ፤ ይህን የሰሙት ዳግማዊ ምኒልክም ለአዛዥ ባደግ የሚከተለውን ደብዳቤ ጻፉላቸው…….
የወላይታ ባላገሮች ችግራችንን ለማመልከት ወደዚህ እንዳንመጣ በየኬላው በር አስጠብቆ አስከለከለን እኛም እሄን ፈርተን በአርሲ ዞረን መጣን ሌሎቹ ግን በመንገድ ሲመጡ ተይዘው ታስረዋል፤ ብለው ጮኹልኝ፤ ጯሂ ወደዚህ ሲመጣ ለምን ይከለከላል? አሁንም ለጩኸት ወደዚህ የሚመጣ ሰው አይከልከል፤ ከዚህ ቀደም ወደዚህ ሲመጡ የታሰሩትም ሰዎች ይፈቱ፤ ነገሩንም በመጣህ ጊዜ ትነጋገራለህ፤ ግብርም ተጨመረብን ብለዋልና ከዚያው እኛ ከሠራንላቸው ከዓመቱ ግብራቸው በስተቀር ሌላ ትርፍ ግብር አይነኩ፤ ነገር ግን ለጩኸት መጥተን ወደዚያ መመለሱን ፈራን ቢሉ ይኸው ከልክሌን ዳኛ ሠጥቼ ሰድጃቸዋለሁ።
እንዲህም ቢያደርጉ የወላይታ ሹማምንት ደሃ መበደላቸውን አላቋረጡም፤ በዚህ የተናደዱት አጤ ምኒልክ የወላይታ ሹማምንቶች በኮሚቴ ራሳቸው እንዲመሩ ነሐሴ 2 ቀን 1900 ዓ.ም.
የሚከተለውን ደብዳቤ ላኩላቸው…..
ከዚህ ቀደም ወላይታ የተሾሙ ሹማምንቶች ሁሉ አላግባብ እየበደሉ ብዙ ገንዘብ እንደጠፋ የሰማችሁት ነው፤ አሁንም እናንተን መርጬ ወላይታ መሾሜ ደሃዬን እንድትጠብቁልኝ ነውና እዚያው ደንብ ካደረግነው ከዓመት ግብሩና እኔ ከማዘው ትዕዛዝ በስተቀር ሌላ በምንም በምንም ደሃው እንዳይነካ ይሁን፤ እንግዲህ ግን ከዚህ ቀደም ተሹመው እንደነበሩት ሰዎች አላግባብ አድርጋችሁ ይህን ተበደልን፣ ይህን ተበላን ብሎ ኅዝብ የጮኸልኝ እንደሆነ በገንዘባችሁ ብቻ አይደለም ብርቱ ቅጣት ትቀጣላችሁ፤ ደግሞም ከእናንተ ሹማምንቶች ውስጥ አንዱ ያላግባብ ደሃ በደለ ገንዘብ በላ ማለት የሰማችሁ እንደሆነ እናንተው ተሰብስባችሁ እሱን አስጠርታችሁ ነገሩን አይታችሁ ጨርሱ፤ እናንተ ለመጨረስ የማይመቻችሁ የሆነ እንደሆነ ግን ወደ እኔ ላኩልኝ በተረፈ ከባላገሩ በምንም በምንም አማካኝታችሁ የምትነኩት ገንዘብ የለም።
አጤ ምኒልክ እንኳ አሽከራቸውን ወዳጃቸውን ፊታውራሪ ወሮታን ትግሬዎች ቢገሉት ነገሩን እያወቁት ሀገር ይበላሻል በማለት አውቀው ተዉት፤ የሰለዋም ሰው ተስፋ አንጣሎን ቢገለው ይህንን አውቀው ነው የተዉት “ሀገር በርህራሄና በብልሃት ነው እንጂ በጭካኔ መች ይገዛል” አሁንም በብልሃት ብታደርግ ይሻላል፤
ጣይቱ ብጡል ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ ¨የዘመን ታሪክ ትዝታዬ ከአየሁትና ከሰማሁት¨ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ
Filed in: Amharic