>

"ቢያንስ እስከ ኖቤል ሽልማት ከዶክተር ዓቢይ ጎን እንቁም!!!" (ታየ ቦጋለ አረጋ - ኢልመ ደሱ ኦዳ)

“ቢያንስ እስከ ኖቤል ሽልማት ከዶክተር ዓቢይ ጎን እንቁም!!!”

ታየ ቦጋለ አረጋ (ኢልመ ደሱ ኦዳ)
የፊታችን ማክሰኞ December 10, 2019 የሀገራችን ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ አሊ (PhD) በኖርዌይ – ኦስሎ ከተማ በሀገራችን ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የኖቤል የሰላም ሽልማት ይቀበላሉ።
ይህ ታላቅ ክብር ያለ ርዕዮተ ዓለም ልዩነት የሁላችንም መድመቂያና በዓለም ፊት ክብርና ጌጣችን ነው።
አኩሪና ወርቃማ ታሪካችን ተደብቆ፤ ዓለም በረሀብ በስደት በችጋርና በክፉ ገፅታዎች የሚያውቃት ኢትዮጵያ በመሪዋ አማካይነት በመልካም ልትታወቅ እነሆ ቀኑ ደረሰ።
*
በዚህ እለት በተለያዩ ዘርፎች የኖቤል ሽልማት የሚቀበሉ የተለያዩ ፍፃሜዎች ተመራጮች በአዳራሹ ይታደማሉ። የዓለም ዐይኖች ትዕይንቱን ለመዘገብና ለመመልከት ወደ አውዱ ያማትራሉ። የተሸላሚ ሀገር ዜጎች ሀገራቸውን ለማድመቅ ሰንደቃቸውን ከፍ አድርገው ይታያሉ። እኛስ?
*
እንደ እኔ እምነት ከ200 በላይ የባህል አልባሳት ተውበን፤ እጅ ለእጅ ተያይዘን፤ ገመናችንን በውስጣችን ደብቀን፤ (መቃወም የሚፈልጉ ሌሎች አጋጣሚዎች በሽበሽ ስለሆኑና ጊዜ መስጠቱም ስለማያጎድለን ታቅበን…) እንድመቅ።
*
በዚህ ክንዋኔ ላይ የትኞቹ ፅንፈኞች ላንቃቸው እስኪቀደድ ለመጮህ እንደተዘጋጁና አሁንም በዚህ ስታተስ ስር በአማራና በኦሮሞ ስም “አዛኝ ቅቤ አንጓች” ሆነው እንደሚከሰቱ አይጠፋኝም። በርግጥ ሁልጊዜም “እኔ ከሞትሁ ሰርዶ አይብቀል” በማለት ታሪካችንን ለማጠልሸት የማያንቀላፉ – የጎን ውጋቶች ቀስፈው እንደያዙን አይጠፋችሁምና ወደ ማብራራት አላልፍም።
ባለፈው በኦሮሚያ ውስጥ በደረሰው ከሰው ገላ እስከ አብያተ ክርስቲያናት መቃጠል – ሁላችንም የልቡና ስብራት ደርሶብናል። ከማናችንም ባላነሰ ግን የዶክተር ዓቢይ ህሊና ደም በደም እንደሆነ መገመት አይከብደንም። የኖቤል ሽልማት ተሸላሚ መሆናቸው ሲሰማ – በከፍተኛ ምቀኝነት፤
• ከሀገር ይልቅ ቅጥረኝነት
• ከሀገር ይልቅ የግል ክብርና ዝና
• ከሀገር ይልቅ ጎጥ… የገነነባቸው በታቀደና በተቀነባበረ አኳኋን ሰቆቃ ፈፀሙ።
ይልቁኑ የእነሱ ጊዜ ይሻለን ነበር መቼም ላንል –  እንድንል፤ 27 ዓመቱን በጭራሽ ላንዘነጋ – ግን እንድንረሳ… ከኦህዴድ የየሥፍራው አመራሮች የዘረፉትም ጭምር –  ወደ መዘበሩት የህዝብ ሀብት እንዳናማትር  ዐይናችንን ለመጋረድ፤  ይጠብቀኛል ብሎ ከፈጣሪ ቀጥሎ ህዝብ ተዘልሎ የተቀመጠበት የፀጥታ ኃይል ሳይቀር መድህን ከመሆን ይልቅ በእነሱ አስተባባሪነት መቅሰፍት ሲሆን፤  ቃላቸው ተሰብሮ “በእሳቸው የሥልጣን ዘመን አሳዳጅና ተሳዳጅ ሲኖር” ምን ያህል እንደሚያዝኑ ለመገመት ዐይንን ጨፍኖ ማሰላሰል ብቻ ይበቃል።
 አዎ የኢትዮጵያውያን ጸሎትና የአቢቹ ትጋት ተጨምሮ – እኛ ማየት አቅቶን ያላከበርናቸውን – ዓለም በየፊናው  በሽልማቶች አጀብ እስክንል ሲያመሰግናቸው – ምክንያቱ የማናስተውለውን የሚያይ አምላክ በመኖሩ ነው።
የከፉ ወንጀሎችን ፈፃሚዎች ከሁሉም ስፍራ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደ ነው። አስፈፃሚዎችም ጊዜ ይፍጅ እንጂ ቢያንስ የፈጣሪን ፍርድ ያገኛሉ። (ያልተያዙ እኩያን – የተያዙ ንፁኃን መኖራቸውም አይጠፋኝም።) የእናቶች፣ የቤተሰብና የሀገር ደም እና ዕንባ በከንቱ ፈሶ አይቀርም። በዚህ ዙሪያ ፈጣሪ ቢፈቅድና ብንኖር የምናየው ለውጥ እንደሚኖር ቅንጣት አልጠራጠርም።
ተማፅኖዬ አንድ ነገር ነው። ለግማሽ ክፍለ ዘመን የተሠራ ሴራ፤ የደደረ የደህንነት መዋቅር፤ የተደራጀ ግዙፍ የሌብነት ተቋም፤ አንድ ትውልድ የዘለቀ የተጠና በብሔረሰቦች መሀከል መናከስ መፍጠር፤ የማያባራ የግብፅ ጠላትነትና ፔትሮ ዶላር፤ ለከርሳቸው የሚያድሩ ባንዳዎች በተሰገሰጉበት፤ ሰኞ ያመናችኋቸው ጓዶች ማክሰኞ ክህደት በሚፈፅሙበት አውድ  … የምር ለህሊናችሁ ይህ በ40ዎቹ መጀመሪያ የሚገኝ የፈጣሪ ችሮታ (God sent opportunity) ባይሆን – ይህንን ሳጥናኤል (ኢብሊስ) ደማችንን ሊያፈስ ያሰፈሰፈበት ወቅት እንደምን እናልፈው ነበር?
ለማንኛውም፦ እባካችሁ በአውሮፓ በአቅራቢያው የምትገኙ ወገኖች ጠላቶቻችን ከዳር እስከዳር ለውርደታችን ሲሰለፉ፤ እናንተ ለትንሳኤያችን በቂ ዝግጅት አድርጋችሁ በአንድነት ቆማችሁ ድጋፋችሁን ግለፁ። በዚህ ወቅት ከዶክተር ዓቢይ ጋር መቆም ከኢትዮጵያ ጋር መቆም ነው።
በተጨማሪ የጠላቶቻችንን ቅስም የሚሰብር ሀገር አንቀጥቅጥ የድጋፍ ሰልፍ – እሁድ December 15, 2019 በአዲስ አበባ አድርገን ዓለም ማንነታችንን ይመልከት።
Filed in: Amharic