>

አራቱ የኢትዮጵያ እጣፈንታዎች!!!  (ያሬድ ጥበቡ)

አራቱ የኢትዮጵያ እጣፈንታዎች!!!

 ያሬድ ጥበቡ
ዴስቲኒ በተሰኘ ፈረንጅኛ ስም የተመሰረተ ተቋም የፖለቲካ መሪዎችን ለማቀራረብ ባለፉት ስድስት ወራት ላደረጋቸው ጥረቶች በተደጋጋሚ ሲመሰግን እየሰማን ነው። ተወያዮቹ፣ ውይይቱ ውጤታማ እንዲሆን ተደርጎ የተቀረፀበትን መንገድ አድንቀዋል። የተፎካካሪ ድርጅት አባል ወይም መሪ ከሆነው ሰው ጋር ተወያይተውና ተነጋግረው እንደማያውቁና፣ የግለሰቡንም ሰብእና ይጠራጠሩ እንደነበር፣ አሁን ግን ያንን ለመቀበል የሚችሉበት እሳቤ ላይ መድረሳቸውን ነግረውናል። እውን ይህን ሳያውቁና ሳይቀበሉ ነበር እንዴ መጀመሪያውኑ የምርጫ ፖለቲካ ውስጥ የገቡት የሚል እንድትጠይቅ ያስገድዱሀል። እኔ ባየሁዋቸው ሁለት የቪዲዮ ውይይቶች የተገነዘብኩት እነሱ ባይናገሩትም በኦነግ ጨዋነትና የመወያየት አቅም፣ ስለኢትዮጵያም እጣ ፈንታ ከሌሎቹ ባላነሰ የሚጨነቅ መሆኑን በማየታቸው ብዙዎች የተደነቁ መሆኑ ነው የገባኝ።
የደረሱበት ስምምነት ተብሎ የቀረበው “የንጋት” ቢሆነኝ (ስናርዮ)፣ የዛሬ ሃያ አመት ኢትዮጵያ የምትደርስበትን ገና ከጨለማ የመውጣት ውጋገን ነው። በነርሱ እይታ እዚህ ንጋት ላይ እስከምንደርስ ሃያ ክረምቶችን የምናሳልፍበት ጨለማ እንዴት እንደምንሸከመው አልነገሩንም። ወይም ጨለማውን ለመክላት በነዚህ ሃያ ክረምቶች ምን ማድረግ እንደሚኖርብን አልተናገሩም። ጨለማው ወደ ንጋት እንደሚወስድ ምን እርግጠኛ እንዳደረጋቸውም ገና አልተናገሩም። በተከታዪቹ ቀናት የምናደምጣቸው ይሆናሉ።
በሰው ግብዣ “እንዴት እገሌን አልጋበዝክም?” ማለት ነውር ቢመስልም፣ በሃገሪቱ ላይ ትልቅ ተሰሚነት ያላቸውን ሰዎችና ድርጅቶች ቢያካትት ይበልጥ በጠቀመ ነበር ብዬ አስባለሁ። ህወሓትን፣ ጃዋርን፣ እስክንድርን፣ የርእዮቱን ቴዎድሮስን፣ አቢይን፣ የቀድሞውን ግራ ወይም ተራማጅ ወዘተ ነበር ማነጋገር የሚገባው (የቀድሞ ተራማጆች ከገቡ ምእራቡ ለውይይቱ የሚረዳ ገንዘብ አልሰጥም ሊል እምደሚችልም ታሳቢ አድርጌ ነው)። ምናልባት በጋባዦቹ ስሌት መጀመሪያ ቀለል ባለው ጀምረው፣ ወደ ወሳኙ “ግጥሚያ” በልምድ ላይ ተመስርተው ሊገቡበት አስበው ሊሆን ይችላል። ኦነግን በአውሬነት ያዩ የነበሩና የተገረሙ የዴስቲኒ ታዳሚዎች ሁሉ ፣ ጌታቸው ረዳ፣ አቢይ፣ ጃዋርና እስክንድርም ተመሳሳይ እድል ቢያገኙ ለሃገራቸው የሚጨነቁ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን የሚረዱበትና ምናልባትም የጨለማ አመታቱን ከሃያ ወደአስር ለማሳጠር ቁልፉ ተጫዋቾች መሆናቸውን ቢረዱ ጠቃሚ ይመስለኛል። የዴስቲኒው ዋና አሰናሳይ እንደነገሩን ሞዴሉ የተወሰደው ከደቡብ አፍሪካ እንደሆነና ወሳኝ ሚና የተጫወቱትም ደክለርክና ማንዴላ እንደነበሩ ሁሉ፣ ኢትዮጵያም ዋናዋ ተደራዳሪዎቿን መለየት ይኖርባታል።  ዴስቲኒ የጀመረውን መልካም ሥራ ይቀጥልበታል፣ ወሳኞቹ ተደራዳሪዎችም ነጥረው የሚወጡበትን ወንፊት ያገኛል ብዬ ማሰብ እወዳለሁ። ምን  ይመስላችኋል?
Filed in: Amharic