>
5:13 pm - Friday April 19, 1241

ዛሬም ሰለሜ ሰለሜ?!? (ያሬድ ሀይለማርያም)

ዛሬም ሰለሜ ሰለሜ?!?

ያሬድ ሀይለማርያም
የፖለቲካ መሪዎቻችን ይችን ሰለሜ ሰለሜ በሚል ሰፈን ጠምትደነሰዋን የደቡብ ዳንስ ይወዷታል። እነሱ ሁሌም ከፊት ከፊት እኛ ሁሌም ከኋላ ከኋላ። ገደል ሲገቡ አብረን፣ ቁልቁል ሲወርዱ አብረን፣ ከፍ ያሉም ቀን አብረን፣ ዝቅ ያሉም ቀን፣ የዘቀጡ ቀን አብረን፣ ሁሌም እነሱ ከፊት ከፊት እኛ ከኋላ ከኋላ። ይችን ዳንስ አቶ ኃይለማርም ደሳለኝ ሕዝቡን አሰልፈው መደነስ ቢያቅታቸው እንኳ ቤተመንግስት ውስጥ ጥቂት ሰዎችን ከኋላ አስከትለው ሰለሜን ደንሰውልናል።
እና ወዳጆቼ ምን ለማለት ነው፤ የሰለሜ ፖለቲካ ዛሬም ቅጥሏል። ዛሬም መንግስት ሰለሜ ሰለሜ ሕዝቡን እና አገሪቱን እያስደነሰ ነው። ጉዞውና መዳረሻው ግን በውል አይለይም። ትላንትና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ከኖርዌይ የኖቤል ሽልማታቸውን ተቀብለው ሲመለሱ ከቦሌ አራት ኪሎ መንገዱ ሁሉ ተዘጋግቶ ወዳጅ ደጋፊዎቻቸው ተሰልፈው እንዲቀበሏቸው ተደርጓል። ነገሩ መልካም ነው። እዛ ላይ ቅሬታ የለኝም። ነገር ግን በሥራ ቀን ያሁሉ ሺ ህዝብ፣ የመንግስት ባለሥልጣናት እና ተማሪዎች ሳይቀሩ ሥራና ትምህርት አቁመው እሳቸውን ሊቀበሉ እንዲወጡ መደረጉ አጃይብ ነው። ያ ብቻ ሳይሆን በሐሙስ ጠዋት ሰዎች ለዕለት ጉርሳቸውም ሆነ ለሌሎች ሥራዎች በሚሯሯጡበት በዚህ ሰዓት መንገድ ዘጋግቶ ሥራቸውን ማስተጓጎል እና ሳይወዱ በግድ የባዕሉ ታዳሚ እንዲሆኑ ማድረግ ምን ይሉታል?
እሳቸውን በደመቀ በሃል መቀበል ካስፈለገ ለምን ሕዝቡ ስታዲዮም ውስጥ ወይም ሌላ አንድ ሰፋ ያለ ቦታ እንዲጠብቃቸው አይደረግም? ግማሽ ቀን ሙሉ ከቦሌ እስከ አራት ኪሎ መንገድ ዘግቶ ሰለሜ ሰለሜ ምን ይሉታል? ይሄንን እሳቸውም ይፈልጉታል ብዮ አላምንም። እታች ያለው ካድሬ የሰለሜዋን ጨዋታ በደንብ ስለሚያቅባት አመል ሆኖባቸው እንጂ።
ሌላው እጅግ ያስደመመ እና ወይ አገር ወይ አገር አስብሎ ያስቆዘመኝ ነገር በአዲስ አበባ ዋና ዋና መንገዶች በየሁለት መቶ እርቀት ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፎቶ በትላልቅ የፕላስቲክ ባነሮች ተሰቅሎ መታየቱ ነው። ባለኝ መረጃ እያንዳንዱን ባነር ለማሳተም ቢያንስ ከአንድ ሺ አምስት መቶ እስከ ሁለት ሺ ብር ያስወጣል። እንግዲህ በሺዎች የሚቆጠሩትን ባነሮች ለማሳተም የወጣውን ገንዘብ ስሌት ለእናንተ እተዋለሁ።
አሁን ማን ይሙት ይህ ሁሉ ግርግር አስፈላጊ ነበር ወይ? ጠቅላያችን መሸለማቸው አስተስቶን እንኳን ደስ ያለዎት ብለናል። ዜናው እንደተሰማም በሚሊኒየም አዳራሽ ቡጊ ቡጊ ሁሉ ነበር። ተገቢም ነው። ሲመለሱም ልክ ቤተ መንግስት እንደተደረገው አይነት የእራት ግብዣ ጥሩ ነው። ይቺ በሰብ አስባቡ መንገድ እየዘጉ፣ ፎቶ እየለጠፉ ሰለሜ ሰለሜ ግን እንደ ኢትዮጵያ ያለ ድሃ አገርን አይመጥንም። ይታሰብበት ለማለት ያህል ነው።
በሉ ደግሞ ቅናት ነው ብላቸው ተሳደቡ። ከልቤ ነው። አገር በእንዲህ መልኩ አይቀጥልም።
ቸር እንሰንብት
Filed in: Amharic