>

ደጃች አያሌውንና ንጉሠነገስቱን ምን አቀያየማቸው? (ሳሚ ዮሴፍ)

ደጃች አያሌውንና ንጉሠነገስቱን ምን አቀያየማቸው?

ሳሚ ዮሴፍ
“አያሌው ሞኙ ሰው አማኙ
የአያል ጠመንጃ ስሟን እንጃ
አያሌው ለኔ ምንሽሬ ጥሩ አልቢኔ
አያሌውማ የኛ ጥሩ የኛ ዞማ
አያል ተባባል ጎፈሬውስ ያባብላል”
 
እንዲህ እየተባለ የሚዘፈንላቸው ደጃዝማች አያሌው ብሩ ማናቸው? 
እንደዚህ ተብሎ የተዘፈነላቸው ምክንያቱ ምንድነው?
ደጃዝማች አያሌው ብሩ በሃያኛው ክፍለ ዘመን ከተነሱት ኃያላን መኳንንት አንዱ ናቸው፤ የራስ ብሩ ወልደ ገብርኤል ልጅና የእትጌ ጣይቱ ዘመድ ሲሆን የወገራ አውራጃ ሹም የሰሜን አውራጃ ገዥ ልጅ እያሱ ከተያዙ በኋላ ደግሞ የንጉሠ ነገሥቱ ጦር አዛዥ ሆነው አገልግለዋል።
ደጃዝማች አያሌው ብሩ ንጉሥ ኃይለሥላሴ ወደ ሥልጣን እንዲመጡ ከፍተኛውን ሚና ከተጫወቱት ሰዎች መካከል ቀዳሚ ናቸው፤ በአምስት ዓመቱ የፋሽስት ወረራ ወቅት እሳቸውን ለማከም ሄደው በዛው ወደ ጦርነቱ የተቀላቀሉትና ቁስለኛን እስከመጨረሻው በማከም ትልቅ ጀግንነት በፈፀሙት  ዶ/ር ሀረልድ ናይስትሮም በተፃፈውና በዶ/ር ገበየሁ ተፈሪና ደስአለኝ አለሙ በተተረጎመው የተደበቀው ማስታወሻ ላይ እስከመጨረሻው አጠገባቸው የነበሩት ዶ/ር ሀረልድ ስለ ደጃዝማች አያሌው ከራሳቸው ከደጃዝማቹ አንደበት የሰሙትንና በዓይናቸው ያዩትን እንደዚህ አስፍረውታል…….
“….የመጀመርያው አውሮፕላን በታየችበት ቀን መሀመድ ኢማም የሚባል ሰው መጣ፤ በጣም ሀብታም አረብ ነው፤ በኤርትራ በሚኖሩ ጣልያኖች ዘንድ የተከበረ ሲሆን በእስልምና አማኞች ዘንድ ደግሞ ታላቅ ተሰሚነት ነበረው፤ ምክንያቱም የራሳቸው የነቢዩ መሀመድ የትውልድ ሀረግ ስለነበረው ነው፤ በደጃች አያሌው ግዛት ውስጥ በንግድ ሥራ ምክንያት ከደጃች አያሌው ጋር ትውውቅና ወዳጅነትም ነበረው።
ከአራት ቀናት በፊት ስለሰውየው መምጣት ሁለት የቴሌግራም መልእክቶች ስለደረሱን አመጣጡ እንግዳ አልሆነብንም፤ አንደኛው ቴሌግራም ከአዲስ አበባ ሰውየው ወደ ደጃዝማች ካምፕ እንደሚመጣ የሚገልፅ ነው፤ ” እንግዲህ ንጉሡ በሚስጥራዊ መንገድ በሰሜን በኩል የሚሆነውን ነገር እንደሚያውቁ ለማሳወቅም ይመስላል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ንጉሡና መንግሥታቸው በደጃች አያሌው ላይ ሙሉ እምነት እንደሌላቸው ሆኖ ደጃች አያሌው የሚያደርጉትን ነገር በቅርብ እንደሚከታተሉ ለማሳወቅም ነውና
የዚህን ሰውዬ መምጣት  አዲስ አበባ እንዲታወቅ ያደረገው የደጃዝማች አያሌው የራሳቸው የጦር መኮንን የድንበር ጠባቂዎች አዛዥ የሆነው ቀኛዝማች መንግሥቱ ከንጉሡ ብዙ ብር ተከፍሎት አለቃውን እየሰለለ ነበር፤ የቴሌግራም ሠራተኛው ደግሞ እንደሰማሁት ከሆነ በደጃች አያሌው እየተከፈለው ለሁለቱም ወገን በመሰለል ሥራ ላይ ስለነበር የንጉሡ ሰላይ ቀኛዝማች መንግሥቱ የመሀመድ ኢማምን መምጣት በቴሌግራም ወደ አዲስ አበባ እንዲያስተላልፍ ፈቀደለት።
ሁለተኛው ቴሌግራም ደግሞ ከአዛዡ ከራሱ ከቀኛዝማች መንግሥቱ ነው፤ በመልክቱም ለአለቃው መሀመድ ኢማምን ያለ ማለፊያ ወረቀት ድንበር ሲያቋርጥ ስላገኘው እስረኛ አድርጎ ስለያዘው ምን ማድረግ እንዳለበት ከአለቃው ትእዛዝ እንዲሰጠው ነው፤ ደጃዝማች በአስቸኳይ በቴሌግራም መልሰው እስረኛው ከጠንካራ ጥበቃ ጋር በአስቸኳይ ወደሳቸው እንዲላክ የሚል መልዕክት ላኩ።
ሰውየው እንደደረሰ ተጎሳቁሏል ለደጃች አያሌው የሚገባውን ሰላምታ ከሰጠ በኋላ ስለደረሰበት በደል ተቃውሞ አሰማ፤ የድንበር ጠባቂዎቹ የያዘውን ንብረት እንደወሰዱበት፣ ውድ በቅሎውን ቀምተው  በእግሩ ሦስት ቀን እንዲጓዝ እንዳደረጉት፣ ምግብ ጭብጦ የገብስ ቆሎ እንደሰጡትና ከሁሉም በላይ ደግሞ ትምባሆና ቡና መከልከሉን ተናገረ፤ ደጃች አያሌው ጥፋቱ የራሱ የመሀመድ ኢማም እንደሆነ ነገሩት፤ ምክንያቱም በጦርነት ጊዜ ያለ ይለፍ ድንበር ማቋረጥ አልነበረበትም፤ ቀጥሎም በደረሰበት በደል የሚያዝኑ መሆኑን ገልፀው ይቅርታ ጠየቁ፤ ለእንግዳው ከዛፍ ስር ድንኳን ከተወጠረ በኋላ ለእንግዳው የሚሆን በግ ባርኮ እንዲያርድ መሀመዳዊ የሆነ ሰው ተጠራ፤ (በፀሐፊው አጠራር የነብዩ መሀመድ ተከታዮች በዚያን ጊዜ መሀመዳውያን ተብለው እንደሚጠሩ ነው የሚያሳየው በሌሎች በዚያን ጊዜ የተፃፉ የአውሮፓውያን ፅሑፎችም አጠራሩን ሲጠቀሙ ይታያል)።
በሚቀጥለው ቀን መሀመድ ኢማምና  ደጃዝማች አያሌው ለብቻቸው በመሆን ለረዥም ጊዜ ተነጋገሩ፤ ማምሻውኑ ደጃች አያሌው ለኔ በሚስጥር መሀመድ የተላከው ከጓደኛቸው ከኤርትራው ገዥ ጣልያን ነው፤ መልዕክቱም ደጃዝማች በጦርነቱ እንዳይሳተፉ ለማሳመንና ለመወትወት ነበር፤ ደጃች አያሌው ከተስማሙ ጣልያኖች ሲያሸንፉ የራስነት ማዕረግ ተሰጥቷቸው የጠቅላላው የሰሜን ምዕራብ ገዥ ሆነው ሊሾሙ ነው፤ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ብዙ ገንዘብ ስለሚሰጣቸው በሀገሪቱ ውስጥ ትልቅ ሀብታም እንደሚሆኑ ነው።
“እውነት ነው ንጉሡ በድለውኛል” ብለው ደጃዝማች ነገሩኝ “ነገር ግን እኔ ሀገሬን በምንም ያህል ገንዘብ የምከዳ አይደለሁም፤ ጣልያኖች እኔን ይከዳል ብለው ማሰባቸው የሚያሳፍር ነገር ነው።”
ደጃች አያሌው ንጉሡን ለምን ተቀየሙ?
ለብዙ ዓመታት የደጃች አያሌው ምቀኞች ደጃዝማቹን ከጣልያን ጋር ወዳጅነት ያበዛል እያሉ ለንጉሡ ነገር ይሰሩባቸው ነበር፤ ሆኖም በንጉሡና በደጃች አያሌው መሀከል ላለው ቀዝቃዛ ግንኙነት ምክንያቱ ይህ ብቻ አልነበረም፤ አያሌው ላላቸው ሥልጣንና ማዕረግ ምኒልክን ነው የሚያመሰግኑት ስለዚህም ከቀድሞ ትውልድ ወገን ነው የሚመደቡት፤ አፄ ኃይለሥላሴ ዙፋኑን ሲይዙ የቀድሞ ባለሥልጣኖችን ገሸሽ በማድረግ አብረዋቸው ያደጉ ወጣት ጓደኞቻቸውን ማቅረብ ጀመሩ፤ ይህም የሆነው በቀድሞ መኳንንቶች ባለማመን ነው፤ ይህ ያለመታመን ሁኔታ ሲታወቅ  ደጃች አያሌውን በጣም ነው ያስከፋቸው።
ደጃች አያሌው ንጉሡ ሥልጣን ሲይዙ በጣም ነው የረዷቸው የምኒልክ አልጋ ወራሽ ከነበሩት  ከልጅ ኢያሱ ጋር በመሀሶ በተደረገው ጦርነት ንጉሡ እንዲያሸንፉ ደጃች አያሌው ከፍተኛ እርዳታ ነው ያደረጉት፤ በኋላም ራስ ጉግሳ ወሌ ሲሸፍቱ በ1930 ዓ.ም. በአንቺም በተደረገው ጦርነት ደጃች አያሌው ናቸው ራስ ጉግሳን ድል ያደረጉት። ለዚህ ሥራቸው በንጉሡ እንደ ሽልማት ቃል የተገባላቸው የራስነት ማዕረግ ተሰጥቷቸው የሰፊው የበጌምድር ገዥ እንደሚሆኑ ነበር፤ ቃል የተገባላቸው ነገር ግን እውን አልሆነም።
ዶ/ር ሀርልድ በኔ ግምት ይላሉ…..
ለደጃች አያሌው መከፋት ዋንኛው ምክንያት ንጉሡ በጠሩት ግብዣ ላይ የተሠጣቸው የመቀመጫ ደረጃ ነበር፤ ከዚህ ቅድም መቀመጫቸው ከከፍተኛዎች መኳንንቶች አንዱ እንደመሆኑ በንጉሡ ቀኝ በኩል ይቀመጡ ነበር፤ የኋላ ኋላ ግን ያን ሥፍራቸውን ለወጣቶቹ ለራስ እምሩና ለራስ ለራስ ደስታ እንዲለቁ ተደረጉ፤ ይህንን ሲያዩ አያሌው ከስድብ ቆጠሩት “በተሰማኝ ምሬት ምክንያት አንድ ጉርሻ እንኳን በጉሮሮዬ ሊወርድ አልቻለም፤ እያሉ ይህ ነገር በተነሳ ቁጥር ያጫውቱኝ ነበር።
ሌላው ምክንያት ደግሞ ለደጃች አያሌው ከማዕከላዊ መንግሥት ጥራት ያላቸው በቂ መሣሪያዎችና ጥይት አለመሰጠት ነበር፤ በሌላ ግንባር ያሉ አዛዦች ዘመናዊ መውዜር ጠመንጃዎች መትረየሶች የአርሊከን መድፎችና አየር መቃወሚያዎች እንደልባቸው ተሰጥቷቸዋል፤ አያሌው ግን አምስት መቶ መውዜር ጠመንጃዎችና አስር መትረየሶች ነበር የደረሳቸው፤ በራሳቸው ገንዘብ እንኳን 150 መውዜር ከመንግሥት ሲገዙ አስቸጋሪ ሁኔታ ፈጥረውባቸው ነበር።
ይሄ ሁሉ ሆኖ ግን ደጃች አያሌው የጣልያን ማታለል ሳይበግራቸውና በደሉም ሳያሸፍታቸው በአምስቱ ዓመት የአርበኞች ተጋድሎ በጀግንነት ተፋልመዋል።
ክብር ለጀግኖች አባቶቻችን!!!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሳሚ – ዘብሔረ ኢትዮጵያ
Filed in: Amharic