>
5:18 pm - Friday June 15, 3923

ደብሪፅ ካልሞተ  "አልሞተም” ማለት እንጂ ቡራ ከረዩን ምን አመጣው? (ነፃነት ዘለቀ)

ደብሪፅ ካልሞተ  “አልሞተም” ማለት እንጂ ቡራ ከረዩን ምን አመጣው?

ነፃነት ዘለቀ

የዚህች አገር ፖለቲካ አሁንስ እጅ እጅ ከማለት አልፎ ጋዝ ጋዝ ሊለኝ ጀምሯል፡፡ ምድረ ሥራ ፈት እየተነሣ የሚነዛው ወሬ ሰዎች ካለሥራ እንዴት እንደሚኖሩ አግራሞትን ከማጫሩም በላይ የዚህች አገር ፖለቲካዊ ዕንቆቅልሽ ይበልጥ እየተወሳሰበና ከመብሰል ይልቅ ከጥሬነትም ወደ ድንጋይነት እየተለወጠ መሆኑን አመላካች ነው፡፡ ሰዎች ኅሊናቸውን እየሣቱ ባልተገባ ተግባር ውስጥ ለምን እንደሚዘፈቁ በጣም ይደንቃል፡፡ በእውኑ የዕለት ጉርሱንና የዓመት ልብሱን በቅጡ መሸፈን በማይችል ማኅበረሰብ ውስጥ እየኖሩ በየትኛው ጊዜ ነው ይህን ሁሉ የሀሰት ወሬ እየፈጠርን የምናሰራጨውና በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ተጥደን በፈጠራ ወሬዎች ወንድምን ከወንድም የምናናክሰው? በየዩኒቨርስቲው የጠላት ሠርጎ ገብ ኃይል ምን እያደረገ እንደሆነ ስንሰማ መረገማችን ቅጥ ማጣቱን እንረዳለን፡፡ ከሞታችን አሟሟታችን ከፋ፡፡ ጥሩ ሞትን መሞትም ለካንስ መታደል ነው! የክፋታችን ልኬት ወሰን አጣ፡፡ ለነፍሳቸውና ለመለኮታዊ ቃሉ ያደሩ እውነተኛ የሃይማኖት አባቶች ቢኖሩን ኖሮ በተለይ አሁን ሀገራዊ የጋራ የምህላና የጸሎት መርሐ ግብር ተዘጋጅቶ በተመሳሳይ ጊዜና ሰዓት እግዚኦ ማለት ነበረብን – እንደጥንት እንደጧቱ ይትበሃል ሁሉም ወገን ከክፋትና ከኃጢኣት ሥራዎች ተቆጥቦና ጥጆችና ሕጻናት ሳይቀሩ እንዳይጠቡ ተደርጎ ፈጣሪን ይቅርታ መጠየቅ አለብን፡፡ 

ሰሞኑን ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል ሞተ ተብሎ ተናፈሰ፤ ፈረንጅ ብሆን ኖሮ So what! ብየ እራቀቅበት ነበር፡፡ እርሱ ቢሞት አፈር አያሟሽም – የመጀመሪያው ሟች አይደለምና፡፡ ይህ ዓይነት ወሬ ከማስፈገግ ባለፈ አገር ይያዝልኝ የሚያስብል አይደለም – እንደሚባለው ሕወሓት ለተለዬ ዓላማ የሞቱን ዜና አቀናብሮት ካልሆነና ያን ካላሳካሁ “ሞቼ እገኛለሁ” ካላለ በስተቀር፡፡ በመሠረቱ እንደዚህ ያለ ወሬ በየትም ሀገር የተለመደ ነው፡፡ ያልሞተን ሰው ሞተ ብሎ አንድ ታማኝ የሚመስል የዜና ምንጭ በስህተትም ይሁን ለአንዳች ፖለቲካዊ ፍጆታ ሲባል ከአንድ ቦታ ተልኮ ሊሰራጭ ይችላል፡፡ ቢቻል ያን ዜና ከተለያዩ ምንጮች በማጣራት ዜናው ቢሠራ ጥሩ ነበር፡፡ ነገር ግን አንዳንዴ ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጪ የሚሆኑበት ክስተት ያጋጥማልና የደብሪፅ ነገር ሆነ፡፡ ሲሆን ግን ሀሰት ሆኖ ቢገኝ “ህልም እልም፤ እንኳንስ ውሸት ሆነ” ተብሎ በትዝብት መልክ ይታለፋል እንጂ ደብሪፅ እንደ ግራኝ ድንጋይ ተተክሎ ዝንታለሙን የሚቀር ይመስል ይህን ያህል ዜናውን ማናር በርግጥም “የሞቱ ዜና” ነገር አለው ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል ሲጤን እንደዘሀበሻ የዩቲዩብ ሀተታ ከሆነ ዜናው በተለጠፈ ከ10ኛው ደቂቃ ጀምሮ አካኪ ዘራፍ ማለት “የሀውዜንን ታሪክ አትርሱብኝ” የማለት ያህል ነው፡፡

ሕወሓት ካሏት ጠንጋራ ጎኖች ማለቴ ጠንካራ ጎኖች መካከል የሀሰት ዜና መፍጠርና ሕዝብንና አገርን ማሸበር አንዱ ነው፡፡ የገደለችውን ሰው አፋልጉኝ ማለት፣ አጣልታና አጋጭታ ላስታርቃችሁ ማለትና በእግረ መንገድም የትንሽ ትልቅነቷን ሥነ ልቦናዊ ደዌ ለማከም መሞከር፣ በአማራና ኦርቶዶክስ መካነ መቃብር ላይ የሕወሓትን የድል ሐውልት መገንባት፣…. ሀገርን ባወጣች በሃራጅ መሸጥ፣ ራሳቸውን ያልቻሉ ክልሎችን ጠፍጥፎ በነሱ በጀትና በነሱ ክልል እንዳሻት መፈንጨት፣ ወዘተ. ሌሎቹ መታወቂያዎቿ ናቸው – ግን ቂልነቷ ይህን ሁሉ ገመናዋን የምናውቅ አይመስላትም – የብልጥ ጅል ነበረች ሕወሓት፡፡ ዝኮነ ኮይኑ ዐረመኔዋ ሕወሓት በሐውዜን ዕልቂት ከፍተኛ ድል እንዳፈሰችበት በወቅቱም ባይሆን ትንሽ ቆየት ብሎ አብርሃም ያየህ ይሁን ገብረ መድኅን አርአያ በሚገባ አብራርተውታል፡፡ ስለዚህ ዐይነ ደረቂቱ ወያኔ እንኳንስ ደብሪፅን በሀሰት ገድላ ድል ለማፈስ መቋመጥና ከ3000 ያላነሰ የሐውዜንን ሕዝብ (አስ)ጨርሳ ብዙ ወጣት እንዲቀላቀላትና ደርግም በጭካኔው በሀገር ደረጃና በዓለም ዙሪያ እንዲታወቅ አድርጋለችና ይህ ነጭ ውሸት በጭራሽ አያስደንቅም፡፡ መደነቅ የሚገባን ይልቁናስ ወያኔ ነፍስ አውቃ ሰው ልሁን ብላ በተግባር የተነሣች ዕለት ነው – ይህ ደግሞ ፈጽሞ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ተፈጥሮን ተመክሮም ሆነ ተሞክሮ እንደማይለውጠው ለ“እንደሠራ አይገድል” ምሣሌያዊ ብሂል ተስማሚ ገላጭ የሆኑት፣ እግዜሩም ከሁለቴ በላይ የሠራቸው የሚመስሉት አባባ ስብሃት ነጋና እማማ ገነት ዘውዴ በቅርቡ ሳይቀር አሣይተውናል፡፡ እንዲህ ጃጅተውም እንኳን ወደሰውነት አይመለሱም እናንተዬ? 

ስለሆነም በዚህ አጀንዳ መንጫጫት አሁንም ልድገመው ሥራ መፍታት ነው፡፡ ዋልታም ሆነ ፍርድ ቤቶች በዚህ ጉዳይ ጊዜያቸውን ሊያባክኑና ሊጨነቁም የሚገባ አይመስለኝም፡፡ ዜናው ከየት እንደመጣ ማጣራት፣ የመጣበትን መንገድ መፈተሽ፣ ከዚያም አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ከሆነ መውሰድ፡፡ እንጂ ያልሞተ ሰው እንደሞተ ታውጆ ሲያበቃ ያ ያልሞተው ሰው በሚዲያ ወጥቶ “አልሞትኩም” ብሎ አገር ይያዝልኝ ማለት ነውር ከመሆኑም በተጨማሪ ፈጣሪን “ለምን አትወስደኝም? ለምን አንቆላጫችሁኝ? ለምንስ ጎምጅቼ እቀራለሁ?” ብሎ የመማጸን ያህል ነው፡፡ ደብሪፅ አለመሞቱ ያን ያህል ካንገበገበውና ከነድርጅቱ መንጨርጨራቸውን የሚቀጥሉ ከሆነ ሀገራችን ህጓን አሻሽላ ወይም አዲስ ህግ ቀርፃ እንደ አንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት በህክምና የታገዘ ሰላማዊ ሞትን (Voluntary Euthanasia) እንዲያገኝ መሞከር ነው፡፡ እንጂ አሁን እያደረጉት ያለው ማፈርን አያውቁም እንጂ በእጅጉ አሣፋሪ ነው፡፡ በደብረፅዮን ሞት የሚጠቀምም ሆነ የሚጎዳ አለ ብዬ በበኩሌ አላስብም፡፡ አንድ ዜጋ ነው፤ ነገም ሆነ ከነገ ወዲያ ወይም የዛሬ 30 ዓመት ሊሞት ይችላል፡፡ የርሱ ሞት የሰማይና የምድር ማለፍ አይደለም፡፡ አቢይም፤ ደመቀም፣ ለማም፣ እኔም፣ አንተም፣ አንቺም፣ እነሱም… በየምንጠራበት ሰዓት “ዘንጠን” እንሄዳለን፡፡ ያ አይደል እንዴ ትልቁ መጽናኛችን? 

የወያኔን ቲያትር ማንም የማያውቀው ይመስል ይህን ነገር ከጉዳይ ጥፎ ጊዜን ማባካን ተገቢ አይደለም፡፡ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ተጨማሪ ሀተታ ለማዳመጥ ዘሀበሻን በዚህ ማስፈንጠሪያ ወይም ሊንክ ተጭኖ መከታተል ነው – ከዚያም መናደድ፤ ተናደድና ይውጣልህ፡፡ https://www.youtube.com/watch?v=hczBVRjPH_U

Filed in: Amharic