>

ለ አማራና ለኦሮሞ የተደገሰ ጦርነት...?! (ዳግማዊ ጉዱ ካሣ)

ለ አማራና ለኦሮሞ የተደገሰ ጦርነት…?!

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

ይህችን ጦማር ባልጽፋት ደስ ባለኝ፡፡ ግን እውነትን ተናግሮ እመሸበት ማደርን የመሰለ የለም፡፡ በመሳጭ የቃላት ፕሮፓጋንዳ “ኦሮማራ” እያልክ ብታሽሞነሙነው እውነቱ እንደሆነ ፈጥጦ እየመጣ ነው – ሴተኛ አዳሪዋ ጨርሳዋለች – “አጭበርባሪ አይተኛኝም!” ብላ፡፡ የምታታልለውንም ሰው ተፈጥሮና የትግስት ልኬት መረዳት አግባብ ነው – ለስንት ጊዜና በምን ያህል ድግግሞሽ ልታታልለው እንደምትችል ጭምር፡፡ ግልጹን ልንገርህ በኦሮሞና አማራ መካከል እኔ ነኝ ያለ ትልቅ ጦርነት ሊከሰት ሰዓታትን ምናልባትም ደቂቃዎችን እየተጠባበቀ ነው፤ መቼስ አርጂን አይከብደውም፡፡ መርዶህን ስማና ተዘጋጅህ ጠብቅ፡፡ ደግሞም ውሸት እንዳይመስልህ፡፡ “የማነው ሟርተኛ”ም አትበለኝ፡፡ ዝኆንና ዝኆን ሲፋለም ሣሩና ዛፍ ቅጠሉ ሁሉ ስለሚደቀደቅ “ጦርነቱ በነሱ ላይ ብቻ ነው ጉዳት የሚያስከትለው” ብለህ ጮቤ የምትረግጥ “ሌላ” ካለህም ውርድ ከራስ፡፡ የጦርነቱ ማስጀመሪያ ፊሽካ መቀሌ ላይም ይሁን ካይሮ ላይ የዐዋጁ እምቢልታና ከበሮ ግን በአክራሪ ኦሮሞዎች ደጅ ፀሐይ እየሞቀ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ካልሞተች አትነሳም፡፡ የአንድ ሣንቲም ሁለት ገጽታዎች የሆኑ ማንነቶችንና ምንነቶችን አጥርተን እናውቅ ዘንድ 27 እና 2 ተከታታይ ዓመታትን በተለያዩ የስሜት ጡዘቶች ውስጥ ሆነን አሳለፍን፡፡ አሁን ግን ጊዜው የ“በቃ!” ሊሆንና ሰማይ ኮረጆውን ከፍቶ የመከራ ዶፉን ሊያዘንብ ምድርም ልትቀበል ሁሉ ነገር አልቋል፡፡ ከይሲ ከይሲው ማገዶ ይሆናል፤ ተራፊው ጥቂት ነው፡፡ ያን ወቅት የማያይ ብፁዕ ነው፡፡

ከየት እንደምጀምርልህ አላውቅም፡፡ ብቻ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ጃዋር መሀመድ ቆይ ቆይማ …. ዶክተር አቢይ የዚህ ጦርነት መሃንዲስ ስለመሆኑ በቂ መረጃ የለኝም፡፡ አንድ የምገምተው ጉዳይ ግን ከራስ ፀጉሩ እስከ እግር ጥፍሩ በአክራሪ ኦሮሞዎች ተጠፍንጎ በመያዙ ጦርነቱን ማስቆም አይችልም፡፡ የሚለውና የሚያደርገው ስለሚለያይ ቃሉን መጠቀም ቢያስጠይፈኝም “ልፋቱ”ን ሁሉ በዜሮ የሚያባዙ ኦሮሞዎች የፌዴራል መዋቅሮችን ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ተቆጣጥረው ኢትዮጵያን የሥንግ አንቀዋታል፡፡ እስትንፋሷ በአምላክ እጅ ሆኖ እንጂ እንደነሱ ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ አብቅቶላት ነበር – አሁን አላበቃላትም ካልን፡፡

ክርስቲያን ታደለ ከባህር ዳሩ “መፈንቅለ መንግሥት” ጋር የሚያያይዘውን ነገር አጢንልኝ – በአጋምም በቀጋም አይገናኝም፡፡ ጃዋር መሀመድ ምንጩ በሚገመት ገንዘብ እንዴት እንደሚኖር፣ ምን ለ(ነ)ማን እየሰጠ ምን እንደሚሠራ፣ በርሱ ጦስና በርሱ ትዕዛዝ በሀገርና በወገን ላይ ምን እየተከናወነ እንደሆነ፣ በአንዲት ሀገር ሁለተኛ መንግሥት መሆኑንና ለዚያ አፍራሽ ተግባሩም እንደወሮታ በመንግሥት እንደሚጠበቅ ደግሞ አስብ፡፡ ዕንቆቅልሹ ሁሉ ቁልጭ ብሎ ይታይህ – ጤነኛ ሰው ከሆንክ፡፡ የምስኪን አማሮችን ኑሮና ቢሯቸውን ሳይቀር በምናብህ ሳላቸውና ተመልከት – ከፈለግህም ወደ ግንፍሌ አካባቢ ብቅ በልና ያቺን የተላላጠች የጭቃ ቤት ቢሯቸውን እይ፡፡ … አያ ጅቦ ከላይ ሆኖ ውኃ እየጠጣ ታች ሆና የርሱን እርጋጭ የምትጠጣዋን አህይት “አታደፍርሽብኝ!” አላት፡፡ እርሷም “አያ ጅቦ ሳታመካኝ ብላኝ!” አለችው ይባላል – በኦሮሞና አማራ መካከል ያለው ወቅታዊ ሥዕልም ይህን የእንስሳት ታሪክ የሚያስንቅ ቁጭ በሉ ነው – ሃሳብን ከጣሉና በትዕቢት ከታወሩ አይቀር ደግሞ እንዲህ ነው፡፡ እነ ክርስቲያን ታደለ ለእስር የተዳረጉትና እየደረሰባቸው ለሚገኘው እንግልትና ውርደት የተጋለጡት አማራ በመሆናቸው ብቻ ነው፡፡ ዘርን መሠረት ያደረገ ምን ዓይነት ስድብና ከወያኔው ዘመን የማይተናነስ ስብዕናን የማጉደፍ ተግባር እየተፈጸመባቸው እንደሆነ ከየእስር ቤቶቹ ከሚወጡ ጽሑፎች እየተረዳን ነው፡፡ ስለሆነም ለውጡም ሆነ የአቢይ እንቅስቃሴ ሁሉ “ብጥለው ገለበጠኝ” ዓይነት የዘረኝነት መተካካት መሆኑን ለመረዳት እማኝ መቁጠር አያሻም፡፡ አቢይም ሆነ እነሱሴዎች በዚህ ማፈሪያ ተግባራቸው ማፈር አለባቸው፡፡ ችግሩ ግን በዘረኝነት ማዕቀፍ ውስጥ ሀፍረት ወይም ይሉኝታ ብሎ ነገር በመዝገበ ቃላታቸው ሳይቀር አለመኖሩያ ነው፡፡

ስለዚህ የኅልውናው ጦርነት አይቀርም፡፡ ጠላት ደስ ይበለው፡፡ ወዳጅንም ይክፋው – ‹መቼስ ማልጎደኔ› ይላሉ አዲሶቹ ጌቶቼ፡፡ ይህ ዝግጅቱ እየተጠናቀቀ ያለ ጦርነት ባላሰብነው ሰዓትና ባላሰብነው ሁኔታ ይነሳል፡፡ የድርሻውን አጥፍቶም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ይቆማል፡፡ ከዚያን በኋላ ነው የኢትዮጵያ ትንሣዔ የሚበሠረው፡፡ ውጭ ያሉት የሀገራችን ጠላቶች እነጃዋርንና መሰሎቹን በማንኛውም ረገድ እስከጥግ አስታጥቀው ልከዋቸዋል፡፡ እንደሚያሸንፉም እርግጠኞች ናቸው፡፡ ግን እውነት እንጂ ዶላርና ዘመናዊ የጦር መሣሪያ አሸንፈው አያውቁምና አሸናፊው የእውነትን ዘገር የጨበጠ ብቻ ነው፤ ይህ የኔ ቃል አይደለም፡፡ ቋሚና ዘላለማዊ እውነት ነው፡፡ 

ጅል ሰው አያሸንፍህ፤ ሞኝ ሰው አይርታህ፡፡ ፈሪ ሰው ጌታህ አይሁን፡፡  ገረድ የጌታዋን ባል በቀማች ጊዜ አገር ምድሩ አይበቃትም፡፡ ደግሞም የደስታዋ ምንጭ የመጥፊያዋ ሰበብ እንደሚሆን አታውቅምና አቅሏን ስታ ትቦርቃለች፡፡ የምታደርገውን ስለማታውቅ የምታደርሰው ጥፋት አንዳንዴ እጅግ ከባድ ሊሆን ይችላልና ከዚህ ዓይነቱ መጥፎ አጋጣሚ ለመዳን በርትቶ መጸለይ ተገቢ ነው፡፡ አይሆንም ተብሎ የሚናቅ ነገር ሊኖር እንደማይገባ በተለይ እንደሀገር ያሳለፍናቸው ዐርባና ሃምሣ ዓመታት በቂ ምሥክር ናቸው፡፡

በአዲስ አበባ ዙሪያ ከኦሮምኛ በቀር ሌላ ቋንቋ በተለይም አማርኛን መናገር በሕይወት እስከ መወራረድ እየደረሰ ነው፡፡ ቄሮ አልተቻለም፡፡ ቄሮ በየተራ ሀገሪቱን እየዘረፈና እየመዘበረ በአንድ አዳር ሚሊዮነር ከመሆን አልፎ የንጹሓንን ነፍስ በገፍና በግፍ እስከመቀማት ደርሷል፡፡ የኦሮሞ ጢነኞች ማዕከላዊ መንግሥቱን የያዘውን ኃይል በመተማመንና ከርሱም ማንኛውንም ዓይነት ድጋፍ በማግኘት በአሁኑ ወቅት የማያደርጉት የለም፡፡ በስሙ ከዐርባና ሃምሳ በላይ ካርታ ፕላን የያዘ ቄሮ መኖሩን ስትሰሙ ወያኔ ማረኝ ልትሉ ይዳዳችኋል፡፡ የምስኪን ሠራተኞችን ኮንዶምኒየም ቀምቶ መውሰድ መንግሥቶቻቸው መርቀው የሰጧቸው መብት ነው – ለዚያውም “ጨርሳችሁ ካላስረከባችሁን አንወስድም” እያሉ እንደሚንቀባረሩ ሰምቻለሁ፡፡ እነዚህን ሰዎች ጅሎች የምላቸው ለዚህ ነው፡፡ ወያኔ ብልጧ በሃያ ሰባት ዓመታት የሠራችውን ግፍና በደል እንዲሁም ዝርፊያ እነዚህ ገልቱዎች ሁለት ዓመት እንኳን ሳይሞላቸው እያቀላጠፉት ነው – ቸኮሉ፡፡ ደግሞም ባፈሱ ሳይሆን በጎረሱ መሆኑን አያውቁም፡፡ ካለዕውቀትና ካለጥበብ ሀብትን ቢያጋፍሩት ዋጋ የለውም፡፡ አንዳንዱ ቄሮ ዛሬ ከብሮ ያድርና ነገ ጧት ይሆናል – የገንዘብ አያያዙን ስለማያውቅበት፡፡ ብዙ ነገሮች ምናልባትም ሁሉም ነገሮች ዕውቀትን ይጠይቃሉ፡፡ ለመግደልም እኮ ዕውቀትን ይጠይቃል – አሁን የቄሮዎችንና የወያኔዎችን “የአገዳደል ሥነ ሥርዓት” እስኪ ታዘቡልኝ፡፡ እነዚያ በሥውርና በዘዴ ነው – እነዚህ ደግሞ በግልጥና በሜንጫ፡፡ አስተዳደግ የበደለው ሰው እንኳን ማዳንን መግደልንም በቅጡ አያውቅበትም፡፡ ታዲያ ሰው መሆን አይቀድምም ትላላችሁ? ነገር አትዘርጥጡብኝ – እየወቀስኩ ያለሁት በጥፋት መንገድ ገብተው ሀገርን እያተረማመሱ የሚገኙ የማንኛውንም ወገን አባላት ነው፡፡ ከዚህኛው ብዙ ከዚያኛው ጥቂት ቢሆኑ የአጋጣሚ እንጂ የኔ ጉዳይ አይደለም፡፡

ወደ ቀበሌ ሂዱ፡፡ ወደ ከፍተኛዎች አቅኑ፡፡ ወደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እግር ጥሏችሁም ሆነ ለሥራ ጎራ በሉ፡፡ ወደ አየር መንገድ ሂዱ፡፡ ወደ ጉምሩክ ግቡ፡፡ ወደ ባንክ ሂዱ፡፡ ሥራ የሚቀጠሩ ዜጎችን ማንነት ፈትሹ፡፡ ባለሥልጣኖችን ሁሉ ተመልከቱ፡፡ ዱሮ አብዚሎ ቅብዚሎ ትሰሙ ነበር፤ አሁን የዚያኑ ግልባጭ “አካም ነጉማ ፈዩማ”ን ትሰማላችሁ፡፡ የቋንቋው ጉዳይ ችግር አይደለም፡፡ ሁሉም የኔው ነው፡፡ ችግሩ ይህን ተራ የቋንቋ ነገር ተመርኩዘው የሚሠሩት ፍትህንና ርትዕን የሚያጠፋ ሥነ ልቦናዊ ስካር ገዝፎ መታየት ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያዊነቴ በዚህ እጅግ አፍራለሁ፡፡ የዚህ ማኅበረሰብ አባል መሆን በዚህ ዘመን ካላሳፈረ መቼም አያሳፍርም፡፡ በየሴከንዱ ሽቅብ ስለሚወነጨፈው የኑሮ ውድነት አንድም አልተነፈስኩም፡፡ እርሱም አንዱ የጦርነቱ ሰበብ እንደሚሆን አትርሱ፡፡ ስለሙስናውና ስለአስተዳደራዊ በደሎች ምንም አልተናገርኩም፡፡ ያም ለጦርነቱ መነሳት ቀላል አስተዋፅዖ የለውም፡፡ የትኛውም ቢሮ ይሁን በእጅህ ካልሆነ በእግርህ ሄደህ የምታስፈጽመው ጉዳይ የለም ወይም ጥቂት ነው፡፡ አዲሶቹ ሰዎችማ ለትንንሽ ጉዳዮች ሳይቀር የሚጠይቁት የገንዘብ መጠን ሲታሰብ ቁጥር ማወቃቸውንም ትጠራጠራለህ፡፡ ለምሣሌ አሥር ሽህ ብር ለምታገኝበት አንድ ጉዳይ ከግንዛቤ ዕጥረት የተነሣ የ50 ሽህ ብር ጉቦ ሊጠይቁህ ይችላሉ፤ ትዕቢታቸው ደግሞ ለጉድ ነው አሉ፡፡ “እከሳችኋለሁ” ብትል ከላይ እስከ ታች ሁሉም በነሱ ቁጥጥር ያለ መሆኑ እንዲገባህ በሚያሳብቅ የሰውነት እንቅስቃሴ ታጅበው “ሰባራ ዶሮ ሳቲቀድሚህ የትም ሄዳህ ኪሰስ” ሊሉህ ይችላሉ፡፡  እንዴ! ጉቦና ጉቦኝነት እኮ ዱሮም ነበር፤ ግን የያኔው ቅጥ ነበረው – “ሞራላዊ ሙሰኝነት” ነበር ያኔ፡፡ዱሮ በስልክ ሲያወራ በአላስፈላጊ ሁኔታ እየጮኸ አካባቢን የሚያደነቁረው የወያኔ ጥጋበኛ ነበር – አሁን ደግሞ ቄሮ ሆኗል፤ ለመጮህም ተረኝነት ማስፈለጉን ተመልከትልኝማ፡፡ ምድረ አሽቃባጭ ባለሆቴልና የምሽት ክበብ ባለቤት ደግሞ ዱሮ “ኮበለይ”ን እየከፈተ እንዳላስደነከረ አሁን “ያ በሬዱ”ን እየከፈተ ያዘልላል፡፡ … ስንገርም! እንዴት ብንረገም ነው!

መነሻና መድረሻየን ወደድከውም ጠላኸውም ይህንን ግን ያዝልኝ – ጦርነቱ አይቀርም፡፡ ሕጻናትና አእሩግ ያላችሁ ለተወሰነ ጊዜ እንዲያገለግላችሁ ከሚበላውም ከሚጠጣውም ለመያዝ ሞክሩ፡፡ ከሁሉም በበለጠ ግን የጦርነቱን ጊዜ እንዲያሳጥርልንና የመስዋዕትነቱን መጠን ከተባለውና ከሚባለውም እንዲያሳንስልን ለፈጣሪ እንጸልይ፡፡ ጥጋበኞችም ሰከን ብትሉና ማሰብ ብትጀምሩ የጥፋት አድማሱ ይጠብና ወጪያችን ይቀንሳል፡፡ 

Filed in: Amharic