>

የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት በምሥራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ 4 መስጊዶች መቃጠላቸውን አስመልክቶ መግለጫ ሰጠ!!!

የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት በምሥራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ 4 መስጊዶች መቃጠላቸውን አስመልክቶ መግለጫ ሰጠ!!!

ዘጋቢ፡- ኪሩቤል ተሾመ
በሞጣ ከተማ በሃይማኖት ተቋማት ላይ በተፈጸመው ድርጊት ማዘኑንና ድርጊቱን እንደሚያወግዝ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አስታወቀ፡፡
ዛሬ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸህ ሰኢድ አሕመድ በጽሕፈት ቤታቸው ትናንት በምሥራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ አስተዳደር በሃይማኖት ተቋማት ላይ የተፈጸመውን የቃጠሎ ድርጊት አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
ታኅሣሥ 10 ቀን 2012 ዓ.ም በምሥራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ አጸያፊ ተግባር መፈጸሙን ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል። በሞጣ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ አራት መስጂዶች መቃጠላቸዉንና የሙስሊም ሱቆችና ድርጅቶች ላይ ዝርፊያ መፈጸሙን ገልጸዋል። ‹‹በተፈጸመው ድርጊት የተሰማንን ሐዘን እንገልጻለን፤ አስጸያፊ ድርጊቱንም እናወግዛለን›› ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ።
ድርጊቱ ከኢትዮጵያ ባህል ያፈነገጠ ተግባር መሆኑንም አንስተዋል። መንግሥት ድርጊቱን በፈጸሙ አካላት ላይ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድም ሸህ ሰኢድ አሕመድ ጠይቀዋል። ሕዝበ ሙስሊሙና ክርስቲያኑ ተደራጅቶ የሃይማኖት ተቋማቱን እንዲጠብቅም ጥሪ አቅርበዋል። መንግሥት ለሁሉም ቤተ እምነቶች ጥበቃና ከለላ እንዲያደርግም አሳስበዋል። ሕዝቡ ተመሳሳይ ድርጊት የሚፈጽሙ አካላትን ማጋለጥ እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።
ከዚህ በፊት የመስጂድ ቃጠሎና ሌሎች የተከሰቱ አደጋዎችን መነሻ በማድረግ በሞጣ ከተማ ጥበቃ እንዲደረግ ለጸጥታ አካሉ አሳውቀው እንደነበርም ሸህ ሰኢድ አሕመድ ገልጸዋል። ከዚህ ቀደም ደቡብ ጎንደር እስቴና ምሥራቅ ጎጃም ቢቸና መስጂዶች ተቃጥለዉ ሕጋዊ እርምጃ እንዳልተወሰደም በመግለጫቸው አስታውሰዋል።
‹‹በሞጣ ከተማ የክርስትያኑና የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ግንኙነት የተጠናከረ ነው። ድርጊቱም የሞጣ ከተማ ነዋሪዎችን አይወክልም›› ብለዋል፡፡ ድርጊቱ የክርስቲያኑንና የሙስሊሙን አንድነት ለመበታተን የሚፈልጉ አካላት የፈጽሙት መሆኑንም አስገንዝበዋል።
Filed in: Amharic