>
4:53 pm - Wednesday May 25, 5363

ምኒልክን  "እምዬ" ያላቸው የኦሮሞ ገበሬ እንጂ ሹመት ያገኘ መኳንንት አይደለም!!!  (ዘላለም ጥላሁን)

ምኒልክን   እምዬ” ያላቸው የኦሮሞ ገበሬ እንጂ ሹመት ያገኘ መኳንንት አይደለም!!!

 

 ዘላለም ጥላሁን
 
ምኒሊክ ቅዱስ ንጉስ ነበር፡፡ እንደ እነ ቅዱስ ላሊበላ፥ ነአኩቶለአብ፥ አብርሃ ወአፅብሃ፡፡ ዘመን አልፎ ዘመን ሲመጣ፥ መታወሱ አይቀርም-በቅዱስነት፡፡ ላሊበላ እየከበሩ የሄዱት፥ የእልፈት ዘመናቸው እየጨመረ ሲሄድ ነው፡፡ ስለ አፄ ዳዊት፥ ስለ ዘርዓያዕቆብ፥ ስለ ፋሲል ንትርክ የለም፡፡ ስለ አፄ ቴዎድሮስ የጎላ ንትርክ የለም፡፡ በአመዛኙ አፄ ዮሐንስ ላይ መላጋቶች አሉ፡፡ ከአፄ ቴዎድሮስ የተሻለ ርህራሄ ነበራቸው-ሚኒሊክ፡፡
“እኒያ አፄ ቴዎድሮስ፥ አቤት ሰው ሲወዱ
የሸዋን መኳንንት፥ እጄ ነስተው ሄዱ” ተብሎላቸዋል፡፡ ሚኒሊክ ይሄን አላደረጉም፡፡ ከአፄ ቴዎድሮስ ራዕዩን ወረሱ፡፡ ያው ከእግሩ ስር ቁጭ ብለው፡፡ ኃይሉን ቀንሰው ብልሃትና ጥበብ ጨመሩበት፡፡ እምነትም ጨመሩበት፡፡ አፄ ዮሐንስ ጎጃም ወርደው ያደረጉት ይታወቃል፡፡ “የጎጃም ሴቶች ለምን የራስ ፀጉራቸውን አያሳድጉም?” ብሎ ጠይቆ የሚያውቅ የለም፡፡ መጠየቁም ጥቅም የለውም፡፡ ከታሪክ ላይ ተኝቶ ማልቀስ ነገን ወዶ ፈቅዶ መግደል ነው፡፡ ግን ከእምዬ ሚኒሊክ ጋር የሚወዳደር አንጀት እንዳልነበራቸው ማሳያ ነው፡፡
“እምዬ” ያላቸው የኦሮሞ ገበሬ እንጂ ሹመት ያገኘ መኳንንት አይደለም፡፡ ደም ሳያፈሱ በጥበብ የቴዎድሮስን ራዕይ እውን ያደረጉበት መንገድ 100 ዓመታትን ተሻግሮ እንኳን ያስገርመናል፡፡ ወላይታ ወርደው ምን እንዳደረጉ፥ ምን እንደሆኑ፥ አንድ ወዳጄ ቦታው ድረስ ሄዶ የጥንት ሽማግሎችን ጠይቆ ያገኘውን መረጃ በቅርብ በሰነድ ጀባ ስለሚለን አልነካካው፡፡
የሆነው ሆኖ ሚኒሊክ በ’ተኮነነ ዘመን’ በእኛ በተኮነነ ትውልድ እጅ ደርሰው እንጂ ፃድቅ፥ ቅዱስ ናቸው፡፡እንዲያውም ያማልዳሉ፡፡ አማልደዋልም፡፡ ልባችሁን ከከፈታችሁ ማስረጃ አለኝ-ቅዱስም አማላጅም የሚያሰኛቸው፡፡ ልቀጥል?
1ኛ) በራዕይ መወለድ
እምዬ በራዕይ የተወለዱ ሰው ናቸው፡፡ በመፅሐፍ ቅዱስ ይሄን እድል ያገኙ የተመረጡ ትቂት ሰዎች ናቸው፡፡ እናታቸው “ከብልቴ ፀሐይ ወጣች” ብለው ራዕይ አዩ፡፡ የንጉስ ሳህለስላሴ ባለቤትም ለልጃቸው ለሃይለመለኮት አጋቧት፡፡ ይህን ታሪክ የመንግስቱ ለማ አባት አለቃ ለማ ፅፈውታል፡፡ ሚኒሊክም ተወለደ፡፡ የዓለም ፀሐይም ሆነ፡፡ ለጥቁር ህዝብ የጨለመች ዓለም ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የፀሐይ ብርሃን አበራ፡፡ ፀሐዩ ሚኒሊክ ጨለማውን ዓለም በብርሃን ወጋገን ሞላ፡፡ ስለ ሰው ልጅ እኩልነት ዓለምን አስተማረ፡፡ ራዕዩ ዕውን ሆነ፡፡
 
2ኛ) በራዕይ ከተማን መገንባት
አፄ ሚኒሊክ በግራኝ የፈራረሰውን የአፄ ዳዊትን ከተማ ፈልገው እንደገና መገንባት ይፈልጉ ነበር፡፡ ቦታው ግን የት እንደነበር አያውቁትም፡፡ ዳዋ ከለበሰ 400 ዓመት አልፎት ነበር፡፡ የአፄ ዳዊትን ቤተመንግስት ቦታ በራዕይ አይተው ቤተመንግስታቸውን ከአንኮበር ወደ አዲስ አበባ (ቀደምት በረራ) እንዳዛወሩ ምን አልባት የሚያውቅ ትንሽ ሰው ይሆናል? የአፄ ዳዊትን የንግስና ቦታ ለመፈለግ፥ አንዴ አዲስ አለም፥ ሌላ ጊዜ መናገሻ፥ ሌላ ጊዜ እንጦጦ እየዞሩ ማረፊያ ይሰሩ ነበር፡፡ መጨረሻ በራዕይ ተገለጠላቸው፡፡ እንጦጦ ላይ ፀኑ፡፡ የኢትዮጵያን መዲና ቆረቆሩ፡፡ የአሁኗን አዲስ አበባን፡፡ አፄ ዳዊትም የኢትዮጵያ ማዕከለ ምድር በሆነችው በወቅቱ ስሟ በረራ (የአሁኗ አዲስ አበባ) ላይ ትልቅ ከተማ ገንብተው ነበር፡፡
3ኛ) ብርቱ አማኝነት
የእንጦጦ ማርያም ቤተክርስቲያን ተሰርታ ስትጠናቀቅ ለምርቃው ድግስ 5395 ከብት ታርዶ ነበር፡፡ እንዲሁም እያንዳንዳቸው 40 ኩንታል ሊጥ የሚያቦኩ ዕቃዎች ተዘጋጅተው ሰዎች በመሰላል እየወጡ የተቦካውን ሊጥ ያወጡ ነበር፡፡ በተጨማሪም ጠጅ በአሸንዳ እየወረደ በጉድጓድ ተጠራቅሞ ሕዝቡ ከዚያ የጠጅ ጉድጓድ እንዲጠጣ ተደርጎ ነበር፡፡ ለእንጦጦ ማርያም ለቤተክርስቲያኒቱ ምረቃ የሚያስፈልገው ድግስ ከተዘጋጀ በኋላ በምረቃው ቀን ዋዜማ መስከረም 20 አየሩ ሁሉ ተለዋውጦ ከፍተኛ ደመና ሆኖ ነበር ፡፡ ቦታውም ተራራማ ነውና ደመና መጥቶ ሳይዘንብ ስለማይመለስ ሁሉም ሰው ድግሱ ሊበላሽ ነው ብሎ ተጨነቀ፡፡ በዚህ ጊዜ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ጸሐፊያቸውን ጠርተው “ዝናቡን ቤትሽ እስኪያልቅ አቁሚው” የሚል ጥቅል መልዕክት ያለው ደብዳቤ ዝናቡ ይመለስ ዘንድ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አፃፉ፡፡ የተጻፈውንም ደብዳቤ የእመቤታችን ታቦት ላይ ሲደረግ ደመናው ጠፍቶ ዝናቡ ተመልሶ ብሩህ ቀን ሆነ፡፡
4ኛ)  የእምዬ እመነትና የአድዋ ድል
የዓለም ብርሃን የሆኑት ሚኒሊክ እምነታቸው ለአድዋም ትልቅ ዋጋ ነበረው፡፡ የአራዳ ጊዮርጊስን ታቦት ሄደው ተሳለሙ፡፡ ለመኑት፡፡ ነጩ ጊዮርጊስ ለተጨቆኑት ለጥቁሮች እንዲቆም ለመኑት፡፡ ታቦቱን በካህናት አስይዘው ወደ አድዋ ዘመቱ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአርበኞች ጎን ሆኖ ለአስራት ሀገሩ ተዋጋ፡፡ አንድ በጦርነቱ የተሳተፈ ጣሊያናዊ ስለ ጦርነቱ ተጠይቆ እንዲህ አለ፡
” አንድ በነጭ ፈረስ ላይ የነበረ መልከ መልካም ወጣት በከፍተኛ ሁኔታ ተዋጋን፡፡ ብዙዎችን ጣላቸው፡፡ ከጦርነቱ በኋላ አዲስ አበባ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን የዚያን ወጣት ምስል ግድግዳ ላይ ከነፈረሱ ተስሎ አየሁት…” በማለት ምስክርነቱን ሰጧል፡፡ በምኒሊክ እምነትና ልመና ሰማዕቱ አድዋ ላይ ታምር ሰርቷል፡፡
5ኛ)  የህግ የበላይነትና ርህራሄ
የእንጦጦ ማርያም ቤተክርስቲያን በምትሰራበት ወቅት ሰው በመግደል የተከሰሰ አንድ ወንጀለኛ በምኒልክ ችሎት ፊት ቀረበ፡፡ ተከሳሹም ወንጀሉን በመፈፀሙ የሞት ፍርድ ተላለፍበት፡፡ በዘመኑም በነበረው የፍርድ ስርዓት መሰረት በገዳይ ላይ ውሳኔው ከመፈጸሙ በፊት የተበዳይ ወገኖች “ወንጀለኛው መገደሉ ቀርቶ ለተገደለው ዘመዳቸው የደም ካሳ የሚሆን ገንዘብ ትቀበላላችሁ ወይ?” ተብለው ተጠየቁ፡፡ እነርሱም ” አይ የወንድማችን ገዳይ ይገደልልን እንጂ ካሳ አንቀበልም” በማለት መለሱ፡፡ በዚህ ጊዜ ፍርድ የተላለፈበት ተካሳሽ ድምጹን ከፍ አርጎ “ጃንሆይ በሥራዬ ነውና መገደሉንስ ልገደል፡፡ ግን የዚችን የእንጦጦ ማርያም ቤተክርስቲያን መጨረሻ እስካይ ዕድሜ ይሰጠኝና ልገደል” ሲል ጠየቀ፡፡ ይህን የሰሙት አጼ ምኒልክ ከዙፋናቸው ተነስተው ወንጀለኞች ከሚቆሙበት ቦታ ሄደው በመቆም ከፊታቸው ላሉት መኳንንት “ከሟች ወገኖች አስማሙኝ፡፡ ካሳውን እኔ ራሴ ከግምጃ ቤቴ እከፍላለው ይህን ሰው ግን እንድታስምሩልኝ እማፀናለው” በማለት የንግሥና ኩራት ሳይዛቸው ከወገባቸው ጎንበስ ብለው ጠየቁ፡፡ በዚህ ጊዜ ወንጀለኛው ይገደልልን ብለው የነበሩት የሟች ቤተሰቦች በምኒልክ እግር ስር ወድቀው እያለቀሱ “ምረነዋል ለእርስዎ ስንል ምረነዋል ካሳውንም አንቀበልም” አሉ፡፡ ምኒልክም መልሰው “ነፍሱን ማሩልኝ አልኩ እንጂ ካሳውንማ መተው ፍርድ ማጓደል ነው” ብለው ገንዘቡን ከፈሉ፡፡
ያለምጣም ምኒልክ:-
“ይገርፉኝም እንደው ይህው እንዳሻዎ
ያለምጣም ምኒልክ ብዬ ሰድብኩዎ” መኳንንቱ ለዚህ ድፍረቷ ትቀጣ ትገረፍ ቢሉም ጠቢቡ ንጉስ ግን “ሁሉ አወዳሽ ሆነ እስኪ አንች እንኲን ስደቢኝ ያልኳት እኔው በምን ሀጢያቷ ትቀጣ? ልያውስ አወደሰችኝ እንጂ መች ሰድባኝ” ብለው መኳንንቱን ምስጢሩን እንዲመራመሩ አድገዋል።
“ባቡሩም ተጫነ፥ ስልኩም ተናገረ
ምኒሊክ ነብይ ነው፥ ሆዴ ጠረጠረ! በዘመኑ የነበረው ሰው።
6ኛ) ከድንግል ማርያም ጋር የነበራቸው ቃልኪዳን
የድንግል ማርያምን ስም ጠርተው አድዋ ዘምተዋል፡፡ በማርያም ከማሉ አይመለሱም፡፡ ህዝቡም ያውቃልና ሁሉም ወደ አድዋ ተመመ፡፡ እንጦጦ ብቻ ሳይሆን. የአዲስ ዓለም ማርያምን በሚያሰሩ ጊዜም በረጅም ከፍታ ላይ ይገኝ የነበረ ርብራብ ተሰብሮ ሁሉም ሰራተኞች ወደ መሬት ወድቀው በአንዳቸውም ሰውነት ላይ ግን ጭረት እንኳን ሳይገኝ በተአምራት ተርፈዋል፡፡ እሳቸውም ቃሏን ይጠብቃሉ፥ እሷም ልመናቸውን አታጎልም፡፡ በቃል ኪዳኗ ታስረዋልና!||| ወዘኩሉ ዘተግብረ በእንተ ንጽሐ ልቡ ለዳግማዊ ምኒልክ እስመ ታፈቅሮ እምኩሎሙ ነገሥት፡፡|||
እንግዲህ ከዚህ የተሻለ ንፁህ ልብ፥ ርህራሄ፥ ቅድስና፥ እምነት፥ ድፍረት ያለው መሪ በ20ኛው ክ/ዘመን ማን አለ? ከቅዱሳን ያማለደ፥ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በጦር ሜዳ አብሮ የተዋደደ ፃድቅ ሰው ማን አለ? 
ጠቁሙንና እናክብረው፥ ቅዱስ እንበለው? 
እኔ ግን እልሃለሁ ሚኒሊክ ቅዱስ ነው፡፡ እሙት ስልህ፡፡ አላመንህም? ኧረ ማርያምን!!!
•••
ምንጭ፦
1) ታሪከ ዘመን ዘዳግማዊ ምኒልክ በጸሐፌ ትዕዛዝ ገ/ሥላሴ
2) ታሪከ ነገሥት ከምኒልክ ፩ይ እስከ ምኒልክ ፪ይ በመ/ር ደሴ ቀለብ
3) አጤ ምኒልክ ጳውሎስ ኞኞ
4) አፈ ተረክ (የቃል ውርስ)
5) የአምባ ጥናታዊ ፅሑፍ
Filed in: Amharic