>
9:49 am - Wednesday November 30, 2022

የ ¨ጓድ¨ ኢሳያስና የ ¨ጓድ¨ መለስ የደብዳቤ ልውውጦች (ተስፋዬ ሀይለማርያም)

የጓድ ኢሳያስና የጓድ መለስ የደብዳቤ ልውውጦች

ተስፋዬ ሀይለማርያም
ኢሱ (ወዲ አፎም) አዲስ አበባ መጥቶ ከታናሽ ወንድሙ ከዶ/ር አብይ ጋር ሽር ብትን እያሉ ነው። ጉብኝቱ በጥሩ ጊዜ የተደረገ ወሳኝ ጉብኝት ቢሆንም፣  ከወደ መቀሌ ቆሽት ቆሽት እየሸተተ ነው። በተቃጠለው የእነ አቦይ ስብሃት ቆሽት የተነሳ።
 
ኢሱ ሲመጣ ከድሮው ወዳጁ ከመለስ ጋር ከ23 ዓመት በፊት በ1989 ዓ.ም የተጻጻፉት ደብዳቤዎች ትዝ አሉኝና መዛግብቶቼን አገላብጬ አቀረብኩት።  ከእነዚህ ደብዳቤዎች በኋላ “የአፍሪካ ኖርማንዲ” የተባለው ጦርነት ተነሳና ከሰባ ሺህ በላይ ሰዎች ሞቱ። ደብዳቤዎቹ ስለ ድንበሩ ግጭትና በተለይም ስለ ብር ቅያሪው የተጻጻፉትን በአጭሩ እንመልከተው።  ደብዳቤዎቹ በትግርኛና የተጻፉ ቢሆንም ወደአማርኛ ተተርጉመዋል።
ኢሳይያስ ለመለስ የጻፈው፣
“ጓድ መለስ፣ እንደምን ሰንብተሃል?ዛሬ እንድጽፍልህ ያደረገኝ ባዳ አካባቢ ያለው አሳሳቢ ሁኔታ ነው። በመካከላችን ያለው ድንበር በዘልማድ የሚታወቅ እንጂ በትክክል ተረጋግጦ ያወቅነው ወሰን አለ ለማለት አይቻልም። ከሌሎች የዛሬና የወደፊት ዝምድናችን አንፃር ብዙም ክርክር አድርገንበት ያቆየነው ጉዳይ አይደለም ። ለወደፊቱም ቢሆን እምብዛም የሚያከራክርና የሚያሳስብ አይመስለኝም።
ዕውነቱ ይሄ ሆኖ ሳለ አልፎ አልፎ ግን ግጭቶች እየታዩ ነው። በአካባቢው የሚገኙ ኃላፊዎችም በወንድማዊነት መንገድ ግጭቶቹን ለማብረድና ችግሩን ለመፍታት ሲሞክሩ ቆይተዋል። በዚህ ሰሞን ግን አዲ ምሩግ አካባቢ ሠራዊታችሁ የወሰደው የኃይል እርምጃ በዕውነቱ እጅግ የሚያሳዝን ነው።
ይህ የተወሰደው እርምጃ አስፈላጊ ወዳልሆነ ግጭት እንዳያመራ ካሁኑ መገታት አለበትና አንተው ራስህ በአስቸኳይ እርምጃ እንድትወስድ አሳስባለሁ”
ከሰላምታ ጋር
 ጓድህ ኢሳይያስ አፈወርቂ።
መለስ ለኢሳይያስ የጻፈው፣
“እንዴት ሰነበትክ? የጻፍካትን ደብዳቤ ተመልክቻታለሁ። የባዳ ችግር ይፈጠራል የሚል ግምት አልነበረኝም። የአጉጉመ (የአፋር አብዮታዊ አንድነት ግንባር) ርዝራዦችን ለማባረር ተንቀሳቅሰናል።  በተረፈ የወሰን ጉዳይን በተመለከተ ቀደም ሲል እነ ተወልደ የደረሱበት ስምምነት ስላለ እሱን መሠረት በማድረግ ሁኔታውን ማርገብ እንዳለብን ይታየኛል።
ካንተ ጋር በተነጋገርነው መሠረት እነ ነዋይን(የጠ/ሚ የኢኮኖሚ አማካሪ) ወደ አሥመራ ልኬያቸው ነበር። ይሁን እንጂ ያደረጉት ስብሰባ ፍሬ አልባ ሆኗል።
በኤርትራ ውስጥ የሚገኘው ብር መጨረሻ ላይ ምን መሆን እንዳለበት ሶስተኛ ወገን ጨምረን እንድናየውና ይህ እስከሚሆን ግን የገንዘብ ቅያሪው መቆየት ስለማይችል፣ ሂደቱንና ከቅያሪው በኋላም ሊኖር ስለሚገባው የንግድ አፈጻጸም እነ ነዋይ እንዲጨርሱ ካንተ ጋር በተነጋገርነው መሠረት ነበር የላኳቸው።
 በእነ ብርሃነ በኩል የተሰጣቸው መልስ ግን ኤርትራ ውስጥ ያለውን ብር ሳናውቅ ወይም ጉዳዩ በአገር ደረጃ ከመውጣቱና ከመገለጹ በፊት ስለገንዘብ ቅያሪው ሂደትና ዝርዝር አገባብ ለመነጋገር አንችልም የሚል ነው።
በዚህም ምክንያት ምንም ዓይነት ዕልባት ላይ ሳይደርሱ ተመልሰዋል። ከገንዘብ ለውጡ በኋላ ሶስተኛ ወገን ጨምረን የምንወስነው ውሳኔም ሆነ አስቀድመን የምናደርገው ውሳኔ ልዩነት አይኖረውም ። ዞረን ዞረን በመግባባት የምንፈታው ጉዳይ ነው።
እኛ አዲሱን ብር በሙሉ አስገብተናል። የመቀየሪያው ጊዜ መስከረም ይሁን የሚል ሃሳብ ታቀርቡ ስለነበር እኛም በዚያው መሠረት ተዘጋጅተናል። መስከረም ቀርቶ ጥቅምትንም ካለፈ ግን በምስጢር የያዝነው ጉዳይ ምስጢርነቱ ያከትምለታል።  እንዲያውም ገና ካሁኑ አዲሳባ ውስጥ መወራት ጀምሯል።
አዲሱን ብር በሙሉ ስላስገባነውና ወሬውም እየተናፈሰ በመሆኑ በጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ ለፓርላማው ልንገልጽና ቀጥሎም ወደ ቅያሪው ልንገባ አስበናል” ከሰላምታ ጋር
መለስ
ኢሳይያስ ለመለስ የጻፈው፣
“ጓድ መለስ እንዴት ሰነበትክ?  በድንበር ላይ ስላለው ሁኔታ ባለኝ መረጃ መሠረት በአዲ ምሩግ የተወሰደው እርምጃ የኛ አካላት በነበሩበት አካባቢ አባሎቻችንን በማንገላታት፣ በማባረርና የቆየውን መስተዳድር በማፈራረስ የተወሰደ እርምጃ ነው።
አጉጉመ (ARDUF)ን በተመለከተም እርምጃ ከመወሰዱ በፊት የየራሳችንን መከላከል እንድናደርግ ባሳወቃችሁን መሠረትየኛዎቹም ለመተጋገዝ በሚቀራረቡበት ወቅት ነው እርምጃ የወሰዳችሁት። በባድመ አካባቢ የተወሰደውም እርምጃ ከዚያ የተለየ አይደለም።
ይህ ዓይነቱ የኃይል እርምጃ አስፈላጊ አይደለም። ሁኔታውን በቶሎ ለመቆጣጠር በኛ በኩል ወዲ ኤፍሬም የማነና ወዲ ካሳ ጉዳዩን እንዲከታተሉት አስበናል። ስለዚህ በናንተም በኩል ተመሳሳይ ሰዎችን ምረጥና በአስቸኳይ ተገናኝተው ለችግሩ እልባት ያብጁለት የሚል አስተያየት አለኝ። እናም ሃሳብህን ግለጽልኝ።
የገንዘብ ለውጡን በተመለከተ እኔና አንተ በተስማማነው መሠረት የሚካሄድ ይሆናል።የዓለም ባንክም በጉዳዩ ላይ የመሰላቸውን አስተያየት እንዲሰጡበት ተስማምተናል።
በድንበር ላይ የሚኖረውን የንግድ ልውውጥ ግን በእኛ በኩል በቀላሉ አናየውም። ምክንያቱም ብዙ ሕዝብ የሚጎዳና የሚያነካካ ይመስለናል። ይሄንን በተመለከተ የኛ ሰዎች ለእነ ነዋይ በስፋት ያብራሩላቸው ይመስለኛል። አሁን በችኮላ እንዲህ ይደረግ ማለቱ ኋላ ላይ እንቅፋት እንዳይፈጥርና ጉዳዩን በየማዕዘኑ  በጥልቀት ለመመልከት ተቀራርበን መነጋገር አለብን”
 ከሰላምታ ጋር
ጓድህ ኢሳይያስ አፈወርቂ
መለስና ኢሳይያስ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚነካ ደብዳቤ እንዲህ ይጻጻፉ ነበር።   ኢሳይያስ በአብዛኛው የሚያስጨንቀው ስለ ድንበሩ ጉዳይ ሲሆን፣ መለስን ደግሞ የሚያስጨንቀው ግን ስለ ገንዘቡ ለውጥ ጉዳይ መሆኑን ደብዳቤያቸው ያስረዳል። ኢሳይያስ ተቀራርበን እንነጋገር ቢልም  መጨረሻ ላይ ንግግራቸው በጥይት ሆነ።
አሁንስ አብይና ኢሳይያስ ምን ብለው ይጻጻፉ ይሆን?
Filed in: Amharic