>
2:03 am - Wednesday July 6, 2022

እፍረተ ቢሱ  ብአዴን ወደ አእምሮ ሕክምና መወሰድ ያለበትን ወፈፌ ሾመ!!!!  (አቻምየለህ ታምሩ)

እፍረተ ቢሱ  ብአዴን ወደ አእምሮ ሕክምና መወሰድ ያለበትን ወፈፌ ሾመ!!!! 

አቻምየለህ ታምሩ
 
* ባጠቃላይ የኢትዮጵያ ፖለቲካ እብደት ነው። ደርግ እብደት ነበር። ደርግን የሚያስንቅ እብደትም እርሱን ተከትሎ መጣ። እብድ ግን ማበዱን አያውቅምና አሁንም ወደ ቀድሞው ከፍታ መመለስን እንደ ኋላ ቀር አስተሳሰብ የሚያዩ ብዙሃን ናቸው። የዱር አራዊት ፖለቲካ (የዘር ክልል አፓርታይድ) ግን ኋላ ቀር መሆኑን እብድ ናቸውና አያውቁም!!!
 
ባንድ ወቅት እውን የሆነ አጭር ታሪክ በዚህ አጋጣሚ ልንገራችሁ
 አፄ ቴዎድሮስ ከመንገሣቸው በፊት አፄ ሣሕለ ድንግል የሚባሉ ንጉሥ ነግሠው ነበር። ዙፋናቸው በጎንደር ከተማ ነበር። ባንድ ወቅት አንድ ራሱን “እጓለ አንበሳ” የሚል የሰሎሞናዊ ንግሥና ሥም የሰጠ ሰው ከገዳም ይወጣና ወደ ቤተ መንግሥት ይሄዳል። ቤተ መንግሥትም ሲደርስ ጥሩምባ (መለከት) ይነፋና “የሚጠበቀው ባለ ትንቢቱ ቴዎድሮስ እኔ ነኝ” ሲል አዋጅ ያውጃል። አፄ ሣሕለ ድንግል ይህን ትርኢት ከቤተ መንግሥታቸው ሆነው ባዩ ጊዜ የሰውዬው ድፍረት ደማቸውን ያፈላውና ራሳቸው ከዙፋናቸው ተነስተውና የተሳለ ሠይፍ ይዘው እየተንደረደሩ ከወረዱ በኋላ ቴዎድሮስ ነኝ ብሎ ያወጀውን እጓለ አንበሳን አንገቱን በአንድ ምት ጎምደው ይጥሉታል። ከዚያም ለሌሎች ትምሕርት ይሆን ዘንድ ልብሱን ሰቅለው አንጠለጠሉት ይባላል።

 

እፍረተ ቢሱ  ብአዴን …
የበለጸገው ብአዴን ጤነኛ አጋሰሶች አለቁበት መሰለኝ አሁን  አማራውን የወፈፌ መቀለጃ እያደረገው ነው። ወደ አእምሮ ሕክምና መወሰድ ያለበትን ወፈፌ  «የአማራ ክልል» የበለጸገው ፓርቲ  የማኅበራዊ ሜዲያ ኃላፊ አድርገው መሾሙን  ብአዴን ዛሬ ነግሮናል። ብአዴን  ጥንትም ሆነ ዛሬ አይደለም በአለም ላይ  ስለሚካሄደው ነገር ቀርቶ በደጃቸው፤ አፍንጫቸው ስር ምን ሲደረግ እንደነበር የማያውቁ፤ የማወቅም ፍላጎት የሌላቸው አጋሰሶች ስብስብ ነው። ለዚህም ነው ብአዴን ሎሌ ያደረጉት የጌቶቹ ጉዳይ አስፈጻሚ እንጂ የአማራ ሕዝብ ባለጉዳይ አይደለም እያልን ግብሩን የምንገልጸው።
የበለጸገው ብአዴን  በአማራው ላይ ኃላፊ አድርጎ የሾመው ወፈፌ አንድ የሆነውን አማራ ለመከፋፈና ግፉን ለማራዘም ያልሰራው የእብድ ስራ የለም።  አማራው ከፋፍሎ አንዱን ክፍል የቅዠቱ ውጤት የሆነ አገር አድርጎ ለመመስረት የተንቀሳቀሰውማ አይነገር ይቅር!
አንድ ሰሞን «አማራ የሚባል ሕዝብ የለም፤ የሌለው አማራ ሊበደል አይችልም» እያለ በአማራ ቁስል ላይ እንጨት ይሰድ ነበር። ሌላ ጊዜ «አማራ ፈሪ ነው፤ እኔም ጀግና የሆንሁት አባቴ የሜጫ ኦሮሞ ስለሆነ ነው» ይል ነበር። አማራ የኦሮሞን አገር እንደወረረ፤ጎጃም የኦሮሞ ምድር እንደሆነ በድፍረት ይሰብክ ነበር።
ሌላ ጊዜ ደግሞ «ትንቢት የተነገረልኝ ቴዎድሮስ የምባለው ንጉስ እኔ ነኝ፤በቅርቡም የንግሥና ቅባት አግኝቼ፤ የዘውድ አክሊል ጭኘ ወደ መንበረ ስልጣን እወጣለሁ፤ አባቶቻቸን የተነበዩልኝ ሕዝብን ከፈፅሞ መጥፋት የምታደግ አዳኝ ንጉሥ ቴዎድሮስ እኔ ነኝ። በአለሙ ሁሉ ላይ ፅድቅ፣ ሰላም እና ብልፅግና አመጣለሁ፤ የመልከፀዴቅ እና ሄኖክ መንፈስ በኔ ላይ ነው። እውነተኛው አዳኝ ንጉስ ቴዎድሮስ እኔ ነኝ። በባሕር ዳር ቤዛዊት አለም በምነግሥበት ጊዜ ለመላው የሰው ልጆች ፅድቅ ሰላም እና ብልፅግና አመጣለሁ። ከኔ በፊት የተነሱት ቴዎድሮሶች ሐሰተኛ ናቸው። የኢትዮጵያ ሕዝብን እና የሰው ልጆችን ሁሉ ነፃ የማወጣው ቴዎድሮስ እኔ ነኝ። የሚያምንብኝ ሁሉ ይከተለኝ» ብሎን ነበር። ይህ ሰው እንግዲህ ዛሬ በብአዴን የአማራ ባለሥልጣን ተደርጎ የተሾመው!
የበለጸገው ብአዴን በለጸግሁ ብሎም ለአማራ ሕዝብ የሚበጅ ነገር ይዞ እንዳልመጣና  ለአማራ ሕዝብ ደንታ እንደሌለው  በለጸግሁ ብሎ ይዞት የመጣው ይህ  ወፈፌና ሕዝብ ከፋፋይ ተሳዳቢ አንድ  ማሳያ ነው።
Filed in: Amharic