>

የመጫወቻ ሜዳቸውን ያጠበቡት እስክንድር እና ጃዋር!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

የመጫወቻ ሜዳቸውን ያጠበቡት እስክንድር እና ጃዋር!!

 

ያሬድ ሀይለማርያም
 

* ከሰፊው ምህዳር ወደ ፓርቲ ጉሮኖ፤ ለምን? ማን ምን ሊያተርፉ?

 

ከዚህ ቀደም እስክንድር እና ጃዋር በማህበረሰብ ውስጥ እንደ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰብ ኢትዮጵያ እንዴት እያስተናገደቻቸው እንዳለ ጽፌ ነበር። እነዚህ ሁለት ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ዛሬም በአንድ ርዕስ ሥር ጉዙዋቸውን እንድቃኝ የሚያደርገኝ አጋጣሚ ስለተፈጠረ በአንድ አፍ ላነሳቸው ወደድኩ።
ሁለቱ ግለሰቦች ባሳለፍነው የትግል ዘመን እስክንድር እየታሰረ፣ እየተደበደበ እና ብዙ መከራዎችን እያየ መሰዋትነት የከፈለለትን ትግል፤ ጃዋር ደግሞ ብዙ ሺዎችን እያሳሰረ፣ እያስገረፈና እያስገደለ እሱን ስንጥርም ሳይበሳው ሁለቱም አሁን ያለንበት የፖለቲካ ምዕራፍ ለማምጣት የየራሳቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል። የህውሃትን ሽሽት ተከትሎ የተፈጠረው የፖለቲካ ምህዳር መስፋት ለሁለቱም የመብት አቀንቃኞች እጅግ የጠበባቸው ሳይውል ሳያድር ነው። ሁለቱም በለውጡ ላይ እና ለውጡ እየሄደበት ባለው መንገድ ላይ የየራሳቸው ቅሬታና ቁጭት አላቸው።
ሁለቱም የአብይ አስተዳደር ወደምንፈልገው ጫፍ አያደርሰንም ብለው በአደባባይ ይሞግታሉ። እስክንድር ሥርዓቱ መድሎ የተሞላው እና በተረኝነት ስሜት የሚናውዙ ፖለቲከኞች የሚሾፍሩበት ነው። በዚህም የተነሳ በዋነኝነት የአዲስ አበባ ሕዝብ፤ ቀጥሎች የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍ ያለ አደጋ ተዳርጎበታል። በአብይ አስተዳደር ሽፋን የተሰጠው የኦዴፓ ተረኝነት አገሪቱን ወደ ግጭት እና ትርምስ እንድታመራ እያደረጋት ነው የሚል አረዳድ እንዳለው በቅርቡም በአካል ተገናኝተን ከራሱ አንደበት ለመረዳት ችያለሁ።
በተቃራኒው ጃዋር ደግሞ አብይ አገሪቱን እኛ ከሰራነው የፖለቲካ ቀመር ውጭ እየመራ ነው። እኛ የታገልነው የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ በአግባቡ እንዲመለስ ነው። ከፊንፊኔ የባለቤትነት ጥያቄ አንስቶ የኦሮሞ ልጆች የተሰውላቸው ጥያቄዎች በአብይ አህመድ እየተዳፈኑና ከቀድሞዎቹ ሥርዓቶች ወዳልተለየ አህዳዊ አስተዳደር እየመለሰን ነው። በመሆኑም አብይን አጥብቀን እንታገለዋለን የሚል አቋሙን በሚዲያዎች ደጋግሞ ሲገልጽ ሰምቼዋለሁ።
እነዚህ ሁለት በተለያየ ጽንፍ የቆሙ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች አብይን ለመታገል ከተለያየ አግጣጫ ቆርጠው የተነሱትን ያህል እርስ በርሳቸውም ሊተናነቁ የፖለቲካ አሰላለፋቸውን ከተጽዕኖ ፈጣሪ የማህበረሰብ ንቅናቄ መሪነት ወደ ፓርቲ አደረጃጀት ቀይረዋል። እርምጃቸው በተመሳሳይ ጊዜ መሆኑ ደግሞ በማህላቸው እጅግ ከፍ ያለ የመፎካከር ስሜትም እንዳለ ያመላክታል።
የጽሁፌ ዋና አላማ ግን እነዚህ ግለሰቦች ከሰፊው ሜዳ ጠባቡን ለምን መረጡ? ምንስ ሊያተርፉ? የትስ ሊደርሱ? አገርስ ምን ታተርፋለች? የሚለው ነው። በእኔ እምነት ማህበራዊ ንቅናቂ (social movement) ልቅ እና ሰፊ ሜዳ ነው። ልክ እንደ ፖለቲካ ድርጅት በፖሊሲ እና በፓርቲ ደንብ የታጠረ አይደለም። ምንኛውንም ወቅጡን የሚመጥን አጀንዳ ማራገብ የሚቻልበት፣ በሁሉም አቅጣጫ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚያሳትፍ፣ ቀልጣፋና ፈጣን የለውጥ ተጽዕኖ መፍጠሪያ መንገድ ነው ብዮ አምናለሁ።

 እስክንድር

እስክንድር ወደ ፓርቲ ያቀናበት ምክንያት ብሶት እንደሆነ ይገልጻል። ብሶቱን በተወሰነ ደረጃ እኔም እጋራዋለሁ። የአብይ አስተዳደር የሕግ የበላይነትን ማስጠበቅ ተስኖት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ንጹሃን ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ እና በደል፣ በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ የሚፈጸሙት አንዳንድ መድሏዊ የአስተዳደር በደሎች እና የስጋት አደጋዎች እስክንድርን ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ስጋት ላይ የሚጥሉ ናቸው። ይሁን እና ይህን ችግር ከመቶ በላይ የፖለቲካ ፓርቲ ድርጅት ባሉበት አገር ሁሉም የሚረቡ ስላልሆነ የፖለቲካ ጨዋታውን እኔ ብይዘው እነዚህ ችግሮች ይቀረፋሉ ብሎ በማሰብ ፓርቲ ማደራጀቱ ላይ ነው ጥያቄ የሚነሳው።
እንደ እኔ እምነት የእስክንድር ስጋቶች አንድ ፓርቲ በማቋቋሚ የሚመለሱ አይመስለኝም። እስክንድር ፓርቲ አቋቁሞ ከሚታገል ይልቅ ከነበረው አለም አቀፍ እውቅና እና ተቀባይነት አንጻር በማህበራዊ ንቅናቄ መሪነቱ ቢገፋበት ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎችን አጣብቂኝ ውስጥ የመክተት እና በሂደትም ከፍተኛ ተጽዕኖ የመፍጠር እድልና አቅሙ ከፍተኛ ነበር። እስክንድር ይህን ሰፊ ሜዳ እና ትልቅ እድል ወደጎን ብሎ ወደ ጠባቧ የፓርቲ ጉሮኖ ውስጥ ለመሸንቆር የጀመረው ጉዞ እያደር ብዙ ነገር የሚያሳጣው ይመስለኛል።
ልክ ፓሪት በመሰረተ ማግስት ከትላልቆቹ የፖለቲካ ድርጅቶች ተርታ ብቻ ሳይሆን እንደ ሱቅ ተከፍተው በአንድ እና በሁለት ሰውም ከሚዘወሩት ፓርቲዎች ተርታም ነው የሚሰለፈው። ያኔ እስክንድ እርምጃውም ሆነ እንቅስቃሴው ፓርቲው በሚቀርጸው ፖሊሲ ይወሰናል። በፖለቲካ ፓርቲ መሪነት አብይ አህመድም፣ ብርሃኑ ነጋም፣ ለደቱ አያሌውም፣ አየለ ጫሚሶም፣ መራራ ጉዲናም ሆኑ ሌሎቹ እኩል ናቸው። ጠንካራ ፓርቲ መፍጠር እና ጠንካራ መሪ መሆን ደግሞ ሁለተኛው ደረጃ ነው።
እስክንድር የፓርቲ መሪ ሲሆን የፓርቲውን አጀንዳ የሚደግፉ ሰዎች ብቻ ናቸው ከእስክንድር ጎን የሚቆሙት። ቀደም ሲል የነበረው ሰፊ ሕዝባዊ ተቀባይነትም ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል። አሁንም የፓርቲ ወሬ ከተሰማበት ጊዜ አንስቶ የቀድሞ ደጋፊዎቹ ሲንጠባጠቡ አይቻለው። እስክንድር ልክ የፓርቲ መሪ መሆን ሲጀምር በጋዜጠኝነቱ እና በማህበራዊ መብት ንቅናቄ መሪነቱ የተጎናጸፈው አለም አቀፍ ቅቡልነት ከላዩ ላይ እየተገፈፈ ይወርዳል። የእስክንድር ትልቁ አቅም ደግሞ ይህ ያተረፈው ከፍተኛ ተደማጭነት እና ቅቡልነት ነው። በዛው ልክ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ተጽዕኖ የመፍጠር አቅሙም ይቀንሳል። እስከ ዛሬ እስክንድር ተጽዕኖ በመፍጠር እረገድ ከፓርቲዎች በላይ ነበር። አሁን ግን ከፓርቲዎች ልክ ይሆናል። በደጋፊዎች ብቻ ሳይሆን በተፎካካሪዎችም ይከበባል። በማህበራዊ ንቅናቄ መሪነት ደጋፊ እንጂ ተፎካካሪ የለም። ግብ ተጽዕኖ መፍጠር እንጂ ሥልጣን ስላልሆነ።

ጃዋር

ጃዋር በኦሮሞ ፖለቲካ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ የፖለቲካ ንቅናቄ ውስጥ ትልቅ ሚና የነበረው እና እጅግ አወዛጋቢ ሆኖ የቆየም ወጣት አክራሪ የብሔር መብት አቀንቃኝ ነው። በተመሳሳይ ሁኔታም ጃዋር እጅግ ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሚባሉ ሰዎች ግንባር ቀደሙ ነው። በተለይም ባለፉት አራት እና አምስት አመታት በኦሮሞ ንቅናቄ ውስጥ ጉልህ ሚና የተጫወተ፣ በኦሮሞ ማህበረሰብ ውስጥ ትልቅ ሥፍራ የተሰጠው፣ በማህበራዊ ሚዲያ እንቅስቃሴው አለም አቀፍ ትኩረትን የሳበ ወጣት ፖለቲከኛም ነው። ጀዋር ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች በተሻለ ከፍተኛ ድጋፍ ያለው እራሱን የቻለ ድርጅት ነበር ማለት ይቻላል።
ይህ ግለሰብ የራሱ የፖለቲካ ግብ ያለው ሰው በመሆኑ በአብይ የሚመራው የለውጥ አካሄድ ያላማረው መሆኑን ገና በጠዋቱ ነው ያሳወቀው። በልጅነቱ ጀምሮ አዕምሮው ውስጥ የተቀረጸችበት ኦሮሚያ የምትባል አገር እውን ሆና የማየት ህልሙን በአደባባይ እየወጣ ተናግሯል። አሁን ደግሞ ያ እንደማይሆ ስላረጋገጠ ይመስላል በኦሮሞ ፍላጎት የምትመራ ኢትዮጵያ መኖሯን ማረጋገጥ የሱ የትግል ግብ እንደሆነ በቅርቡ በሰጣቸው ቃለ ምልልሶች በግልጽ ተናግሯል። ከLTV ጋር ባደረገው ውይይት ላይ ይመስለኛል ይቺ አገር በትግሬ እና በአማራ ተገዝታ ተሞክራለች ግን አልተሳካላትም፤ አሁን ደግሞ ኦሮሞ በራሱ ፍላጎት እና ምልከታ የገዳ አስተዳደርን ተጠቅሞ ሊሞክራት ይገባል ብሎ አስረግጦ ተናግሯል። ጃዋር ይህን ህልሙን የአንድ ሚዲያ ዳይሬክተር እና የማህበራዊ እንቅስቃሴ መሪ ሆኖ ከግብ እንደማያደርሰው ተረድቶ ይመስላል ሰፊውን ሜዳ ለቆ ወደ ፖለቲካ ፓርቲ ጎሮኖ ያመራው።
በጀእዋር በኩል አብረው መነሳት ካለባቸው ነገሮች መካከል ሁለቱን ላንሳ። የመጀመሪያው ግለሰቡ የፈጸማቸው እና ለብዙ ሰዎች ህልፈት ምክንያት የሆኑ የሕግ መተላለፎች ወይም የወንጀል አድራጎቶች ናቸው። ጃዋር ከቡራዩ እና ሲዳማ እልቂት ጀርባ የነበረውን ሚና መንግስት ወደጎን ብሎ ማለፉ ለሌላ ጥፋት ምክንያት እንዲሆን አድርጎታል። ተከበብኩ ብሎ በጠራው ወጀብ የ86 ሰዎች ህይወት ጠፍቷል። አገሪቱ ያዳበረችው ለጥፋት ያለመጠየቅ ባህል ዛሬም ቀጥሎ ግለሰቡ በሕግ ሊጠየቅ ሲገባው እንደውም እራሱን ከአክቲቪስትነት ወደ ፓርቲ መሪነት እንዲያሸጋገር ሰፊ እድል ሰጥቶታል። ምናልባትም ‘እኛም አውቀናል ጉድጓድ ምሰናል’ ያለውም ለዛ ይሆናል። ኦፌኮ የጀዋር የአይጥ ጉድጓድ መሆኗ ይሆን?
ሌላው ከጃዋር ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጉዳይ የዜግነቱ ነገር ነው። ግለሰቡ የአሜሪካ ዜግነቱን ለመመለስ መወሰኑን አሳውቋል። እንግዲህ ዜግነት በመመለስ እና አዲስ የኢትዮጵያ ዜግነት በማግኘት ሂደት ውስጥ የሚጠፋ ጊዜ አለ። በመጀመሪያ የአሜሪካ ዜግነት ዝም ብሎ በቀላሉ የሚተው ነገር አይደለም። እንኳን ዜግነት የትምህርት ቤት መልቀቂያ እንካ ሲጠየቅ ግለሰቡ በእጁ ያሉ የትምህርት ቤቱ ንብረቶች መመለሱ ክሊራንስ ያስፈልገዋል። እናም እረዥም የሆነ የራሱ ሂደት አለው። ዜግነቱን አልፈልግም የሚለው ሰው ከተቀመጡት መስፈርቶች በተጨማሪ በአሜሪካ ሕግ በወንጀል ወይም ከታክስ እና ሌሎች ገንዘብ ነክ ከሆኑ ጉዳዮች ጋር ክስ የሌለበት ወይም ወደ ፊት ሊያስከስሰው የሚችል ነገር ሸሽቶ አለመሆኑ ይጣራል።
በአሜሪካ አገር ጃዋር ላይ ክስ የሚያቀርቡ ወገኖች እንዳሉ ሰምቻለሁ። ያ ክስ ከተገፋበት ጃዋር የአሜሪካ ፓስፖርቱን የመመለስ እድሉ እረዘም ያለ ጊዜ ሊወስድበት ይችላል። ምክንያቱም ዜግነቴን ልመልስ ያለው በአሜሪካ ሕግ ላለመጠየቅ እየሸሸ ነው አይደለም የሚለውን በፍርድ ቤት ማረጋገጥም ጭምር ሊጠይቅ ስለሚችል። ዝርዝሩን ይህን ማስፈንጠሪያ በመጫን ማየት ይቻላል፤
ፓስፖርቱን ካልመለሰ ደግሞ የኢትዮጵያ ዜግነት ማግኘት ስለማይችል ወደ ምርጫ ተወዳዳሪነት ሊገባ የሚችልበት እድል እጅግ በጣም ጠባብ ነው። ስለዚህ ለአሁኑ ምርጫ ባይደርስ እንኳ ለቀጣዩ ምርጫ እጩ ተወዳዳሪ ሊሆን ይችላል። ባሁኑ ምርጫ ለዶ/ር መራራ ጉዲና ጥሩ አንቀሳቃሽ እና ቀስቃሽ ሊሆናቸው ይችላል። እሱም የኢትዮጵያ መንግስት እንደለመደው ጉዳዩን ባላየ ካለፈው ብቻ ነው። ምክንያቱም የውጪ ዜጋ በፓርቲ ፖለቲካ ውስጥ መሳተፍ የአገሪቱ ሕግ ስለማይፈቅድ።?
ማጠቃለያ
ለማንኛውም እስክንድር እና ጃዋር ወደ ፖለቲካ ፓርቲዎች ካምፕ ማቅናታቸው የአገሪቱን ፖለቲካ ትኩሳት ከፍ ማድረጉ ግን ምንም አይጠረጠርም። ምንም እንኳ ሁለቱም የለመዱት ሰፊው ነጻነታቸው በፓርቲ ልጓም የሚሸበብ ቢሆንም ከምርጫው በፊት እና በኋላ ያሉት የተወሰኑ ወራቶች በውጥረት የተሞሉ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።
ግን ምርጫው በጊዜው ይካሄዳል? አይመስለኝም። እሱን በሌላ ርዕስ እመለስበታለሁ።
ቸር እንሰንብት!
Filed in: Amharic