ኦነጋውያን እነማን ናቸው?
[በዶክተር መረራ ጉዲና]
አቻምየለህ ታምሩ
[በጦብያ መጽሔት በጥር 1988 ዓ.ም. «በመስታወት ቤት ውስጥ የሚኖር በሌሎች ላይ የመጀመሪያውን ድንጋይ ወርዋሪ አይሆንም» በሚል ርዕስ የታተመ]
ለኦሮሞ ሕዝብ መብት የሚደረገውን ትግል በተመለከተ ሆዳችን እየቆሰለ ሕዝቡ ይከፋፈላል ብለን እስከዛሬ ድረስ አምቀን የያዝነው በሽታ የተፈጠረው ሰፊ መሰረት የነበረው የሜጫና ቱለማ እንቅስቃሴ ሲጀመር ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በሚሲዮን ጸሎት ቤቶች የተፈለፈሉትና የኦሮሞን ሕዝብ ትግል ለርካሽና ወራዳ ዓላማቸው ለማዋል የቆረጡ እንግዴ ልጆች መፈጠር ተከተለ። ይህን ሐሳብ ዘርዘር አድርጌ ላብራራ።
የሜጫና ቱለማ መስራች መሪዎች የእነ ኮሎኔል ዓለሙ ቂጤሣና የጀኔራል ታደሰ ብሩ መታሰር፣ የመቶ አለቃ ማሞ መዘምር መገደል የሜጫና ቱለማ እንቅስቃሴ ለጊዜውም ቢሆን እንዲገታ አድርጎት ነበር። ይህ ክፍተት የፈጠረላቸውን አመቺ ሁኔታ በመጠቀም ከሚሲዮን ጸሎት ቤቶች የተመረቁት ጥቂት ሰዎች የኦሮሞን ሕዝብ እንቅስቃሴ ከሃይማኖታቸው ጋር አቆራኙት። ይህ ቁርኝት እንዴት የሕዝባችንን ትግል በቀላሉ በማይወጣበት አጣብቂኝ ውስጥ ከተተው? እንቅስቃሴውን ማን መራው? ለዛሬው አጣብቂኝ እንዴት አስተዋጽኦ አደረገ? የሚሉትን ጥያቄዎች መመለስ ያስፈልጋል።
ያልተቀደሰውን የሚሲዮን ጸሎት ቤትና የኦሮሞ ሕዝብ የመብት ትግል ቁርኝት የመሩት ባሮ ቱምሳና ቤተሰቦቹ ነበሩ። ይህ ግለሰብ ያኔ በእውን ላልነበረው የኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባር መሪ አድርጎ ራሱን በመሰየም የኦሮሞ ሕዝብ መሪ ለመሆን ሲያልም እንደቆየ የኢትዮጵያ አብዮት ፈነዳበት። ባልጠበቀበት ጊዜ የአብዮቱ መምጣት የኦሮሞ ሕዝብ መሪ የመሆን ሕልሙን ስላጨለመበት የተበሳጨው ባሮ ቱምሳ እስከዛሬ ለትውልድ ተላልፎ ያልተዘጋውን በኦሮሞ ልጆች ደም የመነገድ ፖለቲካ የመጀመሪያውን ምዕራፍ ከፍቷል። ይህ ምን ማለት እንደሆነ እንደሚከተለው ግልጽ ላድርግ።
አብዮቱ እንደፈነዳ ጀኔራል ታደሰ ብሩ ከታሰሩበት ከሐረርጌ ክፍለ ሀገር ተፈትተው አዲስ አበባ ሲገቡ የውሸት ፍቅር በማሳየት ከተጠጓቸው ተራማጅ ነን ከሚሉት መካከል አንዱ ባሮ ቱምሳ ነበር። ይህ ሰው በአንድ በኩል የጄኔራል ታደሰ ብሩ አስተናጋጅና አማካሪ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በተለይ ደርግ ሶሻሊዝምን ሲያውጅ ሶሻሊስት በመምሰል ደርግ ውስጥ በነበሩ የኦሮሞ መኮንኖች በኩል የደርግን ሹመት ለማግኘት ደጅ መጥናት ጀመረ። ይህ ለስልጣን የቋመጠ ግለሰብ ቀን ቀን እንደ መሬት ዐዋጅ ያሉትን ለማርቀቅ ከተሰለፉት ኦሮሞዎች ጋር እየዋለ ማታ ማታ ደግሞ ጀኔራል ታደስን «የኦሮሞ ሕዝብና ሠራዊት ተነስቷል፤ የሚመራው ሰው ይፈልጋል። ምኒልክ የኦሮሞን መሬት አከፋፍሏል። እንዴት የምኒልክ ልጆች ዳግመኛ በእኛ ላይ ቆመው መሬታችንን ያከፋፍላሉ?» እያለ ጀኔራሉን አላስቆም አላስቀምጥ ይል ጀመር። ዛሬም በሕይዎት ያሉ አንዳንድ የኦሮሞ ልጆችን ጨምሮ «ካስፈለገ ዳገት መውጣትና መውረድ፥ ሮጠህ ማምለጥ የምትችለው አንድ ሸፍት፥ ሽማግሌውን ከሚታወጀው የመሬት ዐዋጅ ጋር አታጋፍጣቸው» ብለው ጀኔራል ታደሰ ብሩን ለማዳን አጥብቀው የተከራከሩ ነበሩ፤ ግን አልተሳካላቸውም።
ዛሬም የሚሲዮንን ኬክ ሲገምጡ ያደጉት ልጆች ሌሎችን እያጋፈጡ መነገድ እንጂ ወደ ጥይቱ መጠጋትን አይሞክሩትም። የነዚህ አጋንንቶች ዋናው ዓላማ ከነሱ በላይ ስም ያለው የኦሮሞ ልጅ እንዳይኖር ነው። ለዚህም ነበር ያኔ ባሮ ቱምሳ ሽማግሌውን መናገሻ አድርሶ ለራሱ ወደለመደው የቅጥፈት ሥራ የተመለሰው። ያለዝግጅት፣ ያለ ድርጅትና ትጥቅ ቀድሞውኑ የትም መድረስ ስለማይቻልና የጀኔራሉን መውጣት ሆን ተብሎ ከመሬት ላራሹ ዐዋጅ መውጣት ጋር እንዲገናኝ ስለተደረገ በተዘጋጀላቸው ወጥመድ ውስጥ የገቡት ጀኔራል ታደሰ ብሩና ኮሎኔል ኃይሉ ረጋሳ ስማቸውን ከማላቀው የአካባቢው ሰዎች ጋር በጥቂት ቀኖች ውስጥ ተይዘው «የመሬት ዐዋጅን ለማደናቀፍ ለመሬታቸው የሸፈቱ ፊውዳሎች» ተብለው ተረሸኑ።
እዚህ ላይ በተለይም የኦሮሞ ተወላጆች ልብ እንዲያደርጉልኝ የምፈልገው አንድ ነጥብ አለ። እነ ጀኔራል ታደሰ ብሩ ሲረሸኑ መለስ ተክሌ የሚባል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የነበረ የትግራይ ልጅ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤትና በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ውስጥ ቦንም ቀብረሃል ተብሎ የተረሸነ። በዚህ ጓደኛቸው መሞት የተቆጩት እነለገሠ ዜናዊ የወደቀ ጓዳቸውን ስም ወስደውውና እነ መለስ ዜናዊ ሆነው ወደ ትግራይ በረሃ ሲንቀሳቀሱ የኦሮሞው ጉድ ባሮ ቱምሳ ግን «እነጀኔራል ታደሰ ብሩና ኮሎኔል ኃይሉ ረጋሳ ለመሬታቸው የሞቱ ፊውዳሎች ናቸው» ብሎ በማስወራት ከደርግ ጋር ወግኖ በጀኔራሉ ላይ ሞት ከፈረዱት የኦሮሞ ደርግ አባሎች ጋር ኢጭአት የሚባል ድርጅት መስርቶ ከደርግ የሥልጣን ፍርፋሪ ፍለጋውን ሲያጠናክር ነበር።
ከርካሽ ዝናና ሥልጣን ሌላ ምንም ዓላማ ያልነበረው ባሮ ቱምሳ የትኛውም ወገን ቢያሸንፍ ሥልጣን እንዳይቀርበት አቅዶ «ነፃነት» ፥ «በከልቻ ኦሮሞ» ፥ «ወራቅሣ» ፥ ወዘተ የሚሉ ከ6 ያላነሱ ልሣኖችን ማሰራጨት ጀምሮ ነበር። እነዚህ ልሳኖች የሚያራምዱት አቋም (አንዱ ከሌላው ሲተያይ) እንደሰማይና እንደ ምድር የሚራራቅ ነበር። «ነፃነት» የኢጭአት ልሳን ሆኖ ይዞት የሚወጣው ጽሑፍ ደርግን ተራማጅ፣ ሶሻሊት፣ አብዮተኛ ብሎ የሚያቀርብ ሲሆን ፤ «በከልቻ ኦሮሞ» እና «ወራቅሣ» ወዘተ የሚባሉት የባሮ ቱምሳ ልሳኖች ደግሞ ይዘዋቸው የሚወጡት ጽሑፎች ደርግን ፋሽስት፣ የነፍጠኞች ጥርቅም፣ ወዘተ የሚሉ ነበሩ። ግለሰቡም በተራማጅነት ካባ ወደሚያገለግልበት የሕዝብ ድርጅት ጊዜያዊ ጽሕፈት ቤት ሲሄድ የማርክሲስት ስብከት፣ ወንድሙ ቄስ ጉዲና ወደሚመሩት ጸሎት ቤት ሲሄድ የኦሮሞ ሕዝብ አዳኝ እየሱስ ክርስቶስ ነው የሚል ስብከት፣ ወጣ ብሎ ከኦሮሞ ልጆች ጋር ሲገናኝ ደግሞ ያለገዳ የኦሮሞ ሕዝብ ተስፋ የለውም የሚል ሥብከት ነበረው። ከዚህም አልፎ ኢሕአፓም እንዳይነካው የግንኙነት መስመር ፈጥሮ ነበር። የዚህ ሰው የፖለቲካ ቁማር ያልገባቸው የኦሮሞ ልጆች ባልገባቸው ነገር ሕይዎታቸውን እስከማጣት ደርሰዋል። ከነዚህ አንዱ አቶ ጉታ ሰርኔና ናቸው። አቶ ጉታ ሰርኔሳ ከባሮ ቱምሳ ጋር ፖለቲካ እየሰሩ በኢሕአፓ ተገድለዋል።
በዚህ ቁማሩ የገፋው ባሮ ቱምሳ በድርጅቱ ውስጥ ከፍተኛ የደርግ አባሎችንና ከፍተኛ የደርግ ፀጥታ ሹማምንትን ሳይቀር አቅፎ ሲቀሳቀስ መኢሶን ብዙ ኦሮሞዎችን መሳቡ ስላደናገጠው «ከነፍጠኛ ልጆች ጋር የሚሰሩ ቀይ ጎበና ናቸው» የሚል አሉባልታ መንዛት ጀመረ። ይህ አሉባልታ ነው እንግዲህ እስከዛሬ እያገረሸ የሚገኘውና የመጀመሪያው የኦሮሞ ልጆች አደገኛ ክፍፍል መንስኤም የሆነው።
ደርግና መንግሥቱ ኃይለ ማርያም አደገኛ አዝማሚያ እየያዙ ሲሄዱና በመኢሶን ላይ የቀጥታም ሆነ የእጅ አዙር ዘመቻ ሲከፈት ሕይወቱ በደርግ ውስጥ በተሰገሰጉ ሥልጣን ፈላጊዎች እስክታልፍ ድረስ የሐረርጌ ክፍለ ሀገር የሕዝብ ድርጅት ኃላፊ የነበረው አብዱላሂ ዩሱፍ ምንም ከማድረግ የማይመለሰው ባሮ ቱምሳ የደርግ መሣሪያ እንዳይሆን ከደርግ ጉያ ለማውጣት ያላደረገው ሙከራ አልነበረም። የኦሮሞ ሕዝብ መሪ ለመባል ባለው ሕልም በተለያየ ስም የሚንቀሳቀሱ ከስድስት ያላነሱ የኦሮሞ ቡድኖችን የምመራው እኔ ብቻ ስለሆንሁ ከኔው ጋር ብቻ ተደራደሩ በማለት ለማስወራት ሞከረ፡ ከማይታመን ተለዋዋጭ የፖለቲካ ቁማርተኛ ጋር መደራደሩ ፋይዳ ስላልነበረው ሙከራው እዚያው ላይ ቆመ።
መኢሶን ከፖለቲካ መድረኩ ሲወጣ ባሮ ቱምሳ ጮቤ ረገጠ። መኢሶን ሲመታም ከደርግ በስተጀርባ ሆኖ እንደ እሱ የተንቀሳቀሰ አልነበረም። የተከተለው ታክቲክም የመኢሶን አባሎች የሚለቋቸውን ቦታዎች በራሱ ካድሬዎች መሙላት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ኦሮሞ የሆኑ የመኢሶን ካድሬዎችን መመልመል ነበር። ለምሳሌ በሽግግር መንግሥቱ ምክር ቤት አንዱ የኦነግ ተወካይ የነበረው ዓለማየሁ ታረቀኝ ያን ጊዜ በባሮ ቱምሳ ከመኢሶን ከተወሰዱት ካድሬዎች አንዱ ነበር።
የኤርትራ ግንባሮች እንቅስቃሴ፣ የሶማሊያ ጦርነት፣ የኢሕአፓ እንቅስቃሴና የመኢሶን መውጣት ደርግን ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ መክተቱን ሲያይ ባሮ ቱምሳ ለኦሮሞ ልጆች እጅግ በጣም አደገኛ የሆኑ ሁለት ቁማሮችን መጫዎት ጀመረ። ይህም በአንድ በኩል ደርግ በአጋጣሚ ካሸነፈ ለመታረቅ እንዲችል እሱ ይመራው የነበረውን ኢጭአትን ከደርግ ጋር እንዲቆይ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ፀረ ደርግ ኃይሎች ካሸነፉ ብሎ ከድል አድራጊዎች ጋር ለመሆን ሲል ከጃራ አበገዳ ጋር ግንኙነት የመመስረት ታክቲክን ተከተለ። የኋላ ኋላ ልዩነቱ እየከረረ ሲሄድ ጃራ አባገዳ ወደሚንቀሳቀስበት ሐረርጌ ክፍለ ሀገር ፈረጠጠ። ይህ ተአምረኛ ግለሰብ እዚያ እንደደረሰ ብዙም ሳይቆይ «የለመደች ጦጣ ሁልጊዜ ሽምጠጣ» እንደሚባለው የለመደውን ሥራውን ጀመረ። ይህም ጃራ አባገዳን ከሥልጣን ለማውረድ ማሴር ነበር።
የዚህ አስቸጋሪ ሰው ሥራ ያላማረው ጃራም ቀደም ብሎ አብሮት የነበረውንና ለረጅም ጊዜ አብሮት ይሰራ የነበረውን ባዶ ደቻሳ ይባል የነበረ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሆነ የጉለሌ ልጅ «ይህ ሰው እየከፋፈለን ነው፤ ምከረው» ብሎ ይነግረዋል። ባዶ ደቻሳ ትግል የጀመሩት ለሥልጣን ሳይሆን የኦሮሞን ሕዝብ ለማደራጀት መሆኑን፣ እሰው ቤት መጥቶ በሰው ላይ ማሴር ብልግና መሆኑን፣ ውጤቱም አደገኛ ክፍፍልን መፍጠር ሊሆን እንደሚችል ደጋግሞ ቢነግረውም ባሮ ግን ሴራውን ከመግፋት አልታቀበም። በመካከሉም ሶማሊያ አካባቢውን ስለተቆጣጥረች የሚመለሰው የደርግ ሠራዊት ግፊት ተጨምሮበት ተስፋ አስቆራጭ ውስጥረት ተፈጠረባቸው።
ይህን የተገነዘበው ባሮ ቱምሳ አዲስ ልብ ወለድ ሲያልም ያድርና «ሥልጣን ላይ በነበርሁበት ጊዜ ጫካ ስገባ ትሰጡኛላችሁ ያልኳቸው የቻይናና የምሥራቅ ጀርመን መንግሥታት ቃል የገቡልኝን ብዙ ገንዘብና የጦር መሣሪያ መጥቶ ይውሰድ ብለው መልእክት ስለላኩብኝ ይንህኑ ለማምጣት ወደ ውጭ አገር ልሂድ» ይላል። ከማንም በላይ የዚህን ሰው ማንነት በትክክል መረዳት የጀመረው ባዶ ደጃቻ፣ ባሮ ሌላ ድራማ ለመሥራት ማቀዱን በመገንዘብ፣ «በምንም መንገድ ባሮ ቱምሳ ወደ ውጭ መሄድ የለበትም» ይላል። የባሮ ወደ ውጭ የመሄድ ጉዳይ ለስብሰባ ሲቀርብ ባዶ ደቻሳ «የሚባለው እውነት ከሆነ ሌላ ሰው ተወክሎ ይሄዳል እንጂ ባሮ በምንም ተአምር ወደ ውጭ መሄድ የለበትም» የሚለውን አቋሙን ያጠናክራል። በዚህ ጥያቄ ላይ የባሮ ግለገሎች እነ ዮሐንስ ለታ የዛሬው ሌንጮ ለታ የፖለቲካ ነፍስ አባታቸውን በመደገፋቸው በጣም የተናደደው ባዶ ደቻሳ ስብሰባ ለቆ ይሄድና መሣሪያ ይዞ በመመለስ «በኦሮሞ ልጆች ደምና አንባ እስካሁን ነግደሃልና ለዘላለም ግን ስትነግድ አትኖርም» ብሎ ባሮን ረሽኖ ራሱንም በመግደል የክብር ሞት ሞቷል።
ከዚህ በኋላ ውጥረትም ክፍፍሉም በከፋበት ጊዜ ወደ ጅቡቲ የተጓዘው ሌንጮ ለታ አንድም የፖለቲካ ነፍስ አባቱ በኦሮሞ ልጅ እጅ ትክክለኛ ፍርድ መቀበሉና ርካሽ ሞት መሞቱ ታሪኩን ስለሚያበላሽበትና በሌላ በኩል ደግሞ የኦሮሞ ሕዝብ የተሻለ እድል ከገጠመው እነጃራ አባገዳ የበላይነት እንዳያገኙ ልክ ባሮ ሲያደርግ እንደነበረው ልብ ወለደ አሉባልታ ማሰራጨት ይጀምራል። «ባሮን የገደለው ጃራ ነው። እስላሞቹ ሁላችንንም ሊጨርሱን ነበር። እኔም አምንጬ ነው የመጣሁት» ብሎ በአንድ ጸሎት ቤት ላሳደጉትና ከኢትዮጵያ መንግሥት የዜና ማሰራጫ አውታሮች የተሻለ ወሬ የማሰራጨት ችሎታ ላላቸው ዘመዶቹ ይነግራል። እነሱም ከጅቡቱ እስከ ሱዳን፥ ከሱዳን እስከ አውሮፓና አሜሪካ ከዚያም ወደሀገር ቤት ይህንኑ ነጭ ውሸት አውርተው ያስወራሉ።
የመጨረሻ ውጤቱም የኦሮሞ ተወላጆች ጃራ በሚመራው «ኢስላሚክ ኦሮሞያ ነፃ አውጭ ግንባር» እና እነ ሌንጮ ለታ በሚመሩት የኦሮሞ ነፃ አውጭ ግንባር ተኮለኮሉ። በዚህ ምክንያት እስካሁን የኦሮሞ ልጆች ደም እየፈሰሰ መሆኑ ብቻም ሳይሆን ለነገው የሚተርፍና የሃይማኖትም መልክ ሊይዝ የሚችል የኦሮሞ ልጆች ሁለተኛው አደገኛ ክፍፍል ተፈጠረ። የኦሮሞ አዛውንቶች በተደጋጋሚ እነጃራንና ኦነግን ለማስታረቅ ሞክረው ያልተሳካላቸውም ጃራ «እነ ሌንጮ ለታ በኦሮሞ ሕዝብ ፊት ወጥተው ዋሽተናል ብለው ካላመኑ እነሱን አምኜ ከነሱ ጋር አልሰራም» በማለታቸው ነበር።
ይህን ሁሉ ያወራሁት ሙት ወቃሽ ለመሆን ፈልጌ አይደለም። ይሁንና በራሱ አምሳል ኮትኩቶ በየሚሲዮን ጸሎት ቤቶች ያሳደጋቸው ሌንጮዎችና ዮሐንሶች ኦነግን በቤተሰብ የጥቅም ሰንሰለት ውስጥ አስገብተው አፍነው በመያዝ ሰዎች በተለይም የኦሮሞ ልጆች የሚታገሉበትን፣ የሚሞቱለትን፣ በእስር የሚንገላቱበትን ዓላማ በቅጡ እንዲገነዘቡ ባለኝ ፍላጎት ነው። ዛሬም ትናንት የጀመሩትን የፖለቲካ ቁማር በስፋት በመቀጠል የኦሮሞ ልጆች በማይታረቁበት ቅራኔ ውስጥ ዘላለም እንዲዳክሩና ልዩነቶቻቸውን አቻችለው በጋራ ለሕዝባቸው እንዳይታገሉ በማድረግ ላይ ናቸው። ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲሉም መኢሶን ከነበሩ ልጆች አልፎ እነ ጃራን፣ ከነጃራ አልፎ እነ ጀኔራል ዋቆ ጉቱን፥ ከሳቸውም አልፎ አዲስና የተሻለ ድርጅት እንዳይፈጠር ውስጣችንን ያውቁብናል የሚሏቸውን የኦሮሞ ወጣት ምሁራንን ሁሉ ከዛሬ መቶ ዓመት በፊት በሞተ ጎበና ስም እየኮነኑ የደራ የፖለቲካ ንግዳቸውን ቀጥለዋል። በተለይ የኦሮሞ ልጆች የችግሮችን ምንጭ ከመሠረቱ እንዲረዱ አይፈልጉም።
የኦነግ መሪዎች እንደወጥ ማጣፈጫ ቅመም ከጽሑፎቻቸው የማይጠፉትን ራስ ጎበናን ጨምሮ በእነዚህ ሰዎች ደጋግመው የሚነሱት ስሞች ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ፣ ራስ አበበ አረጋይ፣ ጀኔራል ጃጋማ ኬሎ፣ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ፣ ወዘተ ናቸው። የእነዚህን የኦሮሞ ልጆች ስም የሚያነሡት ትናንትና እነሱ በነበሩበት ዘመን ከነበሩት ነባራዊ ሁኔታዎች አንጻር፣ ድርጊታውንም በታሪክ ሚዛን ለክተው ከእነሱ የተሻለ ለመሥራት ሳይሆን ከራሳቸው ጸሎት ቤቶችና አካባቢ ውጭ የተወለዱትን የኦሮሞ ልጆች ስም ለማጥፋት አልመውና አቅደው ነው። ሊደርሱበት የሚፈልጉት ግብም ከእነሱ የተሻለ ችሎታና ታሪክ ያላቸውን የኦሮሞ ልጆች ሁሉ ስም በማጥፋት ችሎታውም ሆነ ታሪኩ ለሌላቸው የታሪክ ዝቃጮች ቦታ ለመፍጠርና የደራ የፖለቲካ ንግዳቸውን ለመቀጠል ነው።
እነዚህ ዝቃጮች ስለሚያቅርቧቸው ክሶች እንኳ በትክክል የሚያውቁ አይደሉም። ለምሳሌ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ክርስትና ተነሡ ይሉናል። እነሱ ክርስትና መነሣታቸውና ስማቸውም ዮሐንስ ለታ፣ አብርሀም ለታ ፣ ማርታ ኩምሳ [የሌንጮ ለታ ሚስት] ፣ መሆናቸው ግን አይታያቸው። በመሠረቱ ሁለቱ ልዩነት ቢኖራቸው ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ክርስትና የተነሡት በጥቁሮች ቤተ ክርስቲያን ሲሆን እነሱ ደግሞ በፈረንጆች ጸሎት ቤት መሆኑ ነው። እኛ የምናውቀው ትናንትን የሚሲዮን ኬክ ለመግመጥ ዮሐንስ፣ አብርሀም፣ ማርታ፣ የነበሩት ዛሬም የኦሮሞን ሕዝብ ለማጭበርበር ሌንጮ ለታ፣ አባጫላ ለታ፣ ኩዌ ኩምሳ መባላቸውን ነው።
የፈለገውን ያክል ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ጠልተናል እንበል። እስኪ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻና በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ዓመታት የኖሩትን የፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስና በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ ያሉትን የአቶ ሌንጮ ለታን የማሰብ ችሎታ የሚከተለውን የታሪክ ክንዋኔ በመጥቀስ እናወዳድር።
በአንድ ወቅት እንግሊዞች ኬንያን ከያዙ በኋላ ቦረናንም ለመውሰድ ሠራዊታቸውን ወደ ቦረኖች መሬት አሥርገው አስገብተው ነበር። ቦረኖች የእንግሊዝን ወታደሮች ከፊሎቹን ገድለው ሌሎቹንም ወደመጡበት ይመልሳሉ። በዚህ ወቅት የሠራዊቱ ደም የፈሰሰሰብትን መሬት ለመውሰድ የእንግሊዝ መንግሥት ዲፕሎማቶቹን ወደ ዳግማዊ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ልኮ ነበር። «ወታደሮቻችን ለግጦሽ ቦረና አካባቢ ገብተው ሞቱብን። የግጦሽ ችግር ስላለብን ቦረና በደም ካሣ መልክ ይሰጠን» ይሏቸዋል። ምኒልክም ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስን አናግሩ ይሏቸዋ።
ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ አባመላም የእንግሊዝ ዲፕሎማቶችን በፈገግታ ተቀብለው ከአስተናገዱ በኋላ የመጡበትን ጉዳይ ጠየቋቸው። የእንግሊዝ ዲፖሎማቶችም ለምኒልክ የነገሩትን ይደግሙላቸዋል። ፊታውራሪም «ጥያቄያችሁ ተገቢ ነው። እኛም ለወዳጆቻችን የማናደርገው ነበር የለም። ይመዝገብላችሁ» ይላሉ። የፈለጉትን የተፈጸመላቸው መስሏቸው የፈነደቁት የእንግሊዝ ዲፕሎማቶች ጉዳያቸውን አስመዝግበው ሲጨርሱ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ «እኛም ለወዳጆቻችን የምናቀርበው ትንሽ ጥያቄ አለችንና ይመዝገብልን» ይላሉ። አስከትለውም «የኛ ንጉሥ የዐፄ ቴዎድሮስ ልጅ የነበረው ልዑል ዓለማየሁ ለንደን ከተማ ውስጥ ሞቶ ተቀብሯልና መቃብሩ አካባቢ ያለውን የለንደንን ከተማ ቆርሳችሁ ስጡን» ይላሉ። ቦረናን ለመውሰድ የመጡት እንግሊዞች ለንደርን ከተማ መሬት ሲጠየቁ አፋቸውን ዘግተው ተመለሱ። በአንጻሩ የእንግሊዝን፣ የፈረንሳይን፣ የኢጣሊያንን ዲፖሎማቶች አሳፍረው ሲመልሱ የነበሩትን ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስን በቅኝ ገዢነት የሚከሱት ማፈሪያዎች ከሻዕብያና ከወያኔ ጋር ተደራድረው አንዳች ጥቅም ለኦሮሞ ሕዝብ ማስገኘት ተስኗቸው የሠሩትን እንይ።
የሽግግር መንግሥቱ ሲመሰረት ከፊል አማራ የሆኑት እነ አብዩ ገለታ ወይንም ገላሳ ዲልቦ «አማርኛ አናውቅም» እያሉ በእግሊዝኛ የመናገር ድራማ ሲሰሩ የሚሰሩትን በትክክል የሚያውቁት እነ መለስ ዜናዊ ግን በመንዝ አማርኛ እየተናገሩ የኢሕአዴግን ሠራዊት በሀገሪቱ መከላከያ ሠራዊትነት አስመዝግበው እነሌንጮን አስፈረሙ። ሻዕብያን ከሚያምኑት አምላክ በላይ የሚያመልኩት እነሌንጮ ለታ በሻዕብያ አደራዳሪነት ከኢሕአዴግ ጋር ተነጋግረው በሻዕብያ በሚጠበቅ የኢሕአዴግ ማጎሪያ ውስጥ አስገብተው በማጎር በብዙ ሺህ የሚቆጠር የኦሮሞ ልጆችን ለስቃይና ለሞት ደርገዋል።
ይህም ብቻ አይደለም። የኦሮሞ ልጆችን በሥነ ሥርዓት ሰብስበው ካምፕ አስገብተው ለጥቃት ካመቻቹ በኋላ «እኛ ከሽግግር መንግሥቱ ስለወጣን ካምፖችን ሰብራችሁ ውጡ» ብለው ከዕብዶች ወይንም የተደበቀ አላማ ካላቸው ሰዎች ብቻ የሚጠበቅ ትእዛዝ ሰጥተው ሺዎችን አስጨርሰዋል። እነዚህ ሰዎች በሒልተንና በጉለሌ መካከል እየተመላለሱ አራት ኪሎ በሚገኘው መንግሥት ላይ ጦርነት እያካሄድን ነው የሚሉ አስቂኝ ሰዎች ናቸው። የኦሮሞን ልጆች ከሚሠሩባቸው መሥሪያ ቤቶች፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ጭምር ወደ ጫካ ሸኝተው ለራሳቸው በቦሌ በኩል በመንግሥት አየር መንገድ በመሹለክ ቀደም ብለው በቤተሰቦቻቸው በኩል ወደአዘጋጁት መነሃሪያ ማለትም ወደ አውሮፓ፣ አሜሪካና ካናዳ የበረሩት ትንግርተኛ ሰዎች ነበሩ። እንደገናም ተመልሰው በየእሥር ቤቱ ለሚማቅቁትና በየጫካው ለሚንከራተቱቱ የኦሮሞ ልጆች ለትንሽ ቀንም ቢሆን ስንቅ ሊሆን የሚችል ብዙ ሺህ ዶላር አውጥተው፣ ውቅያኖስና አሕጉሮችን አቋርጠው እንወጋዋለን ለሚሉት ጠላት እጃቸውን የሚሰጡ አሳፋሪ ሰዎች ናቸው።
እጃቸውን ከሰጡ በኋላ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ በየመንግሥት እስር ቤቶች የሚማቅቁ የኦሮሞ ልጆች ሳይፈቱ አንፈታም ብለው ማንገራገር እንኳ ቢቀር እነሱን ለማስፈታት በፍርድ ቤት አካባቢ ተገኝተው የታሰሩት እንዲፈቱ ሳይጠይቁ ማምልከቻ ጽፈው «በሰላማዊ መንገድ እንታገላለን» ብለው ወያኔን በመማጠን እንደተፈቱ ወደ ፈረንጅ ፍርፋሪ ለቀማቸው የሚመለሱ ጉደኞች ናቸው። እንዲህ አይነቶቹ የዘመናችን ጄሉ ሞሮዎችና ጄሌዎቻቸው ናቸው እነ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስን «አጋሰስ» ብለስ የሚከሱት።
እስኪ እነዚህ ሌሎችን «በአጋሰስነት» የሚከሱ ጉዶች ከእነራስ አበበ አረጋይ፣ ከነደጃዝማች ገረሱ ዱኪ፣ ከነጀኔራል ጃገማ ኬሎ ተግባር ጋር ደግሞ እናወዳድራቸው። ራስ አበበ አረጋይ ወጨጫ ተራራ ላይ ሆነ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የመሸጉትን የኢጣሊያን ፋሽስቶች ዙሪያውን ከበው የገረፉ፣ ሀገሪቷንም ከኢጣሊያን ፋሽስቶች ነጻ ያወጡ የኢትዮጵያ አርበኞች ቁንጮ ነበሩ። ከሳሾቻቸው የሌንጮ ለታ ወንድሞች እነ አብርሀም ለታ ወይንም አባጫላ ለታ ግን ከመዲናችን በብዙ መቶ ኪሎሜትሮች ርቆ በደንቢ ዶሎ አካባቢ በሚገኝው የወለል ተራራ ላይ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የኦሮሞ ልጆችን አስፈጅተው በሽሽት ወደ ሱዳን የፈረጠጡ ወኔ ቢሶች ናቸው።
ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ በሸዋና በከፋ እየተዘዋወሩ የፋሽስትን የጦር መንጋ ሲነዱ የነበሩ ጀግና ናቸው። በደፋሮቹ አንደበትና ብዕር «አጋሰስ» እየተባሉ የሚዘለፉት ጀኔራል ጃገማ ኬሎ ሀያ ዓመት ሳይሞላቸው የአዲስ አለምን የኢጣሊያን ምሽግ የደመሰሱት ሕዝባችንን ከነጭ እንቁላል ተሸካሚነት ያዳኑ ጀግና ናቸው። ተሳዳቢዎቹ ኦነጋውያን ለፈረንጆች ያላቸው ታማኝነት የላቀ ስለሆነ ኢጣሊያንን መውጋት እንደጀብዱ ያለመቁጠራቸው አያስደንቀኝም። ጥያቄዬ ግን ሌላ ቢቀር እንደት አያፍሩም? የሚለው ነው።
ለመሆኑ በትክክል የአጋሰስ ሥራ ሲሰሩ የኖሩ እነማን ናቸው? የጎበናን ወደ አካባቢያቸው ወደ ወለጋ መሄድ በስም ብቻ ሰምተው እንደ አጋሰስ ወርቅ ሲሸከሙ የነበሩት የእነዚህ ሰዎች አባቶች አልነበሩምን? የእነሱ ጉድ ሲሆን እንዲነገርም እንዲነሳም አይፈልጉም እንጂ የአፍሪካ የነጻነት ትግል በተጀመረበት ታሪካዊ ወቅት መጀመሪያ እንግሊዝን «ነይና ግዥን» ብለው ማመልከቻ የጻፉ፣ እንግሊዝ እምቢ ስትል ለኢጣሊያን ፋሽስት አጋሰስ ሆነው እንቁላል ሲሸከሙ የነበሩ የእነሱ አባቶች የወለጋ ገዢዎች አልነበሩም? በጥቁር አንበሳ ሥር ተሰብስበው የነበሩትን የኢትዮጵያ አርበኞች ያስፈጀስ ማነው? የኦነጋውያን አባቶች የወለጋ ገዢዎች አልነበሩምን?
ከ1950ዎቹ ጀምሮ ወደ ጎደኞቹ አካባቢ ወደ ደምቢ ዶሎ ለጎረፉት ሚሲዮናውያን የመጽሐፈ ቁልቁሎ ተሸካሚ የነበረው አጋሰስ ማነው? ሶሻሊዝም ትርፍ ያስገኛል ሲባል ደግሞ ከወንጌል ሰበካ ወደ ካድሬነት እጅግ አስገራሚ በሆነ ፍጥነት ተሸጋግረው የቀዩ መጽሐፍ ማለትም የማዖ መጽሐፍ የተሸካሚ አጋሰስ አልሆኑምን? ለዚህ ነው ይህንን ጽሑፌን «በመስታወት ቤት የሚኖር በሌሎች ላይ ድንጋይ ለመወርወር የመጀመሪያው አይሆንም» ያልኩት።
አንድ ሌላ የሚደጋግሙት ተረትም አለ። «ከሐበሾች ጋር አብረን እንኑር እንዴት ትለናለህ?» ይሉኛል። ከአባቶቻቸው፣ ከእንቶቻች፣ ወይንም ከሚስቶቻቸው ጋር እንዲኖሩ መጠየቅ ምን ችግር አለው? እነ አብዩ ገለታን ከአማራ አምቻዎቻቸውና ዘመዶቻቸው እንዲሁም ከሚስታቸውና ከእናቶቻቸው ጋር በአንድ ሀገር መኖራችሁ ይመረጣል ማለቴ እንዴት አስከፋቸው? የሚሉት እውነት ከሆነ እኔ የምለው «የምትሉትንና የምትሠሩት አንድ ይሁን» ነው። ይህን የምለው ያለምክንያት አይደለም። ጉለሌ ላይ «የኦሮሞ ሕዝብ ያለ ገዳ ሥርዓት አዳኝ የለውም» ይሉናል። ትንሽ ፈቀቅ ሲሉ «ያለ እየሱስ አዳኝ የለም» ብለው ይሰብክሉ። ወጣ ብለው ከኦሮሞ ጋር ሲያገኙ ደግሞ «ከሐበሾች ጋር በአንድ ሀገር አንኖርም» ይላሉ። ይህን የሚሉን ሰዎች በፈረንጅ የጸሎት ቤቶች ውስጥ ሲገቡ «የእግዚያብሔር በጎች ሁሉ አንድ ናቸው» የሚል ስብከት ይሰብካሉ። ለነዚህ ሰዎች አበሾች የእግዚያብሔር በጎች አይደሉምን?
የኢትዮጵያ ሕዝብ አብሮ ለመኖር ያሁኗን የደቡብ አፍሪካ ዓይነት መትሔ ማግኘት ይቻላል ስላልኩ ብዙ ብዙ ተባለ። ራሳቸውን ማንዴላ እኔን ቡቴሌዚ አድርገው ለማቅረብ ሙከራ እያደረጉ ነው። እስቲ የማን አቋም የቡቴሌዚን የማን አቋም ደግሞ የማንዴላን እንደሚመስል እንመልከት።
ቡቴሌዚ በነጮች ፍርፋሪ ያደገ፣ ነፃነት ሲመጣ የነጮቹ ፍርፋሪ እንዳይቀርበት አርበኛ መስሎ ሕዝቡን ከሕዝብ እያጋጨው በጥቁር ሕዝብ ደም እየነገደ ለመኖር የሚፈልግ ተራ የፖለቲካ ነጋዴ ነው። ልክ እንደ ቡቴሌዚ እነዚህ እኔን የሚከሱኝም በፈረንጅ ፍርፋሪ ያደጉና ወደፊትም እንዳይቀርባቸው ለዚያ የሚተጉ ናቸው። ልክ እንደ ቡቴሌዚ እነዚህም ኦሮሞን ከኦሮሞ ጋር፣ ኦሮሞን ከተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር እያጋጩ በዚህም ምንያት በሚሰፈው የኦሮሞ ሰፊ ሕዝብ ደምና እንባ እየነገዱ ለመኖር የሚፈልጉ ናቸው። ፕሬዝደት ኔልሰን ማንዴላ ለ27 ዓመታት ከእስር በመለቀቃቸው ቂም ሳይዙ «ከአውሮፓውያን ወይንም ነጮች ጋር ሳይቀር ብሔራዊ እርቅ ፈጥረን ለዛሬና ለነገው የደቡብ አፍሪካ ትውልድ የምትሆን ዲሞክራሲያዊት ደቡብ አፍሪካን መገንባት እንችላለን» የሚሉና የዓለምን የታሪክ ጉዞ የተረዱ የደቡብ አፍሩካ ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ሕዝብ ጀግና ናቸው።
ይቀጥላል. . .